Saturday, 08 August 2020 15:02

ደረጀ በቀለ - ዐይናማው ደራሲ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እሷ ትፀናለች - ይላል ጠቢቡ ሰለሞን፡፡ ሰው ያሰበውን እግዜር ካላፀናው አይከናወንም - ለማለት:: እኔም የዛሬ ጽሑፌን መነሻ ያደረግሁት ወድጄ አይደለም፤ አስቤው የነበረው ነገር ከንቱ ሆኖ - ያላሰብኩት ነገር በመሆኑ ነው፡፡
በእኔ ሃሳብ በዛሬው  ቅዳሜ ላይ የ"ሕያው ፍቅር" ደራሲ ደረጀ በቀለ፤ እንግዳዬ፣ ወይም አዲሱ “ታንጀሪና ሆቴልና ሌሎች ታሪኮች” ርዕሰ ጉዳዬ ይሆናል ብዬ ነበር፡፡ ግን ነገሩ ሳይሆን ቀረና ደራሲው ሕይወቱ አልፎ ግብዐተ መሬቱ ከተፈፀመ አሥራ አምስት ቀኑ ዛሬ ሆነ፡፡ እንደኔው ነገር የተንሸራተተበት ሌላም ጋዜጠኛ ወዳጄ ነበር፡፡ የኪነ-ብስራት ፕሮግራም አዘጋጁ የኋላሸት ዘርይሁን፣ ደረጀ በቀለን ለቃለ-መጠይቅ ባሰበው ዕለት ነበር፣ የደረጀ የቀብር ሥነ ሥርዓት የተካሄደው፡፡
ሰለሞን በመክብብ መጽሐፍ ስለ ሰው ልጆች፤ “ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደወጣ እንዲሁ እንደመጣው ይመለሳል፤ ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለው ምንም ነገር አያገኝም” ይላል፡፡ ደረጀ በቀለ አዲስ ያሳተመውን መጽሐፍ በወጉ እንኳ ሳያከፋፍል፣ ባዶ እጁን ወደ ዘላለም ቤቱ ሄዷል፡፡ “ሕያው ፍቅር” በተሰኘው የረዥም ልቦለድ ድርሰቱ አድናቆትን ያተረፈው ደረጀ፤ ከዚህ መጽሐፉ በኋላ ብዙም አደባባይ ላይ አይታይ እንጂ ውስጥ ውስጡን ሃያ ያህል መጻሕፍት ተርጉሞ ለንባብ ማብቃቱን ነግሮኛል፡፡ በአጋጣሚም በአንድ መጽሔት ላይ ልቦለድ  መጻፍ በማቋረጡ ተሟግተናል፡፡ በናሁ ቴሌቪዥን “የኔታ” በሚለው የልጅነት ፕሮግራም ላይ እንግዳዬ አድርጌው ብዙ አውግቶኛል:: ከጊዜ በኋላ ዝምተኛና ጭምት የሆነው ደረጀ፤ የትናንት ሕይወቱ እንደዚህ አልነበረም፡፡ በዘመኑ የተወለደበት ፍልውሃ አካባቢ የጨሰ አራዳ ነበር፡፡ የዚህን ልጅነት ፍንጭ በአዲሱ መጽሐፉ “ታንጀሪና ሆቴልና ሌሎች ታሪኮች” ውስጥ ይታያሉ፡፡ በኋላም ቤተሰቦቹ የዘውዲቱ ሆስፒታል ከተሠራበት አካባቢ በዘመኑ ልማት ተፈናቅለው አሁን በተለምዶ “ቡልጋሪያ ሚካኤል” አካባቢ ከገቡ በኋላ “አዲሱ አራት ኪሎ” በሚባለው ሠፈር ወጣት ፖለቲከኛ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ጓደኞቹ “ማኦ” የሚል ቅጽል ስም አውጥተውለታል፡፡ እውነትም በፖለቲካ ውስጥ የመዝሙር/ኪነት ግጥሞች በመጻፍ የታወቀና የተወደደ ነበር፡፡
አንድ ከያኒ ወዳጁ ትዝታውን ሲያስታውስ፤ "በዘመኑ አብዮታዊና ሀገራዊን ግጥሞችን በመጻፍ ዝናው የናኘ ነበረ፡፡ ያን የልጅነት መነሻ ይዞ ነው በኋላ በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት የበኩር ስራውን ለገጸ ንባብ ያበቃው፡፡" ይላል፡፡
ደረጀ በቀለ በሞያው ኬሚስት ነው:: ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኬምስትሪ ተመርቆ በማዕድን ሚኒስቴር በጂኦሎጂካል ሰርቬይ የሥራ መስክ ከሃያ አመታት በላይ አገልግሏል፡፡ በኋላ ላይ ዝንባሌው ወደ መንፈሳዊነት በማጋደሉ፣ ብዙ ጊዜውን በትርጉም ስራዎች ላይ ማሳለፍ መርጧል:: ይሁንና በውስጡ ያለው የጥበብ ምንጭ ደግሞ ሲፍለቀለቅ በውስጡ የነበሩትን አጫጭር ልቦለድና እውነት ቀመስ ታሪኮች በሁለት ወራት ድሪያ በማጠናቀቅ ለሕትመት አብቅቷል፡፡ እውነትም “ታንጀሪና ሆቴልና ሌሎች ታሪኮች"ን ያነበበ ሰው፣ ደረጀ ለፈጠራ የተፈጠረ፣ ባለ ድንቅ ምናብ ደራሲ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ ነፍስ ያላቸው ገፀባህርያት፣ ልባቸው ሲመታ የሚደመጥ፣ የቅርብ ሰዎችን ሕያው አድርጐ ሲያኖራቸው ያሳየናል፡፡ እናም ይህንን ስራ ስናስብ፣ እነዚያን በመሃል የዘለላቸውን ዓመታት፣ የፈጠራ ስራ ሰርቶባቸው ቢሆን ኖሮ፣ ምን ያሳየን ነበር የሚል ቁጭት ይፈጥራል፡፡
ቀደም ብዬ እኔም የነገርኩት ይህንኑ ነበር:: የትርጉሙን ስራ ሌላ ሰው ይስራ፤ አንተ ልቦለዶች ጨምርልን ስለው እየሳቀ፣ የሰጠኝ መልስ፣ እኔን መልሶ ያሳቀኝ አልነበረም፡፡ ስለተዳፈነው የጥበብ ቋያ ልቤ አዝኖ ስለነበር በርካታ ማሳያዎችን ከዓለም ደራስያን ታሪክ እየወሰድኩ ላሳምነውም፣ ልማፀነውም ሞክሬ ነበር፡፡ ደረጀ በቀለ ትሁት፣ ቅንና ሰው አክባሪ የመሆኑን ያህል፣ ላመነበት ነገር ደግሞ ወደ ኋላ የማይል ነበር:: ይሁንና ያን የሙግት ጊዜ አልፎ ሕይወት በእውኑ ሲኖራት፣ ብዙ ነገሮችን አይቶ መንፈሳዊውን ነገር ከዚህ ከምንኖርበት ዓለም ጋር አጣጥሞ፣ መኖር መቻሉና መንፈሳዊነት ስጋን አራግፎ ጥሎ፣ መልዐክ መሆን አለማለት መሆኑን ሲገነዘብ “ሀገሬ በሰማይ ነው” የሚሉ ሰባኪያን፤ በዚህ ምድር ጥድፊያ ውስጥ የራሳቸውን ቤት ለመሥራት ጐንበስ ቀና ሲሉ፣ ነገሩን በጥሞና ሲያጣጥም #አ-ሃ” ብሎ በውስጡ የነበረውን ጥበብ ሊያወጣ የመጀመሪያውን ምጥ ሲያምጥ ዱብ ያለው “ታንጀሪና ሆቴልና ሌሎች ታሪኮች” ሳይታወቅ ከሕይወት መሰናበቻ ሥራው ሆነና አረፈው፡፡
እኔ ግን ይህን ስራ ሲሰራ ገና ብዙ ተስፋ፣ ገና ብዙ ጀንበር፣ ገና ብዙ አበቦች ፊት ለፊት እያየሁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ብዙ ይሠራል በሚል ጉጉት ስጠብቀው የነበረ ሰው ድንገት “ረገፈ” ሲባል ድንጋጤዬና ሃዘኔ ቀላል አልነበረም፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፌ ቀጥሮኝ በአዲሱ መጽሐፉ ላይ ፊርማውን አኑሮ “ካልጋበዝኩህ” ያለኝ ወዳጄን ደግሜ አገኘዋለሁ በሚል በችኮላ “ሌላ ጊዜ እንገናኛለን” ብዬው ለዘላለም ስላጣሁት ሰቀቀኑ አመመኝ፡፡ ያለወትሮው ኬፕ አድርጐ ፊቱ ላይ የህመም ስሜት ባይበትም እንደዚህ ያፋጥነዋል አላልኩም ነበርና ፀፀቱ በላኝ፡፡ በርግጥም ቸኩዬ ነበር፡፡ በማይመች ሁኔታ መኪና ይዞ የሚጠብቀኝ ወዳጄ “አደራ ፍጠን” ብሎኝ ነበርና ወጣሁ፡፡ ከዚያ በኋላ የሞቱን ዜና የሰማሁት ከልጁ የአብፀጋ ነው:: “ደረጀ በቀለ አርፏል፤ የምነግርህ ይወድህ ስለነበረ ነው” ስትለኝ ሰውነቴ ሁሉ መርገፉን አስታውሳለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ወጥቼ በረርኩ፤ በደመነፍስ ባንክ ገብቼ ስለነበር በመጻፍ አትችልም እንዴ እንደዚህ ነው የሚጻፈው ብሎ ሲያሳየኝ ምንም አላልኩም፡፡ ከንፈሬ ደርቆ ቃሌም ጠፍቶ ነበር “ይቅርታ ወዳጄ ሞቶ ነው” ስለው እንደገና ፃፈልኝና ላዳ ይዤ በረርኩ፡፡ ለካስ ሰው ሲደነግጥ የሚያውቀው ይጠፋዋል!?..
ቡልጋሪያ ሚካኤል ጋ ወርጄ ደወልኩና ወደ ቤቱ ሄድኩ፡፡ በቀኝ በኩል ገባሁ፤ ድንኳን ተጥሏል፡፡ ወደ ቤት ዘለቅሁ፣ ያ ባለ ህልም፣ ያ - የጥበብ አባት፣ ያ- መሀንዲስ በሳጥን ውስጥ ገብቶ ተኝቷል፡፡ በቅርቡ ስለ ብዙ ነገር ያወራልኝ ወዳጄ፤ ሁሉንም ነገር ትቶ ወደ መጨረሻ ቤቱ ሊጓዝ ሁሉን ነገር ጨርሷል፡፡
ደረጀ በ1951 ዓ.ም አዲስ አበባ ተወልዶ፣ በየነ መርዕድና ተፈሪ መኮንን ተምሯል፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኬሚካል ምህንድስና ተመርቆ በሞያው አገልግሏል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በብዕር ስምና በተፀውዖ ስም፣ በርካታ መጣጥፎቹን ጽፏል፣ በየቀበሌው ለመድረክ የበቁ ቴአትሮችንም ጽፏል፡፡ የዘፈን ግጥሞችን የጻፈላቸው ድምፃውያን እንደነበሩም በልቅሶ ድንኳን ውስጥ ሰምቻለሁ፡፡
በጣም የሚገርመው ግን ደረጀ አንዲት ጽሑፍ እንደፃፈ ሰው እንኳ የሠርቻለሁ ዐይነት ኩራት አላየሁበትም፡፡ ከሚገባው በላይ ትሁት ነው፡፡ ሲናገር እንኳ ድምፁ ብዙ አይሰማም፡፡ ዐይነ አፋር ነው፡፡ ወደ አደባባይ ከመውጣት ይልቅ፣ ጓዳ ጓዳውን መሥራት ይወድዳል፡፡ ስለዚህም አደባባይ ላይ ብዙዎች አያውቁትም፡፡ “ሕያው ፍቅር” በሚለው መጽሐፉ ግን እንደ ነፍሳቸው የሚወዱት ሰዎች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ ከቅርብ ወዳጆቼ ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፤ ደረጀ በቀለን አገኘሁት ያልኩት ቀን እንዴት ባለ ስሜትና አድናቆት እንደጠየቀኝ አልረሳውም፡፡ “ሕያው ፍቅርን ፈጽሞ አልረሳውም” እያለ በተፍለቀለቀ ስሜት ነበር ያስታወሰው፤ በጣም እንደሚወድደውም ነግሮኛል፡፡
ሌላው ወዳጄ ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬ አብሮኝ ሳለ ስልክ አንስቼ ካወራሁ በኋላ “አብሬህ ልሂድ” ሲለኝ ተስማምቼ ወስጄው ነበር፡፡ “ይህን ሰው በማግኘቴ ዕድለኛ ነኝ” ብሎኛል:: ፀባዩንና ንግግሩን፣ እንዲሁም  አስተሳሰቡን አድንቆታል፡፡ ደረጀን በቅንነቱ በእጅጉ የጐዱት ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ የእርሱ የዋህነትና ቅንነት አራምባና ቆቦ ሆኖበት፤ እርሱ ለአምላኩ፣ እነርሱ ለብር እንደቆሙ ሳያውቅ ከርሞ በኋላ ላይ ልቡ ተሰብሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የጐዱትን ሰዎችና የተፈፀመበትን እንኳ ለመናገር አልፈለገም፡፡ በእጅጉ የገረመኝም ያ ነው፡፡ እንደሚታረድ በግ ዝም ብሎ መነዳት ከክርስቶስ በቀር ማን አድርጐታል? ደረጀ ግን እንደዚያ ዐይነት ሰው ነበር፡፡ እርሱ በተጐዳው እኔ ስነድድ፣ እርሱ ሀዘኑን ውጦ ዝም ይላል፡፡
በማዕድን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አብሮት የሠራው ታላቅ ወንድሜ፤ ሰሞኑን በስልክ ያወራልኝም ይህንኑ ነው፡፡ ዘመኑን ሁሉ ጭምት፣ ሰዎችን ሁሉ የሚያምን፣ የቀና ሃሳብ ያለው እንደሆነ ነግሮኛል፡፡
ይሁንና መልካም ሰውም በክፉ ሰዎች ወጥመድ ይወድቃል፡፡ ግን ደግሞ ሁሉም ነገር ያልፋልና ደረጀ በቀለም የዚህ ዓለም ሩጫውን ጨርሶ ወደሚቀጥለውና ተስፋ ወደሚያደርገው ዓለም ሄዷል፡፡ ወደዚያ ዓለም ሁላችንም እንሄዳለን፡፡ ደበበ ሰይፉ እንደሚለው፤ የእጁን ዘር በትኗል፡፡ ለኛ የሚሰጠንን ሰጥቶናል፡፡ ቅንነትና ፍቅርን ላቀረቡት አስተምሯል፤ በትዕግስት ማዕበሉን ፀጥ አሰኝቷል፡፡
ደረጀ  በቀለ ትዳር መሥርቶ አምስት ልጆችን አፍርቷል፤ በሥጋው ዘር ተክቷል:: በስራው ደግሞ በሁላችን ልብ ውስጥ  ይኖራል፡፡ እኛም የየራሳችን ተራ እስኪደርስ የእጃችንን እንዘራለን፡፡ ሕይወት እንዲህ ይቀጥላል፡፡ እኔም ጽሁፌን ከደረጀ በቀለ "ሕያው ፍቅር" በጠቀስኩት ሃሳብ እቋጫለሁ፡፡  
"ለካስ ሞት ምንም አያምም፣ አያስጨንቅም፣ ልክ በደመና ላይ ክንፎቹን እያራገበ እንደሚያንሳፍፍ አሞራ መሆን መቻል ነው፡፡ አቤት ፀጥታው! አቤት እፎይታው! ሁሉም ነገር እንዲህ ነው፤ እንዲህ ያበቃል! ፍቅር …ቅንነት…ትህትና…ግን በሰው ልብ የሚንቀለቀል ጧፍ ሆኖ ይቆያልና መልካሙን ተምረን፣ መልካሙን እንኑረው::"

Read 1630 times