Print this page
Saturday, 08 August 2020 14:09

ምክንያታዊ አማኝ

Written by  ወጋየሁ ማዴቦ
Rate this item
(6 votes)

ባንዱ እሁድ ተጋባዥ የነበረው ሰባኪ፤”ከጎናችሁ ላለ ሰው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ንገሩት”ብሎ አዘዘን፡፡ ቸርች ውስጥ ሆኜ ከጎኔ ያለውን ሰው ልብ ብዬ አይቼ አላውቅም ነበር…በግራ በኩል መተላለፊያ ስለነበር ወደ ቀኝ ስዞር እንደ ትንግርት የምታምር ልጅ የምለውን ልትሰማ እየጠበቀችኝ ነበር…ይህን ውበት ሳላይ እስካሁን በመቆየቴ ሳልጸጸት አልቀረሁም…”ርብቃ ወደ ይስሃቅ ድንኩዋን ገባች; አልኳት… የነበረውን ታላቅ ጉርምርምታ ሰንጥቆ ያለፈ ሳቋን፣ ሩቅ መድረኩ ላይ የቆመው ሰባኪ እንኳን ሰማት…”እንደዚህ የሚያስቅ ጥቅስ ባይብል ውስጥ መኖሩን እጠራጠራለሁኝ” ብሎ ወደ እኛ  አቅጣጫ ጣቱን ሲጠቁም፣ ምእመኑ  ሁሉ ተከትሎት ሳቀ፡፡
ሰባኪው ወደ እለቱ ስብከት ቢገባም፣ እኔ ውበትዋን ሳደንቅ ስብከቱ እያለፈኝ ነበር…ይባስ ብሎ ድንገት ስልኬ ቆረቆረኝ…ዛሬ የጸሎት ቀኔ አይደለም…ወደ ጆሮዋ ጠጋ ብዬ  “እዚሁ ወንበር ላይ ሳምንት እጠብቅሻለሁ  ርብቃ" አልኳትና ተነሳሁ፡፡ አሁንም ሳቅዋ ሊያመልጣት ነበር፡፡
በሳምንቱ ከጎኔ ያለውን ወንበር ሌላ ሰው እንዳይቀመጥበት ስከላከልላት አርፍዳም ቢሆን ትመጣለች የሚል ሙሉ እምነት ነበረኝ… በሰአቱ መጣች…”ቦታ እንደምትይዝልኝ ገምቼ ነበር” አለች በሽኩሽኩታ… “መገመት ሳይሆን እርግጠኛ መሆን ነበረብሽ” አልኳት፡፡
ኳየሩ አስመለከን....መባው ተሰበሰበ..ስብከቱ ቀጠለ…በተመስጦ ውስጥ ነበረች…ሰባኪው መደበኛ ሰአቱን በ10 ደቂቃ አልፎታል…የኔ መቀመጫ ምርጫ ጠቀሜታው ይሄኔ ነው..አስመላኪው አዝማች እየቀያየረ ባዶ ጩኸት ካስጮኸን ..ሰባኪው የሚለው ነገር ነፍሴ ውስጥ ጠብ አልል ካለ…አስቸኳይ ነገር ካጋጠመኝ…በተለይ በተለይ ሰባኪ መደበኛ ሰአቱን ካሳለፈ.. ማንንም ሳልረብሽ መተላለፍያ ላይ ካለችው የለመድኳት ወንበር ላይ ብድግ ብዬ እብስ ነው!!  ለመነሳት ስሰናዳ እንድቀመጥ በምልክት አዘዘችኝ… ስልኬም ደጋግሞ ቢነዝርም ..ሰባኪውም 20 ደቂቃ ቢያሳልፍም፣ የኔ እጣ የቆንጆይቱን ትእዛዝ መፈጸም ነበር፡፡
ወደ ውጭ ስንወጣ ያለው የተለመደ  ግፍያ ..ሰባኪዎቻችን በየቀኑ የሚሰብኩንን ..”መኖርያችን በሰማይ ነው…ሁሉም ነገር ከንቱ ነው..” የሚለውን  ይቃረናል፡፡ ምክንያቱም ምንም ነገር ከንቱ ላለመሆኑ ሩጫችን ማረጋገጫ ነው፡፡ እርቦኝ ስለነበር ምርጫዋን ሳልጠይቅ ወደ ቃተኛ አቅጣጫ ስመራት ስልኬ ኪሴን እየጠበጠበኝ ነበር፡፡ ደጋግሜ ሳየሁ ስለነበር፤
"ለምን አታነሳውም?" አለችኝ…
"ካነሳሁት ጥየሽ እሄዳለሁ ብዬ ነው"
"ገርል ፍሬንድህ ናት?"
"አይደለችም ቦይ ፍሬንዶቼ ናቸው"….
ትንሽ ግር አላት…
"ፍሬንዶች አሉኝ …ኮመን ነገር አለን..አርፍጄባቸው ነው፡፡ ለመሆኑ ስምሽ ርብቃ ነው…እኔ እያሱ እባላለሁ…" አልኳት ታጥበን እየተቀመጥን…
"ስም ሳይተዋወቁ ገበታ የቀረቡ የመጀመሪያዎቹ  ወንድና ሴት ሳንሆን አንቀርም፡፡ …ስሜ ርብቃ ቢሆን ብዬ የተመኘሁበት ሳምንት ነበር…ጣፋጭ እባላለሁ፡፡"
“ሃጢያት ጣፋጭ ናት…”ይላል… አልኳት አፌ እንዳመጣልኝ…
2
"ይህም ጥቅስ ዘፍጥረት ላይ ነው የተፃፈው?" አለች በሳቅ ታጅባ
"በዕውቀቱ ስዩም ነው ያለው…" አልኳት፡፡
"ቸርች ብዙ ጊዜ ትመጣለህ?"
"ላለፉት አምስት አመታት በነበሩት እሁዶች በሙሉ… መጥቻለሁ ማለት እችላለሁ"
"መቀመጫ መርጠህ የምትቀመጠው አቋርጠህ ለመውጣት እንዲመችህ ነው?"
"የሚያስወጣኝ በቂ ምክንያት ካለ መውጣቴ እማይቀር ነዉ… እማይመቸኝ ነገር ካለ መታገስ አልችልም…በዛ ላይ ስልቹ ነኝ…ሰአቱን ያላከበረ የትኛውንም ፕሮግራም አቋርጣለሁ…የራሴ የሆነም ጣጣ አለብኝ..ብቻ ችግሮች አሉ፡፡"
"ጀጅ እንዳላደርግህ… ሶሪ..! ግን እምነትህን ኮምፕሮማይዝ ማድረግ የለብህም… ማመን መታዘዝ ነው…! መታገስ ነው..! ሃላፊነት መውሰድ ነው…!" አለችኝ፡፡
ልክ ናት..ሰዎች ደጀሰላም ረግጬ የማውቅም አይመስላቸውም…በባህርዬ መሆን አለበት…ነገርን ቀለል ማድረግ እወዳለሁኝ፡፡
ምሳችን ቀረበ፡፡
"ትፀልያለህ …?" በትህትና ጠየቀችኝ
"እንፀልያለን!" ብያት እጆችዋን አፈፍ አደረግሁና "ከኔ ቀጥሎ በይ" አልኳት…
"እሺ!" አለች
"መግባትና መውጣታችሁን እጠብቃለሁ… መግባትና መውጣታችሁን እጠብቃለሁ…"
"ክፉ ነገር አያገኛችሁም….ክፉ ነገር አያገኛችሁም…".
"የዘመናችሁን ቁጥር አበዛዋለሁ….የዘመናችሁን ቁጥር አበዛዋለሁ…"
"እህልና ውሃችሁን እባርካለሁ…እህልና ውሃችሁን እባርካለሁ…ያልከን አምላክ ይህን ማዕድ ባርክልን!"
"አሜን!!...አሜን!!..."
እጆችዋን ወደ ቦታቸው ካልመለስኩላት እራስዋ የምትመልሳቸው አልመሰለኝም፡፡ ከገበታው ላይ አነስ ያለች ጉርሻ አዘጋጅቼ ሳያት ሳታንገራግር ለመጉረስ ተዘጋጀች…ከኔ ጋር ገበታ የቀረበች ማንኛውም እንስት የመጀመርያ ጉርሻ መጉረስ የውዴታ ግዴታዋ ነው፡፡
3
"ከጓደኞችህ ጋር የለመዳችሁት ነገር ምንድን ነው…ሱስ ምናምን…ነዉ..?"
"አዎን ሱስ ነው"
"ምን…?? ....እቅማለሁ ምናምን ካልከኝ እጮሃለሁ…"
"ያው በይው…ቁማር ነው፡፡"
"ቁማር…? በገንዘብ…? ካራምቡላ ምናምን…?" ትንሽ ቀለል አለላት…
"የቁማር ሱስ ከጫት ሱስ የተሻለ ነው እንዴ..?"
"ካርታ እንጫወታለን…ኮንከር ይባላል…ብዙ ገንዘብ አስይዘን ነው የምንጫወተው…እኔ የኮንከር  ልክፍት አለብኝ..ካርታ ሲበወዝ ከሰማሁ ገደልም ቢሆን እገባለሁ፡፡"
"ቢሆንም ከጫትና ከመጠጥ ሱስ ይሻላል" አለች
"አይመስለኝም…መቃም የጊዜ ገደብና የስሜት መርካት ስላለበት በቀን ውስጥ የተወሰነ ጊዜ አለው፡፡ መጠጥም ቢሆን ገደብ አለው….ኮንከር ግን ጌሙ እስካልፈረሰና ገንዘብ እስካለሽ ድረስ 24 ሰአት መጫወት ትችያለሽ፡፡"
"ቢሆንም ይሻላል" በሚል ቀለል አድርጋ ሰማችኝ፡፡
ስልኬ እረፍት ሲያሳጣኝ የመጨረሻውን ቴክስት አሳየዃት፡-
“ካርታ ያስቀረችህ ባለፈው ሳምንት የተዋወካት ልጅ መሆን አለባት…” የሚል ነበር፡፡.
ሳቅ ብላ፤ "የተዋወቅነው እኮ ዛሬ ነው" አለችኝ…
"እኔ ያወቅኩሽ ባለፈው ሳምንት ነበር" አልኳት፡፡
ምሳውን ስንጨርስ ልቤ ተንጠልጥሎ ነበር…
“የት ነው ሰፈርሽ?.. የት ላድርስሽ?"… አልኳት…ወደ መኪናዬ እየተመለሰን…
"ሳትዋሸኝ ንገረኝ…እነሱ ጋ ለመሄድ ቸኩለሃል አይደል..?"
"አዎን…ይቅርታ!"
"ችግር የለም…ሂድ..እኔ ታክሲ እይዛለሁ…"
"ኖ..ኖ..እሸኝሻለሁ..ፕሊስ.."
"እውነቱን ስለነገርከኝ ደስ ብሎኛል..ሳምንት እንዳትቀር--" ጉንጬ ላይ ሳመችኝ::
ከነፍኩኝ ወደ ሳሪስ…ካርታው እየተበወዘ ነው…..
ከዛ በዃላ በነበሩት ጥቂት እሁዶች ሁሉንም ፕሮግራሞች ጨርሼ አብርያት ወጥቻለሁ…ቤላና ቃተኛ ድረስ ዎክ እያደረግን ምሳ በልተንባቸዋል …ቶሞካ ማኪያቶ ጠጥተንባቸዋል.. የፈለግችበት… የምትሄድበት ቦታ አድርሽያታለሁ… ከዚያ እንደ ጀት ወደ ሳሪስ በርሬባቸዋለሁ፡፡ ለሁለታችንም ውድ ከሆኑት እሁዶች አንዷን አጎደልኩባትና ኮንከር ላይ ተጥጅበት ስልኳን ሳላነሳ በዋልኩበት አዙሪታም ሰንበት፤ ድንገት አምስት ወንዶች ግጥግጥ ያልንባት በር ተከፈተችና ደጀሰላም የማውቃት ባለ ውብ አይኖች ልጅ ዘው አለች:: የተሰደረውን ካርታዬን እንደያዝኩ ብድግ አልኩኝ...
“ጸሎት ማቋረጥ ከቻልክ ካርታ ጫወታ ማቋረጥ መቻል አለብህ” ጥያቄ የሚመስል ትእዛዝ ነበር፡፡
ሁኔታው  ወላጅ እናቴ ያፋጠጠችኝ ያህል አስጨናቂ ቢሆንብኝም ተረጋግቼ፤
"አንድ ነገር ብቻ ልጠይቅሽ…? እባክሽን…!" አልኳት ..የልመና ያህል ነበር
"እሺ ጠይቀኝ--"
"ኮንከር  ተጫውተሽ  ታውቂያለሽ?"
"አዎን!"
"ይህን ካርታ እይዉ…" ብዬ ሰጠኋት
አይታው ስትጨርስ.. ”ጨርሰሃል እኮ" አለችኝ… በጥያቄ ምልክት….
"ለጆከር እየዞርኩ ነው..ዙሩ ይድረስኝና እንሄዳለን…" ብዬ ተማጸንኳት…
እሺታ ነበር የጠበቅሁት፡፡
"አይቻልም…ውጣ!"
ያሸንፍኩትን ጨዋታ ተሸንፌና ተበልቼ ወጣሁላት፡፡
በመንገዳችን ሁሉ ሳስበው የነበረው…አንድ በጣም  የምወደውን ነገር ሌላ ልውደደዉ አልውደደዉ እርግጠኛ ያልሆንኩበት ነገር ሊተካው ነፍሴ ውስጥ የተጀመረውን ትግል ነበር፡፡
***
ሳምንት ጠብቀን የምንገናኝበት ቸርች በኮሮና ምክንያት ሲዘጋ፣ ካርታውም  እስከ ወዲያኛው ሲቀር ድምጸ ሻካራዋን ልጅ ማግኘት የምችለው በስልክ ብቻ ሆነና አረፈው፡፡ …ጠረንዋን አላውቀውም…ሙቀትዋን አልሞቅሁትም… ገላዋን አልዳበስኩትም…. ግን ..ለዘመናት ከታሰርኩበት የኮንከር ልክፍት እንደ ዘበት ጎትታ ነጻ ያወጣችኝ ልጅ…በውስጤ ገዝፋ …ለዘመናት የማውቃት ይመስል ናፈቀችኝ……ግን ይህ መአት መች ይሆን የሚያልፈው…???
"ምን ታስባለህ…ስለ እኔ…?" በተለመደው ስልክ ተጠየቅሁኝ
"ናፍቀሽኛል…በጣም ወድጄሻለሁ…ምን ላስብ?"
"ለምን አንገናኝም?"
"የትና እንዴት እንገናኛለን..ካፌው …ሆቴሉ ሁሉ ሴፍ አይደለምኮ?"
"በቃ? ይሄ ነው?"
"የተለየ ሀሳብ ምን ሊኖር  ይችላል…? ኢንተርኔት አክሰስ እንዲኖርሽ እያሰብኩ ነው፤ ከተሳካ በቪዲዮ ኮል እንደልብ መገናኘት እንችላለን፡፡"
"ለምን ቤትህ አልመጣም?"
ደነገጥኩኝ…
“ክትባት ተገኘ እንዴ?" ልላት ነበር…”ይህ ነገር መላ ሳይገኝለት መገናኘት አይከብድም..?" አልኳት
“አንተ ክርስትያን አይደለህም…? የምታመልከው አምላክ በእሳት ውስጥ እንደሚያሻግርህ አታምንም?”
ይሄኔ ነው መሸሽ…..
"….የኔ ጣፋጭ…ለጆከር እየዞርኩኝ ተበልቼ ስወጣ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር…ባንቺ ውስጥ ነገዬን አይቼዉ ነበር… እኔ ምክንያታዊ አማኝ ነኝ…አልማዝ ለመሸጥ መርቁልኝ ብዬ ነብይ ዘንድ አልወስድም…ያንተን አልማዝ የሆነ ሰው ጂጂጋ ይዞት እየዞረ ነው ብባል አላምንም…ተገንዞ ተከፍኖ የተቀበረ ሬሳ ይነሳል ተብዬ ጉድጓድ አልምስም…."
"ምንድነዉ እምነትህ?"
"በአምላክ አምናለሁ….!! ተገቢዉን ጥንቃቄ ካደረግን…በእሳት ውስጥ የሚያሻግረኝ አምላኬ ይህንን ክፉ ቀን አሳልፎን እንደምንገናኝ አምናለሁ…!! እናም ድንኳኔ ዉስጥ እንደምትገቢ አምናለሁ…..!!"
ረዥም ትንፋሽዋ ብቻ ነበር የሚሰማኝ….
"በነገራችን ላይ ባልንጀሮቼ ቤቱ በሳኒታይዘር እየጸዳ ማስክ እያደረግን ኮንከር እንጫወታለን እያሉ ቢጎተጉቱኝም አልሄድኩባቸውም…ይህ ያንቺ ውለታ ነው::"
ስልኩን ማናችን እንደዘጋነው አላስታውስም::


Read 3158 times