Wednesday, 12 August 2020 00:00

የግብጽ፣ ከባልሽ ባሌ ይበልጣል!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

    በጣም የታወቀ ምሳሌ ነው- "ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ"፡፡ ብድር ጠያቂዋ ሴት ማን አለብኝ ባይ ናት፡፡ መበደር የምትፈልገው የሌላትን ቢሆንም፣ የምትፈልገውን ነገር እንደ እሷ ፈላጊ ያለው አይመስላትም፡፡ ብድር ተጠያቂዋም እንዴት ተሞክሮ የሚል መንፈስ የሚታይባት ናት:: እንዲያውም የብድር ጥያቄውን ከንቀትና ከድፍረት አንጻር በማየት፣ እንዴት እንዲህ አይነት ጥያቄ ለእኔ ይቀርባል በሚል መንፈስ ደሟ እንደ ሞቀ እንረዳለን፡፡
በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ሲደረግ የቆየው  የሶስትዮሽ ድርድር ከአንድ እልባት ሊደርስ ያልቻለው፣ በተለይ ግብጽ በያዘችውና በተከተለችው "ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ሽሮ አበድሪኝ" መንገድና ለመለወጥ ባለመፈለጓም ነው፡፡ ግብጽ በድርድሩ ወደ ፊት እንዳትራመድ ያቀባትና በቆመችበት እንደተቸከለች እንድትቀር ያደረጋት ደግሞ እራሷ ወዳና ፈቅዳ እግሯ ላይ ያሰረችው ድንጋይ ነው፡፡ ያ ድንጋይ በ2006 ዓ.ም ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ተሻሽሎ የጸደቀው የግብጽ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 44፤ "የግብጽ መንግሥት የዓባይን (ናይል)  ወንዝና የግብጽን  ታሪካዊ የውኃ መብት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ውኃው እንዳይባክንና እንዳይበከል መጠበቅና እስከ መጨረሻው ድረስ ጥቅም ላይ ማዋል አለበት" ይላል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የግብጽ ሕገ መንግሥት፤ ውኃውን አገሪቱ ካላት የተፈጥሮ ሃብት እንደ አንዱ ነበር የሚቆጥረው፡፡
ዘሪሁን አበበ ይግዛው ከሰባት ዓመት በፊት በእንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሑፍ፤ ይሄ የግብጽ ሕገ መንግሥት ከግብጽ የግዛት ክልል አልፎ በሌሎች አገሮች ላይ የሚሠራ አለመሆኑን ጠቁመው፤ ሕጉ የቀድሞው የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር አሳም ሸሪፍ ችግሩን በውይይትና በድርድር ለመፍታት የጀመሩትን መንገድ የዘጋው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም፤ የዚህ አንቀጽ መኖር የግብጽን ተደራዳሪዎች የማይለወጡና ግትሮች እንዳደረጋቸው አስገንዝበዋል፡፡ ግብጽ በሕገ መንግሥቷ የዓባይን (ናይልን) ወንዝ የመጠበቅ ኃላፊነት ለራሷ ብትሰጥም፣ ከእሱ በላይ ሆኖ የሚሠራው ዓለም አቀፍ የወንዞች አጠቃቀም ሕግ (የሔልስንኪ ስምምነት) በመኖሩ፣ በሕገ መንግሥት መደንገጓ ከከንቱ ድካምነት እንደማይዘል ዘሪሁን አስምረውበታል፡፡  
"ግብጾች አባቶቻቸው የሠሩትን ስህተት ደገሙት" የሚሉት ዘሪሁን አበበ፤ ግብጾች እንደ አቡነ ዘበሰማያት  የሚደግሙትን "ታሪካዊ የውኃ የባለቤትነት መብት" የሌለ ነገር ነው በማለት ከማጣጣላቸውም በላይ  "ግብጾች መኖር የሚፈልጉት በ21ኛው ከፍለ ዘመን ነው ወይስ በ19ኛው?" የሚል ጥያቄ እስከ ማንሳት ድረስም  ሄደዋል፡፡ እኔ ደግሞ  ይህ ሕገ መንግሥት ድርድሩን እያወከ መሆኑን ተደራዳሪዎቻችን በታዛቢዎች ፊት ደጋግመው በማጋለጥ፣ የግብጽን የትዕቢት ቆብ እንዲቀዱ አደራ እላለሁ፡፡
ግብጽን ከ19ኛው ከፍለ ዘመን ጋር አጣብቆ ያስቀራት ደግሞ፣ እ.ኤ.አ በ1929 ላይ የግብጽና የሱዳን ቅኝ ገዥ የነበረችው ታላቋ ብሪታኒያ፣ በሱዳን ስም ከግብጽ ጋር ያደረገችው እጅግ ሲበዛ ለግብጽ ያደላ ስምምነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ "የግብጽ የውኃ ድርሻዎች መጓዝ ካለባቸው ረጅም ርቀት የተነሳ ለበለጠ ብክነት የሚዳረገውን ውኃ ሱዳን ትከፍላለች" የሚለውን በስምምነቱ ተራ ቁጥር 17 ላይ የሰፈረውን ሃሳብ ማየት አድሏዊነቱን ለማረጋገጥ  ይበጃል፡፡ ዛሬም ግብጽ እንዲህ አይነት አደግዳጊ ውል እንዲታሠርላት እየቋመጠች እንደሆነ ነገረ ሥራዋ ይመሰክራል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና ተደራዳሪዎች  ለምንም አይነት አሳሪ ውል እጅ ላለመስጠት የሚያደርጉት ትግል አበጃችሁ የሚያሰኝ ነው፡፡
የግብጽ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 44  የተሠራበት ጥሬ እቃ የተገኘው እ.ኤ.አ የ1929ኙን ውል ካሻሻለው በግብጽና ሱዳን መካከል እ.ኤ.አ በ1959 ከተደረገው ስምምነት ነው፡፡ ይህ ስምምነት በተራ ቁጥር ሁለት በንዑስ ቁጥር አራት ላይ የአባይን (ናይልን) አጠቃላይ ውኃ 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለሱዳን፣ 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለግብጽ ከሰጠ በኋላ ምንም አይነት ድርሻ ለላይኞቹ የተፋሰሱ አገሮች አለመተዉ የታወቀ ነው፡፡  ይህ ስምምነት በተራ ቁጥር አምስት ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ፤ ‹‹ከሁለቱ ሪፖብሊኮች ሌላ፣ የውኃ ተጋሪ አገሮች ከዓባይ (ናይል) ውኃዎች ድርሻቸውን ቢጠይቁ፣ ሁለቱ ሪፖብሊኮች ይህንኑ ጉዳይ ለማጤንና ከአንድ አመለካከት ለመድረስ ተስማምተዋል:: ከዓባይ (ናይል) ውኃ የተወሰነ መጠን ለተጠቀሱት አገሮች ለአንዱ ወይም ለሌላው እንዲሰጥ ተቀባይነት ካገኘ፣ ተቀባይነት ያገኘው የውኃ መጠን አስዋን ላይ በሚደረግ ስሌት መሠረት፣ ከሁለቱ አገሮች ድርሻዎች እኩል በኩል ተቀናሽ ይሆናል›› በማለት ማስፈሩን ገብረ ጻድቅ ደገፉ ‹‹ናይል፤ ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ልማታዊ ገጽታዎች ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ማስጠንቀቂያ›› በተባለው መጽሐፋቸው ገልጠዋል፡፡  ይህ ማለት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለላይኛዎቹ የተፋሰሱ አገሮች የውኃ ድርሻ የሚደለድሉት እነሱ ሆኑ ማለት ነው፤ ለዚያውም ፈቃዳቸው ከሆነ፡፡
ይህን ድርድር ሲከታተል የነበረው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መስከረም 12 ቀን 1949 (ሴፕቴምበር 23/1957) በጻፈውና  በካይሮ የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲሁም ለግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲደርስ ባደረገው ማስታወሻ፤ ኢትዮጵያ  84 ከመቶ የሚሆነውን ውኃ ብቻ ሳይሆን አካባቢውን የሚያዳብረውን ለም አፈር ጭምር እንደምትሰጥ አመልክቶ፣ ቀደም ሲል ጥር 29 ቀን 1948 ዓ.ም የሰጠው መግለጫ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስቧል:: አያይዞም፤ ውኃውን ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ እንዳሉ ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ሁሉ እንደሚያየውና  ኢትዮጵያ በንጉሣዊ ግዛቷ ያላትን  የውኃ ሃብቶች ጥቅም ላይ ለማዋል መብት እንዳላት፣ መጠቀምም ግዴታዋ እንደሆነ  ግልጽ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ውኃዎቹ ለደህንነቱ ያላቸውን ጠቃሚነትና አስፈላጊነት እንደሚገነዘብ ጠቁሞ፤  የተፈጥሮ ሃብቱ እያደገ ከሚሄደው የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ ፍላጎት ጋር  እንደሚያያዝ አስረድቷል፡፡  ቅድሚያ ለብሔራዊ ፍላጎት መሟላት እንደሚሰጥ  ያስገነዘበው  የኢትዮጵያ መንግሥት፤  በዓባይ ዳርቻ ለሚገኙ አጎራባች እህት አገር ነዋሪዎች፤ ጥቅም የሚሆን በማበርከቱ እንደሚደሰት አሳውቋል፡፡
ወደ ሥረ ነገሩ እንመለስ፡፡ ሱዳንና ግብጽ የ1959ኙን ውል የተዋዋሉት፣ ሱዳን ነጻነቷን ባገኘች ጊዜ የ1929ኙን ውል እንደማትቀበል በመግለጧ ነው፡፡ በኋላ ነጻ የወጡት የተፋሰሱ አባል አገሮች ይህን ውል እንደማይቀበሉ አረጋግጠዋል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ጉዳዩ እኔንም ይመለከታል እያለች በድርድሩ እንዳትገባ ያደረጉት ሁለቱ አገሮች ናቸው፡፡ ዛሬ ጥያቄአቸው የውኃ ከፍፍል ከሆነ  ሶስቱም አገሮች የ1959ኙን የውኃ ውል እንደ አዲስ መዋዋል እንዳለባቸው ኢትዮጵያ ረገጥ አድርጋ ብትነግራቸው እወዳለሁ፡፡ ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2012 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮፓ ኅብረት ታዛቢነት የተደረገው የሶስቱ አገሮች ድርድር መቋረጡን ፣ ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት የውኃ ውሎች  (እሷን ባይመለከቷትም) ፈርሰው አዲስ ውል እንዋዋል የሚል ሃሳብ በማቅረቧ፣ ግብጽና ሱዳን ከድርድሩ መውጣታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ከካይሮ  ዘግቧል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት  አዲስ  የመደራደሪያ ሃሳብ ማቅረቡን ልዩ ልዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡ ሃሳቡ የቅኝ ግዛት ውሉን አፍርሰን አዲስ እንደራደር ከሆነ (የተጠራጠርኩት ሌላ መረጃ ስለሌለኝ ነው)፣ በደስታ እጄ እስኪላጥ አጨበጭባለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የውኃ ሕግ ማለትም ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲሁም በታችኛው አገሮች የከፋ ጉዳት ያለ ማድረስ መርህን ተከትላ፣ በውኃ ሃብቷ ለመጠቀም እየሠራች ነው:: ግብጽና ሱዳን የሚያቀርቡት በድርቅና በተከታታይ ድርቅ ጊዜ ከሕዳሴው ግድብ የውኃ ይለቀቅልን ጥያቄ፤ ከባልሽ ባሌ ይበልጣል ነው፡፡ እሷም ውኃ ስለሚያስፈልጋት ኢትዮጵያም በድርቅ ጊዜ በግድቧ ያለውን ውኃ ቆጥባ መጠቀም አለባት፡፡ ስለዚህም ጥያቄው ተቀባይነት ማግኘት የለበትም፡፡ ዓለም የደረሰበት ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ድርቅና ተከታታይ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ለመረዳት ስለሚያስችል ሱዳንና ግብጽም  መጠንቀቅና  ችግሩን  ለመቋቋም  በእጃቸው ያለውን ውኃ ቆጥበው መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በምንም መንገድ የኢትዮጵያ ሸክም  እንዲሆኑ እድል ሊሰጣቸው አይገባም፡፡
በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ማኅበር የጸጥታው ምክር ቤት፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ  የመጀመሪያ ሙሌት ላይ ክርክር መከፈቱ ይታወሳል፡፡
አልጄዚራ በቀጥታ ስላሰራጨው ለመከታተል ችያለሁ:: የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ግማሽ ሰዓት ወስደው ለምክር ቤቱ ያስረዱት፣ ከላይ የጠቀስኳቸውን ውሎች ኢትዮጵያ አለማክበሯን ነበር:: አልተሳካም እንጂ  እንድትፈጽማቸው እንድትገደድ የሚችሉትን ያህል ጎትጉተዋል::  መንግሥትና ተደራዳሪዎቻችን እነዚህ ውሎች በኢትዮጵያ ላይ እንደማይሰሩ የሚያስረዳ የበሰለ ጥናት እንዳላቸው አልጠራጠርም:: እንደ እኔ፤ አጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ሰበብ እየተፈለገለትም ቢሆን፣ መረጃው ለሁሉም ያለ መታከትና መሰላቸት መዳረስ አለበት:: ከዚህም አልፎ በየአህጉሩ ለሚገኙ  የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችና ኢትዮጵያዊያን ሊዳረስም ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለሀገሩ ጥሩ ዲፕሎማት መሆን የሚችለው በመረጃ ሲታገዝ መሆኑም ዋጋ ሊሰጠው ይገባል፡፡
 ቸር እንሰንብት!


Read 1678 times