Sunday, 09 August 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


             የዓባይ ግድብ
(መስፍን ወልደ ማርያም)
የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያን ገፍቶ ወደ ፊትና ወደ ላይ እንደሚያስፈነጥራት ሳይታለም የተፈታ ነው፤ እንደ ልብ በርካሽ የሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለቤት መሆን ብዙ የልማት በሮችን ይከፍታል፤ እንጀራ ጋጋሪ ሴቶችም በኮሬንቲ ምጣድ እንጀራም ወጥም እንደሚሠሩ በቲቪ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎችም በኩል የሚደረገው እመርታ ብዙ ተነግሮለታል፤ ምንም አያጠራጥርም፡፡
ነገር ግን አንድ እንደሚመስለኝ ያልታሰበበትና እኛ የሌለን ጠባይ አለ፤ ይህ ጠባይ ለኢንዱስትሪ ልማት ቁልፍ ነው፤ ይህንን ጠባይ ይዘን በኢንዱስትሪ ለመልማት መሞከር የማያዛልቅ ነው፤ አንዱና ዋናው ከኢንዱስትሪ ጋር የማይሄደው ጠባያችን ሰዓትን ማክበር ነው፤ እንኳን በኢትዮጵያና በአሜሪካ ለሠላሳና አርባ ዓመታት ቆይተው በሰባት ሰዓት ለተጠሩበት ሰርግ በዘጠኝ የሚመጡ ብዙ ናቸው፤ በስምንት ሰዓት ለተጠራው ስብሰባ ጥቂቶች በአሥራ ሁለት ሲደርሱ አይቻለሁ፡፡
ለጊዜ መለኪያ አለው፤ ለመሬት መለኪያ አለው፤ ለእንጨትም ሆነ ለብረት መለኪያ አለው፤ ለጤፍም ሆነ ለገብስ መለኪያ አለው፤ ለዘይት ሆነ ለውሀ መለኪያ አለው፤ ሥጋ መለኪያ አለው፤ በረጅሙ ታሪካችን መለኪያዎችን አልፈጠርንም:: የሚጎድሉን ሌሎችም ጠባዮች አሉ:: መለካት ባለመቻል የተነሣ በርም ሆነ መስኮት፣ ቁም-ሣጥንም ሆነ ጠረጴዛ መጋጠሚያው ላይ ሁሌም ችግር አለ፡፡
አንድ ሌላ ለኢንዱስትሪ ልማት አስፈላጊ የሆነ ጠባይ ትብብር ነው፡፡
እንግዲህ የዓባይን ግድብ ሙሉ ጥቅሙን እንድናገኝ ከፈለግን፣ ጠባያችንን ማሳመር ያሻል! ለዚህ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን፣ ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ሠራኞች ሁሉ ተማሪዎች መሆን ያስፈልጋቸዋል፤ አገዛዙ ከአሁኑ ቢያስብበትና አስተማሪዎችን ቢያሠለጥን መልካም ይመስለኛል፡፡
(ሐምሌ 2012)
የቴዲ አፍሮ ፖስተር ወኔ-ቢሱና ዓይነአፋሩ ባንዲራ!
(ጌታሁን ሄራሞ)
እ. ኤ.አ በ1692 የፈረንሳዩ ንጉስ Louis XIV ከሥልጣን የተወገደውን ወዳጁንና ካቶሊኩን የእንግሊዙን ንጉስ “James II”ን ወደ መንበሩ ለመመለስ እንግሊዝ ላይ ጦርነት ከፈተ። እንግሊዝም በአፀፌታው የፕሮቴስታንት ወዳጇ የሆነችውን ኔዘርላንድን ከጎኗ አሰልፋ La Hogue ተብሎ በሚጠራው ሰሜናዊ የፈረንሳይ ባሕር ዳር አካባቢ ጦሯን አሰፈረች። ከአምስት ቀናት ጦርነት በኋላ ፈረንሳይ ድባቅ ተመታች። ጦርነቱም በታሪክ ውስጥ “The Battle of L Hogue” ተብሎ ይጠራል።
ዓላማዬ ስለዚህ ጦርነት መተረክ አይደለም፣ ዋና ትኩረቴ በዚሁ ጦርነት የፈረንሳይ ጦር የተጎነጨውን የሽንፈት ፅዋ በታሪክ ነክ የሥዕል ሥራዎቹ የሚታወቀው አሜሪካዊዉ ቤንጃሚን ዌስት(1738_1820) የገለፀበትን ጥበባዊ መንገድ ጠቁሜ፣ በዚያው ሰሞኑን በቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ፖስተሩ ላይ በተለቀቀው የባንዲራ ምስል ላይ የበኩሌን ለመሰንዘር ነው። የቤንጃሚን ሥዕል ሙሉ ዕይታ ከሥር ፎቶ 1 ላይ ያስቀመጥኩት ሲሆን ትኩረቴን የሳበውን የሥዕሉን ክፍል ደግሞ ፎቶ 2 ላይ “Zoom-in” አድርጌ አስቀምጬዋለሁ። ታዲያ ቤንጃሚን ዌስት የፈረንሳይን ሽንፈት የገለጠው የባንዲራውን ወኔ ሰልቦ ወደ ታች ቁልቁል እንዲዘቀዘቅ በማድረግ ነበር። (ምንጭ፦ National Gallery of Art,Washington, 1992)
እስቲ የቴዲ አፍሮ ፖስተር ላይ ያለውን የባንዲራውን ቅርፅ ደግሞ ተመልከቱት (ፎቶ 3)፣ ባንዲራው በሙዚቃው ሊተላለፍ ከታሰበው የጀግንነት ወኔ በተቃራኒ ወደ ታች አጎንብሶ ልክ እንደ ፈረንሳዩ ባንዲራ ሽንፈትን የተጎነጨ ይመስላል። ይህ ዓይነቱ ዓይነ-አፋር የባንዲራ ቅርፅ የተሸናፊነት ሥነ ልቦና ማሳያ ነው። ስለዚህም በባንዲራው ወኔ-ቢስ ቅርፅና በቴዲ አፍሮ መልዕክት መካከል ከፍተኛ የሆነ ተቃርኖ አለ። ግራፊክ ዲዛይነሩ ባንዲራውን ቁልቁል ለምን እንደደፋው ጠፍቶኝ አይደለም፣ ከዚያች ከመከረኛዋ የመኸል ቅርፅ መኖር/አለመኖር የባንዲራ ፖለቲካ ንትርክ ገለልተኛ ለመሆን ሲባል ቅርፁ በዚህ መልኩ እንደተቀመጠም ይገባኛል።፣ ነገር ግን ለአንድ ችግር መፍትሔ መስጠት ያለብን በመፍትሔነት የተቀመጠው አቅጣጫ ሌላ የባሰ ችግር እንደማያመጣ አስቀድሞ በማስላት ጭምር መሆን አለበት..የመፍትሔው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን። ሌሎች ውጤታማ አማራጮችም መቅረብና ተግባራዊ መሆን ነበረባቸው።

Read 3343 times