Print this page
Monday, 10 August 2020 00:00

ነገርን ማጋጋል ሳይሆን ማብረድ፣ ብርቅ ሆኖብናል።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

• ነገርን የሚያጋግል ሳይሆን የሚያበርድ ሰው ሲገኝ፣ መልካም እድል ነው። እንዳይባክን ብንጠቀምበት ይሻለናል። እስካሁን በተደጋጋሚ እየባከነ፣ ለብዙ ጥፋት ተዳርገናል።
• ውዝግቦችና ብሽሽቆች ቀንከሌት እየተግለበለቡ፣ የእርጋታ እድሎች ደግሞ በከንቱ እየባከኑ፣ ስንቱን ጥፋትና ውድመት አስተናገድን? ይብቃን። በትግራይስ?
• ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፣ ነገር ለማብረድ የሚያግዙ ሃሳቦችን አቅርበዋል። ግን፣ በጐ ምላሽ ይኖራል ወይ? የሚል ነው ጥያቄው። ከሕወሀትም፣ ከብልፅግና ፓርቲም።
• “ነገር ሲበርድ”፣ የማሰብ ፋታ ይገኛል፤ ወደ ህሊና ለመመለስና ወደ ስልጣኔ ለመራመድ፤ ቢያንስ ደግሞ፣ ጨዋነትን ለማስታወስና በይሉኝታ አደብ ለመግዛት ይጠቅማል።
• በእርግጥ፣ ወደ “ስልጡን የሥነምግባር መርህ” ካልተሸጋገርን በቀር፣ “ጨዋነትና ይሉኝታ”፤ ለጊዜው እንጂ አያዛልቁም። ለነገሩ፣ “ጨዋነትና ይሉኝታ” እየተሸረሸሩ ነው።
• ምን ይሄ ብቻ። ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኗል። በተለይ፣ ከኑሮና ከስራ ትንሽ ስንወጣ፣ “በፖለቲካና በፌስቡክ ዓለም”፣ ተላካፊና ተሳዳቢ መሆን “ነጥብ” ያስገኛል።
• “ሳይደርሱበት አይደርስም”፣ “ከአፏ ነገር አይወጣትም”፣… ይባላል፤ የሰው ጨዋነት ሲገለጽ። “ተላካፊ ፀበኛ”፣ “ተሳዳቢ ነገረኛ” ላለመባል፣ “ቆጠብ ለዘብ” የማለት ልማድ ነው - የ“ይሉኝታ” ትርጉም።
• “ጨዋነት” እና “ይሉኝታ”፣…ጠቃሚ እንደነበሩ ለማስረዳት፣ የድሮ ታሪኮችን የሚጠቅሱ ይኖራሉ። ነገር ግን…ዛሬስ? “ጨዋነት”ን አባረርነው? “ይሉኝታ”ን ረሳነው? ወይስ፣ ከድ
      
             “የኑሮና የስራ ዓለም” ሌላ፣ “የፖለቲካና የፌስቡክ ዓለም” ሌላ።
ከጐረቤት ከሰፈር ሰው ጋር፣ ከስራ ባልደረባና ከገበያተኛ ጋር፣ በአብዛኛውና በአመዛኙ፣ ስድ ንግግርና ክፉ ፀብ የማናዘወትረው፣ ለምንድነው? “በስልጡን የስነምግባር መርህ” አማካኝነት ነው? አይደለም። ለዚህ ገና አልበቃንም። ይልቅስ፣ “በጨዋነትና በይሉኝታ አማካኝነት ነው” - ከነገርና ከፀብ የምንርቀው። በጉርብትናና በስራ ቦታ፤ “ቆጠብ ለዘብ” የማለት ልማድ፤ ዛሬም ድረስ አለ - በጨዋነት አልያም በይሉኝታ። ይሄ የኑሮና የስራ ዓለም፣ ነባር ቅኝት ነው።
በፖለቲካና በወሬ ዓለምስ?፣ በአደባባይና በቲቪ፣ በዩቱብና በፌስቡክ ዓለምስ? በብሔር ፖለቲካና በፌስቡክ ዓለም ውስጥ የምናገኘው ገናና ቅኝት፣ ከነባሩ የጨዋነት ቅኝት ይለያል። “ቆጠብ - ለዘብ” የማለት ልማድ፤ በብሔር ፖለቲካና በፌስቡክ ዓለም ውስጥ፣…”ነጥብ” አያስገኝም። ሳይደርሱበት፣ ከመሬት ተነስቶ ተላካፊ ከሆነ፣… ይህ፣ ብዙ ተሰሚነትን የማግኘት እድል አለው። ሳያናግሯት፣ መዓት የምታወርድ ተሳዳቢ ከሆነች፣ ይህች፣ አጨብጫቢዎችን መሰብሰብ አይከብዳትም።
…ምናለፋችሁ! ለከት የለሽ ስድ ነገረኞችና ጠብ ጫሪ ፀበኞች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፖለቲካና በፌስቡክ ዓለም ውስጥ ይነግሳሉ። ባይነግሱ
እንኳ፤ ወደ ዝነኞች ስም ዝርዝር የመቀላቀል፤ ታዋቂነትን የማትረፍ እድል ያገኛሉ። ቁልፉ መፎካከሪያ ምንድነው? ነገረኛና ፀበኛ የመሆን ውድድር ነው፤ ነገሩ።
ነገር ግን፤ በታዋቂነት ለመምጠቅ፣ በዝና ሽቅብ ለመውጣት ብቻ አይደለም። እዚያው አየር ላይ በታዋቂነት እየተንሳፈፉ ለመቆየት፣ እንደደመና በደቂቃዎች ልዩነት የሚንሰራፋና የሚሳሳ የዝና ጉም ላይ ለመክረምና ላለመንሸራተት፣ ያለማቋረጥ ሌት ተቀን ይፎካከራሉ። ለተረብና ለብሽሽቅ፣ ለለከፋና ለስድብ ይሽቀዳደማሉ።
አለበለዚያ፣ በሆይሆይታ ሽቅብ ተተኩሰው፣ በጫጫታ ቁልቁል ለመፈጥፈጥ ጊዜ አይፈጅባቸውም። በጥቂት ቀናት፣ በፍጥነት የነገሰው ፀበኛ፣ በአንድ ጀንበር ዘውድ የጫነችው ንግስት ነገረኛ፣ ለአፍታ ከስድብና ከዛቻ ከቦዘኑ፣ በጥቂት ቀናት ፍጥነት፣ ከዙፋናቸው ይወርዳሉ። እነሱን የሚያስንቁና እጅግ የባሰባቸው ደርዘን ተላካፊ ነገረኞች ይመጣሉ፣ እሳት የላሱ ትኩስ ተተኪዎች ቦታውን ይወርሱታል። አጥፊ የቁልቁለት አዙሪት እንዲህ ነው - እየባሰበት ይባዛል።
በተረብና በለከፋ ተጀምሮ፣ ወደ ብሽሽቅና ስድብ፣ ብዙም ሳይቆይ፣ ወደባሰ ቀፋፊ ብልግናና ወደ ጭፍን ውንጀላ እየተስፋፋ፤ ከዚያም ወደ ማስፈራሪያና ዛቻ፤ ወደ ዘግናኝ ቨጥቃት ዘመቻና ወደጅምላ እልቂት  እየሸጋገረ፣…ከጊዜ ወደጊዜም እየተለመደ የመጣው ለምን ሆነና?
እያንዳንዱ የጥፋት ዙር፣ ቀኑን እየከረረ ውሎ፣ ማታውኑ ብሶበት ሌላ የጦዘ የጥፋት ዙር ተወልዶ ያድራል። “የባሰ አታምጣ” የሚባለው አለምክንያት አይደለም ለካ። የቀድሞውን የሚያስንቅ፣ ከባለፈው የከፋ አዲስ የጥፋት ዙር ሲፈጠር ስንቴ አይተናል? ለጆሮ የሚከብድና አሳፋሪ የነበረው የተረብና የብሽሽቅ ዙር እንደዘበት እየተለመደ፤ በነጋታው እጅግ የባሰ ቀፋፊ ንግግርና ተግባር በእሩምታ እየተደራረበ ይጋጋላል።
ስለጊዜው ለአፍታ ያህል፣ ግርግሩ የተረጋጋ፣ ለሳልስት ለሳምንት ሁከቱ የረገበ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ እስከዛሬ እንዳየነው፣ የጥፋት አዙሪት፣ በራሱ ጊዜ ተረጋግቶ፣ ራሱን የሚፈውስ መፍትሔ አይወልድም። በአይቀሬው የቁልቁለት አዙሪት፣ የጥፋት ጉዞው ይጦዛል። የአምናው ከካቻምናው፣ የዘንድሮው ከአምናው እየመረረ፤ ከድጡ ወደ ማጡ፣ ከማጡ ወደ ረመጡ ሲያመራ፣ በእውን አይተናል።
ለክፉም ለደጉም፤ “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” እንደሚባለው ነው።
በትክክለኛ የእውነትና የእውቀት ብርሃን፣ በተቃና የአላማና የጥረት መንገድ፣ በአስተማማኝ የግል ብቃትና የሃላፊነት መንፈስ ስንጓዝ፣ ዛሬ፣ ከትናንት የተሻለ መልካም ውጤት ይገኛል። ነገ፣ ከዛሬ የላቀ አኩሪ ሕይወት ይፈጠራል። ብሩህ አእምሮ፣ የበለፀገ ኑሮ፣ የከበረ ሕይወት… በአጠቃላይ ድንቅ የግል ማንነትና የሰለጠነ ባሕል፣ እንዲህ ነው መንገዱ። ከጊዜ ወደጊዜ፣ ደረጃ በደረጃ እያማረ ይሄዳል።
እንደ ኦሎምፒክና እንደ አለም ዋንጫ አድርጋችሁ አስቡት። በእያንዳንዱ የማጣሪያ ዙር፣ ፉክክሩ እያማረ ይሄዳል። ቀጣዩ ዙር፣ ከቀድሞው የላቀ ድንቅ ብቃትን አጉልቶ ያሳያል። ያለማቋረጥም ውበቱ ይጨምራል። በተቃና መንገድ የተቃኘ ነውና - ብቃትን የሚያከብር ቅኝት።
የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት፣ ከዚያም የዩኒቨርስቲ ዲግሪና የዶክትሬት ምርምር፣… ትክክለኛ የትምህርት ሥርዓት ሲፈጠር፣ መንገዱም ሲቃና፣ የሰዎች ጉዞ ብሩህ ይሆናል። እያንዳንዱ እርምጃ፣ ደረጃ በደረጃና ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ወደተሻለ እውቀት ይወስዳል። …ከዚያም ወደ አዲስ የእውቀት ከፍታ እየመጠቀ፣ በአእምሮም ይበልጥ እየበለፀገ ይቀጥላል። መንገዱና ቅኝቱ፣ እውነትና እውቀት የሚከበርበት ቅኝት ነውና። “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” እንዲሉ ነው፡፡
ምርታማነትንና የንብረት ባለቤትነትን የሚያከብር የኢኮኖሚ ነፃነትስ? የካቻምና እድገት፣ ለአምና የድርብ እድገት መንደርደሪያ ይሆናል፤ የአምና ስኬትም፤ ለዘንድሮ እጥፍ የምርታማነት አቅምን እየፈጠረ፣ ከዓመት ዓመት ወደ አዲስ የብልጽግና እርከን እየተሸጋገረ ይሄዳል። ቅኝቱና መንገዱ፣ የጥረትና የምርታማነት ቅኝት ነውና።
ወደተሻለና ወደ ላቀ ከፍታ የሚወስድ ነው - ትክክለኛው ቅኝት። “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” እንዲሉ። እውነትና እውቀት፣ ጥረትና ምርታማነት፣ የግል ብቃትና ጽናት ተከብረው፣ ዋና የሕይወትና የማንነት መመዘኛ የሚሆኑበት ነው - ቀናው መንገድና ትክክለኛው ቅኝት።
ነገር ሲበላሽ፣ ቅኝት ሲዛባ፣ መንገድ ሲጣመምም፤ ያው… ወደከፋ ጥፋትና ወደባሰ ጨለማ ቁልቁል ያወርዳል፤ ሕይወትን ያረክሳል። ሰው የመሆን ክብርን እየገፈፈ ያዋርዳል። “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” ነውና፡፡
በእውነትና በእውቀት ምትክ፣ ዋናው መፎካከሪያ፤ ሌላ ይሆናል። የአሉቧልታና የውሸት ፕሮፖጋንዳ፣ መላከፍና መበሻሸቅ፣ ስድብና ውንጀላ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ፣ የዝርፊያና የማቃጠል ዘመቻ እስርና ግድያ፣ የዘረኝነት ቅስቀሳና የጅምላ ጥቃት ናቸው - የጠማማ ቅኝት መፎካከሪያ። ይህንንም፣ ሺ ጊዜ በተግባር አይተነዋል።
“ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” እንዲሉ፤ ከአመት ዓመት፣ በስድ ባለጌነት፣ በአስቀያሚ ቀፋፊነት፣ የጥፋት ፊታውራሪዎች ሲብስባቸው አላየንም? ወይም እነሱን የሚያስከነዱ ተተኪ ተሳዳቢዎችና መርዘኞች ሲፈለፈሉ አልታዘብንም?
ከ10 ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው የጭፍንነትና የዘረኝነት ክፉ ልማድ ጋር፤ የዛሬውን ስናነፃጽረው፣… የትና የት! ከአምና ከካቻምና ጋር ስናስተያየው እንኳ፣ የዘንድሮው የተለየ አይደለምን?
በቃ፤ ቅኝቱ ከተበላሸ፣ እየባሰበት ይሄዳል። ለምን አይብስበት? በታዋቂነት ዝና ማግኘት፣ በተሰሚነት ገናና መሆን የሚቻለው፣ በተረብና በለከፋ፣ በብሽሽቅና በስድብ፣ በውንጀላና በዛቻ፣ በንብረት ዝርፊያና በቃጠሎ፣ በዘረኝነትና በግድያ ሆኗልኮ። በዚህ የጡዘት ቅኝት፣ እያንዳንዱ አለመግባባትና ውዝግብ… ትንሹም ትልቁም፣ በሰበብ አስባቡ እየጦዘ፣ ወደ ለየለት ጥቃት እየተንደረደረ ሲፈነዳ ማየታችን አይገርምም።
የጥፋት አዙሪት፤ በመላ አገራችን፣ ከመሃል እስከ ዳር፣ በየክልሉ፣ በሶማሌና በአማራ ክልል፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልል አይተናል። የትግራይ ክልልን በተመለከተ፣ ከጊዜ ወደጊዜ እየጦዘ የመጣው ቀውስስ? ወደ ጥፋት ከማምራት ውጭ፣ መጨረሻው እንዴት ሊያምር ይችላል? በጡዘት ቅኝት ከቀጠለ፣ መጨረሻው አያምርም።
በእርግጥ፣ ባለፈው ሳምንት አንድ ተስፋ መጥቷል። ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፣ ነገሩ እንዲበርድ፣ አዲስ እድል ፈጥረዋል።
ቀደም ሲልም፤ እርጋታ እንደሚሻል ተናግረው ነበር። ከሕወሓት በኩል፤ አንዳንዶቹ እንደመደበኛ ስራ፣ በጭፍንነት የሚያዥጐደጐዱት የስድብ፣ የሀሰት ውንጀላና የጥላቻ ውርጅብኝ ለምንም እንደማይበጅ ጠ/ሚ ዐቢይ ሲገልፁ፤ ከፌደራል ወይም ከብልጽግና ፓርቲ በኩል፤ በአንዳንዶች የሚወረወሩ የስድብ ቃላትም አያስፈልጉም ብለው ነበር።
“የክልል ምርጫ አካሂዳለሁ” በሚል የተፈጠረው ውዝግብ ላይም፤ ጠ/ሚ ዐቢይ፣ በጣም የሰከነና ትክክለኛ መንገድ ባለፈው ሳምንት አቅርበዋል። “በበሽታ ወረርሽኝ መሃል ምርጫ አካሂዳለሁ” የሚለው የክልሉ አስተዳደር ውሳኔ ተገቢ ባይሆንም፣ ፓርላማ ባወጣው ህግ መሰረት ከጥቂት ወራት በኋላ የተሟላ ምርጫ መካሄዱ የማይቀር ቢሆንም፤ ጉዳዩ ከልክ በላይ ገዝፎ መታየት እንደሌለበት አመልከተዋል - ጠ/ሚ ዐቢይ።
ችግሩን አለቅጥ አግዝፎ ማየት የሌለብን ለምን ይሆን?
በእርግጥም፣ በትግራይ ክልል የሚፈጠር ችግር፣ በመሃል አገር፣ ለምሳሌ በአማራ ወይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚፈጠር ችግር ጋር ሲነፃፀር፣ ጉዳቱ የዚያን ያህል አስጊና አጣዳፊ ሊሆን አይችልም። አንዱ ክልል ወይም በሌላኛው ክልል ሲረበሽ፣ የንግድ መተላለፊያ ዋና ዋና መንገዳችን የመዝጋት አመጽ ሲከሰት፣ ጉዳቱ እኩል አይደለም፤ የአደጋው መጠን ይለያያል:: ይሄ አንደኛው ምክንያት ነው። ሌላኛው ምክንያት ደግሞ፣ “አወዛጋቢው ምርጫ” ብዙም ክብደት የሌለው መሆኑ ነው። እድሜውም አጭር ነው። በሕግና ስርዓት ላይ የሚደቅነው ፈተናም እንዲሁ፡፡ የክልል ምክር ቤት ምርጫ፤ አዲስ ክልል ለመመስረት ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ሲነፃፀር፣ ብዙ ክብደት አይኖረውም። በመንግስት ቋሚ አወቃቀር ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለምና ነው።
በእነዚህና በተመሳሳይ ተገቢ ምክንያቶች፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፣ ነገርን የሚያበርድ ጥሩ እድል መፍጠራቸው፣ ያመሰግናቸዋል።
“የመረጋጋት እድል ተፈጠረ” ማለት ግን፣ በእርግጠኝነት፣ ተመሳሳይ በጐ ምላሽ ያገኛል ማለት አይደለም። ሊያገኝም ላያገኝም ይችላል።
ካሁን በፊት፣ በተለያዩ ክልሎች ዙሪያ፣ ለመግባባትና ለመረጋጋት የሚረዱ በርካታ እድሎች እየተጠሩ በከንቱ ሲባክኑ፣ አላስፈላጊ መጥፎ ውዝግቦች እየጦዙ፣ ወደ ጥፋት ሲያመሩ አይተናል።
የመረጋጋት እድል እንዳይባክን፣ ብርቱ ጥረት ያስፈልጋል። የመበሻሸቅና የመወነጃጀል መጥፎ አዙሪት ውስጥ የተዘፈቁትን ለመግታት፤ አዙሪቱንም ለማስወገድ፣ ጥፋቱንም ለማስቀረት መትጋት፣ የክልሉ አስተዳደር ኃላፊነት ነው። ብልጽግና ፓርቲም፤ እነ ኢቲቪም ጭምር፡፡


Read 1330 times