Saturday, 08 August 2020 13:19

‘እምቧይ’ እና ‘ሎሚ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

 "እኔ የምለው… ስንደግፍም ጥግ ድረስ ስንቃወምም ጥግ ድረስ! ስንባርክም ጥግ ድረስ፡ ስንረግምም ጥግ ድረስ! ስንወድም ጥግ ድረስ፣ ስንጠላም ጥግ ድረስ! ምን ይሻለናል!?"
       
                እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ክረምቱ ጨከነብንሳ! በሳሳ ሰውነት ይህን አይነት ብርድ! ለደግ ያድርግልንማ፡፡ ይቺን ግጥም ስሙልኝማ…
አዲስ ሞድ ለብሳለች
ሹራብ ደርባለች
ጸጉሯን ተተኩሳ…ለፎርም
ሰዓት አድርጋለች
የዛኛው ዘመን ዘፈን ነው፡፡ አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ… አንገቷ ምናምን፣ ከንፈሯ ምናምን፣ ዓይኖቿ ምናምን ጥሎ ለእጩ ሞዴሎች የሚወጣ የሚመስል አይነት መለኪያ መደርደር የለም፡፡ ‘አዲስ ሞድ’ በመልበሷ ብቻ እሱዬው እጅ ሰጥቷል፡፡ በአለባበስ ብቻ ‘ላቭ ኢዝ ብላይንድ’ ምናምን የሚባልበት ዘመን! ልቡ ውስጥ እንድትገባ ሁሉ ግብዣ ይጠራታል፡፡ እንኳንም በዚህ ዘመን አልሆነ:: ልክ ነዋ… የእራት ልብስ ነው ምናምን የሚሉት ይሄ ከጀርባው የተገለጠ ልብስ ቅልጥ ባለው ብርድ የሚለበስባት ከተማ ነች! እናማ…አዲስ ሞድ ለብሳለች የሚለው ግጥም አሁን የሚሠራ ቢሆን ኖሮ፣ ምድረ ቡቲክ ሁሉ ወና ይሆን ነበራ! የሆነ ጥናት ቢጤ ነገርም “ለጥንዶች መለያየት ቀዳሚው ምክንያት የአዲስ ሞድ ወጪ ነው” ማለቱ አይቀርም ነበር፡፡  
እናላችሁ… በአዲስ ሞድ ልብሷ እጅ ሰጥቶ፣ ልቡን ወለል ካደረገ በኋላ ጉድ ይመጣል፡፡  ታዲያላችሁ…አለ አይደል… ምን እንዳደረገችው እንጃ እንጂ እዚሁ ላይ ወረድ ብሎ ምን ቢል ጥሩ ነው…
እኔስ ደህና መስላኝ ቁመናዋን ሳይ
ለካስ አታላዩዋ፣ ገፋፊ ነች ወይ
ከዛሬ ጀምሮ ዓይኔ እንዳያይሽ
የወጣት (የተቆረጠ) አንድ አይበቃው ነሽ
እያለ መአቱን ያዘንብባበታል፡፡ በፈቃደኝነት ልቡ ውስጥ እንደትገባ ከፈቀደ በኋላ የምን ያዙኝ፣ ልቀቁኝ ነው! ነው… ወይስ አዲስ ሞዱን አውልቃ በአሮጌ ሞድ ለወጠችው! (ቂ…ቂ…ቂ…) ከወር ምናምን በኋላ በሚወጣ ሌላ ዘፈን ላይ ቢሆን ጥሩ:: እዛው በዛው!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺ ነገር የእኛን ሀገር ፖለቲካ አትመስልም! ልክ ነዋ… መጀመሪያ ላይ…ምን ይባላል መሰላችሁ…
“ማንም አይነቀንቀንም!”
“ህብረታችን ከምናምን የጠነከረ ነው፣”
ምናምን ሲባል ይከርምላችሁና ትንሽ ሰንበት ብሎ በዚህ በኩል የተወሰነው ይገመሳል፣ በዛ ሌላው ይገመሳል፡፡ ይሄኛው ወገን ይነሳና “ድሮም ቢሆን እኮ አላማችን አይገናኝም…” አይነት “ከዛሬ ጀምሮ ዓይኔ እንዳያይሽ” ነገር ይመጣል፡፡ ኸረ በህግ! አላማችሁ አንድ ካልነበረ ለምንድነው ለምናምን ወር ሁሉ የቴሌቪዥኑን የአየር ሰዓት ስታጣብቡን የከረማችሁት!  
እኔ የምለው… ቦተሊካም ‘አዲስ ሞድ ለብሳለች’ የሚባል ነገር አለው እንዴ! አሀ…ግራ ተጋባና! አይደለም መጠሪያቸውን፣ መኖራቸውን ሳናውቅ “ተጣሉ፣” “የቢሮ ቁልፍ ተነጣጠቁ፣” “ማህተሙን በኪሳቸው ይዘው ሄዱ፣” ምናምን ሲባል ነዋ የምንሰማው!
ስሙኝማ…ሌላ ደግሞ 
እምቧይ ሎሚ መስሎ ለምን ያታልላል
መልኩን አሳምሮ ሰው ያጭበረብራል
የምትል ዘፈን ነበረች፡፡ አሪፍ አይደለች! በዘመኑ ቋንቋ እኮ “ሎሚዋ ስትፋቅ እምቧይ ሆና እርፍ!” አይነት ነው፡፡ እናላችሁ…እኛም ዘንድሮ የሆነ ነገር አይተን ወይም ሰምተን ‘ሎሚ’ የመሰለን ሁሉ ‘እምቧይ’ እየሆነብን ነው የተቸገርነው፡፡
አሁን ለ‘አዲስ ሞድ’ ልቡን የከፈተው ሰውዬ ምናለ ባህሪይ፣ ወይ ጠባይ የሚባሉትን ነገሮች አይቶ ቢሆን ኖሮ! ‘የውስጥ ውበት’ የሚባል ነገር አለ አይደል! (“የእኛ ሞራል ሰባኪ! ‘ፕሪቸር’ ለመሆን እያሟሟቅህ ነው እንዴ!” ምናምን ለምትሉ ወዳጆቼ… “ከዛሬ ጀምሮ ዓይኔ እንዳያይሽ…” የሚለውን ዘፈን መርጬላችሁ አንደኛውን ተቆራርጠን እንዳንቀር፡፡)
ስሙኝማ…ዘንድሮ ወይ ተፋቅረው ዓለም እያየ በ“አይ ላቭ ዩ ሞር ዛን አይ ካን ሴይ፣” ነገር ወይ “ከዛሬ ጀምሮ ዓይኔ እንዳያይሽ…” ብለው ለይቶላቸው አይቆራረጡ…‘በያዝ መለስ’ ግራ እያጋቡን ያሉት ይለዩልንማ! ጥያቄ አለን በ‘ላይቭ ቴሌቪዥን’ ሁሉም ይፋቅልንማ፡፡ አንዴ ‘አወዳሽ’ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ‘ነካሽ’ እየበዛ ተቸገርን፡፡ ወይ ‘ሎሚ’ ሁኑ፣ ወይ ‘እምቧይ’ ሁኑ!
በሰው ድግስ እየዞረ “ብሉ እንጂ፣ “ብሉ እንጂ፣ ጠጡ እንጂ፣” የሚለው የሆነ ነገርዬ አለ፡፡ ምን አገባው! ምን ጥልቅ አደረገው! “ምን ጥልቅ አድርጎን በሰዎች ሥራ፣ በሰዎች ነገር፣” ተብሎ ነበር፡፡  “አያገባህም!” ልንባል የሚገባን ሰዎች አለን፡፡
ስሙኝማ… “ጎረቤትህን እንደራስህ ውደደው”  የሚለው አሁን ይሠራል እንዴ?! አሀ…ልክ ነዋ፣ አንድ ግድግዳ እየለያቸው እንኳን “ጎረቤቴ እንደምን አደርክ/አደርሽ!” ሊባባል ሁለት ዓመት ሙሉ እኮ ተያይቶ አያውቅም፡፡
“ስማ ጎረቤትህ ሙያው ምንድነው?”
“ጎረቤት! ማነው ጎረቤት አለው ያለህ!”
“ጎንህ ያለው ጎረቤትህ አይደለም እንዴ?”
“እንኳን ጎረቤቴ ሊሆን እሱ ይሁን እሷ ትሁን አላውቅም፡፡”
በየመንደሩ ደግሞ…
“ይቺን  ሴትዮ ግን ቁም ስቅሏን ባላሳያት እናቴ አልወለደችኝም፡፡”
“ይህን ያህል ምነው ጠላሻት! ጎረቤትሽ አይደለችም እንዴ!”
“ጎረቤቴ ብትሆንስ…”
“ጎረቤትህን እንደራስህ ውደድ ተብሏላ!”
”በቀን አስር ጊዜ ድመቷን በአጥር ስር እየላከችብኝ እንዴት አድርጌ ነው የምወዳት!”
እኔ የምለው…
ስንደግፍም ጥግ ድረስ ስንቃወምም ጥግ ድረስ!
ስንባርክም ጥግ ድረስ፡ ስንረግምም ጥግ ድረስ!
ስንወድም ጥግ ድረስ፣ ስንጠላም ጥግ ድረስ!
ምን ይሻለናል!
 ስሙኝማ…“አንድ ሰው የመኪናውን በር ለሚስቱ ከከፈተ ወይ መኪናው አዲስ ነው፣ ወይ ሚስቱ አዲስ ነች…” የሚሏት ቀልድ ቢጤ አለች፡፡ የሆነ ሰው ድንገት ከሆነ ባዶ ኤር ውስጥ ዱብ ብሎ በየቴሌቪዥኑ “እዩኝ፣ እዩኝ” ማለት ካበዛ ወይ ፖለቲካው ለእሱ አዲስ ነው፣ ወይ እሱ ለፖለቲካው አዲስ ነው፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…)…
ቸገረን እኮ! ማይክ የጨበጠው ሁሉ “እኛ ያልነው ካልሆነ አዳሜ ወዮልሽ!” ባይ በዛና ግራ ገባን፡፡ ‘ሎሚ’ መሳዮች አምቧዮች በርከት አልን መሰለኝ…ፎካሪ በዛ፡፡ “ዛፍ በሌለበት እንቧጮ አድባር ሆነ” የሚ ለው ተረት ታሪካዊ አመጣጥ ይጣራልን፡፡ አሀ…አሁን በተለይ በ‘ቦተሊካው’ የምናየው ትርምስ ነገር… የ‘ጠፋ ዛፍ’ና ‘አድባር የሆነ እምቧጮ፣’ ነገር እየሆነ ነዋ! ‘እምቧይ’ መሆናቸው ከርሞ መውጣቱ የማይቀር ‘ሎሚ’ የመሰሉ ፖለቲከኞች የዳማ ጠጠር ሊያደርጉን እየሞከሩ ነዋ! ለምን የፖለቲካ ጫማቸውን አይሰቅሉልንማ! ባይሆን መስቀያውን እኛ ከየትም፣ ከየትም ብለን አምጥተን ‘ወጪ እናጋራለን!’
እኔ የምለው….እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚህ ጓዳችን ተርመስመስ ያለ ሲመስላቸው እንደ ናፖሌኦን ነገር የሚቃጣቸው ሰዎች አይገርሟችሁም! ሲገርምሽ ኑሪ ያላት ሀገር! እዛ ላይ ሲፎከር እዚህ የምን የገደል ማሚቶ ነው!
ለከፉ ለደጉም አሪፍ የሚሆነው ነገር ‘እምቧዩም’ በቦታው ’ሎሚውም’ በቦታው! ሲሆን ነው፡፡
ተዉ ግዴላችሁም ለዚች ክፉ ጊዜ እንተሳሰብ…አውሎ ነፋስ ከመጣ እኮ ሁላችንም ነን “አሻ ገዳዎ፣” እያልን የምንወሰደው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2139 times