Print this page
Saturday, 08 August 2020 12:55

ባንዲራ ነክ ወጎች!

Written by  በተስፋዬ ድረሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ወግ 1 - በ2ሺ የባንዲራ ቀን እየተከበረ በነበረበት  ቀን ስለ ባንዲራ አንድ ሁለት መስመር ግጥም ለመፃፍ ፈለኩና ጭብጡን ማሰላሰል ጀመርኩ። ብዙ ሀሳቦችን ሳወጣና ሳወርድ ከቆየሁ በኋላ ባንዲራን፤ ማለት፣ “ጨርቁ”ን፤ እና፣ ሰንደቁን፤ ማለትም፣ ባንዲራውን ተሸካሚውን እንጨት (ብረትም ይሁን እንጨት) እያነፃፀርኩ የሚከተሉትን ስንኞች ቋጠርኩ፡፡ ርዕስ - ጨርቁን? ወይስ ሰንደቁን?፡-
ከስርዓት ጋር ሳትለወጥ - መኖር ካሻህ፤
ምክር እንካ አሁን
ብረትም ሁን ደረቅ አንጨት - ሰንደቁን
ሁን፡፡
አለዚያ ግን ሆነህ ጀግና - የአገር ሞገስ
ባለዝና
ተውለብልበህ እድሜህ ይጠር
ባንዲራውን ሁነውና!
ምናባቱ! ከኖሩ አይቀር እንደ ባንዲራ የአገር መታወቂያ፣ የዜጎች አንድነት መገለጫ ሆኖ …  በነፃ አገር፣ በነፃ ሰማይ ላይ ተውለብልቦ፣ ተውለብልቦ፣ ተውለብልቦ …  ተበጣጥሶ ማለፍ ነው! እንጂ፣ የመጣው ጨርቅ ሁሉ ሲቋጠርበት ዝም የሚለውን፤ ሰንደቁንስ መሆንስ ቢቀር ይሻላል፡፡ … ባንዲራ እንጂ ሰንደቅ የመጣያ፣ የመወዛገቢያ ርዕስ ሆኖ አያውቅም፡፡ ባንዲራኮ  ከመከበሩ፣ ከመወደዱ የተነሳ “ጨርቅነቱ” እንኳ በይፋ ከተነገረ ዜጎች ሊቀየሙ፣ ሊቆጡ፣ ይችላሉ - የሚል ነው የግጥሙ ዋና መልዕክት።
ወግ 2 – የላይኛውን ግጥም ረቂቅ ጽፌ ከመደምደሜ በፊት፣ በረደኝና ፀሀይ ለመሞቅ ከቤት ወደ ደጅ ወጣሁ። ደጁ ሙሉ በሙሉ የማረቆ በርበሬ ተሰጥቶበታል። ሰሌን፣ ጥቁር የፕላስቲክ ምንጣፍ እና የአሻሮ ምጣድ የቻሉትን ያህል አደራ ተቀብለው ከበርበሬው ጋር አብረው ተሰጥተዋል። ማስጫዎች ሁሉ ተሰጥተው እንደሚውሉ ያስተዋልኩት ያን ቀን መሰለኝ።
ስጡን ሳይ ሌላ ጭብጥ አገኘሁ፡፡ እናም፣ ጭንቅላቴ ውስጥ የነበረው የባንዲራ ነገር በመሆኑ ሌላ ግጥም ለመጻፍ፤ ፀሀይ መሞቄን ትቼ፤ ወደ ቤት ተመለስኩ፡፡ ከአገሩ የወጣ፣ በሁለተኛ ዜጋነት ሆድ የባሰው ሰው፤ ከሶስቱ ቀለማት አንዱን ባየ ቁጥር የአገሩ ባንዲራ ትዝ ይለዋል የሚል ስሜት አደረብኝና ባባሁ፡፡ የምናብ ስዕሌንም አመንኩት፡፡ ስለሆነም፣  ቀዩን ቀለም ከተሰጣው በርበሬ ተውሼ እንዲህ ፃፍኩ (ከዚያም ታተመ)፡-
የአገር ፍቅር ስሜት - እንዲህ ቀላል ስሜት
- አይምሰለህ ጓዴ፤
የበርበሬን ዛላ - መቀባት ያስመኛል -
ቢጫና አረንጓዴ።
ወግ 3 - የሆነ ስልጠና ላይ ለመካፈል  ወደ ኖርዌይ ሄጄ ነበር፡፡ ጊዜው ኢህአዴግ ሥልጣን ይዞ፣ “አልጋው” ገና ሳይረጋ ነው፡፡ ስልጠናውን ያዘጋጀው ድርጅት ተሳታፊዎችን ለማስደመም በማሰብ፣ ከየስማችን ጎን የየአገራችንን ባንዲራ በነፍስ ወከፍ በተሰጠን የጠረጴዛ ኮምፒዩተር ውስጥ ከቶ አሳየን። ብዙዎቹ ሰልጣኞች የአገራቸውን ባንዲራ ሲያዩ የተደሰቱ ይመስለኛል። እኔ ግን የሆነ ነገር ወረረኝ፣ አንጠረጠረኝ። የሆነ እልህ፣ የሆነ ቁጣ፣ የሆነ የመጠቃት ስሜት ጉሮሮዬ ውስጥ ተሰንቅሮ አላስተነፍስ አለኝ። ለምን እንደሆነ ልንገራችሁ። የኢትዮጵያ ባንዲራ ተብሎ የተለጠፈው ምስል የመንግሥት ለውጥ ከመደረጉ በፊት የነበረው፤ በላዩ አርማ የሌለው ሌጣ “ጨርቅ” ነው።
ከስልጠናው አስተባባሪዎች አንዱን በእጅ ምልክት ጠራሁትና እንዲህ አልኩት። “ስማኝ፤ አሁን አገሬ እያውለበለበች ያለው ህጋዊ ባንዲራ አይደለም፤ የድሮው መንግሥት ባንዲራ ነው።” የቁጣዬ ፍቺ - “እኛ በገዛ አገራችን ብንፈልግ ልሙጡን፣ ብንፈልግ ባለ አርማውን እያደረግን ከመንግስት ጋር እንፋጠጥ፣ እናንተ ምን አግብቷችሁ ነው የሉዓላዊት አገሬን ባንዲራ ተቃዋሚዎች በሚይዙት አርማ ለውጣችሁ የጠበቃችሁኝ?” የሚል ነው፡፡ አይገርምም ግን? እዚህ ሆኜኮ ስለ የትኛውም ባንዲራ ገጽታ ይህ ነው የሚባል አቋም አልነበረኝም:: ከአገሬ ውጭ ራሴን ማግኘቴ ነው የአገር አምባሳደር የመሆን ስሜት የፈጠረብኝ፡፡
ሰውየውም፤ “sorry, sorry; we will change it right now (አዝናለሁ፣ አዝናለሁ አሁኑኑ እንለውጠዋለን) አለኝና … ኮምፒዩተሬ ላይ አጎንብሶ አዲሱን የኢትዮጵያን ባንዲራ አብረን እንድንፈልግ ጠየቀኝ። ለወጥነውም፡፡ ቁና ተንፍሼ ወደ ተዘጋጀው ትምህርት አመራሁ::
ወግ 4 - ከአሁኑ ህገ መንግስት መረቀቅ ጋር ተያይዞ፣ የቀድሞው ባንዲራ ላይ ለውጦች ተደረጉ። ምን ቢባል፣ ምን ቢደረግ የመንግሥት አካሄድ አልዋጥላቸው  ያላቸው ተቃዋሚዎች፣ የነፃው ጋዜጣ አርበኞች እንዲሁም ሌሎች በርካታ ዜጎች ባለአርማውን ባንዲራ ማየት አንፈልግም አሉ፡፡ ከመንግሥት ጋር እልህ መጋባት እየተካረረ መጣ፡፡
አዲሱ ባንዲራ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በየቀበሌው ይውለበለባል። ዜጎች ደግሞ በየእምነት ቦታቸው፣ በየሰርጉ ቦታ፣ ወዘተ ልሙጡን፣ የድሮውን ባንዲራ፤ መጠቀማቸውን ቀጥለዋል። አትሌቶቻችን ሳይቀሩ ከድል በኋላ ለብሰው ወደ ተመልካቾቻቸው የሚሮጡት የድሮውን ባንዲራ ነበር፤ ቢያንስ በመጀመሪያዎቹ አመታት። ይህን ሳስተውል፤  አገራችን የሁለት አይነት ባንዲራ ተጠቃሚ መሆንዋ ይከነክነኝ ነበር። መቼ ነው እንደ አሜሪካን አገር ብዙ አመታትን ያስቆጠረ ባንዲራ፣ እና የህዝብ መዝሙር የሚኖረን? ብዬ እቆጭ ነበር፡፡ እናም፣ የዚያን ጊዜ ትዝብቴን ሁለት ስንኞች ቋጥሬ አኖርኩ። እነሆ፡-
“ሁለት ባንዲራ አላት - ኢትዮጵያን ታዘቡ
አንደኛው የመንግሥት - ሌላኛው
የህዝቡ!”
እነዚህን ስንኞች፤ ባሳተምኳቸው  የግጥም መጽሐፎች ውስጥ ለማካተት ግን አልፈለግሁም፤ ነገር ማቀጣጠያ እንዳይሆን በመስጋት፡፡ ለነገሩ፣ “ችግሩ” እስከ ዛሬም አልተፈታም፡፡ ዜጎቻችን እዚህም ሆነ ከአገር ውጭ፣ የተለያዩ ባንዲራ ነው የሚጠቀሙት፤ አንዱ  ህጋዊ ሌሎቹ ህጋዊ ያልሆኑ፡፡
ወግ 5 - በመጀመሪያው “የባንዲራ በዓል ቀን” እንዲህ ሆነ፡፡  ባንዲራውን፤ በአርዓያነት፤ ለመስቀል መዝሙሩ  እስኪጀመር ይጠባበቁ የነበሩት ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ልክ የመዝሙሩ ዜማ እንደተሰማ፤ እሳቸው ወደ አውሮፕላን ሲገቡ በምናውቀው ፍጥነታቸው አይነት ገመዱን ሳብ፣ሳብ፣ ሳብ፣ ሳብ፤ ላጥ፣ ላጥ፣ ላጥ ያደርጉት ጀመር። ልብ በሉ፤ ሙዚቃው ገና ሩብ ሳይሄድ ባንዲራውን አጣድፈው ሩብ ጉዳይ አድርሰውታል፡፡ በመጨረሻም፤ መዝሙሩ (ሙዚቃው) ሳያልቅ ጫፍ ሊያደርሱት እንድ ሁለት ስንዝር ብቻ ቀራቸው። በሆነች ቅጽበት ታዲያ፣ የሆነ ምልክት የተሰጣቸው መሰለኝ፣ ትንሽ ዝግ አሉ፡፡፡ ያኔ፣ ቀና ሳይሉ በልባቸው ሙዚቀኞቹን ተገላምጠው፤  “ታዲያ ምን ላድርጋችሁ? ተጎተታችሁብኛ!” ያሉዋቸውም ይመስለኛል። ትዕይንቱን ያየሁት በቴሌቪዥን ቢሆንም፤ እነዚህን ስንኞች ጻፍኩ፡፡ ለካስ ባንዲራ አሰቃቀል ችሎታ ይጠይቃል በሚል፡--
“መሪ በችኮላ ልቡም ቢንቀለቀል
ሌላ ክህሎት ይሻል ባንዲራ አሰቃቀል።”
ወግ 6 - የቅርቡ የእነ ዶ/ር ዐቢይ ለውጥ ከመምጣቱ በፊት፣ ብዙ ኢትዮጵያዊያን፣ አርማ ያለውን ባንዲራ ይጠየፉት ነበር፡፡ ሲያዩት ፊታቸው አይፈታም ነበር፡፡ አሁን፣ አሁን ግን ለውጦች አሉ፡፡ መደበኛውን የኢትዮጵያን ባንዲራ የማይመስሉ ባንዲራዎች እየበዙ፤ የፖለቲካው ሁኔታም እየተወጣጠረ ሲመጣ፤ ዜጎች “አገር በባንዲራ ቁጥር ልክ ልትበታተን ይሆን እንዴ?” የሚል ስጋት አደረባቸው መሰል፤ ባለ አርማውን ባንዲራ ከፍ አድርገው ይታዩ ጀምረዋል:: እርግጥ ነው፤ ለውጡ ተስማምቷቸው፤ “የባንዲራው ቀለም አያጣላንም” (ዞሮ ዞሮ ቀለምና ቅርጽ ጭንቅላት ውስጥ ነው ያለው፤ ሊለወጥ ይችላል) የሚል ስሜት አድሮባቸውም ይሆናል፡፡ ሲመስለኝ፣ ቀደም ሲል፣ ይሉ እንደነበረው “ይለወጥ፤ ወደ ልሙጥነቱ ይመለስ” ቢባሉ ሁሉ መቃወማቸው አይቀርም፤ በዚህ አያያዛቸው፡፡ እርግጥ ነው፤ በኢህአዴግም ሆኑ በቀደሙ መንግሥታት አገራችንን የወከለውን ባንዲራ ለመያዝ የሚጠየፉ አሉ - ባንዲራ የተለያዩ ቡድኖች መለያ ነውና፡፡ አይ ኢትዮጵያዬ፤ እስከ መቼ ይሆን ተጫዋቾችሽ (በልባቸው) የተለያየ መለያ ለብሰው ወደ ሜዳ የማይገቡት?
ወግ 7 - ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር ቴሌቪዥን እያየን በባንዲራ ቀለምና መልክ ዙሪያ ያለውን “ፖለቲካ ነክ” ውዝግብ እየተቸን ሳለ እንዲህ ሆነ፡- በኢህአዴግ ዘመን ከተወለዱ ልጆቼ አንዱ፣ “አባብ፤ እኔ የማውቀውኮ ይህንን ባንዲራ ነው!” አለኝ:: እነ ሀይሌ፣ እነ ደራርቱ ወዘተ በዓለም አደባባይ ሲያውለበልቡ ያየው ይህንን ባለ አርማውን መሆኑን ነገረኝ፡፡
ይሄም አለ ለካ!? ደነገጥኩ፡፡ የደነገጥኩት፣ እንዴት ይኸኛውን ባንዲራ መረጠ? በሚል አይደለም፡፡  እኛ፤ ሶስት ባንዲራ ያየንና እድሜያችን ከሀምሳዎቹ የዘለለ ሰዎች ስለ ባንዲራ የምናወራው እኛን፣ ራሳችንን እንጂ፣ ልጆቻችንን እያሰብን ያለመሆኑ ስለገባኝ ነው፡፡ አይገርምም ግን? በብዙ ጉዳዮች የምንንጨረጨረው፣ የኛንንና  የልጆቻችንን አመለካከት መወከል የሚያምረን አባቶች፣ አያቶች መቼ ይሆን፤ “እኛኮ አርጅተናል፣ የድሮ አስተሳሰቦች (እንዲሁም የትግል ስልቶች) ላይ ተቸክለናል; ብለን የመሪነት በትሩን ለወጣቶቹ ስለማስረከብ የምናስበው? መቼስ ይሆን ውዝግቦች ሁሉ ከስመው አልቀው፣ በባንዲራ ቀለምና ቅርጽ ደም መፋሰስ የምናቆመው?!

Read 1753 times