Saturday, 08 August 2020 12:17

መንግስት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ፍትህ እንዲያሰፍን ተጠየቀ

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተሮች
Rate this item
(5 votes)

 
                 የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተፈፀሙ ኢ-ሠብአዊ ድርጊቶችን ያወገዙት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች፤ በሀገሪቱ በተደጋጋሚ እየተፈፀሙ ላሉ ዘግናኝ እልቂቶችና ውድመቶች ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡
የህግ የበላይነትን ማስከበርና የዜጐችን ደህንነት ማስጠበቅ የሃገር ህልውና መሠረት መሆኑን ያስገነዘበው ኢዜማ፤ ሀገሪቱን በአስተማማኝ የደህንነት መሠረት ላይ ለማቆምና ለዜጐች ዋስትና ለመስጠት የፖለቲካ ሃይሎች ተቀራርቦ መወያየት ወሳኝ ነው ብሏል - ሳይውል ሳያድር ለሁሉም ተስፋ የሚሰጥ አስቸኳይ የባለድርሻዎች ውይይት እንዲጀመር በመጠየቅ፡፡
ዜጐች የሚረጋጉበት፣ ህግ የሚከበርበትና የመኖር ዋስትና የሚያገኙበት ስርአት መፍጠር እንደሚገባ የገለፀው ኢዜማ፤ ይህን ለማድረግም ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ዘመናዊ የሠለጠነ ፖለቲካና የጨዋታ ሜዳውን ህግ ያከበረ አካሄድ መከተል እንደሚገባቸው አስገንዝቧል፡፡
በሀገሪቱ ዘላቂ መረጋጋትና ሠላም ለማስፈን ይጠቅማሉ ብሎ ኢዜማ ካቀረባቸው መፍትሔዎች መካከል መገናኛ ብዙሀንን በህግ መግራት አንዱ ሲሆን የሲቪክ ተቋማትም ስለ ሠላምና አብሮ መኖር በማስተማር፣ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታና ለሀገር መረጋጋት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
ኢዴፓ በበኩሉ፤ በሀገሪቱ ለሚፈጠሩ ደም አፋሳሽ ግጭቶችና ጥቃቶች ዋነኛው መንስኤ ህገ መንግስቱ መሆኑን በመጥቀስ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም ህገ መንግስቱን መቀየር ወሳኝ ነው ብሏል፡፡
በኦሮሚያ የተፈፀመው ድርጊት በእጅጉ የሚወገዝ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ፤ መንግስት በጉዳዩ ላይ በትኩረት እንዲሠራ ፓርቲያቸው መጠየቁንም አስረድተዋል፡፡
ህገ መንግስቱ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚሰብክ መሆኑን ያስረዱት አቶ አዳነ፤ ይህን ህገ መንግስት መቀየር ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይደገሙ ዘላቂ መፍትሔ ነው ብለዋል፡፡
ህገ መንግስቱን በስርአት መለወጥ እስኪቻል ድረስም መገናኛ ብዙሃን፣ ምሁራንና ተጽእኖ ፈጣሪዎች ችግሮችን ከማራገብ ወጥተው፣ ህዝቡ በሠላም ተቻችሎ የሚኖርበትን ድባብ መፍጠር አለባቸው ብለዋል፡፡ ለዚህም ሀገራዊ ንቅናቄዎች እንደሚያስፈልጉ አቶ አዳነ ጠቁመዋል፡፡
የአረና ትግራይ ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታ ደግሞ በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ውጥረቶችን በፖለቲካ ውይይት ማርገብ ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
“በትግራይም ሆነ በኦሮሚያ ያለው እንቅስቃሴ በመንግስታዊ ስርአቱ ላይ እምነት ከማጣት የመነጨ ነው” ያሉት አቶ አብርሃ፤ ይሄ ሁኔታ ገፍቶ ሄዶ የከፋ ችግር ከማድረሱ  በፊት ውይይትና ድርድር ማካሄድ ይበጃል፡፡
ሁሉም ለፍትህ በጋራ እንዲቆም የጠየቁት ታዋቂው የእስልምና መምህር ኡስታዝ አህመድን ጀበል በበኩላቸው፤ ሁሉም ለራሱ ወገን ብቻ መቆሙን ትቶ ለፍትህ በመቆም ሀገር ማዳንና እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችንም መቅረፍ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም በክልሉ የተፈፀመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በጽኑ ያወገዙ ሲሆን አጥፊዎችም ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡
የኦርቶዶክስ፣ የሙስሊምና የፕሮቴስታንት የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት አባላት በክልሉ የተፈፀመው ድርጊት እጅግ አስነዋሪ መሆኑን በመግለፅ ድርጊቱን የፈፀሙ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የጠየቁ ሲሆን የህዝቡ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲጠናከርና በጋራ ሀገሩን የሚጠብቅበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎቹ ተጐጂዎች ያሉበት ቦታ ድረስ በጋራ ሄደው በመጐብኘት መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍ ለማድረግና በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን መንገድ ለመፈለግ ተስማምተዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ተጐጂዎቹ አሁንም ባሉበት ሁኔታ በሚደርስባቸው ዛቻና ማስፈራራት በከባድ ፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት የሀገር ሽማግሌዎች፤ መንግስት ዋስትና እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡   


Read 1015 times