Saturday, 08 August 2020 12:09

በቤይሩት ፍንዳታ የተጐዱ ኢትዮጵያውያን መንግስትን ተማፀኑ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

    - “መንግስታችን እንደ ዜጐቹ ቆጥሮ ከሞት ሊያድነን ይገባል” - ስተደኛ ኢትዮጵያውን
       - “የቆንስላ ፅ/ቤቱ ጉዳያቸውን በቅርበት እየተከታተለ ነው” - የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ
       - የደረሱበት ያልታወቁ ኢትዮጵያውያንን የመፈለግ ሥራ ቀጥሏል
                               በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ውስጥ ሰሞኑን በተከሰተው የፍንዳታ አደጋ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጉዳት እንደደረሰባቸውና እስካሁንም ድረስ ያሉበት ያልታወቀ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በርካታ መሆኑን በቤይሩት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በአሰሪዎቻቸው ስልክ እንዳይዙ ስለሚከለከሉና በቤተሰብ መዝገብ ቅጽ ውስጥ ስለማይካተቱ ጉዳት የደረሰባቸውንና የሞቱ ኢትዮጵያውያንን የማወቁ ሥራ አስቸጋሪ እንደሚሆንም እነዚሁ የቤይሩት ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ተናግረዋል፡፡
በሊባኖስ በደረሰው ከባድ የፍንዳታ አደጋ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢታወቅም በአደጋው የሞቱትንና የቆሰሉትን ወገኖች ለማወቅ እንደማይቻልም እነዚሁ የቤይሩት ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ተናግረዋል፡፡
“እኛ ለእኛ በስደት” የተባለው በሊባኖስ የኢትዮጵያውያን በጐ አድራጐት ማህበር አባላት የሆኑት፡- ብዙአየሁ ጌታቸውና ሠላም ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በፍንዳታው ቁጥራቸውን በውል ማወቅ የማይቻል በርካታ ኢትዮጵያውያን ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ቁጥራቸው የማይታወቁት ደግሞ የት እንዳሉ እንኳን ለማወቅ አልተቻለም፡፡
ላለፉት በርካታ ዓመታት የሊባኖስ ስደተኛ ወገኖችን በተለያዩ መንገዶች በመርዳት ሥራ ላይ የተሰማራችው ብዙአየሁ ጌታቸው እንደምትገልፀው፤ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በአሰሪዎቻቸው ጫና ስለሚደረግባቸውና ስልክ እንዲይዙ ስለማይፈቀድላቸው ደህንነታቸውን ለማወቅና በአደጋው ጉዳት ይድረስባቸው አይድረስባቸው ለማጣራት ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ እርስ በርስ የሚተዋወቁ ኢትዮጵያውያን የሚነግሩንን መረጃ በመያዝ ወገኖቻችን ያሉበትን ሁኔታ ለማጣራት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በአብዛኛው የምናገኘው መረጃ ግን ብዙም ተስፋ ሰጪ አይደለም፡፡
“አሁንም ከመሬት በታች የተቀበሩና በሊፍት ውስጥ ተዘግቶባቸው የነበሩ ሰዎች እየተገኙ በመሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር የሚያሻቅብ መሆኑ አይቀርም፤ እኛ የሚቻለንን ጥረት እያደረግን ነው፤ መንግስት ግን በቂ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለን አናምንም፡፡ ሁሉም አገራት ዜጐቻቸውን ከአደጋው ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የእኛ አገር መንግስት ግን አንዳንድ አካባቢዎችን ተዘዋውሮ ከመጐብኘትና ህሙማኑን ከመጠየቅ የዘለለ ምንም ነገር እያደረገ አይደለም፡፡ ዜጐች ወደ አገራቸው ለመመለስ እንዳይችሉ እንኳን የአየር ትኬት ዋጋውን ሰቅሎብናል፤ ይህ እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነው” ብለዋል - በምሬት፡፡
ላለፉት አራት አመታት ኑሮዋን በቤይሩት ማድረጓን የነገረችን ኢትዮጵያዊቷ ሰላም ተስፋዬ፤ ፍንዳታው የተከሰተው ማክሰኞ ዕለት 12 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፤ በወቅቱ የፍንዳታው ድምጽና ያስከተለው የመናወጥ ስሜት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ የደረሰ ይመስል እንደነበር ገልፃለች፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ የመደጋገፍና የመረዳዳት ተግባራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፃ፤ በእለቱ ፍንዳታው በደረሰበት አካባቢ ለእነዚሁ በከፍተኛ ችግር ለተጐዱ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ድጋፍ በማድረግ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቦታ ተሰባስበው እንደነበር ተናግራለች። ዋርኒኬልና ጅማያት የተባሉት አካባቢዎች በፍንዳታው ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንና በእነዚህ ቦታዎች የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንም በአደጋው ሳይሞቱ እንደማይቀሩ ግምቷን ትናገራለች።
በወቅቱ ብዙ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቦታ ላይ ተሰባስበን ስለነበረ ሁላችንም ወደምናውቃቸውና ስልክ ይይዛሉ ብለን ወደምናስባቸው ኢትዮጵያውያን እየደወልን ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ሙከራ አድርገናል። እስካሁን የሁለት ኢትዮጵያውያንን ሞት (አንድ ወንድና አንዲት ሴት) አረጋግጠናል። በርካቶች ደግሞ በአደጋው መቁሰላቸው ቢረጋገጥም፣ በቁጥር ምን ያህል ይሆናሉ የሚለውን ግን ለማወቅ አልተቻለም ብላለች።  
ከፍንዳታው በኋላ በከተማው ውስጥ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ በመሆኑ ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ያሉበትን ሁኔታ አሁንም ድረስ ማወቅ አለመቻሉን እነዚሁ በቤይሩት ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ተናግረዋል፡፡
ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ጉዳት በደረሰባቸው ሰዎች ተሞልተው እንደነበር የገለፀችው ሰላም፤ በየሆስፒታሎቹና የህክምና መስጫ ተቋማት እየተዘዋወርን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ለመርዳትና ደም ለሚያስፈልጋቸው ደም ለመለገስ ጥረት እያደረግን ነው ብላለች፡፡
በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ አምባሳደር ተመስገን ኡመርን በሆስፒታሎች እየተዘዋወሩ ኢትዮጵያውያንን ሲጠይቁና ሲያበረታቱ መመልከቷን የተናገረችው ሰላም፤ ይህ በጐ ነገር ቢሆንም መንግስት እንደሌሎች አገር መንግስታት ለዜጐቹ ኃላፊነት ሊወስድና ዜጐቹን ከአደጋና ከችግር ሊታደግ ይገባል ብላለች፡፡ ከአደጋው በኋላ ወደ አገራቸው ለመግባት የፈለጉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም የአውሮፕላን ትኬት በመወደዱ ይህንን ማድረግ አልተቻለም ብላለች፡፡  የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ መከሰት በቤይሩት ውስጥ በምንኖር ኢትዮጵያውያን ላይ ያስከተለብን ጫናና መከራ ሳያንሰን፣ አሁን ደግሞ ለእንዲህ አይነት ዘግናኝ አደጋ መጋለጣችን በእውነት የሚያሳዝን ነገር ነው ያሉት ኢትዮጵያውያኑ አሠሪዎቻችን በቫይረሱ ሳቢያ ኢኮኖሚያቸው በመውደቁና እኛን ለማኖር ስላልቻሉ በማናውቀው አገር ከቤት አውጥተው ሜዳ ላይ ጥለውን ይሄዳሉ፡፡ በዚህ መንገድ ተጥለው በየመንገዱ የቀሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በእንዲህ አይነት የአደጋ ጊዜ ደግሞ በመንገድ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥራቸው ስለማይታወቅ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለጉዳት መጋለጣቸው አይቀሬ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በቤይሩት በደረሰው የፍንዳታ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ እዛው በከተማው የሚገኘው የቆንስላ ጽ/ቤታችን በቅርበት እየተከታተለው ነው ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ፤ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል፤ ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ከዘጠኙ ሰባቱ ጉዳታቸው ቀላል በመሆኑ ታክመው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፤ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ አሁንም የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡
በስፍራው የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ አደጋ ከደረሰ በኋላ በ3 የአደጋው ሰለባ  መጠለያ ካምፖች በመገኘት ሁኔታውን ማጣራቱን ገልፆልናል፡፡ አሁንም ክትትል እየተደረገ ሲሆን አሠራር ላይ ክፍተት ሊኖር ይችላል፤ ግን ጽ/ቤቱ ሌሎች በጐ አድራጊ ድርጅቶችን በማስተባበር ለተጐጂዎቹ እርዳታና ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የት እንደደረሱ አልታወቁም የሚባሉትን ኢትዮጵያውያን አድራሻም ለማወቅ ፍለጋውን አጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ በምትገኘው የቤሩት መዲና ሊባኖስ ከተማ ውስጥ ከ400ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን በስደት የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት የመኖሪያ ፈቃድ እንደሌላቸው ይታወቃል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ መስፋፋት በኋላ በአሰሪዎቻቸው ከቤት እየተባረሩ በጐዳናዎችና በኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት ደጃፍ ላይ የሚጣሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በእጅጉ መጨመሩንና ባለፉት አራት ሳምንታት ብቻ 133 ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአሰሪዎቻቸው ከቤት ተባረው እንደተጣሉ ቢቢሲ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት መረጃን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡  

Read 1052 times