Print this page
Saturday, 08 August 2020 12:06

ሽንትን ቋጥሮ መቆየት አለመቻል (OAB)

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(6 votes)

   በእንግሊዝኛው Overactive Bladder (OAB) የተሰኘው ከሽንት ፊኛ ጋር በተያያዘ የሚገለጸው ችግር ምንነት እንደሚከተለው ነው፡፡
Urgency…. አፋጣኝ….. ሽንት ሲመጣ በድንገት ከመሽናት በስተቀር ይዞ ለመቆየት ወይንም በሁዋላ እሸናዋለሁ ብሎ ለመታገስ አለመቻል …ይህ የሽንት ከረጢቱ ሙሉ በመሆኑ ወይንም ተወጥሮ ብቻ አይደለም፡፡  አንዳንድ ጊዜ ሽንት ቤት ለመድረስ ጊዜ ሳይሰጥ በልብስ ላይ እስከመሽናት ሊያደርስ ይችላል፡፡  
Frequency…. ድግግሞሽ…. በ24 ሰአት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ ከስድስት እስከ ስምንት ጊዜ መሽናት እንደ ችግር ባይታይም ከዚያ በላይ ወደ ሽንት ቤት መመላለስ ካለ ግን ድግግሞሹ ከፍ ያለ መሆኑን ያመለክታል፡፡
Nocturia…. በእንቅልፍ ሰአት… ምናልባትም ከሁለት ሶስተኛ በላይ የሆኑ ወንዶችና እድሜአቸው  ከ70 አመት በላይ የሆኑ ሴቶች ቢያንስ አንድ ጊዜ እንደሚነሱ ቢገመትም ሽንትን ይዞ መቆየት የማይችሉ ሰዎች ግን ለሊት በተደጋጋሚ ለሽንታቸው ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ ይገደዳሉ፡፡
‹‹….እናቴ… አባቴ… በክፍለ ሀገር ነዋሪ ነበሩ:: ህይወታቸው ሲያልፍ ግን እኔ ከቤቴ መውጣትና ሄጄ መቅበር አልቻልኩም፡፡  ምክንያቱም ሽንቴን መቋጠር ስለማልችል ነው…››
ወንድይፍራው መሸሻ ከሳሪስ
እነዚህ ስእሎች ሁለት አይነት ናቸው፡፡ በዳር በኩል ያለው ጤናማው የሽንት ፊኛ ሲሆን ከጎን ያለው ደግሞ ሽንትን ይዞ መቆየት የማይችለው የሽንት ፊኛ ነው፡፡  ይህን መረጃ ለንባብ ያለው  Cleveland Clinic 2020 ነው፡፡
ለመሆኑ ሽንትን የመቋጠር ችግር በምን ምክንያት ይከሰታል?
ሽንትን የመቋጠር ችግር በወንድም በሴትም ላይ የሚከሰት የጤና እክል ነው፡፡ በተለይ ግን ሴቶች የወር አበባ በሚቋረጥበት ወቅት ብዙዎች ላይ ሊከሰት የሚችል የጤና ችግር ነው፡፡ በድንገት የሽንት መምጣት፤  ሽንትን ይዞ መቆየት አለመቻል፤ ለሊት ወደ መጸዳጃ ቤት መመላለስ የመሳሰሉት ችግሮች የሚከሰቱት የሽንት ፊኛ ሽንትን ይዞ ለመቆየት የማያስችለው የነርቭ ሕመም፤ የጡንቻዎች መላላት ወይንም መድከም፤ የአልኮሆል ተጠቃሚ መሆን፤ በህመም ምክንያት የሚወሰዱ አንዳንድ መድሀኒቶች፤ ከልክ በላይ ውፍረት ሲኖር መሆኑን ተመራማሪዎች ይገልጻሉ::  ስለዚህ ከሕመሙ ለመፈወስ የአኗኗር ለውጥ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን መረጃውን ያወጣው አካል ይገልጻል፡፡ ህመሙ በብዙዎች ዘንድ የታወቀ እና መፈወስ የሚችልም ነው፡፡ ነገር ግን የህክምና ባለሙያውን ምክርና የህክምና አገልግሎት መጠቀም ብቻ ሳይሆን የታካሚውን እርዳታ በእጅጉ ይሻል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ የህይወት ልምዶችን ከመተው ጀምሮ የመድሀኒቶችን አይነት ለውጥ እንዲሁም ነርቭን የሚያነቃቃ ስራ ስለሚሻ ነው፡፡
ሽንትን የመቆጣጠር ችግር የደረሰባቸው ሰዎች ለሕክምና ባለሙያዎች መረጃ መስጠት ለህክምናው ይበልጥ ያግዛል፡፡  አኗኗርን ለማስተካከል የሚረዱ ነገሮችን ማድረግም ይጠቅማል፡፡   
የእለት ውሎን መመዝገብ…. የአንዱን ቀን ፈሳሽ አወሳሰድ መጠኑን መመዝገብ፤ ወደ መጸዳጃ ቤት የተመላለሱበትን ሰአት መመዝገብ፤ ሽንት ከቁጥጥር ውጭ የፈሰሰ ከሆነ ለምን ያህል ጊዜና መቼ እንደተከሰተ መመዝገብ ፤ ሽንት ከቁጥጥር ውጭ በመሆን ሲፈስ ምክንያቱን ለምሳሌም…..
ሳል በማሳል ጊዜ….
በማስነጠስ…
ሳቅ በመሳቅ….
የመጸዳጃ ቤት ለመድረስ ባለመቻል… ወዘተ.. የሚሉትን በማስታወሻ ማስፈር ያስፈልጋል::
አመጋገብን መቆጣጠር…. አንዳንድ የምግብ አይነቶችንና መጠጦችን አወሳሰዳቸውን መቀነስ ወይንም ማስወገድ የሽንት ፊኛ ሽንትን በመያዝ ጊዜ ሊሰጥ የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡የምግብና መጠጥ አይነቶችም የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሻይ…. ቡና…. አልኮሆል…
ቼኮሌት….
የማነቃቂያ ኬሚካል ያለባቸው ለስላሳ መጠጦች….
ቲማቲም እና ከቶማቶ የተሰሩ ምግቦችን….
ጣፋጭ እና አሲድነት ያላቸው ምግቦችና መጠጦች…
አርተፊሻል ጣፋጭነት ያላቸውን ምግቦችና መጠጦችን ማስወገድ ወይንም መቀነስ እጅጉን ይጠቅማል፡፡
በአጠቃላይም አመጋገብንና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ጤናማ ጡንቻዎችን እና የነርቭ ስርአትንም ለማሻሻል ስለሚያስችል ከህክምና ባለሙያዎች ምክር በተጨማሪ በቫይታሚን ዲ እና ሲ ..የበለጸጉ ምግቦችን በመመገብ እና የአኑዋኑዋር ዘዴን በመቀየር ጤናማ ለመሆን ይቻላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከልክ ያለፈ ውፍረት ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ይጠቅማል፡፡  
ሲጋራ ማጤስን ማቆም…. ሲጋራ ማጤስ የሽንት ፊኛን ጡንቻዎች ሊያስቆጣ ይችላል፡፡  ተደጋጋሚ ሳል ማሳልን ሊያስከትል ስለሚችል የሽንት ማምለጥ ሊኖርይ ችላል፡፡
ብዙ ፈሳሽ መጠጣት…. የሚጠጡ ነገሮች ሁሉ የሽንት ፊኛን ሊያስቆጡ ይችላሉ ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌም ከሚጠጡት መካከል ውሀ ይገኝበታል፡፡ በእርግጥ ሽንትን የመቆጣጠር ችግር ያለባቸው ሰዎች ውሀን ጨምሮ ፈሳሽን በብዛት ከመውሰድ የሚቆጠቡ አሉ፡፡ በዚህን ጊዜ የሚሸናው ሽንት ቀለሙ ወደ ጥቁረት የሚወስደው ብጫ እና ጠንካራ ሽታ ያለው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የሽንት ፊኛውን ሊያስቆጣ እና ሕመም እንዲሰማው ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ሰውነትን ፈሳሽ አለማሳጣትና እስኪረኩ ድረስ ውሀ መጠጣት ያስፈልጋል፡፡ ወደ መኝታ ከመሄድ በፊት ግን ቢያንስ ከሁለት ወይንም ከሶስት ሰአት በፊት ፈሳሽ መውሰድና ከመተኛት በፊት በተቻለ መጠን መሽናት ለሊት ወደ መጸዳጃ መመላለስ እንዲቀንስ ይረዳል፡፡
የሽንት ፊኛን  ማጠንከር….
ሽንትን ይዞ መቆየት ወይንም የመቆጣጠር ችግር ሲፈጠር ጡንቻ ጠንከር እንዲል ለማድረግ የሚያስችል አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡
ሽንትን ለመሽናት የሚመላለሱበትን ሰአት ለማስረዘም መሞከር… ለምሳሌም በየሰአቱ መጸዳጃ ቤት የሚሄዱ ከሆነ ትንሽ ፈቀቅ እንዲል መሞከር…
በድንገት ሽንት የመሽናት ስሜት ሲከሰት በተመቻቸ ቦታ ቁጭ ማለትና ትንፋሽን ወደ ውስጥ መሳብ እና ማውጣት ….
ሌሎች እራስን ማዝናናት የሚችሉ ሀሳቦችን ማሰብ የመሳሰሉትን በማድረግ ሽንት የመሽናት አፋጣኝ ስሜቱን ማርገብ እና በተረጋጋ ሁኔታ ወደ መጸዳጃ ቤት መሄድ ያስችላል፡፡
በመሽኛ አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችን እያኮማተሩና እያጠናከሩ እስፖርት እየሰሩ የነርቭ ሲስተሙም በተሟላ ሁኔታ መስራት እንዲችል ማድረግ ጥሩ ነው፡፡
በተቻለ መጠን ወደ ሕክምና በመሄድ የባለሙያ ምክርን ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡


Read 13158 times