Print this page
Saturday, 01 August 2020 13:29

የኮሌጅ ምሩቃን ወጣቶች የሥራ አጥነት ችግሮች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  - ወጣቶች ሥራ ካልያዙ ወደ ፅንፈኝነት ነው የሚሄዱት
          - ወጣቶች ጠብመንጃ መያዝ መናፈቅ የለባቸውም
          - ግብርናውን ታሳቢ ያደረጉ የሥራ ዕድሎች በስፋት መታሰብ አለባቸው


         በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ተመርቀው የወጡ ወጣቶች ያለሥራ ተቀምጠዋል:: መንግስት ሰሞኑን እንደገለፀው በዘንድሮ ዓመት ከ3ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል ቋሚና ዘላቂነት ያለው ባይሆንም፡፡ ወጣቶች በቀላሉ የነውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገቡትም ከሥራ አጥነታቸው አንፃር እንደሆነም ይነገራል፡፡
ለመሆኑ እስከዛሬ የተቀረፁ የሥራ ዕድል ፈጠራዎች ለምን ውጤታማ አልሆኑም? የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ምን ውጤት አስገኝቷል? ለወጣቱ በቂ የሥራ ዕድሎች መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው? የሌሎች አገራት ተሞክሮዎች ምን ያሳያሉ?
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ  አለማየሁ አንበሴ የኢኮኖሚ ምሁሩና ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ጋር በወጣቶች የሥራ አጥነት ችግሮች ዙሪያ ቀጣዩን ቃለምልልስ አድርጓል፡፡            በአንድ ሃገር ውስጥ ስራ አጥነት የሚያስከትላቸው ችግሮች መገለጫቸው ምንድን ነው?
ስራ አጥነት ለብዙ ሀገሮች ከባድ ችግር ሆኖ የቆየና አሁንም የቀጠለ ጉዳይ ነው:: በተለይ በ1980ዎቹ እ.ኤ.አ አፍሪካ ውስጥ በጣም ተንሰራፍቶ የነበረ ነው:: በወቅቱ ብዙ ረብሻዎችን ያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በእነዚህ በቀጥታ ከስራ አጥነት ጋር በተገናኙ ረብሻዎችም ወደ 40 የሚጠጉ የመንግስት ግልበጣዎች ተካሂደዋል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ይህ አሁንም ብዙም የተቀረፈ ችግር አይደለም፡፡ የአለማቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ራሱ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ብዙ ነገር እየሠራ ነበር፤ ነገር ግን ፈቅ ያለ ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ በየጊዜው የወጣቱ ቁጥር እየበዛ፣ ትምህርት ቤት እየተስፋፋ ዩኒቨርስቲ እየተከፈተ  ነው፡፡ ወጣቶች በዚህ የትምህርት ዕድል አዕምሮአቸው እየተስፋፋ ብዙ ጠያቂ ሆነዋል፡፡ ይህ በሆነ ቁጥር ደግሞ ጥያቄያቸው ውስብስብና ብዙ እየሆነ ነው የሚመጣው፡፡ ይህ ወጣት ትምህርት ቤት ባይገባና ወትሮ እናትና አባቱ በሚኖሩበት መንገድ ቢኖር፣ ብዙ ጥያቄ ላይነሳ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የትምህርት መስፋፋቱ ሲመጣ ወጣቶች ተምረው ስራ መያዝ እንደሚገባቸው፣ ይህን ፍላጐታቸውን፣ ሲያዳምጡ ደግሞ የፖለቲካ ስርአቱ ለእነሱ ጥቅም እንደማይሰጥ የመገንዘብ ሁኔታ ሲጐለብት፣ ነገርየው ወደ ማህበራዊ ቀውስ ነው የሚያመራው፡፡ የወጣቶች ስራ ካልያዙ በየትኛውም መንገድ ወደ ጽንፈኛነት ነው የሚሄዱት፡፡ የሃይማኖትና የጐሣ ጽንፍ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚያ መንገድ አላማቸውን የሚያሳኩ ነው የሚመስላቸው:: በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት በሠራሁበት ወቅት የተገነዘብኩት፣ እንዲህ የስራ ፈላጊነት ሲንሰራፋ ወጣት ጥፋተኝነት እየበረታ መሄዱን ነው፡፡ ፋብሪካዎችን ማቃጠል፣ የሰዎችን ንብረት ማውደም፣ እርስ በርስ መጨራረስ፤ በአጠቃላይ የሚያደርጉትንም አያውቁም፡፡ ለምሣሌ የመካከለኛው አፍሪካ (ሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ) በምትባለው ሀገር የስራ አጥነቱ ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ የተነሳ በሃይማኖት ይጋጩ ነበር፡፡
እኛም ወደዚያ መስመር እንዳንገባ ነው የሚያሰጋው፡፡ ወጣቶች ጠመንጃ መያዝ መናፈቅ የለባቸውም፡፡ ጠመንጃ ከያዙ ማንንም መቀማትና መዝረፍ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ይሄን ደግሞ  የፖለቲካ ሰዎች እንደ መልካም እድል ይጠቀሙበታል፡፡ ወጣቶችን ከራሳቸው ጐን ያሰልፏቸዋል፡፡ በርካቶቹ የአፍሪካ የጦር አለቆችና አማፂያን፣ ይህን የወጣቶችን ስራ አጥነት ነው እንደ መልካም አጋጣሚ የሚጠቀሙበት፡፡ በርካቶቹ የአፍሪካ ሀገራት በዚህ መንገድ አልፈዋል፡፡ አሁንም በዚሁ አዙሪት የሚዳክሩ አሉ፡፡ ኢትዮጵያም ይሄ ነገር እያጋጠማት ይመስላል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ከዩኒቨርስቲ እየተመረቁ ያለሥራ ተቀምጠዋል፡፡ ኢንጂነሮች ሳይቀሩ ስራ አጥ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከተስፋ መቁረጥም ሆነ ነገሮችን ካለማገናዘብ ህንፃ ማቃጠል፣ መዝረፍ፣ ማውደም የሰው ህይወት ማጥፋት የመሳሰሉ አደገኛ ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ዋናው ቁም ነገር፤ እነዚህን ስራ አጥ ወጣቶች በተለያየ መንገድ በኢኮኖሚው ውስጥ ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡
በየጊዜው ስራ አጥነትን ለመቀነስ የሚነደፉ ስልቶችን እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን ችግሩ ሲቀንስ አይታይም፡፡ እነዚህ ስልቶች ውጤታማ እየሆኑ አይደለም ማለት ነው?
በቅርብ ጊዜ እንኳ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ፣ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት 10 ቢሊዮን ብር ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ተዘዋዋሪ ፈንድ ተመድቦ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ስለዚህ ፕሮጀክት ሪፖርት  ሰምቼም አላውቅም፡፡ ምን ላይ ይዋል፣ ምን ይደረግ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል የዋና ኦዲተሩን ሪፖርት በየጊዜው ስንመለከት፣ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው የሚባክነው፡፡ ይሄ ገንዘብ ምናለ ለወጣቶች የስራ ፈጠራ ቢውል ኖሮ ያስብላል፡፡ በርካታ ገንዘብ ነው ለወጣቶች እየተባለም የሚጠፋው፡፡ በማህበር መደራጀት፣ ብድር መስጠት እየተባለ ብዙ ነገር ተደርጓል ግን ምን ያህል ውጤታማ ናቸው? የሚለውን የሚመልስ የለም፡፡ በሃላፊነት የሚቀመጡ ሰዎች ከፖለቲካ ጋር በተገናኘ ስለሚቀመጡ ለብዙ ችግር የተጋለጠ የአሠራር ውጤት ነው የሚሆነው፡፡ በአብዛኛው የፖለቲካ አላማን ግብ ታሳቢ ያደረገ እንጂ በትክክል ወጣቶችን ስራ ለማስያዝ የመሆን እድሉም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህ ነው ፈቅ ያለ ነገር የማናየው፡፡ በየአመቱ ከዩኒቨርስቲ በመቶ ሺህዎች ይመረቃሉ፤ ነገር ግን ስራ የለም:: በማስተርስ ደረጃ ተመርቀው እንኳ ስራ የሚያጡ እየተበራከቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ጉዳይ በስፋት ሊመከርበትና ጥሩ ስትራቴጂ ሊነደፍበት ይገባል፡፡
እርስዎ በተደጋጋሚ ሃገሪቱ ያላትና የግብርና አቅም ያነሳሉ፡፡ ወጣቶችን ከግብርና ስራ ጋር የማቆራኘትና የተማሩ ወጣት አርሶ አደሮችን በማፍራት ረገድስ ምን ያህል መሥራት ይቻላል? ያንን ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች አሉ?
አንዱ ትልቁ ችግር የሀገራችን የግብርና አቅማችን በጣም ብዙ ቢሆንም፤ ግብርና ተኮር የሆነ ልማት መስራት ያቃተን መሆኑ ነው፡፡ በቂ ውሃ፤ በቂ መሬት፣ በቂ የተፈጥሮ ፀጋ አለን፣ ነገር ግን ያንን በተገቢው አሟጦ ለመጠቀም ያለመ ስራ ሳይሰራ መቅረቱ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የግብርና አቅም እያለን እኮ እስካሁን ድረስ ስንዴ ከውጭ እያስመጣን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የመንግስት ሠፋፊ እርሻዎች፣ የግል እርሻዎች እየተባሉ የተሠሩ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ የእርሻ ኢንቨስትመንት ተብሎ በግል የተያዙ እርሻዎች ነበሩ፡፡ ምን ያህል ውጤት እንዳመጡ ሳይታወቅ ኢንቨስተሮች ተመልሶ መሬቱን እየተቀሙ መሆኑን እንደጋምቤላ ካሉ ክልሎች ማየት ይቻላል፡፡
ይሄ እንግዲህ ወጥ የሆነ ጠንካራ ስልት እንደሌለን ያሳያል፡፡ ግብርና ተኮር የሆነ የኢኮኖሚ መሠረት ይዘን፣ ለወጣቶች ሌላ የስራ ዕድል እንፈጥራለን ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ፋብሪካ እየተባለ ብዙ ጥረት ተደርጓል:: የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግን ሚሊዮኖችን ሊቀጥሩ አይችሉም፡፡ የሚቀጥሩት ውስን ነው፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ስራ አጦችን ማስተናገድ የሚችለው ትልቁ የሀገሪቱ አቅም ግብርናው ነው፡፡ ግብርናውን ታሳቢ ያደረጉ የስራ እድሎች በስፋት መታሰብ አለባቸው:: ትልቁ ሌላው አቅም የግል ዘርፉን ማሳደግ ነው፡፡ የግል ሴክተሩ ቢያድግ ሚሊዮኖች የራሳቸውን ገቢ ያመነጫሉ፤ ይሰራሉ:: በሀገሪቱ በቂ የስራ እድሎችን መፍጠር ይቻላል፡፡ ችግሩ ያለው መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር ፖሊሲያቸው መቀያየሩና ፖሊሲያቸው ወደ ተግባር አለመለወጡ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ እስካሁን ድረስ በነበረው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራም፣ ገበሬው ገና ንቃተ ህሊናውና የፖለቲካ ባህሉ ስላልዳበረ በአስቸኳይ ለማዳበር ይጠቅመናል ተብሎ ሲሠራበት ነበረ፡፡ ነገር ግን እሱ የሠራም አልመሠለኝም፡፡ ስለዚህ መደረግ ያለበት አንደኛ የወጣቶችን ንቃተ ህሊና ማሳደግ ነው፡፡
እኛ አሁን ወደ 11 2ሺህ ስካውቶች አሉን፡፡ ስለ ዜግነት እናስተምራቸዋለን:: ስለ ሀገራቸው ስለ ሠላም ነው፤ የምናስተምራቸው፡፡ ስለዚህ ወጣቶች፣ በስራ ዲስፒሊን፣ በሀገር ፍቅር በመቅረፁ በኩል የሲቪል ማህበራት ድርሻ የማይተካ ነው ስለዚህ የሲቪል ማህበራት እንደ ልባቸው እንዲንቀሳቀሱ መንግስት ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ እንደምናውቀው እስካሁን የግል ሴክተሩ እንዲያድግ የሚፈልግ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን አልነበረም፡፡ አሁን ጅምሮች አሉ፡፡ በመንግስት ተይዘው የነበሩ እንደ ቴሌኮም ያሉትን ሊበራላይዝ ለማድረግ መታቀዱ መልካም ጅምር ነው:: ይህ መሆኑ ስራ አጥነቱን በመቅረፍ ረገድ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ እንደሚታወቀው አንድ መንግስት ልማታዊ መንግስት ነኝ ማለት የሚችለው ሶስት ዋነኛ ምሰሶዎች ሲኖሩት ነው፡፡ አንደኛው መንግስት መዋለ ንዋይ ስትራቴጂ ያቀርባል፤ የግል ሴክተሩ የማይሰራውን ይሠራል፤ የግል ሴክተሩ ደግሞ አግሮ ኢንዱስትሪ ይከፍታል፤ ስራ ያስፋፋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የግል ሴክተሩ ሚና ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ውስን ነው:: ምሁሩ ደግሞ ምርምር እየሠራ ስትራቴጂ ፖሊሲ ይነድፋል፡፡ በዚህ በግል ሴክተሩንም መንግስትንም ይደግፋል፡፡ እነዚህ ሶስቱ አገራችን ላይ ቅንጅት የላቸውም ብዙዎቹ የመንግስት ስልጣን የሚይዙ ሰዎች፤ እነሱ የሚሉትን ነገር የሚያደንቁላቸውን ሰዎች ነው ከየሴክተሩ የሚሰበስቡት፡፡ ስለዚህ ለየት ያለ ሃሳብ አያገኙም፡፡ የሃሳብ መፋጨትና የዳበረ ውይይት ከሌለ ደግሞ የነጠረ ነገር አይገኝም፡፡ እነዚህ አካሄዶች ካልተስተካከሉ፣ ሀገራችን ውስጥ ያን ያህል የሚቀየር ነገር ይኖራል ማለት አይቻልም፡፡
እስከዛሬ በነበረው ሂደት ሀገሪቱ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ሁነኛ መፍትሔ የሆነ ፖሊሲ ነበራት ማለት ይቻላል?
ፖሊሲ አለ፡፡ መንግስትም በየጊዜው በጀት ይመድባል፡፡ ችግሩ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በየጊዜው የሴቶችና የወጣቶች ስራ አጥነት እየተባለ ሴሚናርና ወርክሾፕ ሲዘጋጅ እናስተውላለን፡፡ ከሁሉም ነገር ሴሚናርና ዎርክሾፕ ላይ ያበቃል መሬት ላይ የሚወርድ ነገር አይኖርም፡፡
መንግስትን መንግስት የሚያደርገው ታች ያለው ከህዝቡ ጋር በቀጥታ የሚያገናኘው አሠራር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የወረዳ አስተዳደር ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ እዚያ ያሉ አስተዳዳሪዎች ከህዝቡ ጋር ሊያገናኙ የሚያስችሉ ናቸው ወይ? ብቃት አላቸው ወይ? ልምዱስ? እውቀቱስ አላቸው ወይስ ካድሬ ብቻ ናቸው? የሚለውን መጠየቅ ያስፈለጋል፡፡ እነዚህን መፈተሹ ተገቢ ነው:: አሁን ላይ ይሄን የወጣቶች መነሳሳት ወደ መልካም እድል ካልቀየርን በስተቀር ማንም የግል ባለሀብት ወደነዚህ አካባቢዎች ሄዶ መስራት አይፈልግም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ከስሩ ማጥራት፣ የወረዳ መዋቅሮችን መፈተሽ፣ በባለሙያ ማደራጀት ያስፈልጋል:: ያለውን መሠረተ ልማት እያፈረሱ፣ ባለሃብቶች ገብተው ይስሩ ማለት የማይሆን ነገር ነው፡፡ በዚህ በኩል ሰፊ ምክክር ያስፈልገዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የግል ሴክተር ስንል 85 በመቶ ገበሬውንም ይጨምራል፡፡ ገበሬው የግል ሴክተር ነው፡፡ ራሱ ያመርታል፤ ራሱ ይሸጣል፡፡ በዚህ በኩል ያለውን አቅምም በፖሊሲ ደረጀ መፈተሽና ከወጣቶች ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች እጅና እግር አላቸው፤ ትምህርት አላቸው፣ እውቀት አላቸው፡፡ ስለዚህ እድል ካገኙ ሀገር ሊያሳድጉ ይችላሉ፡፡ ግን ሁልጊዜ ዎርክሾፕ እየተባለ የሚደረገው ምናልባት ከአፍሪካ ውስጥ የኛ የላቀ ሳይሆን አይቀርም፤ ነገር ግን መሬት ላይ የሚወርድ ነገር የለም፡፡ ይሄ ከካድሬዎች ይልቅ ባለሙያዎችን ባሳተፍን ቁጥር እየተቀረፈ የሚሄድ ችግር ነው፡፡
ለምሣሌ አ.አ.ዩ እኔ እንኳ ያስተማርኳቸው ወደ 320 የሚሆኑ አሉ፤ በልማት አስተዳደር የተመረቁ፡፡ ከእነዚህ ባለሙያዎች አንዳቸውም የወረዳ ጽ/ቤት ገብተው እየሠሩ ነው ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ ለምን እንደነዚህ አይነት ባለሙያዎች ወረዳዎችን አይቆጣጠሩም? ጉዳዩ በአጠቃላይ ሰፊ የመዋቅር፣ የአመለካከትና የስትራቴጂ ፍተሻ የሚያስፈልገው ነው፡፡ መንግስት በዚህ በኩል ጠንካራ ስራ ይጠበቅበታል፡፡
የተማሩ ወጣቶችን እንዴት ውጤታማ አርሶ አደር ማድረግ ይቻላል?
ተሞክሮው እኮ እዚሁ እኛ ሃገር አለ፡፡ አብዛኛው ደርግ የወረሰው ሠፋፊ እርሻ እኮ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ወጣቶች የጀመሯቸው ናቸው፡፡ እነ “አምባሽ”፣ አዋሽ ሸለቆ ላይ የተጀመሩ እርሻዎች ወጣት የዩኒቨርስቲ ምሩቃን የጀመሯቸው ናቸው፡፡
ባሌና አርሲን የስንዴ ሀገር ያደረገው የ“ካዱ” ፕሮጀክትን የጀመሩት’ኮ ከዩኒቨርስቲ የወጡ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህም እንዲህ መስራት ይችላሉ፡፡
የዎላይታ አግሪካልቸራል ደቨሎፕመንት ተብሎ የተጀመሩ ስራዎች ሁሉ ነበሩ፡፡ አሁንም እንደነዚህ አይነቶቹ ፕሮጀክቶች ናቸው ሊያግዙን የሚችሉት፡፡ ስኳር ፋብሪካዎች ሲኖሩ፣ ሠፋፊ የሸንኮራ አገዳ እርሻዎች መፍጠር ይቻላል፣ የፍራፍሬ፣ የአትክልት የተለያዩ እርሻዎች አሉ፡፡ የግብርና ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች ይሄን ማሰብ አለባቸው፡፡ ትላልቅ የግል ሴክተሮች ሲመጡም፣ ሙያ ማጋራት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የግብርና ባለሙያዎችን ማሰልጠን ያስፈልጋል፡፡ ሠፊፋ ሜካናይዝድ የግብርና ኢንቨስተሮችን ከውጭ መጋበዝ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ለወጣቶች ልምድ ልውውጥም ለስራ እድልም ጠቃሚ ነው፡፡ አስታውሳለሁ  ከዚምባብዌ ነጭ ገበሬዎች ሲባረሩ፣ ወደኛ ጋ መጥተው ኢንቨስትመንት ለማድረግ ጠይቀው ነበር፤ መንግስት አንፈልጋችሁም ብሎ መለሳቸው:: እነሱ ሞዛምቤክ ሄደው የሃገሪቱን የእርሻ ውጤት በሁለት አመት ውስጥ በሶስት እጥፍ አሳደጉት፡፡ እንደዚህ አይነት ኢንቨስተሮች በሚመጡበት ጊዜ ወጣቱም ይማርና ወደዚያ አይነቱ ኢንቨስትመንት ይሳባል፡፡ የራሱን አቅም እስኪገነባ በእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ተቀጥሮ መስራት ይችላል:: በዚያውም የግብርና ግብአቶችን ማምረት፣ ለኤክስፖርት የሚሆን እሴት የጨመረ ምርትም ማምረት ይችላል ወጣቱ፡፡ እኛ እኮ ዛሬም የቅባት እህል በርካሽ እየላክን፣ የላክነው ተጨምቆ የሚቀርብልንን ዘይት በውድ ዋጋ እየገዛን ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች እንኳ በተግባር ለመስራት የሞከረ የለም:: ሁልጊዜ ነገሮች በዎርክሾፖች ተውጠው ያልፋሉ፤ በዚያው ይቀራሉ፡፡
በቀጣይ ስራ አጥነትን ለመቅረፍ ምን አይነት ስትራቴጂዎች መንደፍ አለባቸው ይላሉ?
አሁን እንደማየው፤ ጠ/ሚኒስትሩ ጥሩ መነሳሳት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የግል ሴክተሩን ለማሳደግም ብዙ እየጣሩ ነው፡፡ በዚህ ሂደት አንድ ቢሞክሩት የምለው፣ የተወሰነ ቦታ መርጠው ዞን ሊሆን ይችላል፤ ጥሩ ቦታ መርጠው የሙከራ ፕሮጀክት ቢዘረጉ መልካም ነው፡፡ አስቀድሜ እንደጠቀስኩት፤ የባሌና አርሲን የስንዴ አቅም ያጐለበተው “ካደ” የተሰኘው ፕሮጀክት ነበር:: ያ ፕሮጀክት በተማሩ ወጣቶች ነበር የተመሰረተው:: አሁንም አንድ ቦታ መርጠው ይሄን መሰሉን ፕሮጀክት ነድፈው ወጣቶችን ወደ ስራ ቢያሰማሩ መልካም ነው፡፡ የእርሻ ስራ ደግሞ ውጤቱ አመታት የሚያስጠብቅ አይደለም፡፡ አንድ አመት በቂ ነው፡፡ በአመቱ ውጤቱን ያገኙታል፡፡ ይሄን ለማድረግ ግን በዚያ በተመረጠ ቦታ ያለውን አስተዳደር ማስተካከል፣ ብድር ማመቻቸት የመሳሰሉት ተደርገው ቢሞከር፣ ወጣቶቹን በአንዴ ሊያሻግራቸው ይችላል፡፡ ይሄ የሙከራ ስራ ውጤተማ ሲሆን ሌላውም ያንን እያየ ይተገብራል፡፡ ሊለሙ የሚችሉ አካባቢዎችን መለየት ያስፈልጋል፡፡ የወጣት ጥፋተኝነት ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየትም፣ ከዚሁ ግብርና ስራ ጋር የተያያዘ ፕሮጀክት መንደፍና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡        


Read 3140 times