Saturday, 01 August 2020 13:21

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

  “የመጪው ትውልድ ሃብት አስተሳሰቡ ነው”
                                  
               ለህፃናት መማሪያ በተዘጋጁ ስዕላዊ መጽሐፍ ላይ “ህልም ሰራቂው” (DREAM STEALER) “የሚል ስቶር አለ። ታሪኩ የቤታቸው መንገድ የጠፋባቸው፣ ሁለት ወንድምና እህት የሆኑ ልጆች ገጠመኝ ነው። ልጆቹ የቤታቸውን አቅጣጫ ፍለጋ ጫካ ውስጥ ሲዘዋወሩ አንድ ቤት ያገኛሉ። ጠጋ ብለው ቢጣሩ በአካባቢው “አቤት” የሚል አልነበረም። በሩን ከፍተው ሲገቡ፣ በላስቲክ ተሸፍነው የተደረደሩ ነገሮች በጫጫታ ተቀበሏቸው።
“ምንድናችሁ?”
“ከሌሎች ሰዎች ተሰርቀን የታሰርን ህልሞች ነን!”
“ማነው ያሰራችሁ?”
“ህልም ሰራቂው”
ህልሞች አንድ በአንድ ፈትተው ወደ ባለቤቶቻቸው እየመለሱ ሳሉ እያሉ ህልም ሰራቂው መጣ። …ከዛስ?
***
ወዳጄ፡- ግሎባላይዜሽን በአንድ ወቅት የጥቂት አሳቢያን ህልም ነበር። ዛሬ ግን ዓለማችን በዓለም አቀፍ የግንኙነት መረብ ተጠላልፋለች ወይም Connected ናት። የኢንተርኔት አገልግሎት ለጥቂት ደቂቃዎች ሲቋረጥ፣ ምድራችን ኮማ ውስጥ ትገባለች። ኢንተርኔት ለሰለጠኑ ህዝቦች እስትንፋስ ነው…የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ!
ዓለምአቀፍ ኮሙዩኒዝም ወይም ህብረተሱታፊያዊነትም የብዙ አሳቢያን ህልም ነበር። ነገር ግን “ይኼ ነው” የሚባል የተጨበጠ ፍሬ አላፈራም። ደራሲው፡-
“ኦ! ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ” እንዳለው፤ በኮሙዩኒዝም ስም ብዙዎች ተጐሳቁለዋል፤ ተሰደዋል፣ ታስረዋል፣ ሞተዋል። በግሎባላይዜሽን ስም ግን ማንም ምንም አልሆነም።
ኮሙዩኒዝም የተቀደሰ ህልም ነው። ምክንያቱም ግማሾቻችን በበሬ አርሰን፣ በደቦ አጭደንና ወቅተን እንራባለን። አንዳንዶቻችን ደግሞ ብቻችንን በአንድ ማሽን አርሰን፣ ዘርተን፣ አጭደን ወቅተን ይተርፈናል፣ ይትረፈረፈናል፣ እንሸጣለን። ገዥ ቢጠፋ መንግስት ገዝቶ ሌሎችን ይረዳበታል።
የምግብ አቅርቦት ላይ ብቻ ሳይሆን መድሃኒት፣ ትምህርት የመኖሪያ ቤት፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና የመሳሰሉት የኑሮ ጉዳዮች ሁሉ፣ በእጅጉ የተራራቀ ልዩነት በመሃላችን አለ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኮሙኒዝምን ዓለም አቀፍ ማድረግ አልተቻለም። የማምረቻ መሳሪያዎችን ወይም የጭነት መገልገያዎችን በማሳደግና በሁሉም መንገድና በተሟላ ሁኔታ ራስን ሳይችሉ ኮሙኒዝምን ማሰብ ሞኝነት ነው። ኮሙዩኒዝም የተቀደሰ ግን የታሰረ ህልም ነው ቢባል አያስከፋም፤ ዕውቀትና ስልጣኔ የሚፈታው።
ዕውቀትና ስልጣኔ ኖሮ ሁሉም ራሱን ከቻለና ፍትህ በሚገባ ከሰፈነ ደግሞ ኮሙዩኒዝም ተባለ ካፒታሊዝም፣ መንግስተ ሰማያት ተባለ ገነት ማን ግድ አለው? የሁሉም ትኩረት ውበትን፣ ጥበብን መፈለግ፣ ተፈጥሮን መረዳትና መመራመር ይሆናል። ለራስ ጥሩ ጊዜ በመስጠት መኖርን መውደድ ሩቅ አይደለም።
ወዳጄ፡- የመጪው ትውልድ ሀብት አስተሳሰቡ ብቻ ነው። ምርቱን የሚያመርቱና ስራውን ጐንበስ ቀና ብለው የሚያቀላጥፉለት፣ ተጨቆንን ተረገጥን የማይሉ፣ ንብረት የማይዘርፉ፣ ዘር የማይቆጥሩ ታማኝ ባርያዎች አሉት - ሮቦቶች!
አንተ ካልተሳሳትክ እነሱ አይሳሳቱም። የእኔና አንተ እጅ ገጀራና ሽጉጥ ሲጨብጥ፣ የመጪዎቹ ወጣቶች እጅ ግፋ ቢል የሚጨብጠው ሪሞት ኮንትሮል ነው።
ወዳጄ ላንተና ለኔ ስልጣኔ የታሰረ ህልም ሆኖብናል! ዓባይን መገደብ ህልም ነበረ - የታሰረ ህልም ያለፈው ትውልድ በጊዜው በነበረው የመገበያያ ገንዘብ፣ የሃምሳ ብር ኖት ላይ የግድቡን ንድፍ በማተም፣ መጪው ትውልድ ከታሰረበት እንዲፈታው አደራውን ትቶ ነበር። ትውልዱም አላሳፈረውም። የዓባይ ግድብ ከሞላ ጐደል ዕውን ሆኗል።
ምስጋና ለቁርጥ ቀን ልጆች!
አፍሪካም ነፃ አህጉር የመሆን ህልም ነበራት፤ ለምዕተ ዓመታት የታሰረ። በልጆቿ ትግል ሊፈታ ችሏል። በዚህ ዘመን ቅኝ ግዛት አይታበብም። አፍሪካ የቀራት ጓዳ ጐድጓዳዋን ማጽዳት ነው - “ዘጐሰኝነትና ድህነትን።
ወዳጄ፡- ግለሰቦች ማህበረሰቦች፣ ማህበረሰባት አገርን፣ ሀገራት አህጉርን፣ አህጉራት ዓለማቀፋዊነት ይፈጥራሉ። እውነትን መሰረት ያደረገና አርቆ አሳቢነትን የተመረኮዘ ህልም በግለሰቦች ቢገለጥም ጥቅሙ የመላው ዓለም ህዝቦች ነው። ለምሳሌ የማርቲን ሉተር ህልም፤ የጥቁር አሜሪካውያን ብቻ አልነበረም። የአብዛኛውን የአሜሪካን ህዝብ ጨምሮ የመላው ዓለም ህልም ነበር። ምክንያቱም የወቅቱ ስርዓት (Order of the day እንደሚባለው እንዲሉ ብዙ የዓለም ህዝቦች ለጭቆና የተጋለጡበት ነበር። ግሪካውያን ግሪካውያንን፣ ጣሊያናውያን ጣሊያናውያንን፣ ፈረንሳውያን ፈረንሳውያንን፣ ነጭ አሜሪካውያን ነጭ አሜሪካውያንን (White trash እያሉ) ረግጠው ገዝተዋል። በኤሽያና በመካከለኛው ምስራቅም ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሟል። ሁሉም በጊዜያቸው ታልመው የተፈቱ አሮጌ ህልሞች ነበሩ።
የህልም ነገር ካነሳን አይቀር… ዘመናዊው የአሜሪካ መንግስት ሌሎች ሀገራት እንደሚያደርጉት ሁሉ የሀገሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ታሪክ፣ የመንግስቱን ግዛቶች አስተዳደርና ህገ መንግስታዊ ተቋም፤ የፍትህ ስርዓቱን፣ የሳይንስና የጥበብ ደረጃውን ለሌላው ዓለምና ለጐብኝዎች የሚያስተዋውቅበትን ተከታታይነት ያለው “This is America” በሚል ርዕስ የሚያዘጋጀው Guid line አለው። በዚሁ ጥራዝ (Booklet) ውስጥ በሚገኘው የስነ ጽሑፍ ዕፍታው በኦላን ፊዝጄራልድ የተፃፈውን “The great Gats by” የተባለውን መጽሐፍ የሀገሪቱ የስነ ጽሑፍ ሃብት አድርጐ ለአንባቢ ያስተዋውቃል። መጽሐፉን ባነበብኩበት ጊዜ ከተራ ልብወለድነት የተለየ ምንም ስሜት አልሰጠኝም ነበር። እንደውም ስንትና ስንት መሬትን የሚያንቀጠቅጡ የድርሰት ስራዎች ባሉበት አገር ይኸ መጽሐፍ ምሳሌ “icon” ሆኖ መመረጡ አስገርሞኛል። ጉዳዩ የገባኝ በኋላ ነው። መጽሐፉ (ልብ ወለዱ) አንድ ወጣት የወደዳትን ሴት ቀልብ ለመግዛት ሲል የሚያደርገውን የማንነት ግንባታ ይተርካል። በታላቁ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተምሮ፣ ገንዘብ አጠራቅሞ፣ ልጅቱ በትዳር በምትኖርበት ሰፈር ቤት ገዝቶ ይጐራበታል - ስትገባና ስትወጣ ለማየት። መልዕክቱ አንድ አሜሪካዊ የሚፈልገውን ወይም የሚመኘውን ለማድረግ ወይም ለሚወደው ሰው ሲል ማናቸውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም ነው። በአጭሩ “Yes, we can!” እንደሚሉት - “The Amcrican Dream!!”
ወዳጄ፡- ኢትዮጵያውያኖች ስር የሰደደ፣ የተዛመደ፣ የተጋመደ ቋጠሮ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ዓባይን ለመገንባት እንደተረባረቡት ሌሎች ህልሞቻቸውምንም የሚያሳኩት በጋራና በመተጋገዝ አንዱ ለሌላው መኖር ሲችል ነው። የአንዱ ጉዳት የሌላው ጉዳት፣ የአንዱ ድህነትና መፈናቀል የሌላው ህመምና ሸክም ነው። “አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል።”…እንደሚባለው።
…ሰውየው በህልሙ እግዜርን አገኘውና “እባክህ ለአንድ ደቂቃ አንተን ልሁን” ብሎ ለመነው አሉ።
“እሽ” ብሎት ስልጣኑን ለቀቀለት። አጅሬውም ከከፍታ ቦታ ላይ ቆሞ፣ የከተማውን ህዝብ፤ “ችግራችሁን ንገሩኝ” አላቸው፡፡ አንዱ እጁን አወጣና፤
“ራበኝ” አለ።
“ጥጋብ ይትረፍረፍልህ” አለውና ጠገበ።
ሌላኛው “አሞኛል” ሲል አመለከተ፡፡
“ጤና ሁን” ተብሎ ዳነ።
ሶስተኛው “ቤተሰቦቼን በግፍ ተነጥቄያለሁና ተበቀልልኝ” አለ
“ከእነዘርማንዘሩ እንዲወገድ ይሁን” አለው።
በዛው ቅጽበት የመጀመሪያዎቹ ጠያቂዎችን ጨምሮ የአገሩ ህዝብ ደብዛው ጠፋ። ጠያቂው ብቻ ቀረ…
“እግዜር” ስለነበረ ደነገጠ። የነበረው እንዲመለስ ቢፈልግ እንኳ የሚጠይቀው ማንም አልነበረም።
“ደቂቃዋ አልቃለች” አለ ዋናው ተገልጦ። እየሳቀም
“ሰው መሆን እንኳን አልቻላችሁም እንኳንስ…” አለና።
“ዳሩ ላይገባቸው ምን አዳረቀኝ” በማለት ያሰበ ይመስል… የጀመረውን ዓረፍተ ነገር ሳይጨርስ ተሰወረ።
“እፎይ!” አለ ሰውየው፤ ህልም መሆኑን ሲያውቅ።
***
ወደ ተረታችን ስንመለስ፡- ህልም ሰራቂው፤ ልጆቹን እንዳገኛቸው፡-
“ህልሞቹስ?” በማለት ጠየቃቸው
“ለባለቤቶቻቸው ተመልሰዋል?”
“ለምን?”
“ቦታቸው እዛ ነው። የአንተ ህልም ቢታሰር ምን ይሰማሃል?”
“እኔ ህልም የለኝም” ለማለት አፉን ሲከፍት፤
“አለሁ!” የሚል ድምጽ ከውስጡ ጮኸ። ለካስ አጉል አስተሳሰቡ የራሱንም ህልም አስሮት ኖሯል።
“እንዴ…ሁላችንም ህልም አለን ማለት ነው?”
“አዎና!” አሉ፤ ልጆቹ አንድ ላይ።  
“የናንተ ህልም ምንድ ነው?”
“ተደስቶ መኖር!”…
እሱም፤ “የኔም እንደናንተ ነው” ብሎ እየተደሰተ ወደ ቤታቸው ሸኛቸው።” ይባላል። አንተም ወዳጄ በአረፋ ደስ ይበልህ!
መልካም በዓል!
ሠላም!


Read 1385 times