Print this page
Saturday, 01 August 2020 13:19

ያልታረመው…

Written by  ዋሲሁን
Rate this item
(0 votes)

  መ
በማለዳ ደመና የተጎነጎነው የጀምበሯ ሹሩባ ያምራል፡፡ ተራራው በጤዛ እርሶ ደረቱን ለሙቀት አጋልጦ ሰጥቷል፡፡ ነፋስ ሁሉን በፍቅር ለመዳበስ ይመስል ለስለስ ባለ የዋሽንት ስልት ይርመሰመሳል፤ የባህሩ ውሃ እናቱ ደረት ላይ ጡት እንደሚዳብስ ህጻን ፈገግታው ልከኛ ነው፣ እስክስታም ለመውረድ ተዘጋጅቷል፡፡
ማለዳው እንደ ዛሬ ተውቦም አያውቅ፣ ሜዳውን የሞላው ሰብል ዝማሜው ለአምላክ መስዋዕት ለማቅረብ ይመስል ሥልቱ፣ ውበቱ፣ እንቅስቃሴው በመላዕክት የተቀነባበረ ነው ሁኔታው፤ ተፈጥሮን ለተፈጠረለት ሰጥቶ አለማድነቅ አይቻልም::

ሙሉ ቤቱ ለተበጣጠሱ ወረቀቶች መልክና ቀልቡን ሰጥቷል፡፡ ድባቤን እንድትጠርገው ሲነግራት ቆይቷል፣ ሥራ ስለበዛባት ይሁን ይስሃቅ የበለጠ እንዲጫወት ፈልጋ ብቻ የቤቱ ወረቀቶችና የጠረጴዛው የዳቦ ፍርፋሪ ሰው አልባ አስመስሎታል፡፡ ዘሪሁን የተማሪዎቹን የቤት ሥራ ካየ በኋላ የጀርባውን ባዶ ቦታ ልጁ ያሻውን እንዲያደርግበት ይተውለታል:: (ባዶ ቦታዎችን ማንም እንዳሻው እንደሚያደርጋቸው)
ድባቤም የወረቀቱ ምንጭ እንደማይነጥፍ ስለምታውቅ አፍሳ የቆሻሻ ማዳበሪያ ውስጥ ለመጨመር እምትጠይቀው አይኖራትም:: ለጥቁረት የሚያደላው ፊቱ ላይ ጀምበር እስክስታ ትመታለች። ዘሪሁን ያለ እድሜው ከግምባሩ በላይ እና ከጆሮው ጥግ ጥግ ያሉት ፀጉሮች ጥቁረት በቃኝ ብለዋል። ለስላሳ ፀጉሩ ከለስላሳ ፀባዩ ጋር ይመሳሰላል…፤ አቻነት፣ በቁመቱም፣ በመልኩም፣ በአነጋገሩም በጠቅላላ ተቁመተ ሥጋው ላይ ይነበባል፤ ገባ ካለው ግምባሩ ሥር ጠዋት ጠዋት ሳቂታዋ ፀሐይ የምትወጣ ነው የሚመስለው። የአመልም የገንዘብም ደሃ አይደለ፣ ለጋ የበቆሎ እሸት ከመሰሉት ጥርሶቹ የዕውነት ፈገግታ ነጥፎ አያውቅም።
ቀለሟ በብዙ ነገር ከዘሪሁን ትለያለች፤ ርዝመቷ ቅጥ ቢያጣም የተሟላው የሰውነት ቅርጿ ቁመቷን  ደብቆላታል። ማንም ተመልካች አይኑ ከሰውነቷ ቅርፅ ላይ እንጂ ከተትረፈረፈው ቁመቷ ላይ ተንጠልጥሎ አይቀርም። ጠባይዋም አይጎረብጥም፤ ግልፅነቷን የቀረቧት ሁሉ ቶሎ ስለሚረዱ በተለይ የወንዶች ልብ ውስጥ ስፍራዋ የተደላደለ ነው። ጠባቧ ሦስት ክፍል ቤት ውስጥ አራት ሰዎች ይኖራሉ። ሕጻኑ ይስሃቅ የቤቱ ጌጥ፣ የፍቅራቸው ፈርጥ ነው።

 እርቃን የቀረው ጭቅጭቃቸው ለሰሚው የዘወትር ነው የሚመስለው። ቀለሟ ቶሎ ትቆጣና ቶሎ ትበርዳለች። ዘሪሁን ለመቆጣትም ጮክ ብሎ ለመነጋገርም አቅም የለውም። ነገሮቹን በሙሉ ባለቤቱ ታወጣቸዋለች። ራሷ ቋጭታ ትሸኛቸዋለች። በዚህ በዚህ በቤታቸው የሚያድር የቂም ጥንስስ የለም።
ድባቤ (በቤት ሠራተኝነት ገብታ ቤተሰብ ከሆነች ስድስት ክረምት በበጋ ተራትቷል) ለአንድ ልጃቸው የተለየ ትኩረትና ክብካቤ ስታሳይ ቀለሟ ሁሌም ተቃዋሚ ናት፣ ዘሪሁን ደግሞ ‘በሕይወት እስካለን ድረስ ለአንድ ልጃችን የሚከፈለውን ሁሉ መክፈል አለብን’ ባይ ነው።
በተጋቡ በአምስት አመታቸው ወለዱ፤ ከዛ መደጋገም ፈልገው ነበር እምቢ አላቸው፣ ሕይወት ይኸው ናት… ድባቤም የዘሪሁንን ለልጁ የበዛ መንሰፍሰፍ ደመነፍሷ ይደግፈዋል። ገጠር የልጅነት ልጇን ክፉ ትዝታ ይመልስላታል፤ ልጇ ለጨዋታ ካጠገቧ ብር ብሎ ሄዶ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ መቅረቱን ህሊናዋ ውስጥ ይስልባታል። ተኝቶ አታምነውም፣ ሲበላም ሆነ ሲጠጣ  ካጠገቡ አትርቅም። ለዚህ ይመስለኛል ከመቅበጥም በላይ የምታሞላቅቀው (አንዴ ምርር ብሎ ሲያለቅስባት ደረቅ ጡቷን አጉርሳው ከእንባ ታግደዋለች) ይስሃቅም ከእናቱ ከቀለሟ ይልቅ ለድባቤ የሕጻን ልቡ ያደላል። ነፃነት በገፍ ትቸረዋለች። ይስሃቅ እቃ ቢሰብር፣ ምግብ ቢደፋ፣ ያሻውን ቢቀድ፣ ግድግዳ ላይ ወላ በቀለም ወላ በእስራስ ቢቸከችክ … ወዘተ የድባቤን ጉልበት ይጭነቀው እንጂ….

ዛሬ እንኳን ሥጋ ነፍስ ትቀብጣለች። ባዕቷን እንደ እንቁላል ሰብራ ነፃነቷን ታውጃለች።
“ፓንት ቀየርህ…?”
“ዛሬ እ’ኮ ነው ያደረግሁት…”
“እ.እ.”
“እና ሌላ?”
“አዲስ የገዛሁልህን መስቀያው ላይ አላየኸውም?”
“ቀሌ… ነጭ እንደማልወድ ነገሬሽ የለ…?” ተሰቅሎ አይቶት ነበር።
“አይዞህ የኔ ባርያ… ገላህ የሚለቅ መስሎህ ከሆነ አትጨነቅ፤ ከለቀቀም ከኔው ላይ ነው…” ከንፈራቸውን ገርበብ አድርገው ሁለቱም ፈገግ አሉ…
“ማታ’ኮ…” አላስጨረሳትም
“የተማሪዎችን ፈተና አርማለሁ እያልኩሽ…”
ብሽቀቷን ዋጥ አደረገች፣ (መጠማት ምርጫ ያሳጣል ለካ) ፊቷ ላይ ያለው ፈገግታ ወዲያው ፀሐይ በክረምት ደመና ስትጋረድ አይነት ሆነ…
“ከነገ ወዲያ ብታርም ምን ትሆናለህ?”
“ግሬድ ቶሎ አስገቡ ተብለናል!”
“እና ላንተ ከባድ መሆኑ ነው…?”
“ሳይሆን…” ጥፍር ቀለሙ ያልደረቀውን ጣቷን ከንፈሩ ላይ አስደገፈች፣ ታውቃለች የጥፍር ቀለም ሽታ ለአፍንጫው እንደማይስማማው… ዛሬ እሺ ከማለት ውጪ ምርጫም ማምለጫም እንደሌለው የሰራ አካላቷ ነገረው። እንዲህ በተመስጦ ይቅር ሲላት የሚለብሳቸው በተለይ የውስጠኛዎቹ ነጭ ሲሆኑላት ቀድሞ ደስታ ይሰማታል። ስለዚህ ዛሬ ማታ ዘሪሁን ያውቃታል… የልጁን እናት ቀለሟን።
የቤቱ የውስጥ አካል እንደ አዲስ በታደሰ የፍቅር ሙቀት እንዳበደ፣ የመስታወቶቹ ገላ መወርዛት ያሳብቃል። ቀለሟ ከሁሉም ቀድማ ነበር የተነነችው… (የልቧ ደርሶ የልብ አድርሳለች) ገና ከመኝታዋ እንደወረደች የሰውነቷን መሰባበር ወዲያው ነው ያጤነችው። የጎሽ ሰራዊት የተራመደባት ይመስል ድቅቅ ብላለች… ጣዕም ያለው ፍቅር ስላሳለፈች የልቧን ብብት የኮረኮሩት ያህል ነፍሷ የሳቅ ምጣድ ላይ ተጥዳ ትታመሳለች። እንዲህ አይነት ሌሊት ስታሳልፍ ይህ ባለ ግርማ ሞገሱ ከምትለው ውስጥ ነው (የዛሬውን ሌሊት አይነት ግን ይሄን ሳምንት ቀጣይ ነው) ‘ለካስ ፍቅርን ናፍቀው በንግግር ይከውኑታል’ አለች ለራሷ፡፡ እንደ ምንም ድካሟን እያጣጣመችም ቢሆን ለቤተሰቡ ጣፋጭ ቁርስ ለመስራት ወደ ማብሰያቸው አመራች… ይስሃቅና ድባቤ ክፍላቸው እንደተኙ ነው።
ዘሪሁን ከውጭ ሲገባ ተሰባስበው ቲቪ እያዩ  ነበር… ይስሃቅ እናቱ እግር ስር የተለመደውን የወረቀት ጨዋታውን ይዟል… የዛሬ ተመስጦው በመቀስ ወረቀቶችን መልክና ቅርፃቸውን ማሳጣት ነው…
ዘሪሁን ከኤኔሪኮ ያመጣላቸውን ኬክ ፊት ለፊታቸው አስቀመጠና ፈተና ለማረም ወደ መኝታ ቤቱ አመራ፣ እዛ ሲደርስ የጠበቀው የተለየ ነገር ነበር… የተማሪዎቹ የፈተና ወረቀት ተዘበራርቋል… ግማሹ መሬት ላይ ተበትኖ፣ ገሚሱ ተቀዳዶ፣ ሌሎቹም ይስሃቅ ለስዕል በበጠበጠው ቀለም እውነተኛ ቀለማቸውን አጥተው ተመለከተ… ግራ ተጋባ… እንደ መከፋት እንደ መናደድም አደረገው፤ ከመውጣቱ በፊት ውጤት የሰጠበትን ወረቀት ተመለከተ፤ ምንም አልሆነም…. ቀለሟን ያለ ልምዱ በቁጣ ጠርቶ “ልጅሽ የሰራውን ታያለሽ…” የአዳሯን ጣዕም ማበላሸት ስላልፈለገች ተረጋግታ “ወትሮ ከሚያደርገው ምን አጠፋ?”
“ገና ያላረምኳቸውን ቀዳዷቸዋል!” ግራ የገባው ስሜት ይታይበታል፡፡
“እና ምን ችግር አለው…?” አለችው፤ የከፋ ችግር እንዳለው እየተረዳች…
“እንዴት ችግር የለውም?!”
“የተቀረውን ፈልገን እንሰጥሃለን!”
“ምኑን ከምን አድርጌ ላርም… ጨርቅ አይደል አይሰፋ…”
“ኧረ ዘርሽ ይሄን ያህል አታካብድ!”
“ተይ ቀሌ፤ ይሄን ቃል እንኳ በዚህ ሰዓት በሌላውም ቀን አልወደውም…”
“እውነቴን ነው ሳታርም የቀረሃቸውን ልጆች የክፍል አክቲቪቲያቸውን ታውቃለህ --- ከዛ ተነስተህ ትሞላላቸዋለህ በቃ!” ውጤት የሰጠበትን ወረቀት አንስቶ በጥሞና ከላይ እስከ ታች ቃኘ…
“ይኸው የደሳለኝ አልታረመም…”
“እና?”
“እና ትይኛለሽ እንዴ!... ፈተናውን ከየት አምጥቼ ላርም!...” አሁን የምሩን ቁጣ እንደሆነ የግምባሩ ደም ስሮች መገታተራቸው አሳበቁ… ቀለሟ ተለሳልሳ ልታበርደው ወሰነች (እዚህ ቤት እሷ አትጋል እንጂ ሌላው እዳው ገብስ ነው)
“ቆይ ማሬ ምን ችግር አለው--- ወይ “ሲ” ወይ “ቢ” ስጠው”
“በጣም ጎበዝ ተማሪ’ኮ ነው… በዛ ላይ የተግባሩ ፈተና ውጤቱን አሳድሼባቸዋለሁ”
“እና ምን ታደርጋለህ?” መላ አምጣ አይነት እጇን አወራጨች…
“የሆነ ነገርማ መፈጠር አለበት…?!” የምርም ግራ ገብቶታል…
“ምን ይፈጠር…?” መልሳ ጠየቀችው
“እኔንጃ…” ተንቆራጠጠ… ጠባቧን ቤት እልህ ባጠቃው ትንፋሹ ፈጃት… ሳሎን ሄደ፣ የልጁን ፊት ማየት አቃተው፤ አንገቱን ደፍቶ ሲመለከት ብርክ ያዘው…
“ኧረ በማርያም ዘርሽ ደግሞ ለቲአትር ተማሪ! የኔ ፍቅር ኧረ አትጨነቅ!”
በንግግሯ ራሱን ሲያዞረው እንዳይወድቅ ፈራ…
“ግዴለህም በጣም የምትጠብቀውና ፈተናውን ይሰራዋል ብለህ የምትተማመንበት ከሆነ “ኤ” ስጠው…”
“እንዴት አይነቱ ሸጋ ተዋናይ መሰለሽ፤ በሱ በጣም ነው የምኮራው ግን ሌሎቹስ…?”
“እነሱንም እንደ ባህሪያቸው…”
የተበላሸበትን ከኮርኒሱ ሥር ያገኘው ይመስል አይኑን ሽቅብ ሰቀለ…
“ካልሽው ውጪ ምንም ምርጫ የለኝም…” ውጤት የሰጠበትን ወረቀት አነሳና ለደሳለኝ “ኤ ማይነስ ሰጠው… በድርጊቱ በጣም አዘነ…
(የሴት ብልሃት ሁለት ስልት ነው።)

እውነቱ…
ደሳለኝ ሲፈተን ረዥም ሰዓት ተቀምጧል… መልስ መስጫው ወረቀት ላይ ያሰፈረው ግን ይሄን ነበር…
“ይቅርታ… ይሻለኛል ብዬ ነበር የመጣሁት… ከቻልህ ሌላ ቀን ለብቻዬ ፈትነኝ… ካልሆነ አንተን ማሳዘን ስለማልፈልግ ኮርሱን እደግመዋለሁ… ዳረጎት እንደማያጠግበኝ ታውቃለህ…!
አክባሪህ…”።


Read 2222 times