Print this page
Saturday, 01 August 2020 13:17

"የእረኛው ሃኪም" ተርጓሚ - የሥነ ጽሁፍ ተሞክሮዋን ታወጋለች

Written by  ከአዲስ አድማስ አምደኛው ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 ሁለገቧ የሥነጽሁፍ ባለሙያ አዜብ ወርቁ ተዋናይ ናት፤ ደራሲ ናት፤ ተርጓሚም ናት፤ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅም ነበረች፡፡ አሁን ደግሞ አርትስ ቲቪን በዳይሬክተርነት እየመራች ትገኛለች፡፡ የጀመረችውን ከዳር ለማድረስ በትጋትና ታታሪነት ትሰራለች፡፡ "የምሰራው የተሻለና ከፍ የሚያደርገኝን ነው፤ ዝቅ ያለ ነገር አልወድድም" ትላለች፡፡ ከሳምንት በፊት ከአዲስ አድማስ አምደኛው ደረጀ በላይነህ ጋር ያደረገችው ማራኪ ቃለ ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል ለአንባቢያን ደርሶ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ቀጣዩን ክፍል እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ የመጀመሪያውን ክፍል ያላነበባችሁ ከዚህኛው ብትጀምሩም ችግር የለውም፤ ሁለቱም በየራሳቸው ሙሉ ናቸው፡፡ ለየብቻ ሊነበቡ ይችላሉ፡፡  ቃለ ምልልሱን እነሆ፡-    
                  እስቲ ስለተረጎምሻቸው ቴአትሮች አጫውቺን? ቴአትር የመተርጎም ሥራ ምን ይመስላል?
“ስምንቱ ሴቶች”ን ስፅፍ፣ ስተረጉም፣ ብዙ ነገሮችን ወደዚህ ሀገር፣ ወደዚህ ዘመን፣ ወደዚህ ባህል ማምጣት ነበረብኝና ያንን በመሥራት ውስጥ እጄን አፍታትቻለሁ፣ ልምድ አዳብሬያለሁ፡፡ በዚህ ቴአትር አዘጋጅ፣ ፕሮዲዩሰር፣ ተርጓሚ/ፀሐፊ የሚለውን ሙያዊ ማዕረግ እንዲሰጡኝ አስገድጃለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን የማፈርና የመሸማቀቅ ነገር ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎችም “እርሷ ደግሞ ከመቼ ጀምሮ ነው ተርጓሚ የሆነችው” ብለው ነበር፡፡ እኔ የተረጐምኩት የማይመስላቸው፤ ባለቤቴ እንደተረጐመልኝ የሚያስቡ እስከ ቅርብ ጊዜ ነበሩ፡፡ ባሌ’ኮ አማርኛ አይጽፍም፡፡ ያው “ሴቶች አይችሉም፤ ወንዶች ናቸው” ከሚል እሳቤም የሚመጣ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ፤ “ስምንቱ ሴቶች”ን ራሴን “ፀሐፊ ነኝ” ብዬ ለመውጣት አቅም አድርጌዋለሁ:: በዚያ ውስጥ በድፍረት አልፌያለሁ፡፡ ተቀባይነትን ወደ ማግኘት አምርቻለሁ፡፡ በዚያው አዘጋጅም ሆንኩ፡፡ ቀጥዬ “የሚስት ያለህ” የተሰኘውን ቴአትር አዘጋጃለሁ ብዬ ተዋንያንን ስጠራ፣ “አዜብ ከመቼ ጀምሮ ነው አዘጋጅ የሆነችው?” አላሉኝም፤ ምክንያቱም በቀደመው ሥራዬ አስመስክሬያለሁ፡፡ መጀመሪያ በራስ ማመን ይቀድማል፡፡ ሰዎች ባንተ ሲያምኑ፣ አንተም ከዚያ ደረጃ ላለመውረድ ትበረታለህ፡፡ ሰዎች ተቀብለውኛል፤ አምነውኛል፤ ከዚህ የወረደ ነገር ብሠራ በኔ ያላቸው እምነት ይሸረሸራል - ብለህ ስለምትፈራ፣ አንተም ከፍ ከፍ እያልክ መሄድን ትለምዳለህ፡፡ ገደቡንም ትሠብራለህ፡፡
በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ ላይም በጸሃፊነት ተሳትፈሻል?
የ“ገመና” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ - አንድን የጀመረው አዱኒስ ነበር፡፡ ቁጥር ሁለት ላይ አራት ወይም አምስት ደራሲዎች ነበሩ፡፡ እነ ተስፋዬ ገብረማርያም፣ ፍቅሩ ካሣና ሌሎችም የነበሩ መሠለኝ፡፡ በቡድን ነበር የሚጽፉት፡፡ እኔ ወደ “ገመና” ስመጣ ጥላሁን ታፈረ የድራማው አዘጋጅ ነበር:: ብዙ ጊዜ ስክሪፕት እንደሚዘገይበት ይነግረኝ ነበር፡፡ በጥድፍያ ነበር የሚሰራው:: ከስር ከስር መጻፍ ከባድ ነው፡፡ ይህንን ሲነግረኝ “እኔ ልጻፍ?” ብዬ ጠየቅሁት:: ጥላሁን ታፈረን በዚህ በጣም ነው የማመሰግነው፡፡ በሰዎች ላይ እምነት አለው፤የሚመዝንህ በሥራህ ነው፡፡ ስለዚህ ወዲያው “ጻፊ” አለኝ፡፡ ድራማው ክፍል 44 ደርሶ ነበረ፡፡ እሺ አልኩና ከዩቲዩብ አውርጄ ሙሉውን አየሁት:: ከዚያም ስፔክ ስክሪፕት የሚባል አይነት ጻፍኩ፡፡ ሙከራ አይነት ነገር ነው፡፡ መቼቱን እንደያዘ - ገፀባህርያቱን መሠረት እንዳደረገ… ሁለት ክፍል ጻፍኩኝ፡፡ ክፍል 45 እና 46 ይመስለኛል፡፡ ያንን ለጥላሁን አሳየሁትና ወደደው፡፡ ከዚያ እርሱ ለእቁባይ “አዜብ እየጻፈች ነው” ብሎ ነገረው፡፡ ዕቁባይም፤ “አዜብ መተርጐም እንጂ ከመቼ ወዲህ ነው መጻፍ የጀመረችው?” ማለቱን ሰማሁ:: አልፈረድኩበትም፡፡ እኔም ብሆን የምለው ይህንኑ ነው፡፡ ጥላሁን “አይ እጽፋለሁ” ብላ ጽፋለች፤ የጻፈችውን ታሳይሃለች አለው:: እኔና እቁባይ አልተገናኘንም፡፡ ጥላሁን  ስክሪፕቱን ሰጠውና ወደደው፡፡ “ይኸው ራሱ ይቀረጽና፣ ይቀጥል!” ተባለ፡፡ በዚህ ዓይነት አጋጣሚ ወደ ገመና ተከታታይ የቲቪ ድራማ ገባሁ፡፡ ይሁን እንጂ የዚያን ጊዜ “የሚስት ያለህ” ቴአትርን እየሠራን፣ ክልል ላይ ደግሞ በየዩኒቨርስቲዎች እናሳይ ስለነበር ጊዜ ያጥረኛል ብዬ ሰጋሁ፡፡ ሐሙስ ሐሙስ ብሔራዊ ቴአትር እናሳይና ዐርብ እንወጣለን፤ ተመልሰን እሮብ እንመጣለን፡፡
“ገመና ሁለት”ን ወደ ሃያ ክፍል የጻፍኩት መንገድ ላይ ነው፤ አንዳንዴ ሆቴል ውስጥ፣ ሌላ ጊዜም ከመድረክ ጀርባ እጽፍ ነበር፡፡ መዝናናት የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ በዚያ ላይ ሰውየውን አጉል አደርገዋለሁ የሚል ስጋት ነበረብኝ፡፡ በእውነቱ ለኔ በጣም ከባድ ጊዜ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያ በከባድ ጊዜ ውስጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ መጻፍን ተማርኩኝ፡፡ በዚያውም እንዴት ነው የሚጻፈው እያልኩ፤ እያነበብኩ፣ እየሠራሁ፣ ዕውቀት ቀሰምኩ፡፡ ብዙ ጊዜ፤ “እቁባይ ከፍሎ አስተማረኝ” እላለሁ፡፡ በየኢፒሶዱ ይከፈለኛል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ለመሥራት ስል ተገድጄ እያነበብኩ ተምሬያለሁ፡፡ ሁልጊዜ የምሠራው ነገር የተሻለና ከፍ የሚያደርገኝን ነው፤ ዝቅ ያለ ነገር አልወድድም፡፡ እኔን ብቻ ሳልሆን ሌሎች ሴቶችንም አስባለሁ:: ሴት ስትሆን ሰብሮ ለመውጣት ብዙ ይጠበቅብሃል፡፡ በጥርጣሬ ትታያለህ፡፡ ድሮስ የሴት ነገር! ይባላል - እናም በመከራ ያገኘሁት ዕድል ስለሆነ፣ ከሠራሁኝ አይቀር በ-ጣ-ም መስራት አለብኝ ብዬ አምናለሁ:: እኔ በመሥራቴ ምክንያት ተመልካቹ የሚያገኘው ነገር መጉደል የለበትም፡፡ ወይ እተወዋለሁ እንጂ! እርግጥ አልተወውም፤ እሞታታለሁ እንጂ! (ሣቅ)
 “እረኛው ሃኪም” በሚል ወደተረጐመሽው የፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው ግለ-ታሪክ መጽሐፍ እንምጣ፡፡ የታሪኩ ፍሰት ጥሩ ነው:: በቋንቋ አጠቃቀምም ቢሆን ግሩም ነው:: በተለይ መልክአ ምድራዊ ገለጻውን ሳነብ “አዜብ ናት ወይስ ደራሲው?” ብያለሁ:: ለመሆኑ መጽሐፉን ለመተርጐም ያነሳሳሽ ምንድነው?
ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸውን በወዳጅነት በፊትም አውቃቸው ነበር፡፡ ሞሮኳዊት ባለቤታቸው ሊሴ ገብረማርያም የSpeech therapy መምህርት ነበረች፡፡ እርሷ በመጣችበት ጊዜ እርሳቸውም መጥተው ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ ሊሴ ገብረማርያም ትወና አስተምር ነበርና እዚያ ተዋወቅን:: ከእርሳቸው ጋር በተደጋጋሚ የመገናኘት ዕድሉ ነበረኝ፡፡ በዚያ አጋጣሚ ሰውየው ጨጓራ ላይ የሚታሠረውን ቀለበት የፈለሰፉት ናቸው ሲባል በጣም ያስገርመኝ ነበር፡፡ እና አልፎ አልፎ አወራቸዋለሁ:: አንድ ጊዜ አልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ “የሃሳብ ምሽት” የሚል ፕሮግራም ጀምሮ ነበር፡፡ ውይይቱ በሃሳብ ላይ የሚደረግ ነበር፡፡ እዚያ ላይ ተጋባዥ ሆነው፤ የሕይወት ታሪኬን ፅፌአለሁ ብለው ስለ መጽሐፉ አወሩ፡፡  ሃሳብ ራሱ መከበር አለበት በሚለው ውይይት፤ሃሳቸውን ያቀረቡበት መንገድ ሳበኝ፡፡ ያኔ “የደራው ጨዋታ” የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ እሠራ ስለነበር እዚያ ያየሁትንና የሰማሁትን ሬዲዮ ላይ አቀረብኩት፡፡ እሳቸው የዚያን ዕለት ለኔና ለባለቤቴ መጽሐፍ ፈርመው ሰጥተውን ነበር፡፡ መጽሐፉን አነበብኩትና በጣም ወደድኩት፡፡ እሳቸውንም የበለጠ አወቅኋቸው፡፡ ከዚያም አስተማሪ ይሆናል ብዬ “የደራው ጨዋታ” ላይ ቃለ መጠይቅ እንዲደረግላቸው ፈለግሁና ደረጀ ኃይሌን፤“ደሬ ሰውየው በጣም ግሩም ናቸው፤ ቃለ ምልልስ ብታደርጋቸው” ስለው፣ “መጽሐፉን ያነበብሺው አንቺ ነሽ፤ እኔ ፈረንሳይኛ አላነብብም፤ አላነበብኩትም፤ አንቺ ራስሽ ጠይቂያቸው” አለኝ፡፡ በጣም ፈራሁ፡፡ ከደረጀ ኃይሌ ጋር እየሠራህ “ቃለ መጠይቅ አድርጌ መጣሁ” ማለት ትንሽ ይከብዳል፡፡ የሆነ ጊዜ ካልሰበርከው ነገሮች Intimidate ያደርጉሃል፤ ያስፈራሩሃል:: እስከ ዛሬም እየፈራሁ፣ እየሰበርኩ ነው የወጣሁት ስለው፣ ደሬ አበረታታኝ፡፡ “አንቺ ካልጠየቅሻቸው ማን ይጠይቃቸዋል፤ ካልሆነ እኔ ኤዲት አደርገዋለሁ” አለኝ፡፡ “እሺ” ብዬ ቃለ መጠይቅ አደረኩላቸው:: ያ ቃለ መጠይቅ #የደራው ጨዋታ; ላይ ተላለፈ፡፡ አድማጮች በጣም ወደዱት:: ብዙ አስተያየቶች መጡ፡፡ ብዙዎቹ “አዜብ እባክሽ ቃለ መጠይቃቸውን ስንሰማ በጣም ወደድነው፤ ይህ መጽሐፍ በአማርኛ ቢተረጐም ለኢትዮጵያውያን በተለይ ለወጣቶች ብዙ ነገር ያስተምራል፡፡ እባክሽ ተርጉሚው!” አሉኝ፡፡ ፕሮፌሰሩም ይህ መጽሐፍ ቢተረጐም ጥሩ ነው አሉኝ፡፡ ከዚያም “አዜብ ብትተረጉመው” የሚል ነገር መጣ፡፡ አንብቤ  የተረዳሁበትን መንገድ ስለወደዱት ፕሮፌሰሩ፤ “ደስ ይለኛል ተርጉሚው” አሉኝና ሥራው ተጀመረ፡፡ መጽሐፉን ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ መለስኩት፡፡ ከዚያ ታተመ፤ ይኸው እናንተ እጅ ገባ፡፡ ሂደቱ ይሄው ነው፡፡
በትርጉም ሂደቱ --ፈረንሳይኛውና አማርኛው፣ የሚከረከም፣ የሚዛመድ፣ የሚወሰድ፣ የሚጣል - ይኖረዋል፡፡ ሥራውን እንዴት አገኘሽው?
በጣም ብዙ ነገር አለው፡፡ ምክንያቱም ፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው የስነ ጽሑፍ ሰው አይደሉም፤ ሐኪም ናቸው፡፡ ጽፈውም አያውቁም፡፡ እና እርሳቸው የተነሱት ግለ-ታሪካቸውን ለመጻፍ ነው፡፡ ለመጻፍ የተነሱበትም ምክንያት፣ የእርሳቸውን “ከየት ነው የመጡት?” የሚለውን ጥያቄ መመለስን ግብ አድርገው ነው፡፡ የውጭው አንባቢ፣ ስለ ኢትዮጵያ ምንም አያውቅም:: ዓላማቸው ኢትዮጵያ የት እንደምትገኝ፣ ምን ምን እንዳላት፤ ስለ ተፈጥሮ ሀብቷ፣ ባህልና ታሪኳ መረጃ ለሌለው ሕዝብ ለመንገር ለማስተዋወቅ ነው፡፡ በመጽሐፉ እንደገለፁት፤ ዋና መነሻቸው የልጅ ልጃቸው ጥያቄ ነው፡፡ የልጅ ልጃቸው ቤልጂየማዊ ነው፡፡ ስለ እርሳቸውና ስለ መጡበት ወገንና ሀገር ምንም አያውቅም::  “ይሄ ልጅ እኔ ባልፍ ከመጣሁበት ታሪክ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖረውም:: እርሱ የመጣበትን የዘር ግንድም ማወቅ አለበት:: ስለዚህ መዳፍ አለብኝ” ብለው ተነሱ፡፡ በተጨማሪም ሙያቸውን ለሕክምና ባለሞያዎች ለማካፈልና ዕውቀት ለማውረስ ከመሻትም ነው መጽሐፉን ያዘጋጁት፡፡   
ከስነጽሑፍ አንጻር ሲታይ፣ በፈረንሳይኛ የተጻፈው ከአማርኛው ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ የእርሳቸው ዓላማ እንደነገርኩህ፤ የሞያ ልምድን ማካፈል ስለነበር ስነጽሑፋዊ ቅርፁን ትኩረት የሰጡት አይመስለኝም:: በፈረንሳይኛ የመጽሐፉን የአርትኦት ስራ የሠራው ሰው ስለ ኢትዮጵያ ዕውቀት ያለው አይደለም::  ሆኖም በዚያ ዐውድ ቆንጆ ተደርጐ ተሠርቷል፡፡ ወደ አማርኛ ስንመልሰው ግን ለኢትዮጵያውያን አንባቢዎች አላስፈላጊ የሆኑ ወይም ለኢትዮጵያውያን መንገር ለቀባሪ ማርዳት ያህል የሆኑ ነገሮች አሉት:: ለምሳሌ ኢትዮጵያ በዓመት አስራ ሦስት ወራት አላት፣ ብለህ ለእኛ ሀገር አንባቢ መጻፍ ማሠልቸት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ፊደል እንዳላት መግለጽም ለዚያ ሀገር እንጂ ለዚህ ሀገር ብዙም አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፡፡  እዚያ ላለው አንባቢና ለልጅ ልጃቸው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡
በተረፈ ደግሞ እሳቸው ሊገልፁበት የፈለጉበትን መንገድ መረዳትና ቃል በቃል ከማስቀመጥ ይልቅ በጥሩ ስነጽሑፋዊ ውበት ማቅረብ፣ የራሱንም የተርጓሚውን ቸርነትና ለዛ ማግኘት ያስፈልገዋል፡፡ እኔም እንደዚያ አድርጌያለሁ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ በኢትዮጵያ ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ሁነቶች አሉ፡፡ ለምሣሌ የ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወይም አንዳንዶች “የታህሳስ ግርግር የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እሳቸው ከሀገር ርቀው ስለኖሩ፣ በቅርበትና በጥልቀት ላያውቁ ይችላሉ፡፡ የጻፉትም የዚያን ጊዜ የሰሙትንና ያዩትን ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ነገሮች ይዛቡ ይሆናል፡፡ እኔ ደግሞ በደራው ጨዋታ ፕሮግራም ላይ ስንሰራ ታሪክ እንፈትሽና እንመረምር ስለነበር፣ ያለኝን እውቀት የመጽሐፉን ክፍሎች ቅርጽ ለማስያዝ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ያን በማድረጌ እሳቸውም ደስተኛ ናቸው፡፡ በተቻለ አቅም አንባቢው ሽርፍራፊ ታሪክና ሁነት እንዳይገጥመው፤ አንድም ነገር እንዳይጐድልበት ለማድረግ ጥሬአለሁ፡፡ ተፈጥሮን የሚገልፁበትን መንገድ፣ የባህላችንን መስመርና ሁኔታ ኢትዮጵያዊ በሆነ ለዛና ቃና እንዲያምርም፣ ሣይጋነንና የርሳቸውም ሳይጐድል፣ የራሴን አሻራ ለመጨመር በጥንቃቄ ሠርቻለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለአንባቢያን የወጣውም በዚያ ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ መጽሐፍ በፊት ቴአትር ተርጉሜ፣ በመጽሐፍ ወጥቶ ያውቃል፡፡ የሕፃናትም መጻሕፍት ጽፌያለሁ፣ ግን በመጽሐፍ ትርጉም ደረጃ “እረኛው ሐኪም” የተባለው የፕሮፌሰር ምትኩ በላቸው ግለ ታሪክ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ በአንባቢዎች ዘንድም ጥሩ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡
ወደ መጽሐፉ መጨረሻ ላይ ያሉት የሕክምና ሙያዊ ቃላት ከተተረጐሙ በኋላም እንኳ ጠጠር ያሉ ናቸው፡፡ እንደምን ተወጣሻቸው?  
አንድ ሰሞን እንደ ሀኪም ሊያደርገኝ ዳድቶኝ ነበር፡፡ የሕክምና ቃላትንና የሕክምና ሞያ ስልቶችን ለማጥናት ጊዜ ወስጄ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ግን በጣም ከባድ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ቃላት አይተረጐሙም፤ ስለዚህ በእንቅስቃሴና በድርጊት ውስጥ ባሉ ሂደቶች ነበር የምረዳቸው፡፡ ቋንቋው ፈረንሳይኛ ይሆንና ኢትዮጵያ ውስጥም ያው ቃል በእንግሊዝኛ ተወስዶ ይጠቀሙበታል፡፡ ስለዚህ እንግሊዝኛውን ደግሞ ምን እንደሆነ በሂደት (Process) መግለጽ ይገባኝ ነበር፤ በጨጓራ ውስጥ እንዲህ አድርጐ፣ በዚህ አልፎ እንዲህ አሥሮ ምናምን እያልኩ:: ለምሳሌ በውጭ ሀገር የሕክምና ቃላትን (Terms) ብዙ ሰው ሊያውቃቸው ይችላል፡፡ ያንን ልታስረዳ አይገባህም፡፡ ወደ እዚህ ግን ስትመጣ፣ በአማርኛ ማስረዳት አለብህ፤ ያ ማስረዳት ደግሞ አሠልቺ መሆን የለበትም:: እነዚያን ለማስረዳት የምትጠቀምበት መተንተኛ መጽሐፍ ውስጥ የምታገኘው አይደለም፡፡ እኔ ከፕሮፌሰሩና ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሐኪሞች ጋር በመነጋገርና በማውራት ነው ለማስረዳት የሞከርኩት፡፡ እንዳይሰለች ማድረግ ደግሞ ፈታኝ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር ስለ ሕክምና - ስለ የውስጥ አካላችን በ-ጣ-ም የተማርኩበት ስራ ነው፡፡ እኔ እንግዲህ የሕክምና ሞያ በዘሬም የለምና እንደ አዲስ ተማሪ ብዙ ተምሬበታለሁ:: በምችለው ልክ አንባቢያን መረጃው ሳይጐድልባቸው ማወቅ የሚገባቸውን እንዲያውቁ ጥሬያለሁ፡፡ በተለይ የሕክምና ተማሪዎች እንዲያውቁት፣ በርካታ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስቶችን አናግር ነበር፡፡ በመጨረሻም ለአንድ ሃኪም ገምግመው ብዬ ረቂቁን ሰጥቼው ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ምትኩም ጋ በጣም እደውል ነበር፤ የኢትዮጵያ ሀኪም ደግሞ እንዴት ያየዋል በሚል እጠያይቃለሁ:: ትልቅ የሕክምና መዝገበ ቃላትም ገዝቼ አስመጥቼ ከፈረንሳይኛ እንግሊዝኛ እጠቀም ነበር፡፡ ከእንግሊዝኛው አነብብና ደግሞ ከሀኪሞች ጋር እያወራሁ ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡ ይሄ ክፍል እጅግ አድካሚ ስለነበር፤ ዘልዬው ከሔድኩ በኋላ መጨረሻ ላይ በጥንቃቄ የሠራሁት ምዕራፍ ነው፡፡ ይሁንና ጐደሎ እንዳይሆን የሚቻለኝን ሁሉ አድርጌ የተሻለ ነገር ያቀረብኩ ይመስለኛል:: ሰዎችም የተሻለ ነገር ያገኙበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምናልባት ጥቃቅን ጉድለቶች ቢኖሩ፣ ቀጣይ እትሞች ላይ እያረምን መሄድ እንዳለብን አምናለሁ፡፡ ስነጽሑፍን አንተም ታውቀዋለህ፤ ፈትሞ አያልቅም፤ ሁሌም የሚጠራ፤ የሚታረምና እየተዋበ የሚሄድ ነው፡፡ አሁንም ሳነብበው “ይቺ ነገር” እያልኩ ቅር የሚለኝ ነገር አላጣም፡፡ መጽሐፍም እንደ ቴአትር የማሻሻል፣ ይበልጥ የማስዋብ ዕድሎች አሉት፡፡ ሙከራዬ ይቀጥላል፡፡    Read 2183 times