Print this page
Tuesday, 04 August 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ያ ትውልድና እነዚያ አበው
የ20ኛውን ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ዘመናዊ የምሁር መደብ የሚተነትኑ መርማሪዎች በሦስት ይከፍሉታል፡፡
(1) ቅድመ ጣሊያን የነበረው የእነ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት፣ የእነ ሐኪም ወርቅነህ፣ የእነ ፕ/ር አማኑኤል፣ የእነ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም፣ የእነ ብላታ ደሬሳ አመንቴ… ትውልድ ነው:: ይህ ትውልድ የሀገሩ ወደ ኋላ መቅረት አስጸጽቶት አንድ ጊዜ ወደ ምዕራብ አውሮፓ፣ ሌላ ጊዜ ወደ መስኮብ፣ እንደገና ወደ ሩቅ ምሥራቅ እያማተረ ሳለ ጉዞው በጣሊያን ወረራ ተቀጨ፡፡
(2) ከጣሊያን ወረራ በኋላ የመጣው ትውልድ በተቋማት ግንባታና በጣሊያን ጦርነት የወደቀችውን ሀገርና ብሔራዊ ስሜትን ማነፅ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በከፊል ተሳክቶለት አለፈ፡፡ ‹‹ከፊሉ›› ግን ቀላል ከፊል አልነበረም፡፡ የተከለው ዘመናዊነት ትውፊትን ቸል ያለ ምናልባትም የተጸየፈ ነበረ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እንደ መሣሪያና የቀደመው አሮጌ ዘመን አጋፋሪ የመመልከት አዝማሚያ ነበረው፡፡
(3) ያ ትውልድ ከዚህ አዝማሚያ ተወለደ:: ከማንነቱ የተነቀለ (በዶ/ር ዮናስ አድማሱ አነጋገር nihilist) ትውልድ ተፈጠረ፡፡
በቤተ ክህነቱ በኩል ስንሄድም ብዙም ያልራቀ ተጋድሎ እናያለን፡፡
(1) ቅድመ ጣሊያን የነበሩ ሊቃውንት በቅዱሳት መጻሕፍት ኅትመትና ከብሔራውያን ሊቃውንት ጳጳሳትን ለማስሾም አስደናቂ ተጋድሎ ያደርጋሉ፡፡
ተሳክቶላቸውም ሰማዕቱን አቡነ ጴጥሮስን ጨምሮ ጥቂት ጳጳሳትን ያስሾማሉ፡፡ ሆኖም ሂደቱ ቀጥሎ ወደ መንበረ ፕትርክና ከማደጉ በፊት የጣሊያን ወረራ መጣና ለጊዜው ታጎለ፡፡ ሊቃውንቱ ከዐርበኞች ተቀላቅለው ተሠዉ፣ አጽናኑ፣ ጸለዩ፣…፡፡ ግብጻዊው አቡነ ቄርሎስ ግን ‹‹ለማን ሀገር ማን ሊሠዋ!›› በሚመስል መልኩ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡
(2) ድኅረ ጣሊያን የነበሩ ሊቃውንት የግብጻዊው አቡን ሽሽት፣ የዴር ሡልጣን ተገፍዖ፣ የስብከተ ወንጌል ጥማት፣ ቁጭት፣ የሥርዋጽ ሤራ፣… ገፋፋቸውና መንበሩን ከሊቀ ጵጵስና ወደ ፕትርክና አሳድገው፣ በራሷ ተወላጅ ፓትርያርክ የምትመራ ቤ/ክ ቀኖናንና ሐዋርያዊ መተካካትን ባከበረ መልኩ ለማቋቋም በብርቱ ታገሉ፡፡ ተሳካላቸው!
(3)ሦስተኛው የቤተ ክህነት ትውልድ ዐላማ ትውልዱን መድረስ፣ ተቋሙን ማጠንከር ነበር፡፡ ያሳዝናል! ከማንነቱ ከተነቀለው ትውልድ ጋር የሚገጥመው ይህ የቤተ ክህነት ቢሮክራሲ ነበር፡፡ ተበላ! የሆነውን ሁሉ ለማዘከር በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የደረሰውን ማሰብ ይበቃል፡፡
በእነዚህ የቤ/ክ ውጣ ውረዶች ሰው ብንፈልግ ብንዘክር፣ የእነ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን፣ የእነ መልአከ ብርሃን አድማሱን፣ የእነ አቡነ ዮሐንስ (ዘትግራይ)፣ … ስም እንጠራለን፡፡ ሦስቱንም ትውልድ ያዩና የታዘቡ ናቸውና፡፡ መልአከ ብርሃንን ስንዘክር መንበር ለማቆም በ1918 ዓ.ም. በመንፈሰ ጉባኤ የተደረገውን ትግል፣ በጣሊያን ወረራ ጊዜ የነበረውን የሊቃውንት ኀዘን፣ ቅድመ ጣሊያን መንበር በማቆምና ከቆመም በኋላ የሊቃውንት ጉባኤ መቋቋሙን፣ የ1948ቱን ክልስ ሕገ መንግሥት፣ የሃይማኖት ነጻነት እውቅና ተከትሎ፣ ቤተ ክርስቲያን የሠራችውን የዕቅበተ እምነት ተግባር በእርሳቸው እናያለን፡፡ መልአከ ብርሃንን ጨምሮ የወቅቱ ሊቃውንትና የቤተ ክህነቱ ትኩረት ወጣቱ ነበር፡፡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መከፈት፣ እንደታሰበው ባይዘልቅም የሃይማኖተው አበው ማኅበር መመሥረት፣ የቤተ ክርስቲያን ልሳን የሆኑ ጋዜጦችና መጽሔቶች መጠናከር፣ የእነ ተምሮ ማስተማር ጅምር፣ በታዋቂው የመጫ ቱለማ መሥራች ጄ/ል ታደሰ ብሩ ይደገፍ የነበረው የስብከተ ወንጌል ተልእኮ፣ ሀገርና ሃይማኖትን ሳያጣርሱ መሥዋዕትነት የከፈሉትን አቡነ ጴጥሮስን መዘከሩ፣… ሁሉም ወጣቱን ለመያዝ የተደረጉ ነበሩ:: እነዚያ አባቶች፣ ያ ትውልድ ከመሥመር እየወጣ መሆኑ ገብቷቸው በመዋቅር ሊያቅፉት፣ በመጽሐፍ ሊነግሩት፣ በስብከት ሊስቡት፣ … ደከሙ፣ ተራወጡ፣ ኳተኑ:: አልሆነም፡፡ ተላለፉ፡፡ የኔ ትውልድ ዛሬ እነዚያን አበው፤ በመልአከ ብርሃን አድማሱ ርእስነት ሲዘክር ደስ ይለኛል፡፡ ሀገራዊ መርገምን ከማብረድ፣ ከትውፊት ያልተፋታ ዘመናዊ ሕይወትን ከመዋጀት እቆጥረዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን!
(ከአማን ነጸረ. ፌስቡክ)

ትሁቱን ደራሲ ለመዘከር
“ሕያው ፍቅር “የተሠኘውን ረዥም ልቦለድ መጽሐፍ የጻፈውና በቅርቡ “ታንጀሪና ሆቴልና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” በሚል ርዕስ አዲስ መጽሐፍ ያሳተመው ደራሲ ደረጀ በቀለ፤ ሠሞኑን ከዚህ ዐለም በሞት ተለይቷል። የበኩር ሥራው “ሕያው ፍቅር” በተለይ በገጸባሕርያት አሣሣሉ፣ በመቸት ገለጻው አይረሳም።ታሪኩ ብሔራዊ ቴአትር ጀምሮ፣ ብዙ ጊዜ ቴአትር አካባቢ ቢቆይም፣ የተለያዩ የሕይወት ደጆችን ይረግጣል።
ዋና ገፀባሕርይው ቻርሊም ከሃያ ዐመታት በላይ እንደ ጧፍ የነደደበት መድረክ፤ እንጀራ ሣያጠግበው ቀርቶ፣ ሚስቱን ነጥቆት ስለነበር በመሀላ ያበቃል፤ በምሬት ይደመድማል። ወንጀሎች፣ የአብዮቱ ሠልፎች፣ የፍቅር ቋያዎችን የያዘው ሕያው ፍቅር፤ በእውነታዊነት የሚመደብ፣ ዘመናዊ የምንላቸው ድርሰቶች አካል ነው። ቻርሊ፣ ናፖሊዮን፣ ሣራ ጋዴም፣ ዕብድዋ የንጋት ንግሥት፣ እህል አስፈጪው፣ ውሻ ጎታቹ፣ ባለሱቁ ወዘተ የማይረሱ ናቸው።
ደረጀ ወደ ሃያ የሚጠጉ መጻሕፍት የተረጎመ ሲሆን ሃያ መጻሕፍትን በአርታኢነት አቃንቷል።
ደራሲ ደረጀ በቀለ፤ በግል ባሕርይው ከሚገመተው በላይ ትሁት፣ የበደሉትን ሰዎች ክፋት እንኳ ቆፍረውት የማያወጣ፣ የኢዮብን ትዕግስት የሰጠው ነው። ሰው ሕይወቱ ሲያልፍ የሌለውን ፀባይ፣ችሎታና ማዕረግ መደርደር የተለመደ ቢሆንም እኔ በበኩሌ እቸገርበታለሁ። አልስማማም። አሁን ስለ ደረጀም ስናገር፤ ከዚህ ውጭ ሆኜ ነው። “ታንጀሪና ሆቴልና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች”በሚል ርዕስ የታተመውን አዲሱን መጽሐፉን አንብቡና፣ ያንን በፊደላት ኅብር የሚፈስስ ሙዚቃ፣ያንን በቃላትና ሀረጋት የሚተምም የፊልም ሕይወት እዩት።ለኔ ድንቅ ነበር።
(ከደረጀ በላይነህ ፌስቡክ)

የሰለሞን ደሬሳ ፍልስፍና
“ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ እኔ የትግራይ ሰው ነኝ፣ እኔ አማራ ነኝ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገሩ አለማወቅ ይመስለኛል። በሴት አያቶቻችን በራፍ ላይ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችን ነው የምናውቀው? የኔን ጥሩ ኦሮሞነት እግዚሃብሔርና የሴት አያቶቼ ብቻ ናቸው የሚያውቁት። የሁሉንም እንዲሁ። ሰው ጦር ባለፈ ቁጥር በመዋለድ፣ በንግድ በመገናኘት፣ ተቸግሮ ከአገር ወጥቶ ሌላ ቦታ በመኖር ይቀላቀላል።
ሰለሞን ደሬሳ 1992 ከሪፓርተር ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ
(ከሱራፌል አየለ ፌስቡክ )

“እኛ እና ሚዲያዎቻችን”
በዚህ ዘመን WiFi መጠቀም የሃብት መገለጫ ሆኖ መታየቱ እንዳለ ይቆየንና የመረጃ አቀባበላችንን በተመለከተ አንዳንድ ነገር እንወያይ .... ምክንያቱም ዳታም ይጠቀም WiFi ...ያው ተመሳሳይ ጠረጴዛ ላይ ነው የተቀመጥነው፡፡
ትላንት ስለ ሚዲያዎቻችን በእንግሊዝኛ የተወሰነ ነገር ፅፌ ነበር፣ ነገር ግን በሰዓቱ ትንሽ ስሜታዊ ነበርኩ፣ የሰጠሁት ድምዳሜዎችም ወደ ጭፍንነት ያደሉ ናቸው...! የመረጃ አሰጣጣችንና አቀባበላችንን መሰረት አድርገን ስንመዝነው፣ ማንኛውም ማህበራዊ ሚዲያ የራሱ የሆነ ጥቅምና ጉዳት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ። በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሂደት የምንጎዳውም ሆነ የምንጠቀመው ለምናገኘው መረጃ በምንሰጠው ሚዛንና ክብደት ልክ ነውና!!
ታድያ ይሄንን የሚያውቁ ጥቂት  ግለሰቦች፣ እንደ ማንኛውም የሥራ ዘርፍ መተዳደሪያና የገቢ ምንጭ አድርገው ተጠቅመውበታል፤ ጥቂቶች ደግሞ ያለ ምንም ክፍያ በራሳቸው ተነሳሽነትና በራሳቸው ወጪ አዝናንተውናል፣ አስተምረውናል፣ ከምንም በላይ ደግሞ የንባብ ልምዳችንን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፣ ባጠቃላይ መንግስትና ህብረተሰቡን ለማንቃት ብዙ ጥረዋል። ከዚህም በተጨማሪ... ሚዲያዎች፣ ብልሹ አሰራርንና ኢ-ዲሞክራሳዊ የሆነ አስተዳደርን ተቃውመውበታል፣ ጨቋኝና አምባገነን መንግስታትን ለመገርሰስ በሚደረገው ትግል የራሳቸውን ሚና አበርክተዋል!!
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ፣ በርካቶች ይሄንኑ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቅመው በርካቶች መርዛቸውን ረጭተውብናል፣ አባልተውናል፣ ጥላቻን ሰብከውበታል፣ ህዝብ ለህዝብ የጎሪጥ እንዲተያይ አድርገዋል።
እነኝህን አካላት በአንድ ጨርቅ ከመቋጠር ይልቅ በሦስት ምድብ ክፍሎ መመልከት ይሻላል ...
1. የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ብቻ ተጨባጭ ያልሆነ ሀሰተኛ መረጃ የሚሰራጩ አሉ፣
2. የህዝቡን ሠላምና መረጋጋትን ወደ ጎን በመተው፣ ከተመልካች የሚያገኙትን ገንዘብና ላይክ ብቻ በመመልከት ወይም የራሳቸውን ሆድ ብቻ በማድመጥ፣ ጥዋትና ማታ አወዛጋቢ የሆነ መረጃ የሚያቀብሉ አሉ፣
3. መሄጃ ስላጡ ብቻ ወይም ሌላ መደበሪያ ስለሌላቸው ብቻ እዚህ ተጎልተው የሚውሉ... ነገር ግን ከላይ 1ኛ እና 2ኛ ቁጥር ላይ ከጠቀስኳቸው አካላት የሚሰራጩ መረጃዎችን እንደ ጋማ ከብት ሳያመነዥጉ፣ ያለ አንዳች ማንገራገር እየተቀባበሉ የሚያስተጋቡ የገደል ማሚቱ ሆነው፣ የሚያገለግሉትን ደግሞ ቤቱ ይቁጠራቸው....!
ትልቁና ዋነኛው የችግሩ ምንጭ ሆነው የሚታዩትም እነኝሁ ናቸው፣ 3ኛው ላይ ያሉት ማለቴ ነው... የሚዲያ ሚዲያ (ግም ለግም...)፣ እናንተ ከፈለጋችሁ ነብስ ያላቸው ሚዲያ (Living speakers) በሏቸው።
ስለ አንድ መረጃ ተጨባጭነትና እውነተኝነት ሊያረጋግጥ የሚችል ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ሳይንሳዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ አየር ንብረታዊ፣ ሌላም ምክንያት መኖር አለመኖሩን ሳያጣሩ፣ በየቦታው ተዘዋውረው ሳያረጋግጡ፣ ... ከሁሉም በላይ ደግሞ በህሊናቸው መዝነው ከግምታቸው በላይ ሳያልፍ፣ እንዴት ክቡር በሆነው አእምሮአቸው ላይ ይለጥፋል? ይኼ ነው እንግዲ የጋማ ከብትነት...!
(ከሌንጮ በዳዳ ፌስቡክ)

Read 7840 times
Administrator

Latest from Administrator