Sunday, 02 August 2020 00:00

አረንጓዴ አሻራን ለልማትም ለዕውቀትም

Written by  ዓለሙ በቀለ
Rate this item
(0 votes)

   የተከላችሁት ችግኝ ምን ይባላል? ስሙን ታውቁታላችሁ?
                       
               የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት መከናወኑ በፈጠረው የደስታና የመነቃቃት ስሜት ታጅቦ፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በወኔ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የችግኝ ተከላው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ነው ያለው፡፡ የተፈጥሮን ሚዛን ለማስጠበቅና ለግብርና ልማት ያለው ፋይዳ የላቀ ነው፡፡ ለአባይ ወንዝ ብሎም ለህዳሴው ግድባችን ህልውና ወሳኝ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ዓምና 4 ሚሊዮን ችግኞችን በመላው አገሪቱ በመትከል ድንቅ ታሪክ ያስመዘገበው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፤ዘንድሮ ደግሞ ወደ 5 ቢሊዮን ችግኞች አድጓል፡፡ አስደማሚ ዕቅድ ነው፡፡ ዕፁብ ድንቅ አገራዊ  ፕሮጀክት! እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በዜጎች የሚከወን፡፡ ይሄም ታሪካዊ ያደርገዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ሃላፊነቱን በቅጡ ከተወጣ በኩራት የሚተርከውና  ለመጪው ትውልድ የሚያስተላልፈው ተፈጥሯአዊ ቅርስ ነው፡፡ የአረንጓዴ አሻራ!
 ግን ግን የምንተክላቸውን የዛፍ ችግኞች እናውቃቸው ይሆን? ምን እያልን ነው እየተከልናቸው ያለው? ሌላው ቢቀር እኮ ስማቸውን ልናውቅ ይገባል፡፡ እውነታው ግን እንዲያ አይመስልም፡፡
በአረንጓዴ አሻራ የምንተክላቸውን ብቻ ሳይሆን በግቢያችን ወይም በመዲናችን ከሚገኙ የዛፍ አይነቶች ውስጥ በስም የምናውቃቸውም እኮ ብዙ አይደሉም:: እርግጠኛ ነኝ በትክክል ስማቸውን የምናውቃቸው በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ዝግባ፣ ብሳና፣ ኮሶ፣ ክትክታ፣ ወይራ፣ ጥድ፣ ባህር ዛፍ …ከዚህ በላይ መዝለቅ አልቻልኩም፡፡ አንዳንዶች የስም ዝርዝር ስለጠቀሱ ብቻ ዛፎቹን ያውቋቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የኮሶ ዛፉን ክትክታ የምንል ሞልተናል፡፡ ግን ደግሞ አይፈረድብንም፤በት/ቤት ቆይታችን ያስተማረን  የለም፡፡
በተመሳሳይ፤በአገራችን ከሚገኙ በርካታ የአዕዋፍ ዝርያዎች ውስጥ አንዳቸውንም እንኳን በስም የምናውቃቸው አይመስለኝም:: ከመላው ዓለም ግን የአዕዋፍ አድናቂዎች ወደ አገራችን ይመጣሉ፤አዕዋፍን ለማድነቅም ለማጥናትም፡፡ እኛ ግን አዕዋፍን የማድነቅም የማወቅም ባህል ገና አላዳበርንም፡፡  
በዚህም የተነሳ ፊደል ለቆጠርነውም ላልቆጠርነውም “ዛፍ - ዛፍ ነው”፤ “ወፍም - ወፍ ነው” በጋራ ስማቸው ነው የምንጠራቸው፡፡ እያንዳንዱን ግለሰብ በራሱ ስም ሳይሆን #ሰው; ብሎ እንደ መጥራት ማለት ነው፡፡
እርግጥ ነው በሃገራችን የሚገኙትን በሺዎች የሚቆጠሩ እፅዋቶችና ከ850 በላይ የአእዋፍ ዝርያዎች ሁሉ በስም ማወቅ አይጠበቅብንም፡፡ እያንዳንዱን አብጠርጥሮ ማወቁን ለባለሙያዎቹ እንተውላቸው፡፡  ይሁንና ቢያንስ ቢያንስ ግን የምንተክላቸውን የዛፍ ወይም የዕፅዋት ዓይነቶች በስም ማወቅ ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ መልካም አጋጣሚን ተጠቅመንም፣ ከዛፎችና ዕፅዋቶች ጋር ያለንን ትውውቅ ማስፋት እንችላለን፡፡ ይህን የምናደርግ ከሆነ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” ማለት ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ልማትም ዕውቀትም፡፡
በነገራችን ላይ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የተከልነውን የዛፍ ችግኝ ዓይነት ስንጠየቅ፣ በጥቅሉ ዛፍ ከማለት ይልቅ ትክክለኛውን ስም መናገር ይገባናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከተቻለ ዝርዝር መረጃ መስጠት ብንችልም አይከፋም፡፡ ስለ ዛፉ ዓይነት፣ ተፈጥሮው፣ ዕድሜው፣ ስለ ልዩ ባህርይው አውቆ ማሳወቅ እሴት እንደ መጨመር ነው የሚቆጠረው፡፡   
መቼም በዚህ የሰለጠነ ዘመን "ዛፉ ሁሉ ዛፍ፣ ወፉ ሁሉ ወፍ፣ አበባው ሁሉ አበባ; … እያልን ሁሌ መቀጠል  አንችልም:: በጥናትና በጥረት ዕውቀታችን አዳብረን ሁሉንም በየስማቸው መጥራት መልመድ አለብን፡፡ በተለይ ስለምንተክላቸው ዛፎች መጠነኛ ዕውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ ተክለን የምናጸድቀውንና የምናሳድገውን ችግኝ፤ በቅርበት ስናውቀውና በስሙ ስንጠራው የተሻለ እንክብካቤ የምናደርግለት ሁሉ ይመስለኛል፡፡
ምዕራባውያን አዕዋፍ አድናቂዎች አገራችን መጥተው በኢትዮጵያ 856 አይነት የአእዋፋት ዝርያዎች እንዳሉ፤ ከእነዚያም ውስጥ ወደ ሰላሳ ያህሉ በእኛ ሃገር ብቻ እንደሚገኙ በመግለጽ “Abyssinian Roller, Abyssinian cat bird, Ethiopian boupu, Thick bill raven, Abyssinian sluty fly catcher, etc” እያሉ ስማቸውን ሲዘረዝሩልን -- እኛ ግን ባዳ መሆናችን ያስገርማል፡፡ የበለጠ የሚያስገርመው ደግሞ ባለማወቃችን አለመቆጨታችን ነው፡፡ በአእዋፋት ዙሪያ ከእፅዋት በተሻለ ሁኔታ የተሰሩ ጥናቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ በአንጻሩ ቢራቢሮዎችን በተመለከተ ግን ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የሚገርመው ታዲያ ሃገራችን (እንደ አእዋፍቱ ሁሉ) የቢራቢሮ አፍቃሪ ቱሪስቶችን ለመሳብ የሚያስችል ትልቅ የቢራቢሮ እምቅ ሃብት ያላት መሆኑ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ባለፈው ዓመት የተተከሉትን የዛፍ ችግኞች በተመለከተ በዝርዝር የሚታወቅ ነገር የለም፡፡  ቢያንስ በኛ ተራ ተርታ ዜጐች ዘንድ፡፡ ከ4 ሚሊዮን ችግኞች ውስጥ ምን ያህል ባህር ዛፍ፣ ጥድ፣ ፓፓያ ወይም ማንጎ እንደተተከለ መረጃ የለንም፡፡ ቢኖረን ጠቃሚ ነው፡፡ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ሊተከል ከታቀደው 5  ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ ምን ያህሎች የፍራፍሬ ተክሎች ይሆናሉ? ምን ያህሎቹስ ሌሎች የዛፍ ዓይነት ናቸው? በጅምላ የዛፍ ችግኞች ከሚል አጠራር ወጥተን በስም፣ ዝርያና ባህርይ ብንገልጻቸው የተሻለ ይሆናል - በባለሙያዎች እየታገዝን ማለት ነው፡፡
ሃሳቤን ሳጠቃልል፣ በትልቅ ራዕይ በተሰነቀው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ችግኝ ከመትከል ጐን ለጐን የዛፎቻችንንና ዕፅዋቶችን ስምና ተፈጥሮ የምናውቅበት ዕድልና ሁኔታ ቢመቻች ውጤቱ አመርቂ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በየመርሃ ግብሩ ማብቂያ ላይ የዛፍና ዕጽዋት ማብራሪያ የሚሰጡ ባለሙያዎች ቢኖሩም አይከፋም፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ጠንሳሾችና አስተባባሪዎች እስቲ ጉዳዩን አስቡበት፡፡ በነገራችን ላይ  የምንተክላቸውን የዛፍ ችግኞች ስም እስክናውቅ ድረስ ችግኝ መትከል የለብንም እያልኩ አይደለም፡፡ ችግኙን እየተከልን ጎን ለጎን ስለ ዛፍ ዓይነቶች ትምህርትና ዕውቀት እናግኝ ለማለት ያህል ነው፡፡ አረንጓዴው አሻራ ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው ህያው ቅርስ ነው፤ ልክ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ!  (ለመሆኑ በዓለማችን ላይ ከ60ሺ በላይ የዛፍ ዝርያዎች እንዳሉ ታውቃላችሁ?)


Read 3227 times