Saturday, 01 August 2020 12:49

“የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት” በኦሮሚያ ሁከት ለተፈናቀሉ ድጋፍ እያሰባሰበ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 • ማህበራዊ ሚዲያዎች ተዘግተው በመቆየታቸው ድጋፉ እንደቀድሞው አይደለም - ያሬድ ሹመቴ
                 • ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ
                       
            “የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት” በኦሮምያ የተፈጠረውን ሁከትና ግርግር ተከትሎ ለተፈናቀሉና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች እርዳታ ማሰባሰብ መጀመሩን አርቲስት ያሬድ ሹመቴ ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡
እርዳታው እየተሰበሰበ ያለው የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች ሲሆን ድጋፍ የማሰባሰቡ ስራ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን መያዙንም የጥምረቱ አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ ጠቁሟል፡፡
እስከ ትላንት በስቲያ ሀሙስ ድረስ ሁለት የመኪና ጭነት የሚያህል ድጋፍ መሰብሰቡን የገለፀው አርቲስቱ፤ በሁከቱ ሰሞን ማህበራዊ ሚዲያው ተዘግቶ በመቆየቱ እየመጣ ያለው ድጋፍ እንደ በፊቱ አይደለም ካለ በኋላ እርዳታው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ባወጣው መረጃ መሰረትም ከምዕራብ ሐረርጌ 725፣ ከምስራቅ ሐረርጌ 800፣ ከባሌ አጋርፋ 2 ሺህ 360፣ ከምዕራብ አርሲ 805 እና ከጅማ 225 በድምሩ 10 ሺህ 415 ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ታውቋል፡፡
ጥምረቱ ለድጋፍ አድራጊዎች ባስተላለፈው ጥሪ፤ የማይበላሹ የምግብ አይነቶች፣ የህፃናት የታሸጉ ወተቶች፣ አልሚ ምግቦች፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ንፅህናቸው የተጠበቀ ብርድ ልብሶች፣ አንሶላ፣ የአዋቂና የህፃናት አልባሳትንና መሰል ቁሳቁሶችን በመያዝ፣ ወደ ሀገር ፍቅር እንዲመጡ ያስታወቀ ሲሆን፤ የድጋፍ ማሰባሰቡ ሂደት እስከ መጪው ረቡዕ ሐምሌ 29 ድረስ እንደሚቀጥልም አርቲስት ያሬድ ሹመቴ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡


Read 11438 times