Saturday, 01 August 2020 12:35

በሁለት አካባቢዎች በተከሰተ ግጭትና ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች ተገደሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ባሳለፍነው ሳምንት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና ጥቃቶች 33 ያህል ሰዎች ሲገደሉ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ፣ በምሽት በሠላማዊ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት 13 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ100 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በአካባቢው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ናቸው የፈፀሙት በተባለው ጥቃት ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ የአንድ ቤተሰብ አባላት (ባልና ሚስት እንዲሁም ልጆች) መሆናቸው ታውቋል፡፡ በጥቃቱ እስካሁን አንድ ሰው የደረሰበት የማይታወቅ ሲሆን፤ ሌሎች 6 ሰዎች መቁሰላቸውን የክልሉ መንግስት መረጃ ያመለክታል፡፡ በጥቃቱ የተጠረጠሩ ታጣቂዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ሌሎችንም ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል፤ ባሳለፍነው ሣምንት መጀመሪያ ላይ በደቡብ ክልል ኮንሶ ወረዳ በተፈጠረ የመሬት ይገባኛል ውዝግብ 20 ያህል ሰዎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡
በመሬት ይገባኛል ምክንያት በአካባቢው ተጐራብተው በሚገኙት አሌ እና ኮንሶ ማህበረሰቦች መካከል በተፈጠረው በዚህ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን ምንጮች ያስታወቁ ሲሆን፤ ለተፈናቃዮች እርዳታ እየቀረበ አለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በዚህ ግጭት መኖሪያ ቤቶች፣ የእህል ጐተራዎችና ሰብሎች በእሣት መውደማቸውንም ምንጮች አመልክተዋል::

Read 1064 times