Print this page
Saturday, 01 August 2020 11:43

"እቃ፣ እቃ ጨዋታ"

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  "እናማ…‘እቃ፣ እቃ ጨዋታ’ የሚመስሉ ወሬዎች፣ ‘እቃ፣ እቃ ጨዋታ’ የሚመስሉ አስተሳሰቦች፣ ‘እቃ፣ እቃ ጨዋታ’ የሚመስሉ ድርጊቶች በዝተዋል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ…በብዙ ዘርፎች…‘እቃ፣ እቃ ጨዋታ’ የሚመስሉ ነገሮች በዝተዋል፡፡ ፊልም ላይ “ቁረጠው!” የሚሏት ነገር እውነት በሆነችና ከፊሉን እንኳን በገነደስነው እንዴት አሪፍ በሆነ ነበር!"
            
              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እየመሻሸ ነው አሉ፡፡ በስተውጪ ጭር ያለ የሚመስለው ውስጡ ሰዉ እንደ ጉድ ነው፡፡ ውጪ መአት መኪና ተደርድሯል፡፡ ውስጥ ደግሞ ሰው በዝቷል ሳይሆን ግጥም ነው ያለው፡፡ እናማ…ምን መሰላችሁ… መግቢያው ላይ ምን ተደርጓል መሰላችሁ…ወይራ እንደ ጉድ ይጨሳል፡፡ በቃ እየታጠኑ መግባት ነው፡፡ መቼም ‘ትርጉም አያጣም’:: በፊት እኮ “ቢያጣ፣ ቢያጣ ሱሪውን ሸጦ ይምጣ” የሚባል ነገር ነበር፡፡ ወይራ ነገርዬውም ይህንኑን የተካ ይመስላል፡፡
የሚገርመው ነገር ምን መሰላችሁ…ሰዋችን እንዴት ነው የሚያስበው! ነጋ፣ ጠባ ወረርሽኙ የሚተላለፍባቸው መንገዶች በሚዲያ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው፡፡ አይደለም ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን የደረሰው፣ አብዛኞቹ ህጻናትም የሚያውቁት ነው:: እናማ…አትሰብሰቡ እርቀታችሁን ጠብቁ እየተባለ በር ዘግቶ ተሰብስቦ መጠጣት ምን የሚሉት ‘አራድነት’ ነው? (ይሄ ‘አራድነት’ የሚሉት ነገር…አለ አይደል… ‘ኮፒራይት’ ነገር የለውም እንዴ! አይ ግራ ስለገባን ነው፡፡)
የመጣው ችግር ማንንም  ከማንም አይለይ፡፡ የክፉ ቀን ጓዴ አያባብል! የምታውቀው ዘመድ አለህ ተብሎ አይከላከሉት ነገር! እና…ከተማችን ውስጥ በየስፍራው ከመሸ በኋላ በር ተዘግቶ ‘አስረሽ ምቺው’ እየተባለ እንደሆነ አየሰማን ነው:: አሁን ወረርሽኙ በምን አይነት ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ እየሰማን ነው:: አምስትና ዘጠኝ ሰው ተያዘ ምናምን ሲባል ስንደነግጥ እንዳልነበርነው፣ ከተማው ጭር እንዲል  እንዳላደረግነው፣ ተደናግጠን በየቤታችን እንዳልከተምን  አሁን አምስት መቶና ሰባት መቶ ተያዙ ሲባል ቅርባችን ካሉት ጋር በወሬ ደረጃ እንኳን ማውራት ችላ ማለታችን ደግሞ የምር አስደንጋጭ ነው፡፡ ከተማው እንደሆነ አይደለም አደጋው እየባሰ ያለበት ሊመስል ጭራሽ ‘ቢዝነስ አዝ ዩዥዋል’ ነው የሆነው፡፡
ስሙኝማ… ኑሮ እንዴት ነው! “እንዴት ሊሆንልህ ነው! የደላው ሙቅ ያላምጣል፣” ምናምን ቢባልም አይገርምም፡፡ ግን ‘ፖቭርቲ’ ወለሏ ላይ ወይ ከበታቿ ሆናችሁ ስታዩ ግራ የሚገባ ነገር መአት ነው፡፡ “እኛስ እሺ ብንል ወንፊት እያደረገው ያለው ጆንያችን፣ ባዶ ከሆነ የከረመ የሹሮ እቃችን ይመሰክራሉ፡፡ (‘መረጃ ሳይሆን ማስረጃ’ እንደሚባለው ማለት ነው፡፡) ብርዬው እንደልብ ያላቸው ሰዎች ለምንድነው ጩኸታችንን የሚቀሙን! ‘ማማረር’ ለእኛ የተተወ ነዋ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የኦሎምፒክ አሎሎ የሚያክል ጎልድ ጣቱ ላይ ጉብ አድርጎ፣ ቡቺን ጥፍንግ አድርጎ የሚያስር ጎልድ ሀብል አንጠልጥሎ… “አሁን እኮ መኖር አልቻልንም!” ሲላችሁ…አለ አይደል… የሆነ መጽናኛ ቢጤ ታገኛላችሁ:: “ለካስ ገንዘብ ደስታን አያመጣም!” አይነት ‘ዘግይቶ የደረሰን’ የሚባል ፍልስፍና አይነት ነገር ብልጭ ይልላችኋል፡፡ አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ…በራሳችሁ ላይ ‘ፈርስት ኤይድ’ እንደማካሄድ በሉት፡፡ ግን ደግሞ ‘ደስታን ባያመጣም’ ቢያንስ ሆድ ይሞላል፣ ቢያንስ በሰባት ወር አንድ ጊዜ ‘ኢን ታደርጓት’ የነበረችውን ስፔሻል ክትፎ በየሰባት ቀኑ አንድ ጊዜ ልትዝናኑባት ትችላላችሁ፡፡ (ክትፎ ‘የድሎት ሚዛን’ ተደርጎ ስለሚታሰብ ነው፡፡)
እናላችሁ…ድሮ ሲኒማ ቤት ተመልካች የሆነ ፊልም የደበረው እንደሆነ “ፊልሙን ቁረጠው!” እያለ ይጮህ ነበር፡፡ ፊልም የሚያሳየው ሰውዬ አጠገቡ ትልቅ መቀስ ይዞ የተቀመጠ ነበር የሚመስለው፡፡ ደግሞላችሁ… የሆነ የ‘እሷና እሱ’ አይነት ‘ሲን’ ይመጣና ግማሽ ጎረምሳ ዶሮ ማነቂያ በዓይኑ ውል እያለ (ቂ…ቂ…ቂ…) ከአሁን አሁን ሰባ ሰባት ኮከቦች ሊረጩ ነው ብሎ ሲጠብቅ በመጨረሻዋ ሴከንድ ቁርጥ ይልና አንጀት ቁርጥ የሚያደርግ ነገር ነበረው፡፡ (ዘንድሮ ሁሉም ነገር “ሶ ሁዋት፤ ላይፍ ኢዝ ላይፍ!” ሊባል!) እናላችሁ… በዚህ ጊዜ “ቆረጠው እኮ! አቦ ይቁረጥህ!” እየተባለ የሚጮህበት ነገር ነበር፡፡
አሁን በእውነተኛ ህይወት ውስጥ “ቁረጠው!” ብለን ጮኸን ቢቆረጡልን ደስ የሚሉን መአት ነገሮች አሉ፡፡ የኑሮው ክብደት ማለቂያ የሌለው ተከታታይ ፊልም ነገር ስለሆነብን “ቁረጠው!” ብለን ‘የሚቆረጥልን’ ቢሆን እንዴት ደስ ይል ነበር! የምር እኮ ዘንድሮ አስቸጋሪ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ የኑሮው መክፋት አልበቃ ያለ ይመስል የእኛ ነገር መያዣ፣ መጨበጫ ማጣት ነገሮችን አስቸጋሪ እያደረጋቸው ነው:: ብዙ ቦታ የምትሰሙት ‘ተጣሉ፣ ተጋጩ፣ አትደርስብኝ፣ አትድረሺብኝ ተባባሉ፣’ ምናምን ሲባል ነው፡፡ ‘ይሄ ማህበር ፈረሰ፣’ ‘እንዲህ የሚሉት እቁብ መሀል ላይ ተበተነ፣ እንዲህ የሚባል የዘመድ ጉባኤ ፈረሰ’ ሲባል ነው፡፡ እናማ…“ምን ነካን" የሚያስብል ዘመን ውስጥ ነን፡፡
እኔ የምለው…ኮሚክ እኮ ነው፣ ፈረሱ የሚባሉ ትዳሮች ፍጥነታቸው ግርም የሚል ነው፡፡ በፊት እኮ ቢያንስ የተወሰነ ዓመታት አብሮ ከተኖረ በኋላ ነበር መለያየት የሚመጣው፡፡ ዘንድሮ እኮ…አለ አይደል… በቀናት ውስጥ ፈረሱ ከሚባሉት ‘ኤክሴፕሽናል’ ትዳሮች ባለፈ በወራት የሚፈርሱ ብዙ ናቸው ይባላል፡፡ ምን ነካን!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የሰርግ ካርድ አሁንም አለ እንዴ! የሚልክ ቢጠፋብን ጊዜ ነው፡፡ ደግሞስ…‘ፕሮፌሽናቸውን ሚዜነትነት’ አድርገው የነበሩት ወገኖቻችን ‘ቢዙ’ እንዴት ነው! ያው አሁን ‘ነገርዬው’ ብዙም ስለሌለ ሚዜ ምን ያደርጋል፡፡ (የጥንት ሚዜዎች የሆነ የኢመርጀንሲ ለየት ያለ ሀላፊነትም ይጣልባቸው ነበር አሉ… የሙሽራውን ስም ለመጠበቅ! አንዳንድ ሀሳብ እኮ ዝም ብሎ መጥቶ ነው ስንቅር የሚልባችሁ!)
“ስማ እኔ እንደሌሎቹ ሶስት ምናምን ሚዜ አልፈልግም፡፡”
“እውነትሽን ነው፡፡ እንደውም አንድም ሚዜ አያስፈልገንም፡፡ ወጪና ግርግር ማብዛት ነው፡፡”
“እውነት፣ ተባለ እንዴ! ጭራሽ የእኔ ሠርግ ነው ግርግር የሆነው?”
“እየው እንግዲህ ነገር መጠምዘዝ ጀመረሽ:: አሁን እንደዛ የሚል ቃል ከአፌ ወጣ!”
“አጅሬ እኮ ምን እያሰብክ እንደምትናገር አውቃለሁ፡፡”
“መጀመሪያ ራስሽ አይደለሽም እንዴ ሚዜ አልፈልግም ያልሽው?”
“እኔ ሚዜ አልፈልግም አላልኩም፡፡ ሦስት ሚዜ አልፈልግም አልኩ እንጂ ሚዜ አልፈልግም አልኩ?”
“መልካም ፈቃድሽ ሆኖ ብታስረጂኝ…”
“እኔ ከጓደኛ ጓደኛ መለየት ስለማልፈልግ ከትምህርት ቤት ጀምሮ አብረውኝ የነበሩት ሰባቱ አብሮ አደጎቼ በሙሉ ሚዜዎቼ ናቸው፡፡”
“ሰባት! ሰባት ነው ያልሽው!”
“አዎ ሰባት! ምነው ዓለም ሊያልቅ ነው ያሉህ ይመስል ታንባርቃለህ!” (‘የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል’ እንደሚባለው ‘የማያዛልቅ ትዳር ከሚዜ መረጣ ያስታውቃል’ የሚል የምርምር ውጤት ከእለታት አንድ ቀን መስማታችን አይቀርም!)
 “ለምን ከእኔ በኩል አራት  ዘመዶቼን አላመጣልሽምና በስምሽ አንድ የእግር ኳስ ቡድን አትመሰርቺም!”
የምር ግን አይደለም በእውነተኛ ሰርግ በእቃ እቃ ጨዋታ ሰርግ ሰባት ሚዜ ይኖራል? ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እቃ፣ እቃ ምናምን መጫወት የሞከራችሁ… ‘ኖስታልጂያ’ ምናምን ነገር የለም! እና ምን ለማለት ነው…እንደ ‘ሜሞሪ’ ነገር እያነሱ እኮ ዳር፣ ዳር ማለት ይቻላል!
“ስሚ፣ ድሮ እቃ እቃ ስንጫወት ትዝ አይልሽም?”
“ምን ስታስብ ነው አሁን ምርኩዝ መያዣህ ሲቃረብ እሱ ትዝ የሚልህ!”
“ለምን ትዝ አይለኝም! እንደውም አንድ ቀን አጠገቡ ደርሼ የተመለስኩት ነገር ትዝ አይልሽም?”
“ምን አጠገብ?”
“አንቺ ደግሞ…ዳሹን እየሞላሽ አድምጪኝ እንጂ!
“እና ምን ይጠበስ?”
“ማለቴ… መቼም ይጀመር መቼም ዋናው ነገር መጨረሱ ነው ሲባል ሰምተሸ አታውቂም?”
“ሰምቼ አላውቅም፡፡”
“እንግዲያው አሁን እኔ አልኩ፡፡”
“ተባለ እንዴ!
“ተባለ እንዴ!” ከሚባልበት ቃና የነገርዬውን አቅጣጫ ማወቅ እንደሚቻል መጠቆም እንወዳለን! ቂ…ቂ…ቂ… (እኔ የምለው…እሱዬውስ ቢሆን በ‘ኤይት’ና በ‘ናይን’ እድሜው የከሸፈበትን በ‘ፊፍቲ’ ማለቂያ ላይ እንጨርስ ብሎ ነገር ምን የሚሉት ባዮሎጂ ነው! ወይም በእንደዛ አይነት ነገርም ‘ሂሳብ ማወራረድ’ የሚሉት ነገር አለ እንዴ!)
የምር ግን እቃ እቃ ጨዋታ በዩኔስኮም ባይሆን የሆነ ድርጅት በቅርስነት ሊመዘግበው ይገባል፡፡ ልክ ነዋ…የልጆች መጫወቻ የፕላስቲክ ሽጉጥና የባርቢ አሻንጉሊት ከመሆኑ በፊት ጊዜውን የቀደመ እቃ፣ እቃ የሚሉት የህጻናት ጨዋታ ነበር ለማለት ያህል ነው፡፡
እናማ…‘እቃ፣ እቃ ጨዋታ’ የሚመስሉ ወሬዎች፣ ‘እቃ፣ እቃ ጨዋታ’ የሚመስሉ አስተሳሰቦች፣ ‘እቃ፣ እቃ ጨዋታ’ የሚመስሉ ድርጊቶች በዝተዋል፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ…በብዙ ዘርፎች…‘እቃ፣ እቃ ጨዋታ’ የሚመስሉ ነገሮች በዝተዋል፡፡ ፊልም ላይ “ቁረጠው!” የሚሏት ነገር እውነት በሆነችና ከፊሉን እንኳን በገነደስነው እንዴት አሪፍ በሆነ ነበር!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2002 times