Saturday, 25 July 2020 16:00

በአለማችን የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ከ15.5 ሚሊዮን አልፏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በአሜሪካ የተጠቂዎች ቁጥር ከሚነገረው በ24 እጥፍ ሊበልጥ ይችላል ተባለ

           የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም በመላው አለም መሰራጨቱን የቀጠለ ሲሆን፣ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ የተጠቂዎች ቁጥር ከ15.5 ሚሊዮን በላይ መድረሱንና የሟቾች ቁጥርም ከ632 ሺህ ማለፉን ወርልዶ ሜትር ድረገጽ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችና በሟቾች ቁጥር ከአለማችን አገራት መሪነቱን ይዛ በዘለቀችው አሜሪካ፤ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ከ4.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መጠቃታቸውና የሟቾች ቁጥርም ከ146 ሺህ ከፍ ማለቱን ዎርልዶ ሜትር ድረገጽ ባወጣው መረጃ ቢያመለክትም፣ የአገሪቱ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል ግን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እየተነገረ ካለው በ24 እጥፍ ያህል ሊበልጥ እንደሚችል በጥናት አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ብራዚል በ2.3 ሚሊዮን፣ ህንድ በ1.3 ሚሊዮን፣ ሩስያ በ795 ሺህ፣ ደቡብ አፍሪካ በ395 ሺህ ያህል የቫይረሱ ተጠቂዎች ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ስፍራ የያዙ የአለማችን አገራት ሲሆኑ፣ በሟቾች ቁጥር ደግሞ ብራዚል በ83 ሺህ፣ እንግሊዝ 45 ሺህ፣ ሜክሲኮ 41 ሺህ፣ ህንድ 30 ሺህ እንደተመዘገበባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ለድሃ አገራት ዜጎች በጊዜያዊነት ደመወዝ በመስጠት በአገራቱ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት ማሰቡንና ለዚህም በየወሩ አስከ 465 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ማስታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ድርጅቱ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገውና በ132 ታዳጊ አገራራ ውስጥ የሚገኙ 2.7 ቢሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ባለው ዕቅዱ፣ ለዜጎች ደመወዝ በጊዜያዊነት በመስጠትና አገራተእንዳይወጡ በማድረግ ወረርሽኙን ለመግታት ማሰቡን ገልጧል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት መሪዎች በበኩላቸው ከሰሞኑ ባደረጉት ስብሰባ፤ ለ27 የህብረቱ አባል አገራት በድጋፍና በብድር መልክ የሚሰጥ የ859 ቢሊዮን ዶላር የድህረ ኮሮና ቫይረስ ማገገሚያ በጀት ማጽደቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በአፍሪካ አገራት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን የአለም የጤና ድርጅት በሳምንቱ መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሌሎች የአለም አካባቢዎች አንጻር እምብዛም የከፋ እንዳልነበር ያስታወሰው ድርጅቱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የቫይረሱ ስርጭት አስጊ በሆነ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱንና የቫይረሱ ስርጭት መጠን ባለፈው ሳምንት በናሚቢያ በ69 በመቶ፣ በዛምቢያ በ57 በመቶ፣ በማዳጋስካር በ50 በመቶ፣ በኬንያ በ31 በመቶ፣ በደ/ አፍሪካ በ30 በመቶ መጨመሩን አመልክቷል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ ከ770 ሺህ በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና ወደ 17 ሺህ የሚጠጉትን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የዘገበው አልጀዚራ፣ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም ወደ 435 ሺህ መጠጋቱን አስነብቧል፡፡
በአህጉሪቱ የተስፋፋውን የቫይረሱ ስርጭት ለመግታት የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግና ያሉትን አማራጮች ሁሉ ለመጠቀም መትጋት እጅግ አስፈላጊ ነው ብሎ ያመነው የአለም የጤና ድርጅት፤ከሰሞኑ ከአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል ጋር በመቀናጀት በአፍሪካ አገራት ለኮሮና ቫይረስ ባህላዊ መፍትሄዎችን ለማፍለቅ ለሚሰሩ ምርምሮች ድጋፍና የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ኮሜቴ ማቋቋሙን ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
የዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ መንግስት በአገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በማሰብ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳቱን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ሲያደርግ፣ የዚምባብዌ መንግስት በበኩሉ ስርጭቱን ለመግታት በመላው አገሪቱ ሰዓት እላፊ ያወጀ ሲሆን በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከዚህ በፊት የተጣሉ ደንብና መመሪያዎችን ተላልፈዋል ያላቸውን ከ1 ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰሩን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

Read 1583 times