Saturday, 25 July 2020 15:47

በእውን ተስፋ፣ ለዘመናት የሚዘልቅ ትልቅ ታሪክ - የሕዳሴ ግድብ

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

የዛሬ 9 ዓመት፣ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ገና “ሲታወጅ”ና የመሰረት ድንጋይ ሲገለጥ፣ የጐባ አካባቢ፣ ገደላገደል በረሃ ነበር። ወራት አለፉ፤ ግንባታው 5% ደረሰ። ዓመት ሞላው፣ ግንባታው 10% አለፈ። ሁለት ዓመት ሆነው፤ ወደ 20% ተጠጋ… እንዲህ እንዲህ እየተባለ ሲነገር፤ ደስ ቢልም፤ ገና የግድብ “መልክ” አይታይበትም ነበር።
ትልቅ ስራ፣ ትዕግስትን ይፈታተናል። የግድብ ግንባታው፣ አንድ በመቶ፣ ሁለት በመቶ እየተራመደ፣ እያንዳንዱ መቶኛም፣ 50 ሚሊዮን ዶላር እየፈጀ፣ በርካታ ወራት ያልፋሉ። “እውን ለወግ ለማዕረግ ይበቃል ይሆን? ወደሚጨበጥ ውጤት፣ ወደ ብርሃናማ ስኬት ይደርስ ይሆን?” ያስብላል።
ደግነቱ ግን፣ ተግተው ከሰሩና ፀንተው ከተጓዙ፣ ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ ይደርሳሉ። አዲስ ታሪክ ይፈጥራሉ። ለውጡን ተመልከቱ። ከአባይ ዳር፣ ከውሃ አጠገብ ቢሆንም እንኳ፣ እስካለፈው ወር ድረስ፣ ለእልፍ ዘመናት ተራቁቶ ሲታይ የነበረው ገደላገደልና ሸለቆ፤ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ውሃ መታቀፍ ጀምሯል። ከኢትዮጵያ ማህፀን ለሚፈልቀው ውሃ፣ አዲስ ማረፊያ ሆኗል።
ይሄ አዲስ ታሪክ ነው። ገላጣው ገደል ሸንተረር፣ ውሃ የተጠማው አፈር፤ ካሁን በኋላ፤ ዳግመኛ አይራቆትም። በካሜራ ተቀርፆ የተቀመጠ ቪዲዮ እያየን፣ “ድሮ እንዲህ ነበር” እንል ይሆናል፤ ያለፈውን ታሪክ ለማስታወስ። እድሜ ለሕዳሴ፣ በድሮው ምትክ፣ አዲስ ታሪክ እየተፈረጠ ነው። ለእልፍ አእላፍ ዓመታት ያልነበረ አዲስ ሐይቅ ተወልዷል።
ከዓመት ዓመትም እያደገ፣ ውሃው እየበዛና ሐይቁ እየሰፋ ይሄዳል። “የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳምር አዲስ ተዓምር ነው” ማለት ይቻላል። ምን ይጠራጠራል? ለጣና ሐይቅ ክብር የሚመጥን፣ ባለግርማ ሞገስ ሙሽራ ሐይቅ፤ እነሆ እየደረሰ ነው።
ለሺ እና ለሺ ዓመታት፣ ከህልምና ከምኞት ሳያልፍ የቆየው የሩቅ ተስፋ፣ ይሄውና በእውን የሚከሰትበት ዘመን ተፈጠረ።
በአንድ ጀንበር አይደለም የተወለደው። ከብዙ ዓመታትና ከብዙ ሚሊዮኖች ምኞት ነው የተፀነሰው። ግንባታው፤ በእውን ሀ ተብሎ ከተጀመረ በኋላም፣ ከባዱ ስራ፣ የኢትዮጵያውያንን አቅም መፈታተኑ አልቀረም። አደገኛ እንቅፋቶችና መሰናክሎችም ገጥመውታል።
ከ5 ዓመት በላይ መጓተቱ ብቻ አይደለም ችግሩ። ደግሞስ፣ በግንባታው ውስጥ የመንግስት ድርጅት (ሜቴክ) ሲገባበት፣ ግንባታው መጓተቱ ምን ይገርማል? አዎ፤ ያሳዝናል፤ ያስቆጫል፤ ግን አይገርምም። አስታውሱ። ግንባታው ከ10 ዓመት በላይ እንደሚፈጅ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከዛሬ 7 ዓመት በፊት ተዘግቧል።
እንዲያም ሆኖ፣ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ ከሌሎች የመንግስት ፕሮጀክቶች በእጅጉ የተሻለ ነው። ሜቴክ ሳይሆን፤ ሌሎች የመንግስት ድርጅቶች የገቡበት የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት፣ በ1998 ዓ.ም እንደተጀመረና፤ እስከዛሬ በወጉ ለውጤት እንዳልበቃ አስቡት። 15 ዓመት ሆኖታል። የሕዳሴ ግድብም ተመሳሳይ ችግር ደርሶበታል። ግን ይሻላል። ለምን? ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ ችግሩን ለማረም ተሞክሯል። ግንባታው፤ በአገር በዜጐች አቅምና ወኔ፣ በአብዛኛው በግል ኩባንያና በባለሙያ ሰራተኞች የሚከናወን መሆኑም ጠቅሟል። ውጤቱም እያማረ ነው።
ለ9 ዓመታት፣ ከመሃል አገር እስከ ዳር ድንበር፤ ኢትዮጵያውያን ባለ በሌለ አቅምና በፅናት የዘመቱለት፣ ጐንበስ ቀና ያሉለት፣ ሃሳብ ጥሪታቸውን ያፈሰሱለት ትልቅ ግንባታ፣ እናም በተስፋና በወኔ የደገሱለት ታላቅ በዓል፣ ይሄውና ዋዜማው ታየ።
ለግድብ ግንባታ የዋለው፣ የኮንክሪትና የብረት ብዛት ብቻ፣ ግዙፉነቱን ይመሰክራል። የእግር ኳስ ሜዳ ላይ ቢጠቀጠቅ፣ ሽቅብ ስንት ፎቅ እንደሚሆን አስቡት!
ስፋቱ የኳስ ሜዳ፣ ቁመቱ ከ1000 ሜትር የሚበልጥ ግንባታ፣… ይሄ ትልቅ ታሪክ ነው። “በዘመናችን የተገነባ፣ ለዘመናት የሚዘልቅ የኢትዮጵያ ፒራሚድ ነው” እንበል?
የግድቡን ግዙፍነት፣ ሐይቁን ስፋትና የውሃውን መጠን በማየት ብቻ፣ “ግንባታው፣ ትልቅ የኢትዮጵያ ፒራሚድ፣ የዘመናችን አውራ ሐውልትና ቅርስ ነው” ማለት እንችላለን።
ቁም ነገሩ ግን፣ ይህ ብቻ አይደለም። ከግንባታ በኋላ፣ ህይወትን የሚያለመልም መልካም ፍሬ የሚሰጥ ነው - የሕዳሴ ግድብ።
በ9 ዓመታት ብርቱ ትጋትና ጽናት፤ በሚሊዮኖች ጥሪትና ሃሳብ፤ ስንዝር በስንዝር በእውን እየገዘፈና መልክ እየያዘ የመጣው ውድ የጥበብ ሥራ፣ ወደ ውጤት ለመሸጋገር ስንቅ መያዝ ጀምሯል። ከዚህ ጋርም፣ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የሚውልበት፣ ተናፋቂው የስኬት ድግስ እየተቃረበ፤ ዋዜማውን ለማየት በቅተናል።
አዎ፣ ዛሬ፣ ስራው ገና አላለቀም። የጥበብ ስራውና የድግሱ ዝግጅት አይቋረጥም። ግን፣ እልልታው ተጀምሯል። እርጥብ ቄጤማ ሲነሰነስ ይሄውና ከሰሞኑ አይተናል። ከ15ቱ ብርቱ መንኮራኩሮች መካከል፣ ሁለቱ ከፊት ቀድመው፣ መሽከርከር ሲጀምሩ፣ ብዙ ርችቶች፣ የኢትዮጵያን ምድርና ሰማይ ያበራሉ።
ለጥቀው ሌሎቹ መንኮራኩሮችም፣ ነፍስ ዘርተው በሙሉ ሃይል ይሽከረከራሉ። ያኔ፤ ከህዳሴ ግድብ የሚፈልቀው ሃይል፣ ጨለማውን ይገፍልናል።
ለሚሊዮኖች ቤት፣ ደማቅ ብርሃኑን ይፈነጥቃል። ይህም ብቻ አይደለም።
ያንቀላፉ ፋብሪካዎች ይነቃሉ። እንደ ሰርግ ሙዚቃና ጭፈራ፣ የፋብሪካዎች ድምጽ አምሮ ይደምቃል። ሃይል አንሷቸውና ጉልበት አጥተው፤ በሃሳብና በጅምር ብቻ የቀሩ ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም ሌሎች አዳዲሶ ገቢዎች ለኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት፣ ከቅርብና ከሩቅ እየተጠራሩ ወደ ስኬት ድግስ ሲቀላቀሉ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ይታደሳል።
የኢትዮጵያ ትልቅነትና ደስታ፣ ማለትም የኢትዮጵያውያን ሕይወት፣… በአእምሮም፣ በአካልም፣ በመንፈስም እየተዋበና እየበለፀገ፣ ከከፍታ ወደ ከፍታ፣ ከሕዳሴ ግድብ ወደ እልፍ የሕዳሴ ፋብሪካ፣ በእያንዳንዱ ሰው የግል ኢንቨስትመንትና የሙያ ብቃት፣ ወደ ላቀ የእውቀትና የኢንዱስትሪ፣ ወደላቀ የሕዳሴና የስልጣኔ ደረጃ ይጓዛል፤ እርምጃውም ወደ ግስጋሴ ይሸጋገራል።
ይሄ ተስፋ ነው፤ ምኞት ነው። ግን እውን ልናደርገው እንችላለን። የሕዳሴ ግድብ ይመሰክራል።
በጭፍን ስሜት ሳይሆን በአስተዋይነት ካወቅንበት፣ በምቀኝነት ለጥፋት ከመንጋጋት ይልቅ በጥበብ ተግተንና ፀንተን ከሰራንበት፣ አዳዲስ ድንቅ ታሪኮችን መፍጠር እንችላለን። በዚህች ትልቅ የተስፋ አገር፣ ሕይወትን በእውን ማለምለም እንችላለን።



Read 2300 times