Wednesday, 29 July 2020 00:00

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ‹‹ብልፅግና እናትሽ….››
               (አሌክስ አብርሃም)
ልጆች ሆነን የከተማችን መውጫ ላይ በደርግና ኢህአዴግ ጦርነት ተቃጥሎ የወደቀ ታንክ ነበር! እዛ ታንክ ላይ እየተንጠላጠልን እንጫወት ነበር ….ታዲያ ታንኩ ውስጥ የመጨረሻው የደርግ ወታደር ሲከበብ ራሱን ከታንኩ ጋር አጋይቶ ነበር አሉ የሞተው፡፡ ከመሞቱ በፊት ግን በጩቤ ይሁን በምን ብቻ የታንኩ ውስጠኛ ክፍል ላይ ፈቅፍቆ እንዲህ የሚል ፅሁፍ ፅፏል ‹‹ወያኔ እናትሽ….›› ተስፋ የቆረጠ ሰው የመጨረሻ ጉልበቱ ስድብ ነው፡፡ ህወኃት ሰሞኑን እያደረገች ያለው ነገር እንደዚህ ወታደር እየመሰለኝ ነው፡፡ ሚዲያዎቹ ስድብ በስድብ ሆነዋል! የአክቲቪስቶቹማ ዝም ነው፡፡
የሆነ ሆኖ የህወኃትና የመንግስቱ ኃይለማሪያም ዕጣ ፈንታ በመጨረሻ አንድ አይነት የሚሆን እየመሰለኝ ነው! በቅርቡም ሆነ በሩቁ …ብቻ የህወሀት መሪዎች "ለአገርና ህዝብ ደህንነት ሲባል አንጋፋ የህወኃት መሪዎች ስልጣን ለቀው ከአገር ውጭ ሄደዋል" የሚል ዜና ሳያሰሙን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ለምን ….ምክንያቱም አሁን የሚያሳዩት አጠቃላይ ባህሪ፤ ደርግ ሊወድቅ አካባቢ የነበረውን አይነት ባህሪ ነው …ራሱ የደርግ ባህሪ!! በዲፕሎማሲው ጎራ ጀንበር እየጠለቀችባቸው መሆኑን ዓለም ቢያውቅም፣ አልሞትንም ለማለት በርካታ የውሸት ዜናዎችና ድሎች ማወጅ፣ በዛቻና በክስ የተሞላ አልፎ አልፎም ስድብና ዘለፋ የቀላቀለ መግለጫ ማብዛት፣ ባንዳ ፣ አድሃሪ ፣ አገር ሻጭ ወዘተ! (ደርግም አገር ገንጣይ፣ አድሃሪ፣ አገር ሻጭ ነበር የሚላቸው!)
እንደ አንድ አቋም አለኝ እንደሚልና አገር እንደመራ ድርጅት፤ ወጥ የሆነ አቋም ይዞ ከመቆም ይልቅ ፖሊስ እንደሚያሯሩጠውና ነብሱን ለማዳን እንደሚቃትት ተራ ዱርየ ያገኙት ጉድጓድ ውስጥ ዘለው መግባት … ነብሰ ገዳዩም ጋር፣ ንብረት አውዳሚውም ጋር፣ አገር ትፍረስ የሚለውም ጋር መግበስበስ፣ እና ሊያርዱህ ነው፤ ሊያጠፉህ ነው በሚል ማስፈራሪያ ህዝብን ለጦርነት መቀስቀስና በጦር ሰራዊታቸው ክፉኛ መተማመን …. ደርግም እንዲሁ ነበር፡፡ ከህዝባችን ጋር በክብር እንሞታለን ምናምን ማለት (ይዞ ሟች ) ደርግም አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር አልነበር ያለው …በመጨረሻም …አሜሪካን ሲአይ ኤንና መንግስት ጋር ግንኙነት አላቸው የሚሏቸውን አገራትና መሪዎች ማሞለጭ! ደርግም እንደዚሁ ነበረ ያደረገው! አሁን ህወሀት በሚዲያዎቿ የቀራት ስድብ "ብልጽግና እናትሽ…." የሚል ነው


           ትእግስቱ የማያልቅበት ጨዋ ሕዝብ
የሚሰሙኝ ከሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዶ/ር. ዓቢይ አሕመድ፣ ለአዲስ አበባ ከንቲባም፣ ለወይዘሮ ሙፈሪያት የሰላም ሚኒስትር፣ ምናልባት ሌሎች መኖሪያ ቤት መፍረስ የተጠናወታቸው ባለሥልጣኖች ካሉ ለነሱም የኅሊናዬን ጩኸት አስሰማለሁ፤
የሚያዩኝና የሚያዝኑልኝ ከሆነም ተንበርክኬ እለምናቸዋለሁ!
በዚህ የክረምት ወቅት፣ በዚህ የማትታይ ጉድ ዓለምን በሙሉ አንበርክካ በየዕለቱ ሰዎችን በምትጨርስበት ዘመን፣ በዚህ ዘመን እጃችሁን ቶሎ-ቶሎ ታጠቡ፤ አፍና አፍንጫችሁን ሸፍኑ፣ ስትገናኙ ተራራቁ በተባለበት ዘመን፣ በዚህ ሰው ሁሉ ሥራ ፈትቶ በቦዘነበት ዘመን፣ በዓባይ ጉዳይ ከግብጽ ጋር በተፋጠጥንበት ዘመን፣ የድሆችን ቤት በጉልበት ማፍረስና ድሆችን ማስለቀስ አቤቱታቸው የላይኛው ጌታ ዘንድ እንደሚደርስ ባለማወቅ ነው? ወይስ ኮሮና በቂ አልሆነምና ነው? እግዚአብሔር እንደሆነ ከኮሮና የባሰ ለመልቀቅ ችግር የለበትም፡፡
ዶ/ር ዓቢይ ስለ ይቅርታ የሚናገረው ስለነዚህ ደሀዎች አይሠራም? ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልልቅ ዓላማዎች አንዱም እነዚህን እንባቸው የእግዚአብሔርን ደጃፍ የሚድኆች ያጨቀይ ደሀዎችን አይነካም?
በመጨረሻም እነዚህን ድሆች እግዚአብሔር አያያቸውም ብላችሁ ታስባላችሁ? ወይስ አይቶ መልስ ሳይሰጥ ይቀራል ብላችሁ ታምናላችሁ?
እግዚአብሔር ነገን ይግለጥላችሁ!
***
የነገው ብሔራዊ ዕዳ
(መስፍን ወልደ ማርያም)
የወጣቱ ዘፋኝ ሞትና አገዳደል በጣም ያሳዝናል፤ ይበልጥ የሚያሳዝነው ግን ‹‹ፖሊቲካ›› የሚሉትን የገደለው ሽብርተኛነት መሆኑ ነው፤ ከሽብርተኛነት የምንሄደው ወዴት ይሆናል? የወጣቱን ነፍስ ይማር ስል፣ በሕይወት አለን ለምንለውም የእግዚአብሔርን ምሕረት እለምናለሁ፤ ለጊዜው ብዙዎቻችን ተርፈናል፤ እኔም መስኮቴ ተለይቶ በድንጋይ በመሰበሩ ብቻ እግዚአብሔርን እያመሰገንሁ እጅግ በጣም ለተጎዳው ለሚከተለው ትውልድ አዝናለሁ፤ የተገነባው መፍረሱ እያሳዘነን እንዴት እንደተገነባና በግንባታው ያዘኑና ያለቀሱ መኖራቸውን አንርሳ! እንዲያውም ለወደፊቱ ይኸው የደሀው ለቅሶ የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ አባዜ በያዛቸውና ሕግን መሣሪያቸው ባደረጉ ጉልበተኞች እየተካሄደ ነው፤ የደሀዎች እንባ መሬቱን አጨቅይቶ ጎርፉ ወደ ሰማይ እየነጠረ ነው፤ ለነገ የምናጠራቅመው ብሔራዊ ዕዳ ነው! ያሳዝናል! የዛሬው የቤት ማፍረስ ዘመቻ ለነገው የሽብርተኛ ዘመቻ መነሻ ይሆናል፡፡
***
አባይ ታጥቋል ብረት
በኔ ሞት በኔ ሞት
አደራ አትርሱት
ትንሽ ይጠጣለት
ሳይቀጥን ይሄ ሙሌት
ጥሩት ያንን ጠላት
---
አዎን አባይ ወደፊት
ግንድ አያውቅም በሉት
አግኝቶ የሚያድርበት
ተሸክሟል መብራት
---
ንገሩ ለጠላት
ተሸክሟል በሉት
እሳትና እራት
---
አዎን ለሚጠሉት
ንገሩ ለጠላት
ተሸክሟል በሉት
ክብርና ክብሪት
አዎን ንገሩት
ደርሰው ለሚነኩት
---
አባይ ሰልችቶት
ግፍና ግንድ መግፋት
ተጨንቆ አስገድደውት
ተሸክሟል ብረት
የሚያስፈራ ጥይት
አባይ የሁሉ አባት
(በቃሉ ይመኑ)
(Habtish Dôø Yilma)
***
ለሠው ስያሜ የዋሉ ወንዞቻችን ....
"ይገደብ አባይ" ብለው ለልጃቸው ስም ያወጡት የጎጃሙ ሰው አቶ አባይ፤ ታላቁ ወንዝ መገደቡን ሲሰሙ ምን ተሰምቷቸው ይሆን?
Freshman Ethiopian Geography ያስተማረኝ መምህሬ ረ/ፕ ብርሃኑ በስም አወጣጥ ዙሪያ እንዲህ ብሎ ነግሮን ነበር ።
"የጎጃም ሰዎች በአባይ ወንዝ ስለሚመኩ ለልጆቻቸው አባይ፣ አባይነህ፣ አባይነሽ እያሉ ስም ያወጣሉ። የሸዋ ሰዎች ደግሞ በአባይ ዋና ገባር በሆነው በጀማ ወንዝ ስለሚመኩ ለልጆቻቸው ጀማዬ፣ ጀማነሽ፣ ጀማነህ እያሉ ስም ያወጣሉ።"
እንዲህ አይነት ስያሜዎች በሌሎች የአባይ (የጥቁር፣ የሶባትና አትባራ) ገባር በሆኑት እንደ በሽሎ፣ ሙገር፣ ፊንጫ፣ ዴዴሳ፣ ዳቡስ፣ ዲንዲር፣ በለስ፣ ሶር፣ ገባ፣ ብርብር፣ መረብ፣ ተከዘ፣ አንገረብ፣ ባሮ፣ አኮቦ፣ የሌሎች ወንዞቻችን አዋሽ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ /ዳዋ፣ ዋቤ፣ ጊቤ፣ ጎጀብ፣ ኦሞ ...ዙሪያ ለስም መጠሪያነት የሚያገለግሉ ይኖሩ ይሆን? የምታውቁ ካላችሁ ወዲህ በሉ እስኪ ...
(አቤል አያሌው)
***
ችግሩ...
በተለያየ ጊዜ፣ አንድን ሕዝብ “ፀሓይህን ማታ ማታ የሚሰርቅህ አብሮህ ያለው የሌላ ዘር ሕዝብ ነው፣ ምግብህንም የሚያሻግተው እሱው ነው፣ የዝናብን ውኃ ከላይ የሚደፋብህም ራሱ ነው...” እያልክ አእምሮውን ስትመርዘው ከኖርክ፣ የሚጠብቀው ጊዜ ነው። ባቄላ ዘርተህ ጤፍ ልታጭድ አትወጣም። የዘራኻትን ታጭዳለህ።
በየተገኘው አጋጣሚ “ነፍጠኛ እንዲህ በድሎህ ብድር ሳትመልስ” ብሎ የከረመው የተፈራረቀ መንግሥትና “ደንቆሮ ኤሊት”፤ ለራሱ ሥልጣን መቆናጠጫ ሲያዘጋጀው የኖረውን ምስኪን ሕፃን ሲያድግ ምንም አትጠብቅበትም። እሳተ ጎሞራ በፈነዳም ጊዜ፣ ንፋስም በነፈሰ ጊዜ፣ መብረቅም በጮኸ ጊዜ ከጎን ያለውን ውኃ አጣጩን ሕዝብ ነው የሚፈርጀው። “ያ ሕዝብ ነዋ የመብረቁ መነሻ።”
አዲስ አበባ ላይ አንድ ወዳጄ የነገረኝን የሰሞኑ አጋጣሚ ልናገር፡-
“የገዛ ሰፈሬ ዱላ ይዞ ተደራጅቶ የመጣውንና ንብረት እየሰባበረ፣ ያገኘውን እየደበደበ የመጣውን ቄሮ ለመመከትና ለማስጣል “ተደራጅተን” ስንወጣ ያገኘነው አስራ ሦስትና አስራ አራት ዓመት የማያልፋቸውን ታዳጊዎች፣ ድንጋይ ሲወረውሩና ዱላ ይዘው ሲፎክሩ ነበር። እኚህን ሕፃናት ምን ብሎ በኔ ዕድሜ ያለ ሰው ይመታል? ጃስ አልናቸው፣ ሮጡ።”
ችግሮቹ፣ በየጊዜው የሚቀርቡት የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚናገሯቸውና የሚፎክሯቸው “በለው” ዓይነት የክፋት ዘሮች ናቸው።
ችግሮቹ፣ እነዚህን ሕፃናት እያደራጁ ከመኻልና ኋላ ዱላ ይዘው “በለው፣ አቃጥለው፣ ግደለው” የሚሉት አረመኔዎች ናቸው።
ችግሮቹ፣ “ከጎንህ ያለውን ሌላ ዘር መንገድ ዝጋበት፣ ጨርሰው” እያሉ በግልጽ የዘር ጭፍጨፋን የሚቀሰቅሱ የክፋት ሚዲያዎች ናቸው።
ችግሮቹ፣ ቄሮ ሌላውን ዘር መጨፍጨፉን ልክ እንዳልኾነ መናገርና አረመኔውን ከመኻል ማውገዝ ሲገባቸው የተለያየ ማነጻጸሪያና ምክንያት የሚያቀርቡ “የኔ ዘር ጻድቅ አራጅ ነው” ባዮች ናቸው።
ችግሮቹ ናቸው መቀረፍ ያለባቸው። ሕዝብማ እንደመሩት ነው። በዘሩ ጻድቅ፣ በዘሩ እርጉም የለም።
ወንጀለኞቹን ባለሥልጣናት፣ ወንጀለኞቹን የክፋት አደራጆች፣ ወንጀለኞቹን ገዳይና አራጆች፣ ወንጀለኞቹን ሚዲያና ፖለቲከኞች በግልጽና በሚገባቸው ልክ ፍርድ ካልሰጠ፣ ፍትሕ አካል የለንም። ምንም ዳር ዳር ማለት አያስፈልግም፣ በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ የሌላ ዘር ተወላጆች፣ በተለይም ዐማራና ጉራጌዎች(በአንዳንድ ስፍራዎች ክርስቲያን ኦሮሞዎችንም ጨምሮ) መጨፍጨፋቸውና ንብረቶቻቸው መውደማቸው ግልፅ ነው። ሃያ ምናምን ሰው አይደለም ወንጀለኛው፣ ኹሉም ለፍርድ ይቅረብ!
ችግሩ የፖለቲካ አይደለም። ድንቁርና ፖለቲካ ኾኖ አያውቅም። በዘር በሃይማኖት አብዶ በወንጀል የመዝቀጥ ጥግ ነው።
(ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ)
***
ግድያው ለዚህ  ቀን እንዳንደርስ ነበር!
ከአርቲስት ሃጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ምን እንዲከሰት እንደተፈለገም የአደባባይ ምስጢር ነው። እጅግ የተቀናበረው ግድያ ዋንኛ ግቡ፣ የህዳሴው ግድብ የውሀ ሙሌትን ማደናቀፍም ነው። የአቋራጭ ስልጣን ጉጉትም ተጨማሪ ገፊ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። የተለያዩ የውስጥና የውጭ ሀይሎች የድምጻዊውን ሕይወት ወደ ራሳቸው ፍላጎት ስበውታል። ይሁንና እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ግድያው የሀጫሉን ሕይወት ቢቀጥፍም የተሴረው አልተሳካም፡፡ የአስገዳዮቹ ግብ ሳይመታ ቀርቶ ሀገር ሳትፈርስ ቀረች። የግድቡ የዚህ ዓመት ውሀ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ።
ነፍስ_ይማር!
***
በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልላዊ
መስተዳድር ዙሪያ ለመነጫነጭ ያህል
(በአማን ነጸረ)
1. የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ፌደራል መንግሥቱ የያዙት ወከባ እየተመቸኝ አይደለም፡፡ ሰሞኑን የማየው የአሽሙር፣ የ‹‹ፕሮክሲ›› ጨዋታ፣ አንዱ የሌላውን ተቀባይነትና ሕልውና ለማሳጣት የሚካሄድ (የአባይ ግድብ ደስታ እንኳ ያላረገበው) የፍረጃ ድርደራ፤አሳፋሪና የዘቀጠ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
2. ፌደራል መንግሥቱ ሆደ ሰፊ ሊሆን ይገባል:: የትግራይ ወንድም እኅቶቻችን የመገለል የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማቸው ከልቡ መሥራት አለበት፡፡ ጠ/ሚ/ሩ በ‹‹መደመር መጽሐፋቸው›› ደጋግመው ‹መደመር ያክመዋል› በሚል የሚጠቅሱት የ‹‹ብቸኝነት›› ስሜት በትግራይ ሕዝብ ላይ እየተስተዋለ ነው:: ፌደራል መንግሥቱ ጉዳዩን በቀና ልቡና ሊያየው ይገባል፡፡ ካለበለዚያ ‹ሰነፍ እረኛ ከሩቅ ይመልሳል› ማስተረቱ ነው፡፡ ኃላፊነቱን ከልብ ይወጣ! መንግሥትነቱ ‹‹የኢትዮጵያ›› የሚል ቅጽል ያለበት መሆኑን አይዘንጋ!
3. በክልሉ መንግሥት በኩል የማየው ያላቋረጠ ለፌደራል መንግሥቱ እውቅና የመንፈግና የማሳጣት ተግባርም ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የክልሉ መንግሥት በዲጅታሎች ተፅዕኖ ስር ወድቆ በአክቲቪዝም መንፈስ እየተመራ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከመንግሥታዊ አክቲቭዝምና "ብሶት ወለድ"ነት ወጥቶ (ሀገራዊ ኃላፊነቱን ሳይዘነጋ) የመንግሥት ቁመና ይላበስ!
እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የትግራይ ታሪክ፣ የትግራይ ሕዝብ፣ … አካሌ ነው ብዬ ከልቤ አምናለሁ፡፡ በትግራይ ምድር ኖሮ እንደሚያውቅ፣ ከነዚያ የዋኃን እናቶች እጅ እንደበላ ሰው መቼውንም የትግራይን ክፉ መስማት አልፈልግም፡፡ ኢትዮጵያን ካቆሙ አዕማድ አንዱ የሆነው ሕዝብ በሠራው ቤት ባይተዋር ሲሆን ማየት አልፈልግም፡፡ እናም … በሁለቱ (በእኔ እምነት) እልኸኛ ዝሆኖች መጓተት ደስተኛ አይደለሁም፡፡ አህጉር ስለሚከፍል ወንዝ ባለቤትነት እያወጋን በጅረት ተከፋፍሎ ‹‹የት አባቱ!›› መባባል አይመጥነንም:: ዝሆኖች ሆይ … ሕዝቡን ያከበረና የመጠነ ንግግር ውይይት አድርጉ፣ ዲጅታሎችም ከ‹‹ወያላው ዝም!›› እንውጣና ሁለቱን ዝሆኖች በመግራት (ከውርክብ ወደ እውነተኛ ‹‹ርክብ››) ወደ ጠረጴዛ እንግፋቸው ለማለት ያህል ነው፡፡
ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር!


Read 5991 times