Tuesday, 28 July 2020 00:00

በዓባይ ጉዳይ ስኬታማ እንሆን ዘንድ ምን እናድርግ?

Written by  ከተመስገን ጌታሁን (temesgengt@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

   ኢትዮጵያና ግብጽ እንዲፈራረሙ የፕሬዚዳንት ትራምፕ መንግሥት ያረቀቀውና የከሸፈው የውኃ ሙሌት ውል አንድምታ ምን ሊሆን እንደሚችል በኢቢኤሷ ሄለን አማካኝነት የተጋበዙ የእኛዎቹ ፈረንጅ አገር የሚኖሩ ሰዎች በእንግልጣር ልሳን የተነተኑትን ተከታትየዋለሁ፡፡ በተለይ የውኃ ምህንድስና ባለሙያው ሦስት አንቀጾችን ብቻ መዝዘው ያስደመጡን ትንታኔ እውን ቢሆን ኖሮ፣ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ስረዳ በጣም ነበር  የደነገጥኩት፡፡
በረቂቅ ውሉ ላይ እንደተጠቀሰው፤ ኢትዮጵያ ተስማምታ የውኃ ሙሌቱን ብትገፋበት ኖሮ፣ በግድቡ ውስጥ የሚከማቸው የውኃ መጠን ቅንጣት ከፍ ሳይል እስከ ዓለም ፍጻሜ ሳይሞላ ይቀር እንደነበር ነው ያስረዱን፡፡ ታላቁ የሕዳሴ ግድብም እስከ ምጽዓተ ዓለም ባዶውን ላንቲካ ሆኖ ይቀር ነበር ማለት ነው፡፡
የግድቡ ሙሌት ቀመርና ግድቡ ለመሙላት የሚፈጀውን ከቴክኒክ አንጻር በፊዚክስ ቀመር እስከተሰላ ድረስ አንዱ ባለሙያ ከሌላው ተቀራራቢ የሆነ ግምት ሊኖረው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ይሁንና የእኛዎቹ ተደራዳሪዎች አሜሪካ ያዘገጀችው ረቂቅ ስምምነት እውን ቢሆን ኖሮ፣ ግድቡ በ28 ዓመታት ውስጥ ሊሞላ ይችል ነበር ካሉት ጋር ፈጽሞ አይገናኝም፡፡
አንድ ዓይነት ሙያ ያላቸው የውኃ መሀንዲሶች በዚህ ልክ ያውም ተመሳሳይ የፊዚክስ ቀመር ተጠቅመው ግምታቸው ይህን ያህል የሰማይና የመሬት ያህል የተለያየ ከሆነ ዓባይን በተመለከተ ምንም ውል ከመፈረሙ በፊት ቴክኖክራቶቹ በአደባባይ ተከራክረው አንድ ስምምነት ካልደረሱ አደጋው የከፋ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ዓባይን የሚያክል እሳት ላይ መንግሥት ተጥዶ አንዳች ነገር ትንፍሽ ሳይል የግድቡ መሠረት ከመጣሉም በፊትም ሆነ ከተጣለበት ዕለት ጀምሮ የእኛ መንግሥት ሲደራደር ኖሯል፡፡ ይህ ትክክለኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡  
ከልማድ መውጣት አቀበት ነውና አሁንም ይህ አስተሳሰብ በዶክተር ዐቢይ አህመድ መንግሥት በጣም በመደጋገም ይታያል፡፡ ለእኒህ ወቅቱን ለዋጁ መሪ የምለው ነገር ቢኖር፣ በተለይ በብሔራዊ አጀንዳዎቻችን ላይ በጥቂት ሰዎች ትከሻ ላይ ጥሎ ጉዳዩን ለድርድር መተው እጅግ አደጋ እንደሚያስከትል ልብ ሊሉ የሚገባ መሆኑን ነው፡፡
ከቅን ህሊና የተነሣ ድርድር ተደርጎ ያልተጠበቀና ሊታረም የማይችል ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡  የተለያዩ ምሁራን የሚሰጡትን ግብዓት መሰረት አድርጎ አንድ መቋጫ ላይ መድረስ እንደሚገባ ትምህርት ሆኖን ሊያልፍ ይገባል፤ ጉዳዩ በየጊዜው የሚቀያየሩ አገር የሚገዙ ፓርቲዎች ተራ ጉዳይ አይደለምና፤ ጉዳዩ ገና ወደፊት የሚወለደውን ትውልድ የሚመለከት ነውና፤ ጉዳዩ በር ተዘግቶ በጥቂት ሰዎች ብቻ በድርድር የሚያበቃ ጉዳይ አይደለምና፤ እያንዳንዷ የድርድር ቃል በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ተበጥሮ ተንጠርጥሮ ለውይይት መቅረብ አለበት፡፡ የዓባይ ጉዳይ ከሕዝብ ጋር ምክክር፤ ከምሁራን ጋር ጥልቅ ክርክርና ውይይት የሚደረግበት ብሔራዊ አጀንዳ ነው መሆን ያለበት፡፡ ይህም በቂ ስለማይሆን ዓባይን በሚያክል አጀንዳ በዝግ ተደራድሮ ለመፈራረም ፈጽሞ የመንግሥት መብትና ኃላፊነት ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ መንግሥት በዓባይ ጉዳይ በምንም ነገር ተስማምቶ ውል ከመፈረሙ በፊት ዝርዝር ጉዳዩ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ለውይይት መቅረብ አለበት:: አስፈላጊ ከሆነም እስከ ወሳኔ ሕዘብ (ሪፈረንደም) ድረስ ሕዝቡ ድምጽ ለመስጠት መብት እንዳለው ሊታወቅ ይገባል፡፡  
በረቂቁ ላይ የተጻፈው ሁለተኛው አደገኛ እጅ ጠምዛዥ አንቀጽ፤ በድርቅ ጊዜ ኢትዮጵያ ለግብጽ ማቅረብ ያለባትን የውኃ መጠን የማቅረብ ግዴታ እንዳለባት በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ድርቁ ከፍቶ ከታሰበው በታች የውኃው መጠን ካነሰ ኢትዮጵያ ከየትም ከየትም ብላ ውኃ ሰብስባ መላክ ግዴታዋ ይሆናል፡፡ በገባነው ውል መሠረት የተጠራቀመ ውኃ ካለን ሙልጭ አድርገን እንልካለን፡፡ የተጠራቀመ ውኃ ከሌለ ደግሞ ከሌሎች ወንዞች እየጠለፍንም ቢሆን ለግብጽ ውኃ ማቅረብ አለብን ማለት ነው፡፡  
ሦስተኛው ደግሞ ወደ ዓባይ የሚፈስ ውኃ ልኬት እነርሱ በሚፈልጉት ሞዳሊቲ ኢትዮጵያ ለግብጽ ሪፖርት ታደርጋለች:: ይህም ከየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር ወደ ዓባይ መፍሰስ የሚገባው ገባር ወንዝ ሁሉ መጠኑን እየለካን ለግብጾች ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ እንደማስበው ውሉን ያረቀቁት አሜሪካዊያን ሳይሆኑ ግብጾች ናቸው፤ የተለየ የሚያደርገው በአሜሪካኖቹ እጅ መቅረቡ ብቻ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ብዙኃን መገናኛዎች ተደራሽ መሆን የሚችሉ ኢትዮጵያዊያን፤ ኢትዮጵያ ግድብ የመገደብ መብቷ ተፈጥሮአዊ መሆኑን፤ ግድቡንም ስትገድብ ጉልህ ጉዳት የማድረስ ፍላጎት የሌላት መሆኑን፤ ግድቡ ኤሌክትሪክ አመንጭቶ የአገራችንን ኢኮኖሚ የሚያሳደግ መሆኑን፤ የሕዝቡ ኑሮ የሚሻሻል መሆኑን፤ ግድቡ የሚያመነጨው ከፍተኛ የውኃ መጠን ተርባይኑን ከመታ በኋላ ዓመቱን ሙሉ ወደ ጎረቤት አገራት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚፈስ መሆኑን፤ በዚሀም የታችኛው ተፋሰስ አገራት ተጠቃሚዎች መሆኑን፤ የሚመረተውም ኤሌክትሪክ ለሱዳንና ለግብጽ ሚጠቅም መሆኑን፤ እየተነነተኑ ለዓለም ሕዝብ ቢያስረዱ ጥቅሙ የሁሉም ይሆናል፡፡ ሁለቱ አገሮች ለጋራ ጥቅም መቆም እንዳለባቸው፤ አልሲሲ ፊት ቀርባ በኤሌክትሪክ እጥረት የኢትዮጵያ ሴቶችን ሥቃይ፤ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን መከራ የግብጽ ሕዝብ በቀጥታ በሚሰማው የብዙሀን መገናኛ አንዲት ሴት ኢትዮጵዊት ያደረገችው ንግግር በትክክለኛው ቦታ የተደረገ ትልቅ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ነው፡፡
ግብጾች ድርድሩ ሳይቋጭ ቢቀር የሚደርስባቸው አንዳች ነገር የለም:: ከስምምነት በፊት ሙሌቱን ብንጀምር የሚደርስባቸው ቅንጣት ታክል ጉዳት የለም፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ከኤሌክትሪክ ግድብ በቀር ለሌላ አግልገሎት የሚውል ግድብ እንዳትሰራ ስለሆነ የግብጽ የመጨረሻ ግብ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ትልቅ ስጋት መሆኗን ለማሳየት እየጣረች ነው፡፡ ተመድ ጽ/ቤት እስከ ጸጥታው ምክር ቤት በማቅረብ የሄዱበት መንገድ በዚሁ የስጋት መንፈስ ታስረን እንድንኖር አስበውበት ያዘጋጁት ስልታዊ ወጥመድ ነው፡፡   
ታላቁ ህዳሴ ግድብ በስትራቴጂ ደረጃ ለግብጽ ፈጽሞ ስጋት አይሆንም፡፡ ዓባይ ታቆረም አልታቆረም  ጠብታ ሊትር ሳያጎድል ኤሌክትሪክ ካመነጨ በኋላ ለሽህ ዘመናት እንዳደረገው አሁንም ወደፊትም ለዘላለሙ ወደ ግብጽ ይፈሳል፡፡ “ግብጾች አንድ ሊትር ውኃ አናስነካም” የሚል ፖሊሲ በግልጽ እያራመዱ “እኛ ጉልህ ጉዳት አናደርስም” ብለን ለግብጾች ዘብ ከቆምን ለእኛ ትልቅ የዲፕሎማሲ ውድቀት እንዳይሆን ስጋቱ አለኝ፡፡
ለድርድሩ የጀርባ አጥንት የሆነው መደበኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ተጠናክሮ የመቀጠሉ ስራ አጠያያቂ አይሆንም:: ይህንን ታላቅ ተጋድሎ የሚያደርጉ ዓረብኛ ተናጋሪ ወጣቶች ከመንግሥት የተለየ ድጋፍ ሳይደረግላቸው በራሳቸው ጊዜና በራሳቸው ወጪ ለዚህ የተቀደሰ ታላቅ ሥራ መትጋታቸው ያስደስታል፤ ትውልዱንም በደምሳሳው ከመውቀስ ያድነናል:: የኢትዮጵያ ውጭ ፖሊሲ ቀዳሚ አጀንዳ የሆነው የአፍሪካ አገሮች ጉዳይ ላይም የተጠናከረ ስራ ለመስራት ስዋህሊ፤ እንግልጣርና (እንግሊዝ) አፍርንጊ (ፈረንሳይ) ቋንቋ የሚናገሩ ሳተና ወጣቶች የሚመሩት የብዙሀን መገናኛ በተለይ የሳተላይት ጣቢያ ቢኖረንና አፍሪካዊያን ወንድሞቻችንን ብናሳትፍበት ትልቅ ውጤት እናገኝበታል የሚል እምነት አለን፡፡ሰላም፡፡


Read 1853 times