Monday, 27 July 2020 00:00

ሐምሌ፤ የክረምት ንጉሥ

Written by  አዲሱ ዘገየ
Rate this item
(0 votes)

 "በ1962 ባስራ አንደኛው የሐምሌ ወር ላይ ግብጽ ለ11 ዓመታት (10 ዓመት የሚሉ ምንጮችም አጋጥመውኛል) ያህል ስትገነባው የነበረውን የአስዋን ግድብ ፍጻሜ ያበሠረችበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ41 ዓመታት በኋላ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጀመረች፡፡ ዘጠኝ ዓመት ከአራት ወራት በኋላ የግድቡን የውሃ ሙሌት ለመጀመር በኢትዮጵያ የሐምሌ ወር ተመረጠ፡፡--"

ሐምሌ የኢትዮጵያ አስራ አንደኛ ወር ናት፤ ይህቺውም ለውስጣዊ አመለካከት አጽንዖት የሚሰጥባት ቅድስት፣ ምርጥ፣ ዕድለኛ ቁጥር መሆኗ ይታመንባታል፡፡ በዚህ የተነሳ ሕይወትን በአዲስ የተነቃቃ ስሜት መጀመር ማለትም ዘርን መዝራት፣ ወተት መስጠት፣ ልምላሜ ማሳየት፣ አዲስ የበጀት ዓመት ወዘተ ታመለክታለች፡፡ አስራ አንድ ቁጥር በሥነ-ቀመር መፈክራን ዐቢይ/ሁለገብ ቁጥር ማለት ናት፡፡ ተምሳሌታዊነቷም እምነት/ሃይማኖት ባንድ በኩል፣ ተፈጥሯዊ ተውኅቦ/ደመነፍስ/ቀልብ (በእንግሊዝኛ Faith and  Instinct ይባላሉ) በሌላ በኩል ጸንተው የሚታዩባት አጋጣሚ ትወክላለች፡፡ ባስራ አንደኛዋ ሰዓት ማለት ማለቂያ፣ ማሰሻ፣ መደምደሚያ፣ መቋጫ በተቃረበባት የመጨረሻ ሰዓት የሚከናወን ድርጊትንና አጋጣሚን ትገልጻለች፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የፊደል ተራ ቅደም ተከተል መሠረት አስራ አንደኛዋ ፊደል K ስትሆን፣ ላዕላይ ፍቺዋ (ኪንግ) ንጉሥ፣ ሽህ ቤት (ሻለቃነት)፣ ኪሎ ሜትር፣ ኪሎ ባይት፣ ካራት ወዘተ ትወክላለች፡፡ በዕብራይስጥና ግእዝ ቋንቋዎች “በአበገደ” ፊደል ቅደም ተከተል አስራ አንደኛዋ ፊደል ካፍ ተብላ ትጠራለች:: ትርጓሜዋም ውስጥ እጅ መስጫ፣ ማቀበያ ማለት ስትሆን፣ ለእግር፣ ለማንኪያና ለአካፋ ወዘተ በተመሳሳይ ታገለግላለች፡፡ ካፍ እጅ በጅ መስጠት፣ ማቀበል፣ ማስያዝ፣ ማስጨበጥ፣ ማቅረብና ማስረከብ የሚሉ ፍቺዎች አላት፡፡
የሐምሌ ፍቺ ባንድ ወገን ባለ ቅጠል ቅጠላም፣ ባለ ልምላሜ ወር ማለት ነው፡፡ ቅጠል ቅጠላ ቅጠሎች፣ የሣር ዘሮች፣ የተክልና ዕፅዋት ቡቃያዎች፣ ወዘተ በየስማቸውና በያይነታቸው የሚበሉና የማይበሉትን በማካተት የምትይዝ ወር ስያሜ ናት፡፡ ሥንቆ የተሰኘ በየቦታው የሚበቅል ለምግብነት የሚያገለግል ተክል የሐምሌ ፍሬ ነው፡፡ ይህ ቅጠል ክረምትን የሚያዛልቅ የክፉ ቀን ደራሽ ምግብ ነው፤ የክረምት ሥንቅ ይሉታል፡፡ ከቅመማት መካከል ጎመን፣ ኑግና ተልባ የሚደርሱባት ወር ሐምሌ ናት፡፡ ”በሚያዝያ ጎመን የዘራ ክረምቱን ሁሉ በላ” የሚለው ምሳሌ በሀገሬው ልማድ፤ ክፉን ቀን ለመዝለቅ ከሚያስችሉ ቅድመ-ዝግጅቶች መካከል ጎመን መዝራት አንዱ መላ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሐምሌ በሥንቆና የጎመን ቅጠላ ቅጠሎች አረንጓዴ ልምላሜ ታሳያለች፡፡  
ሐምሌ የሚለውን ቃል ያስገኘው የግእዝ ቃል በሌሎች የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎች የተወሰነ የቅርጽ ለውጥ እያሳየ ባገልግሎት ይውላል፡፡ ቃሉ በግእዝ፣ በትግረ፣ በትግርኛ፣ በአርጎብኛ፣ በክስታንኛ፣ በሙኸር፣ በስልጢና በወለኔ፣ በቸሀና በጌይታ ልሣናት ተቀራራቢ ስያሜ እንዳለው በጥናቶች ይጠቀሳል፡፡ በትግርኛና በአርጎብኛ ቋንቋዎች ደግሞ ሐምል ጎመን ማለት ነው፡፡ ይህም በክረምት ምክንያት ምድር አረንጓዴ የምትሆንበትን የልምላሜ ወቅት አመልካች ነው፡፡ በነገሬ ላይ የሐምሌ መጋቢ መንታ ከዋክብት የቀለማት ምርጫ ነጭ፣ ብርቱካናማ፣ አረንጓዴ/ጎመኔ/ቅጠልያ ወርቃማና ቀይ ሲሆኑ ውሃማ፣ ደመናማ፣ መብረቃማና ለምለም መስክን፣ ያመለክታሉ፡፡ ወርቃማው ቀለም ደግሞ እዩኝ እዩኝ ባይነትን፣ የማዕረግ ልዕልናን፣ አንጸባራቂ ድልን፣ ግርማ ሞገሳማነትን፣ ውድ፣ ምርጥ፣ የተለየ መሆንን፣ የመሪነት ሚና መቀዳጀትን ወዘተ ተምሳሌት ያደርጋል፡፡
ሐምሌን ካወሳን ዘንድ የክረምት ወቅትን ዐውድ መተንተን ተገቢ ነው፡፡ በሰኔ 26 በኩል ወደ ክረምት ሽግግር ተደርጓል፡፡ ስለዚህ የክረምት ወቅት መጋቢ ኮከብ ውሃ ነው፡፡ የውሃ ሥልጣንና አዛዥነት በያንዳንዱ የክረምት ወራት ይናኛል፡፡ እያንዳንዱን ወራት እየተፈራረቁ የሚመግቡ የወር ተረኛ ከዋክብት አሏቸው፡፡ በበጋ እሞኝ ቤት ተንጋጋ፣ በክረምት በቤትህ ተከተት የሚለው ምሳሌ የሚሰራው ለከተሜው ነዋሪና ፍየሎች ነው፡፡ ከከተሜውም ለተማሪና አስተማሪ፣ ለነገር አባቶች/እናቶች፣ ለእንደራሴዎች፣ ለወታደሮች የሥራ እንቅስቃሴ የማትመች ጊዜ ሐምሌ ናት፤ የገጠሩ አርሶ አደር እቤቱ የሚከተትበት ወር ሐምሌ አይደለችምና:: ገበሬው “በቤቴ መከተት አለብኝ” ቢል ደግሞ በቤቱ ይልሰውና ይቀምሰው አያገኝም፡፡  በሐምሌ ዋዜማ አራሹ ገበሬ፤
በርዬ ግፋ እንጂ ገፋ ገፋ አድርገው
ቀኑ እየመሸ ነው ሐምሌ እየገባ ነው፡፡ (የሕዝብ ሥነቃል)
የሚል ማነቃቂያ ጥሪ ለበሬው ያቀርባል:: ይኸውም ብርሃናማ የነበሩ የሰኔ ማሰሻ ቀናት አልቀው ምሽቱ መግባቱን፣ ጎን ለጎንም ጨለማማዋ ወርኀ ሐምሌ መባቷን ያሳያል:: ቀኑ አብቅቶ ወደ ሌሊት መሻገርና ብርሃናማ የበጋ ወራት አብቅተው የወር ሌሊቷ ሐምሌ  ልትብት እንደሆነ በስንኞቹ ተመላክቷል፡፡ በገበሬው ቤት ሐምሌ ከልምላሜ ባሻገር የጎተራ መራቆትን፣ የማዕድ መሳሳትን፣ ለእንቅስቃሴ አለመመቸትን፣ ውሽንፍር፣ በረዶ፣ ጎርፍ፣ መብረቅ እየተፈራረቁ በሰውና በዓለም/የብስ ላይ ምቾት ማሳጣታቸውን ይገልጻል፡፡ ለዚህ ይመስላል ከቤት ከመከተት ይልቅ በክረምት በእርሻ ማሳዎች አቅራቢያ ጊዜያዊ መክረሚያ ቅልስ ጎጆን፣ መስራት የሚመከረው፡፡ ይህቺ ጊዜያዊ ቤት ክረምት እስኪነጋ ድረስ ታቆያለች፤ ስሟም አካርሚኝ ነው፡፡ ክረምትን መውጫ (መወጫም ቢሉ) በቀላሉ የተሰራች የችግር ቀናት መጠለያ ናት፡፡
ጎመን የሐምሌ ምርት በመሆኑ ለክረምት ሁነኛ ፋይዳ አለው፡፡ ጎመን በተለያዩ የሀገሪቱ ቦታዎች ለልዩ ልዩ ማኅበረ-ባህላዊ ፋይዳዎች ይመረጣል፡፡ ለምሳሌ ያህል በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና በሌሎች ስፍራዎች 12ቱን ወራት በሙሉ ጎመን የማይጠፋባቸው ቦታዎች አሉ፤ በነዚህም ጎመን ከችግር አውጭነት የተለየ ሚና አለው:: በኒህ ቦታዎች ጎመን ለምግብ ግብዓትነት ሲመረጥ በዘወትር ማዕድ ላይ ጣዕም ለማከል፣ የተመጣጠኑ የምግብ ንጥረነገሮችን/ግብዓቶችን ለማካተት፣ ከማንነት ጋር በተሳሰረ የባህል ዕሴት ለመድመቅ፣ ከሥጋ ብስና ጎመን በጤናን ከመሻት በፊት ጎመንን ለጤና በመምረጥና በመሳሰሉት ምክንያቶች ነው፡፡ ጎመንን ለችግር ዘመን መሻገሪያ መራጩ ክፍል አብዛኛውን ጊዜ ከእጅ ወደ አፍ የሚጎርስ፣ በክረምት ዝናብ ላይ የተወሰነ፣ አማራጭ የውሃ ሃብት የሌለው አርሶ አደር ክፍል ነው፡፡   
ሐምሌና የሀገሬ አርሶ አደር ተዋደው፣ ተፈላልገው፣ ተመራርጠውና ተቻችለው ይኖራሉ፡፡ አንጋፋው የኢትዮጵያ ባህል ተመራማሪ ካሕሳይ ገ/እግዚአብሔር፤ይህን ዐውድ አሳምረው ይገልጹታል (ነፍስ ኄር!)፡፡ ፍየልና የከተማ ሰው ዝናብና ጭቃ አይወድም!...ገበሬ ግን በሐምሌ ዝናብን ብቻ ሳይሆን ጭቃንም አይፈራም፤ ባይሆን ጭቃን ያፈቅራል ቢባል ይሻላል፡፡ “የሐምሌ ጭቃ፣ ቅቤ ለጋ” ናትና፡፡ በሐምሌ የገበሬው ስራ ይበዛል፤ ዝናቡም ረሃቡም ያይላል፡፡ ስለሆነም በገበሬው ቤት ሐምሌ እንግዳ ባይመጣበት ይሻላል፡፡
ገበሬው የእንግዳ ማስተናገጃ ማዕድ ብቻ ሳይሆን እንግዳውን የሚንከባከብበት ጊዜ የለውም፡፡ ሐምሌና ሰኔ የዘር ጊዜያት ናቸው:: ዘርዕ ደግሞ ሸነ በሚል ይገለጻል፡፡ በዚህ ጊዜ ከቤት እንስሳት መካከል ላሞች ወልደው ወተታቸውን የሚሰጡበት በመሆኑ የምግብ እጥረትን ለመክላት ተፈጥሮ የዘየደችው መላ ወተትን አስገኝቷል፡፡ በነገራችን ላይ የኅልውና ምንጮች የሆኑ እንደ ወተት/ሐሊብ ወይም ትነት/እንፋሎት/ላብ፣ ዘር/ሽንት፣ ዝናም/ውሃ ከምግብ ግብዓትነት አልፈው ለፈውስ ይመረጣሉ:: ለአብነት ያህል የአህያ ወተት ለሳል (በዘመነ ኮሮና እንደ አንድ መፍትሔ ሊፈተን የሚገባው ባህላዊ የሕክምና ጥበብ ነው)፣ የግመል ወተት ለሆድ፣ የቅንቦ (የቆላ ተክል) ወተት ለመጋኛ ፍቱን መድኃኒቶች ናቸው፡፡
ሐምሌ ወተታም ወር ናት፡፡ የላም ወተትን ጨምሮ በተልባና በኑግ የታሸ አነባብሮ ቂጣ በተለይ ከሐምሌ አቦ ጀምሮ፣ ጎመንና ድንች በአብዛኛው ለምግብነት ይመረጣሉ፡፡ ሐምሌ ላዩና ታቹ የውሃ ምንጭ ነው፡፡ ስለዚህ ሐምሌ የክረምት ወርኀ ንጉሥ (ንግሥናዋን በኮከቧ በኩል ልትጨብጥ ትችላለች) ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ ንግሥቷ ደግሞ ቀጣይዋ ነሐሴ ናት፡፡ የሐምሌ ደመና ታማኝ ናት፤ ሳይዘንብባት አትውልም፡፡ ሐምሌን አጥፊና ጠፊ የተፈጥሮ አካላት ለምሳሌ እባብና እንቁራሪት ይወዳጁባታል፡፡ ምክንያቱም እባብ የመርዝ መሳሪያውን በውሃ ዘመን ፈትቶ ያስቀምጣልና:: በተቃራኒው ዓሳና ውሃ የሚጣሉባት፣ ወይም ጎርፍና ማዕበል የሚበዛባት ሐምሌ ናት፡፡ ዝናብ መዝነብ አለመዝነቡን ከቤት እንስሳት አኳኋን መገመት እንደሚቻል የሚናገሩ ሀገርበቀል ዕውቀቶች አሉ፤ ለምሳሌ አህያ ዝናብ መዝነብን ስትጠቁም፣ ወጨፏማ ዝናብ በየትኛው አቅጣጫ እንደሚነፍስ፣ እንደሚወነጨፍ በወፎች ቤት አሠራር መገመት ይቻላል፡፡ አእዋፋቱ ቤታቸውን ሲሰሩ መግቢያ በራቸው ከሚገኝበት በተቃራኒ አቅጣጫ ውሽንፍሩ ይመጣል ማለት ነው፡፡
መስከረም ጠብቶ ይላል ወታደር፣
ዘጠኝ ወር በጋ የት ሄዶ ነበር? (የሕዝብ ሥነቃል)
መስከረም ሲ/ጠባ ሲባል ከመስከረም በፊት ያሉ የክረምት ሦስት ወራት ደመናማና ጥላሸታማ፣ መልካቸውን፣ ከጸሐይ ብርሃንና ሙቀት የተራቆቱበትን የቅዝቃዜ ሁኔታ ያመለክታል፡፡ አራቱን ወቅቶች ወደ መንታነት አጥፈው ከሚያሰሉ የሀገሬው ልማዶች አንዱ በስንኞቹ ተጠቅሷል፡፡ ዘጠኝ ወራትን በጋ፣ ሶስቱን ደግሞ ክረምት ብሎ የሚጠራ ያልተማረ/ጨዋ ወታደር አመለካከት ሊባል ሁሉ የሚያስችል አመለካከት በሀገሬው ሰፍኗል፡፡
ውሃ ካራቱ የዘፍጥረት አሃዶች አንዷ ስትሆን በፍጥረታት አካላት ሰፊውን ክፍል ትሸፍናለች፡፡ ባንድ ሰው ገላና በዓለም 2/3ኛውን ወይም 66.6 በመቶ ያህል ውሃ መልታለች:: በነገራችን ላይ ባንድ ባለሙሉ አካል ጎልማሳ ላይ 666 የደም ሥሮች እንዳሉ የሚያስረዱ ምንጮች አሉና በዚህ መሠረት ውሃ በሰውና ዓለም ሥጋዊና መንፈሳዊ ርእዮተዓለም ውስጥ የ666ን ሥራ ትሰራለች ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ የሰውና የዓለም ልምላሜ፣ ርጥበት፣ ወዝ፣ ሥረ-መሠረት ውሃ ናት፡፡ የምድር አላባዎችን/ሀብቶችን አዋላይና አጓጓዥ ውሃ ናት፡፡ የምግብ ግብዓቶችን በሰውነት ውስጥ ማዋሐድና ማንሸራሸር፣ ከፊሉን ለግንባታ፤ ከፊሉን በዕዳሪነት ማስወገድ፣ ውስጣዊና ውጫዊ ዕድፍን፣ መርዝን፣ አመለካከትን/አስተሳሰብን ማጽዳትና ማጥራት ወዘተ በውሃ አማካይነት ይተገበራሉ፡፡ ውሃ የተለየ ሕብረ-ቀለም፣ ጣዕምና መዓዛ የላትም፤ ግን ንጽሕና ጽሩይነት ባህርይዋ ነው፡፡ ውሃ ከአቻ አሃዶች ጋር ያላት ዝምድና ከመሬት ጋር በርጥበት፣ ከእሳት ጋር በሙቀት/በብርሃማነት፣ ከነፋስ ጋር በቀዝቃዛነት/በመልክ አልባነት ትስማማለች፡፡ ይህቺ አሃድ የዓለምን ፍጥረት ከማዋሐድ ይልቅ ዘረኛነት የተጸናወታት ቢሆን ኖሮ፣ ጸሊምነቷ የጥቁር ሰው ወገን አያስብላትም?
ሐምሌ የሰኔ ማግስት/ታናሽ እህቷ ስትሆን፣ ማዶ ካሉ አቻዎቿ መካከል ከታኅሣሥ/ታሣሥ ጋር ጥብቅ ዝምድና አላት፡፡ ይኸውም ሐምሌ 1 እና ታኅሣሥ 1 ዕለተ ረቡዕ ላይ መባቻቸውን ማድረጋቸው አንዱ ሲሆን፣ ዝምድናቸው በመባቻ ብቻ አያበቃም፡፡ ሁሉም ወርኀዊ ቀናት በተመሳሳይ ዕለት ይውሉባቸዋል እንጂ:: ታሣሥ አራተኛ ወር ናት፤ በአራተኛዋ ወር በኩል ወደ አራተኛዋ ዕለተ ፍጥረት/ረቡዕ ወደ ኋላ በመመለስ የተገኙ ፍጥረታትን ብንመረምር የምናገኛቸው ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትን ነው:: በአንጻሩ ሐምሌ ግን 4 + 7 = 11 ናት፤ ወርኀ-ታሣሥ አብቅቶ አንድ ሳምንት (ሰባት ቀናት/ወራት) ከተቆጠሩ በኋላ ሐምሌ ባተች:: ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ወራት የሐዋርያትና የበቁ የእምነት አባቶች (ጳጳሳት፣ በኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.) ክብረ በዓላትን በብዛት ከሌሎች ወራት በተለየ፣ መያዛቸው ለዝምድናቸው አብነት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የታሣሥና ሐምሌ ዝምድና በሚከተለው መልኩ ሰፍሯል፡፡
ሐምሌ 2፣ ታዲዮስ፣ 3፣ የቀዳማዊ ምኒልክ ዜና ረፍት፣ 5፣ የ12ቱ ሐዋርያት ጉባኤ፣ ጴጥሮስ ወጳውሎስ፣ 72ቱ አርድዕት፣ የአፄ ዮሐንስ ልደት፣ የአፄ ዮሐንስ የዓድዋ ድል (ተ/ጊዮርጊስን)፣ የአቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክነት ሹመት (1984)፤ 6፣ ዕርገተ ዕዝራ፣ 7፣ የአብርሃሙ ሥላሴ እንግድነት ሲከበርባት፣ በ1971 ደግሞ አቡነ ቴዎፍሎስ በወታደራዊው የደርግ መንግሥት የተገደሉበት ቀን ናት፡፡ ሐምሌ 10፣ ናትናኤል/ስምዖን፣ 12፣ ቅዱስ ሚካኤል፣ 13፣ የጻድቁ ዮሐንስ ፋሲል ረፍት፣ 17፣ ዮናስ ከሶስት ቀናት ያሣ አንበሪ ሆድ ቆይቶ የወጣበት፣ 18 ያዕቆብ የጌታ ወንድም፣ 19፣ መጋቤ ሐዲስ ገብርኤል ቂርቆስና ኢየሉጣን ያዳነበት፣ 20፣ ማርያም በ80 ቀኗ ቤተመቅደስ የገባችበት፣ 22፣ አቡነ ጴጥሮስ በሰማዕትነት የወደቁበት፣ 25፣ ቅዱስ መርቆሬዎስ፣ ዕርገተ ሄኖክ (የቀድሞው ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ከስደት መልስ ዳግም በመንበራቸው ላይ የተቀመጡበት፣ ከ28 ዓመታት የስደት ሕይወት በኋላ)፤ 26፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም እንዲሁም አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን (አባ ፍሬምናጦስ) ዜና ረፍት ይከበርባቸዋል፡፡
በታሣሥ አቻ ወር ደግሞ 3፣ የማርያም ቤተመቅደስ መግባት (ከሐምሌ 20 አቻ)፣ የዳግማዊ ምኒልክ ዜና ረፍት (ከሐምሌ 3 አቻ)፣ 4፣ እንድርያስ (ከሐምሌ 2፣ 5፣ 10፣ 18፣ አቻ)፤ 5፣ ጀኔራል መንግሥቱና ገርማሜ ነዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ያደረጉበት (ከሐምሌ 16 የቀ.ኃ.ሥ ልደት አቻ)፣ 7፣ መጋቤ ብሉይ ክፍሌ በፋሽስት የተገደሉበት (ከሐምሌ 7፣ 22 አቻ)፣ 10፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መከፈት በ71 ተማሪዎች/1943 (ከሐምሌ 5ቱ የ72 ተማሪዎች አቻ)፣ 12፣ ዳግማዊ ቂርቆስ (ከሐምሌ 12 እና 19 አቻ) 18፣ ሥርዓተ-ሲመት አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን (ከሐምሌ 26 አቻ)፣ 19፣ በዓለ ቅዱስ ገብርኤል፣ (ከሐምሌ 19 አቻ)፣ 21 በርናባስ (ከሐምሌ 2፣ 5፣ 10፣ 18፣ አቻ)፣ 28፣ አብርሃም፣ ይስሃቅ፣ ያዕቆብ (ከሐምሌ 7ቱ የአብርሃሙ ሥላሴ እና 26ቱ አቻ) በዓላቶቹ መከበራቸው የወራቱን የዝምድና መልኮች ተመጋጋቢነት፣ ተወራራሽነት፣ ተነጻጻሪነት አስተሳስሮ ያሳያል፡፡
በረዶን ለመከላከል የሚረዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ሐምሌ ላይ ይከወናሉ፤ ከእነዚህ አንዱ ጸሎተ በረድ ይሰኛል፤ ጸሎተ በረድ የበረዶ መከላከያ ጸሎት ሲሆን፣ በክረምት ወራት በረዶ ዘንሞ የአርሶ አደሮችን አዝመራ እንዳያጠፋባቸው በሐምሌ 5 ወይም ሐምሌ 7 ቀን የሚደረግ የመከላከያ ጸሎት ሥርዓት ነው:: ይህ ከታሣሥ 5ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማክሸፊያ ተግባር ጋር አይዛመድም?
በመቀጠል ሐምሌን በኮከቦቿ ምሪት እንቃኛት፡፡ የወርኀ ሐምሌን መጋቢ ከዋክብት በከፊል የሰኔ ወር ማሰሻና የሐምሌ መጀመሪያ ቀናት መጋቢዋ እንስት፣ መሪ ኮከብ ስትሆን ምልክቷ a፣ በባህር ማዶ ስሟ ካንሰር (ባህርይዋ ውሃ) አንጻር፣ በከፊል ምልክቱ b፣ ባህርይው ቋሚ በባህር ማዶኛ ሊዮ (ባህርይው እሳት) መንታ የግብር ሚናዎች ማውሳት የሐምሌን ዐውዶች ለመገንዘብ ይረዳል፡፡ ሸርጣን በሰኔ መደብ እንደተገለጸች ሁሉ ለጥፋት በተሳለ ግብሯ መታወቋ ነገረ ሰይጣንነቷን ይገልጻል:: ሸርጣን/ጉርምጥ የተሰኘችው መኖሪያዋ ውሃ የሆነላት ፍጥረት የማይድን የቆላ ነቀርሣ በሽታ መንስኤ ናት፡፡ ሸርጣን ውሃ ማለት የምንጭ ውሃ ማለት ናት፡፡  ከሸርጣን አዎንታዊ የግብር መገለጫዎች መካከል በጥቂት ነገር መነዋወጥ፣ መደነቅ፣ ስሱና ጥልቅ ስሜት፣ ቀልብንና ሕልምን አማኝነት፣ እግረ ርጥብነት፣ ራስን ለማዳን መታተር ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከአሉታዊዎቹ ደግሞ ወላዋይነት፣ ተለዋዋጭነት፣ የማትጨበጥነት፣ ሽንገላ/ድለላ መራጭነት፣ ወረተኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ ስለዚህ ሐምሌን በሸርጣን ከላይና ከታች የውሃ ምንጮች ከፋፍቶ ማጉረፍ ማለት ነው፡፡ ይህም ውሃን በውሃ መመገብ፣ ማቅጠን፣ መለሞጥ (ወጥ ማድረግ)፣ ማቀዝቀዝ፣ ማዋሐድ (መልክ፣ ቃና፣ መዓዛ፣ ጣዕም አልባ ማድረግ) የብስን፣ ገላን፣ አዝርዕትን ማለምለም፤ ማዋለል፣ ማውዛት፣ ማለት ነው፡፡ የካንሰር ኮከብ ገዥዋ ጨረቃ ናት፡፡ ስለዚህ ከጨረቃ በሚወረስ ተመሳስሎ ምላት ጉድለትና የባህርይ መለዋወጥ እንዲታይ ታደርጋለች፡፡ እንስቶቹ ካንሰር እና ጨረቃ የወላጅነት/እናትነት፣ የደም ዝውውር ዑደት፣ እና የምግብ ማንሸራሸሪያ የሆድ ዕቃ አካላትን በበላይነት ትመራለች፤ ትቆጣጠርማለች፡፡ ሴቷ የምንጭ ውሃ በንቁ የማስታወስ ችሎታዋ ስትታወቅ፣ ማዕበል፣ ሞገድና የደም ዝውውር ሂደት ተቆጣጣሪ ናት፡፡
ሁለተኛውን ፈረቃ የሚመግበው የሐምሌ ኮከብ በሀገሬው አሰድ፣ በባህር ማዶ ሊዮ ሲሰኝ የመብረቅ እሳትን፣ በፀሐይ (ገዥዋ ፕላኔት ፀሐይ ናትና) እና በጫካው ንጉሥ አንበሳ ይመስላል። ይህን ኮከብ የታደለ ግለሰብ የፊት ቅርጽ/ቢጋር ያንበሳን ፊት የሚመስል እና በደልዳላ ቁመናው ይለያል፡፡ ከእናቱ ማኅፀን የተመረጠ፣ ትልቅ የዓይን ኃይል ያለው፣ ቋሚ የማይናወጽ፣ ጠላቶቹ ሲያዩት የሚፈሩት፣ የማይሸነፍ ባህርይ ነው፡፡ ሐምሌን በአሰድ ደግሞ ውሃን፣ ደምን፣ የብስን፣ ገላን በእሳት ማፍላት/ማሞቅ፤ በመብረቅ ማረስ/መጥበስ፤ ቅዝቃዜንና በረዷማ ገጽን ማሞቅ፣ ማትነን፣ ማቅለጥ፤ አልረጋ ያለችን ዋላይ መሬት ማርጋት፣ ይከወንበታል፡፡ እሳት ውሃን አድራቂና አሟጣጭ ነው፡፡ ሐምሌ ውሃ በውሃ ተጥለቅልቃ የምትታይበት ወር ብትሆንም፣ አንዳንዴ ክፉ የውሃ ጥም ሊገጥም ይችላል፡፡ ያባይን ልጅ ውሃ ሲጠማት ማየት የተለመደ ነው፡፡ እሾህን በሾህ እንዲሉ ክረምትና ሐምሌ ገብቶባቸው በረሃብ ሰቆቃ የረገፉ አፍሪካውያንን ለመርዳት የሚያግዝ የሙዚቃ ዝግጅት፣ የዓለም ታዋቂ ሙዚቀኞች በ1977 አካሂደው ከ30 ሚሊዮን  ፓውንድ በላይ መሰብሰብ የተቻለው በሐምሌ ነበር፡፡
ይቀጥላል

Read 1999 times