Print this page
Saturday, 25 July 2020 15:31

‘መሳም’ ወይስ ‘መንክስ’? እሱ ላይ ነው ጥያቄው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እኔው ልጅህ ነኝ፣ ምስኪኑ ሀበሻ፡፡
አንድዬ፡— መጣህ! መጀመሪያ እንደ በቀደሙ ተሰልፋችሁ ነው የመጣችሁት?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ፣ ብቻዬን ነኝ::
አንድዬ፡— ይሻላል፣ ይሻላል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ሰብሰብ ብለን መምጣታችንን ጠላኸው እንዴ!
አንድዬ፡— አልወጣኝም፡፡ አሁን እንደሱ የሚል ነገር ወጣኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አይ ድንገት እረብሸንህ እንደሆነ ብዬ ነው፡፡
አንድዬ፡— ዛሬ ደግሞ ጭራሽ ምርመራ ልታደርግልኝ ነው እንዴ የመጣኸው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ፣ ምን ቁርጥ አድርጎኝ!
አንድዬ፡— እኔ አንዳንዴ ስለ እናንተ ሳስብ ምን ይመጣብኛል መሰለህ…እነኚህ ሰዎች ብለው፣ ብለው እኔንም ማን መረጠውና ነው እዛ ላይ የተቀመጠው ይሉኝ ይሆን የሚል ሀሳብ ይመጣብኛል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ…ይኸው የዛሬው ቀን…
አንድዬ፡— ግዴለም፣ መሀላ አያስፈልግም፡፡ ደግሞም አዎ፣ እንደዛ ብትሉኝም እንዳያያዛችሁ አይገርመኝም:: አሁንማ የእናንተ አፈጣጠር ላይ የተሳሳትኩት ነገር ይኖር ይሆን እላለሁ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ይሄን ያህል አንድዬ! ይሄን ያህል ግራ አጋብተንሀል ማለት ነው?
አንድዬ፡— ግራ መጋባት በለው፤ ጎሽ አሁንስ ቀና፣ ከፍ ከፍ ሊሉ ነው ስል መልሳችሁ ትንሸራተታላችሁ፤ አሁንስ ብድግ አሉ፣ በሁለት እግራቸው ሊቆሙ ነው ስል መልሳችሁ ሸብረክ ትላላችሁ፤ ልትሳሳሙ ነው ስል ጭርሱን ትዘላዘላላችሁ:: እኔ ግራ ያልገባኝ ማን ግራ ይግባው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡—  ኸረ አንድዬ ይህን ያህል ተስፋ አትቁረጥብን…
አንድዬ፡— ተስፋ፣ ተስፋ መቁረጥ አልከው! ተስፋ ብቆርጥ ኖሮማ አይደለም ደጄ ድረስ ልትመጣ፤ በበሬም አታልፍም ነበር!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ዛሬስ ዓይኔንም ማየት የጠላህ ነው የሚመስለው:: ገና ብቅ ከማለቴ እኮ ተቆጣኸኝ፡፡
አንድዬ፡— አየህ፣ አየህ አይደል፡፡ የእናንተ ነገር እንዲህ ነው፡፡ አሁን እኔ ላይ ምን የሚሉት ቁጣ አየህብኝ! የተሰማኝን መናገር ቁጣ ሆነና አረፈው!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አይ አንድዬ አነጋገርህ ጠንከር አለብኝ፡፡
አንድዬ፡— አነጋገሬ ጠንከር ስላለበህ ቁጣ ብለህ ተረጎምከው? አየህ አንዱ፣ እንደውም ትልቁ ችግራችሁ ይኸው ነው:: ሁሉንም ነገር በተነገረው መልኩ ሳይሆን እናንተ መስማት በምትፈልጉት መልኩ ነው የምትተረጉሙት:: ዝም ብዬ ስታዘባችሁ ግርም ይለኛል፡፡ “አፈር ልሁንልህ” የተባላችሁትን “አፈር ያስበላህ፣” ብላችሁ እየተረጎማችሁ እንዴት ነው መደማመጥ የሚቻለው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን መሰለህ…ሰዋችንም እኮ ፊት ለፊት መናገር ትቷል፡፡ ዙሪያ ጥምጥም ነው የሚናገረው፡፡
አንድዬ፡— እሱ ዙሪያ ጥምጥም ተናገርኩ ሳይል፣ አንተ ዙሪያ ጥምጥም መሆኑን በምን አወቅህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ያስታውቃላ አንድዬ፣ ያስታውቃላ! እኔ የሆነ ሰው ሳመኝ ብዬ ሳስብ እንደነከሰኝ የማውቀው ወሎ፣ አድሮ ሲቆጠቁጠኝ ነው፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ፣ አሁን ጨዋታ አመጣህ:: ምነው ታዲያ ወዲያውኑ አይቆጠቁጥህ! ማለቴ ውሎ የሚያሳድር ነገር ምን አለ? ንክሻ፣ ንክሻ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እሱን አይደል የምልህ አንድዬ፣ እሱን አይደል የምልህ! ለነገሩ እኮ መሳሙን ይስማል፡፡
አንድዬ፡— እኮ፣ ሳመኝ ያልከው ጉንጭህ ከተነከሰ ምነው ወዲያውኑ አይቆጠቁጥህ?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አየህ አንድዬ፣ አሁን ተረዳኸኝ…
አንድዬ፡— አሀ፣ ነገር ቶሎ አይገባህም እያልከኝ ነው?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ! ኸረ እንደው የዛሬዋ…
አንድዬ፡— እየው ነገር በሚገባ ከማስረዳት መሀላ ይቀናችኋል፡፡ እኔ መቀለዴ ነው፡፡ በል ስትነግረኝ የነበረውን ቀጥል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ይኸውልህ አንድዬ፣ የእኛ ሰው ዛሬ ግጥም አድርጎ ሲስምህ ነገ እንዲቆጠቁጥህ አድርጎ ነው፡፡
አንድዬ፡— ጉድ በይ የምን ቅጠል ነበር የምትሉት?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ጉድ በይ የአንኮበር ቅጠል…
አንድዬ፡— እኔም ጉድ በይ የአንኮበር ቅጠል ልበል እንጂ! ዛሬን ስሞ ነገን መቆጥቆጥ የሚባሉ ነገር መኖሩን ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቴ ነው:: ደግሞ እንደዛ ማድረግ የሚችለውን ሰው አስተምረኝ ብሎሀል በልልኝ…
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ!
አንድዬ፡— እንደሱ አትደንግጣ! ይኸውልህ እኔ የምልህ ይህንኑ ነው:: መጀመሪያ ነገር ለምን እንደሁ ግራ እስከሚገባኝ ድረስ አትደማመጡም፡፡ በዛ ሰሞ እንደውም ነገራችሁ ሲበዛብኝ ጊዜ ከዚህ በፊት ግራ ገብቶኝ እንደነበረው አሁንም ግራ ግብት ብሎኝ በድጋሚ እነዚህን ሰዎች አፍ ብቻ ፈጥሬ ጆሮውን ረሳኋቸው እንዴ ብዬ ስጨነቅ ነበር፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ይህን ያህል?
አንድዬ፡— አዎ፣ ይሄን ያህል፡፡ ይሄን ያህል ነው ግራ ያጋባችሁኝ፡፡ ‘ነጭ’ የተባለውን ‘ጥቁር’ ብላችሁ እየተረጎማችሁ፣ ‘ተነሳ’ የተባለውን ‘ወድቆ ፈረጠ’ እያላችሁ፣ ቡራኬውን እርግማን እያደረጋችሁ ምን ልል ጠብቀህ ነበር!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አለመደማመጥ እኮ አይደለም፡፡
አንድዬ፡— በዚህ ክርክር ልትገጥመኝ ከሆነ ስለማልችል በቃ አሸንፈሀል፤ ተሸንፋችሁ መሬት ለመሬት እየተንከባለላችሁም ‘አሸንፈሀል’ ስትባሉ ትወዱ የለ! በቃ ደስ ይበልህ አሸንፈሀል፡፡ አንተ አንድ፣ እኔ ዜሮ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አስቆጣሁህ መሰለኝ፡፡
አንድዬ፡— ምን ያስቆጣኛል! እናንተ ላይ የምቆጣ ቢሆን ኖሮ እዚህ ድረስ መምጣት ሳያስፈልግህ፣ ቁጣዬን እዛው ምድር ላይ የምታየው አይመስልህም! አለመደማመጥ አይደለም ነበር ያልከኝ፤ እስቲ አስረዳኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አዎ አንድዬ፣ አለመደማመጥ አይደለም፡፡ ስለምንተዋወቅ ነው…
አንድዬ፡— ስለምንተዋወቅ ማለት…እኮ አስረዳኝ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— በቃ አንድዬ፣ እንተዋወቃለና! መተቃቀፉ መሞጫመጩ…አንድዬ፣ ለቃላት አጠቃቀሜ ይቅርታ፡፡
አንድዬ፡— ግዴለም ቀጥል፡፡ እኔም የቋንቋ ችሎታዬ ይሻሻል ይሆናል፡፡ ምናልባት እስካሁን የምትሉት ሁሉ አልገባህ ያለኝ ለዚህ ይሆናል፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደሱ ስትል…
አንድዬ፡— እንደሱ ስል ቅር ይልሀል፡፡ አሁን የጀመርከውን ቀጥል!
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ ሁሉ ነገር የውሸት ማስመሰያ መሆኑን እንተዋወቃለን! ሳቁና ፈገግታው ሁሉ የውሸት እንደሆነ እንተዋወቃለን፡፡ “ሳይህ ደስ ይለኛል” የሚለው ሰው “አንተን የማላይበት የት ልሂድ; እያለ እንደሆነ እንተዋወቃለን፤፡ አንድዬ፣ በደንብ ነው የምንተዋወቀው፡፡
አንድዬ፡— እና ምን ይሻላል?
ምስኪኑ ሀበሻ፡— ምን ይሻላል ማለት…
አንድዬ፡— ሳቁ ሁሉ የውሸት ከሆነ፣ መተቃቀፉ ሁሉ ውሸት ከሆነ፣ ደግሞ…መሞጫሞጩ አይደል ያልከው…መሞጫሞጩ ውሸት ከሆን ምን ይሻላል እያልኩህ ነው፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ፤ በእሱ በኩል አንተ ድረስልን እንጂ እኛማ አልቻልንበትም::
አንድዬ፡— እሱን እንኳን ተወው፣ ሲቸግራችሁ፣ ሲቸግራችሁ ብቻ ወደ እኔ እንደምንታንጋጥጡ መች አጣሁት! ብቻ ለዛሬው ይብቃን፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— እሺ አንድዬ፣ እሺ፡፡
አንድዬ፡— ደግሞ እንዳልስምህ ውሎ፣ አድሮ ይቆጠቁጠኛል እንዳትለኝ ትቸዋለሁ::
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አንድዬ!…
አንድዬ፡— በል በሰላም ያግባህ፡፡
ምስኪኑ ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን::
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 2855 times