Saturday, 25 July 2020 15:02

አየር ላይ የተንጠለጠለው የብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ መድረክ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


          መንግስት ለምን ውይይትና መመካከር እንደሚፈራ አይገባኝም ኮቪድ - 1 9 የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት እንቅስቃሴን ገድቦታል

                  የአገሪቱ ፖለቲከኞችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚመክሩበትና የሚወስኑበት የጋራ መድረክ መፍጠር ለምን ተሳናቸው? ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰላማዊና የተረጋጋ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለመፍጠር የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሚና ምን ነበር? አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ከአፋቸው የማይጠፋው የብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ መድረክ ለምን በአየር ላይ ተንጠልጥሎ ቀረ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ  የህብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ም/ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ግርማ በቀለን ከላይ በተጠቀሱትና በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡


               ሀገሪቱ አሁንም በተለያዩ የፖለቲካ ውጥረቶችና መካረሮች ውስጥ ነው የምትገኘው:: ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
እነዚህ መካረሮች ምንጫቸው ሁለት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንደኛው፤ በመንግስትና ህዝብ መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ ቃልና ተግባር አልስማማ ማለታቸው ነው፡፡ በመንግስት በኩል የሚገቡ ቃልኪዳኖች መሬት ላይ ወርደው ተተግብረው ባለመገኘታቸው የሚፈጠር ቅሬታ ነው፤  ወደ ተካረረ ሁኔታ እየተለወጠ ያለው፡፡ ሁለተኛው፤ የፖለቲካ ባህላችን ነው፡፡ ሁልጊዜ ገዥ ፓርቲ የገባውን ቃል ኪዳን ካለመፈፀም ባሻገር የፖለቲካ ድርጅቶችን ያሳተፈ ሳይሆን አግላይና ጠቅላይ የሆነ አካሄድን የመከተል ሁኔታ መፈጠሩ ነው፡፡ አሁንም ገዥው ፓርቲና መንግስት ተለይቶ መሄድ የማይችልበት የአግላይና ጠቅላይ አካሄድ ውስጥ መገባቱ ነው ችግር እየፈጠረ ያለው፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ እያሳተፉ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚህ አንፃር አግላይና ጠቅላይ ሊባሉ ይችላሉ ብለው ያምናሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ ሁሌም መንግስታት ሲመጡ በጅማሮአቸው ላይ ለሁሉም ነገር ቀና ይሆናሉ፡፡ ቃል ይገባሉ፡፡ ያንን ተከትሎ ሰው ድጋፍ ይለወጣቸዋል፡፡ ያንን ድጋፍ ተገን አድርገው ብዙም ሳይቆይ ወደ አምባገነናዊነት ይለወጣሉ፡፡ በኛም ሁኔታ ይሄ የተለመደ ነው:: ከሁለት አመት በፊት ለውጡ ሲጀመር ጥሩ ነበር፡፡ ሁሉም ሃሳብ የሚደመጥበት፤ ሁሉም ፖለቲካ ድርጅት እኩል የሚስተናገድበት፤ ሁሉም ፓርቲዎች በሀገሪቱ ጉዳይ የሚመክሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ እንዲያውም ፓርቲዎች ተቃዋሚ ሳይሆኑ “ተፎካካሪዎች” ናቸውም ተብለን ነበር:: እነዚህ ሁሉ ቀርተው አሁን ተቃዋሚዎች፤ በተቃዋሚነታቸው የሚፈረጁበት፣ ከዚያም ሲያልፍ “ከሃዲ”፣ “ባንዳ” የሚባሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ በፓርቲዎች መካከል ሊኖር የሚገባው መቻቻልና መደማመጥ እንዲሁም ችግሮችን ተነጋግሮ የመፍታት ልምምድ የዛሬ ሁለት አመት በተጀመረበት መልኩ እየሄደ ነው ወይ? የሚለውን ሁሉም ጠይቆ ሊገነዘበው የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡
ይህ ለምን የተፈጠረ ይመስልዎታል?
የለውጡ ጅማሮ ውስጥ ስንገባ፣ የለውጥ ሃይል የሚባለው ወገን ሊያመጣ የፈለገው ነገር ብዙ ርቀት ሳይሄድበት የተሰናከለበት ነገር እንዳለ ነው የምረዳው፡፡ በተለይ የዲሞክራሲ ተቋማትን ነፃነት ማስጠበቅ በሚለው ብዙ ያልምም የተሳካለት አይመስልም፡፡ ሚዲያን የፍትህ ተቋማትን፣ ምርጫና ሌሎችም የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማስተካከል ለህዝብ የተነገረው ቃል ኪዳን  ብዙም ውጤታማ የሆነ አይመስልም፡፡ የፖለቲካ ድርጅበችም የጠበቁትን ያህል እንቅስቃሴ ማየት አለመቻላቸው፣ ማህበረሰቡም የሚፈልጋቸው ወሳኝ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦች አለመቀላጠፋቸው ችግር የፈጠረ ይመስለኛል፡፡
እርስዎም የሚመሩት የእርቅና ብሔራዊ መግባባት እንቅስቃሴ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የተጀመረው እንቅስቃሴ ምን ላይ ደረሰ?
እንደተባለው ከለውጡ በፊት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች አሜሪካን ሲያትል ላይ ስብሰባ አድርገው ሀገሪቱን ለመታደግ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ መድረክ በአስቸኳይ እንዲፈጠር፤ ከዚያም የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም መክረው ነበር፡፡ ወዲያው ግን ለውጡ ተፋጠነና ዶ/ር ዐቢይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ መጡ ከዚያም “እኔ አሻግራችኋለሁ” ሲሉን መንግስት በዚህ መልኩ በራሱ ውስጥ ወሳኝ ለውጥ ካመጣ የሽግግር መንግስት የሚለው ይቅርና ከዚያ ይልቅ ሁሉንም ፓርቲ የሚያሳትፍ ብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም ይፈጠር በሚል ስንንቀሳቀስ ነው የነበረው:: 29 ፓርቲዎች ነበርን፤ ሌሎችም ተቋማት አብረውን ነበሩ:: ይሄን ሃሳብ ይዘን ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ በወቅቱ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመንም አነጋግረናል:: በእውነት ዶ/ር ሙላቱ ትልቅ ድጋፍ ሲያደርጉልንና ጉዳዩንም ሲያበረታቱን ነበር፡፡ ይሄን ሃሳብ ሙሉ ጊዜ ሰጥተን ገፍተንበት እያለ ግን ከመንግስት በኩል በቂ ምላሽ አላገኘንም:: በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እየተፈጠረ ሲመጣ፣ ይሄ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ አካሄድ በመንግስት በኩል ብዙም የተወደደ አይመስልም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ሃሳባችን እግር አውጥቶ መራመድ ያቃተውና ተሰነካክሎ የቀረው፡፡ እውነት ለመናገር፤ ያን ጊዜ እንዲህ ያለው መድረክ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የምናየው የፖለቲካ ችግር በቀነሰ ነበር፡፡ ብዙም የተወሳሰበ ችግር ውስጥ ባልገባን ነበር፡፡
መንግስት ያቋቋመው ብሔራዊ የእርቀ ሠላም ኮሚሽንም አለ፤ ነገር ግን እስካሁን መሬት ላይ የወረደ ተግባር አልታየም?
አንዱ ችግር የፈጠረው እኮ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ ሂደት ውስጥ አለመገባቱ ነው:: ኮሚሽኑም ምንም እንቅስቃሴ የለውም፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለው አካል፤ ፍፁም ገለልተኛና የሆነ፣ በራሱ ተነሳሽነት የተቋቋመ ቢሆን ነበር የሚመረጠው፡፡ አሁን ለደረስንበት ችግር ሁሉ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ሂደት ውስጥ አለመገባቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችም በልካቸው እንዳይስተናገዱ እንቅፋት ሆኗል፡፡
እርስዎ በም/ሊቀመንበርነት የሚመሩት የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለውጡን በማገዝ ረገድ ምን አስተዋጽኦ አድርጓል?
ካለን የፖለቲካ ባህልና ልምድ እንዲሁም መንግስት ከሚያደርገው የቃልና ተግባር አለመጣጣም አንፃር እስካሁን ባሰብነው ልክ መጓዝ አልቻልንም፡፡ መንግስት ለእንደነዚህ ያሉ መድረኮች የቱን ያህል ፈቃደኛ ሆኖ ትብብር እያደረገ ነው? የሚለው ነው የሚያጠያይቀው:: የጋራ ም/ቤቱም ከዚህ አንፃር በሚታይበት ጊዜ ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ የራሱን ነፃነት እጠብቃለሁ ሲል የቱም የፖለቲካ ፓርቲ ወደራሱ ስቦ የራሱ አገልጋይ እንዲሆንለት ይፈልጋል፤ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሁኔታ አንፃር ም/ቤቱ ያጋጠመው ችግር አለ፡፡ በምርጫ ቦርድ በኩል ጠንካራ ተቋም ሆኖ እንዲወጣ በምርጫ ቦርድ በኩል የተደረገለት ድጋፍ ዝቅተኛ ነው:: በሌላ በኩል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በለውጡ ውስጥ የሚጠበቀውን ያህል እንቅስቃሴ አድርገናል ማለት አይቻልም፡፡ በተጨማሪም ኮቪድ 19 መምጣቱም ም/ቤቱ በበቂ ሁኔታ እንዳይንቀሳቀስ ገድቦታል፡፡
በቀጣይ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ተወያይቶ ለመፍታት ረገድ የጋራ ም/ቤቱ የሚኖረው ሚና ምንድን ነው?
ይሄ ም/ቤት አስቀድሜ የጠቀስኳቸው ችግሮች አጋጠሙት እንጂ አንድ ትልቅ ስራ ሠርቷል:: ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ከምርጫ 2012 በፊት ሊመክሩባቸው ይገባል ያላቸውን 7 ጉልህ ሀገራዊ አጀንዳዎች ቀርጿል፡፡ እነዚህ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ስናደርግ በምንስማማባቸው ላይ የጋራ አቋም እየያዝን ማለፍ፣ በማንስማማባቸው ላይ ደግሞ ላንጣላ ላንጋጭ የምንማማልበትን ሂደት ለመጀመር ነበር የቀረጽናቸው፡፡ ይህ ሲሆን ቀጣዩ ምርጫም ያለ ግጭት በሠላማዊ መንገድ የሚከናወንበት እነዚህ አጀንዳዎችም በተመሳሳይ በአስተዳደራዊ ቢሮክራሲ ምክንያት እንዳይፈፀሙ የተደረገበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉ ይሄ አጀንዳ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥረውበታል፡፡ ነገር ግን የጋራ ም/ቤቱ እነዚህን አጀንዳዎች ዝም ብሎ አልጣላቸውም አሁንም ይዟቸዋል፡፡ ወቅቱ ሲፈቅድ ይተገበራሉ፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ሂደት ውስጥ መግባት ይቻላል ብለው ያስባሉ?
ገዥው ፓርቲ ይሄን አጀንዳ ወደ ኋላ ጐተት ያድርገው እንጂ በተለያዩ መድረኮች ስለ አስፈላጊነቱ ያነሳል፡፡ “ከዚህ በኋላ በመሣሪያ ሳይሆን በሃሳብ ኑ” እያለ ጥሪ እያቀረበ ነው፡፡ ግለሰባዊ አምባገነንነትና አሃዳዊነት እየመጣ ነው የሚለው ህወኃትም ቢሆን፣ የሀገሪቱ ችግሮች የሚፈቱት ሁሉን አቀፍ ውይይት በማድረግ ነው እያለ ነው፡፡ በቅርቡ በተፈጠረው ቀውስ የታሠሩ አመራሮችም ይሄንኑ እያሉ ነው ያሉት፡፡
ይሄን በሚሉበት ጊዜኮ በሌላ ቋንቋ ተገናኝተን እንምከር ማለታቸው ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ፍላጐትን መሠረት ያደረገ የውይይት መድረክ መፍጠር አይቻልም፡፡ በሚገባ ይቻላል፡፡ ጊዜው ይፈቅዳል፡፡ ዳር ዳር ቆመው እየተካረሩ ያሉት ሳይቀሩ እኮ ተገናኝተን እንነጋገር እያሉ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ “መነጋገር መፍትሔ አይሆንም፤ ሃይል ነው መፍትሔው” የሚል የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ሁሌም ከፖለቲካ ውይይት ነው መፍትሔ የሚመነጨው የሚል አቋም ነው ያላቸው፡፡ አሁን ያልተቻለው ወደ ተግባር መግባት ነው፡፡
ለምንድን ነው ወደ ተግባር መግባት ያልተቻለው?
የፖለቲካ ልማዳችንና ተሞክሮአችን ነው ማነቆ የሆነብን፡፡ ስልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ይሄን ውይይት ማድረግ ልክ ስልጣንን እንደ ማካፈል አድርጐ ነው የሚመለከተው:: ስለዚህ በአፍ ይለዋል እንጂ ተግባር ላይ ማዋሉን ይፈራዋል፡፡ ከምንም በፊት ሀገር ነው መቅደም ያለበት፡፡ ፓርቲዎች ስልጣን ሊይዙ የሚችሉት መጀመሪያ ሀገር ሠላም ሲሆን ነው:: ዛሬ በመቶዎች የሚቆጠሩ በአንድ ቀውስ በሚያልቁበት፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት በደቂቃዎች ውስጥ ዶጋ አመድ በሚሆንበት ወቅት እንዴት ተብሎ ነው ስልጣን ምኞት የሚሆነው? ማንም  አይመኝም፡፡ ስለዚህ መንግስት ይሄን ስጋቱንና ጥርጣሬውን ትቶ፣ ብንነጋገርና መፍትሔ ብናበጅ መልካም ነው:: መመካከር ለምን እንደሚፈራ በእውነቱ አይገባኝም፤ እስከመቼ ይሄን ችግር ተሸክመን እንደምንሄድ አይገባኝም፡፡
አሁን ለሚታዩት የፖለቲካ ቀውስና ችግሮች መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
ይህችን ሀገር ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስና ቅርቃር የምናወጣበትን መንገድ የምንመክርበት የብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሠላም መድረክ መፍጠር አንደኛው መፍትሔ ነው፡፡ ይህ አይሆንም ከተባለ ደግሞ ሁለተኛው አማራጭ፣ የጋራ ም/ቤቱ ተሰብስቦ አንዳች መፍትሔ እንዲያስቀምጥ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁለት አማራጮች የማይፈፀሙ ከሆነ፣ ሀገሪቱ ወደ በለጠ ችግር ታመራለች የሚል ስጋት አለኝ፡፡ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ውይይት መድረክ መፍጠር ካልተቻለና “እኔ ብቻ” ያልኩት ካልሆነ፣ “መፍትሔው በኔ እጅ ላይ ብቻ ነው” “የገባኝ እኔ ብቻ ነኝ” “እኔ ብቻ ነኝ ለሀገር አሳቢ” የሚለውን አካሄድ ትቶ፣ ወደ ውይይትና ብሔራዊ መግባባት ካልተመጣ የፖለቲካችን አካሄድ ከአዙሪት ያልተላቀቀ ሊሆን ይችላል፡፡Read 1440 times