Wednesday, 22 July 2020 00:00

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 • በኃይል ማመንጨት አቅሙ ከዓለም 7ኛ ከአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ፤ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በግንባታ ወጭው ከዓለም 5ኛ ከአፍሪካ 1ኛ
          • የውሃ ሙሌት በተፈጥሮ ተጀምሯል 560 ሜትር
          • ለግንባታው ከህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ 13.5 ቢሊዮን ብር
              
               የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ቀን እንስቶ ይህ ፅሁፍ እስከተዘጋጀበት ወቅት ድረስ ግንባታው ሲካሄድ 9 ዓመታት፤ 111 ወራት፤   3,395 ቀናት፤485 ሳምንታት፤ 81,480 ሰዓታት 293,328,000 ሰከንዶች፤ 4,888,800 ደቂቃዎች ተቆጥረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገነባው ግድቡ አይነቱ በሮለር የታጠረ ኮንክሪት ሲሆን ዋናው ዓላማው ኃይል ማመንጨት ነው፡፡ በግንባታ ላይ የሚገኘው ግድቡ  70 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን የውሃ ሙሌቱ ዘንድሮ በክረምቱ ዝናብ በተፈጥሮ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ከሳተላይት የተገኙ ምስሎችን በመንተራስ ሰሞኑን ከቢቢሲ የወጣ ዘገባ የግድቡ ሙሌት በክረምቱ ዝናብ ብቻ 560 ሜትር መድረሱ ተጠቁሟል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታ የሚያስፈልገው ወጭ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ ከ13.5 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ የተነሳ ከዓለም እጅግ ግዙፍ ግድብ ገንቢዎች ተርታ ተመድባለች፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት በኃይል ማመንጨት አቅሙ ከዓለም 7ኛ ከአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን  ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለግንባታው ወጭ ስለሚሆን ከዓለም 5ኛ፤ ከአፍሪካ በ1ኛ ደረጃ የሚነሳ ሆኗል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ቁመት 155 ሜ ፤ ርዝመት 1,780 ሜ፤ ከፍታ 655 ሜትር  ሲሆን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይይዛል፤ 6,450 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል፡፡  500 ሺህ ሄክታር መሬትን ያለማል፡፡  246 ኪ.ሜ ሐይቅ ይፈጥራል፤ ከ10 ቶን በላይ ዓሳ ማምረት ይቻላል፤ ለውሃ መጓጓዣና ለቱሪዝም ያገለግላል፡፡
ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በኋላ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ የምታመነጨው ኃይል  14ሺ ሜጋ ዋት ይደርሳል፡፡
የኢትዮጵያ ኃይል የማመንጨት አቅም ከሃይድሮፓወር 45ሺ ሜጋ ዋት ፤ ከጂዮቴርማል 10ሺ ሜጋ ዋት፤ እንዲሁም ከንፋስ ሃይል 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ይሆናል፡፡
በመሬት የተከበበች ብዙ ህዝብ ያላት አገር በመሆን ከዓለም ሁለተኛ  ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ እንዲሁም በህዝብ ብዛት ከናይጄርያ ቀጥሎ በአፍሪኳ ሁለተኛ ናት፡፡ 85 በመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ በገጠር ነዋሪ ሲሆን 2 በመቶው ብቻ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኛል፡፡ ኢትዮጵያ 90 በመቶ ኤሌክትሪክ የምታመነጨው በውሃ ሃብቷ ሃይድሮፓወር ነው፡፡ የአፍሪካ ውሃ ማማ ተብላ የምትጠራው ኢትዮጵያ፤ በመልክዓ ምድሯ በድምሩ 44 ወንዞች ይፈሱባታል፡፡ በሐይቆች ብዛት  በአፍሪካ የሚስተካከላት የለም፡፡ በሃይድሮፓወር ባላት አቅም ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አገር ስትሆን ከውሃ ኃይል የማመንጨት አቅሟ 10 በመቶውን ብቻ ገንብታለች፡፡ ኢትዮጵያ ከሃይድሮፓወር ግንባየምታመነጨው ኃይል 4330 ሜጋ ዋት ሲሆን በግንባታ ላይ ቢሆንም ተጨማሪ 6600 ሜጋ ዋት አላት፡፡ ከታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብና ሌሎች ፕሮጀክቶች  በኋላ በአጠቃላይ የምታመነጨው ኃይል  14ሺ ሜጋ ዋት ይደርሳል፡፡ የኢትዮጵያ ኃይል የማመንጨት አቅም ከሃይድሮፓወር 45,000MW፤ ከጂዮቴርማል 10,000MW እንዲሁም ከንፋስ ሃይል 1.3 ሚሊዮን MW ነው፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ  በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል
ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኃይል አቅራቢነት አዲስ ኢኮኖሚ እየገነባች ነው፡፡ ከዓመት በፊት ለሱዳንና ለጅቡቲ በተሸጠ 1.5 ቢሊዮን kWh የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ81.6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል፡፡ 47.5 ሚሊዮን ዶላር ሱዳን እንዲሁም 34.1 ሚሊዮን ዶላር ጅቡቲ ከፍለዋል፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ደቡብ አፍሪካ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማሰራጫ መስመር ተገንብቶ ወደስራ እየተገባ ነው፡፡ በዚሁ የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሃዌይ ፕሮጀክት 1000 ኪሜ መስመር በመዘርጋት እስከ 2000 ሜጋ ዋት ለኬንያና ለሶማሊያ የምታቀርብበት ስምምነት አለ፡፡ ታንዛኒያም ፍላጎት አላት፡፡በዓለም ባንክ ትንታኔ መሰረት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ሙሉ ስራ ሲጀምር በዓመት እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ነው፡፡
በአባይ ተፋሰስ አገራት ውስጥ ያለው የኃይል ማምነጨት አቅም ከ20 GW የሚበልጥ ቢሆንም ጥቅም ላይ የዋለው 26 በመቶው ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በሚቀጥሉት 15 ዓመታት 300 በመቶ ይጨምራል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ 6450 ሜጋ ዋት በማመንጨት ከዓለም 7ኛ ከአፍሪካ 1ኛ
በኃይል የማመንጨት አቅም ከዓለማችን ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው በሁባይ ቻይና የተገነባው ስሪ ጎርጀስ  Three Gorges Dam ነው፡፡ በ37 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የተገነባ ነው፡፡ ከህዋ የሚታይ ነው ተብሎ የሚደነቀው ይህ ግድብ በአርማታና ብረት የተገነባ ሲሆን የመሬት ዙረትን አቃውሷልም  ተብሏል፡፡ ስሪ ጎርጅስ  እስከ 22500 ሜጋ ዋት በማመንጨት የዓለማችን ከፍተኛው ኃይል አመንጪ ግድብ ሲሆን ከአሜሪካው ሁቨር ግድብ 11 ጊዜ እጥፍ ኃይል ያመነጫል፡፡ የስሪ ጎርጀስ ግድብ ለመገንባት 510ሺቶን ብረት ጥቅም ላይ ሲውል፤ በፈረንሳይ ፓሪስ የሚገኘውን ኤፍል ታወር 60 ያህል ለመስራት ያስችላል፡፡ የግድቡ ሐይቅ 42 ቢሊዮን ቶን ውሃ የሚይዝ ሲሆን የቀንን ርዝማኔ በ0.06 ማይክሮ ሰከንድ ጨምሯል፡፡  ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ሲያልቅ 6450 ሜጋ ዋት በማመንጨት ከዓለም 7ኛ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃን የሚይዝ ይሆናል፡፡
ታላቁ የኢንጋ ግድብ፤ የካሪባ ሃይቅ እና ሌሎች የአፍሪካ ግድቦች
በዓለም ዙርያ እና በአፍሪካ እጅግ ግዙፍ ግድብ እንደሚሆን የሚጠበቀው በኮንጎ ወንዝ ላይ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ ውስጥ በ100 ቢሊዮን ዶላር  ለመገንባት የታቀደው ‹‹ታላቁ ኢንጋ ግድብ›› ሲሆን 50000 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ ታቅዷል፡፡
በዚምባቡዌ እና ዘምቢያ ድንበር ላይ የተገነባው የካሪቡዋ ግድብ ደግሞ በ5580 ስኩዌር ኪሜትር በመስፈሩና 185 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ በመያዙ ከዓለም 1ኛ ነው፡፡ የካሪቡዋ ሃይቅ 280 ኪሜ ርዝመት እና 32 ኪሜትር ስፋት አለው፡፡
ግብፅ ውስጥ በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የአስዋን ግድብ  2100 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሲሆን ግድቡ የፈጠረው ናስር ሃይቅ 132 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ይይዛል፡፡ የአስዋን ግድብን የግብፅ ኢንጀነሮች ከራሽያ ሃይድሮፕሮጀክት ኩባንያ ጋር ሰርተዋታል፡፡ በግብፅ የሜሮዌ ግድብ ፤ በጋና የኦኮሶምቦ ግድብ በደቡብ አፍሪካና ሌሶቶ የካታሴ አርክ ግድብ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በከፍተኛ የማመንጨት ኃይል 5 ታላላቅ ግድቦች በአፍሪካ
Grand Ethiopian Renaissance ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) 6000MW
 Katse Arch የካቴሴ አርክ ግድብ በማሊባማቶ ወንዝ ሌሶቶ
 The Aswan High የአስዋን ከፍታ ግድብ በሞዛምቢክ 2,100 MW.
 Cahora Bassa ካሆራ ባሳ ግድብ በሞዛምቢክ 2075 MW
 ግልገል ጊቤ 3 በኦሞ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ 1,870 MW
በከፍተኛ ወጭ 5 ታላላቅ ግድቦች በዓለም ዙርያ
    Grand Inga, በዲሞክትራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ     $ 80 Billion
    Belo Monte, በብራዚል     $ 18.5 Billion
    Baihetan Dam, በቻይና     $ 13 Billion
    Xiluodo Dam, በዩናን ግዛት ቻይና     $ 12 Billion
    Grand Ethiopian Renaissance Dam, በኢትዮጵያ     $ 5 Billion
በከፍተኛ የማመንጨት ኃይል 5 ታላላቅ ግድቦች በዓለም ዙርያ
Three Gorges Dam በያንግትዜ ወንዝ ቻይና 22.5 GW
Itaipu Dam በፓራና ወንዝ ብራዚልና ፓራጓይ 14 GW
Xiluodu በጂንሻ ወንዝ ቻይና 13,860 MW
Guri በካሮኒ ወንዝ ቬንዝዋላ 10,235 MW
Tucuruí በቶካንቲስ ወንዝ ብራዚል 8,370 MW.
Sources: www.energydigital.com  , International Rivers , BBC, Water-technology.com ,Reuters,  Nile Basin Initiative, World Bank, …Read 825 times