Tuesday, 21 July 2020 00:00

በነውጥ የወደሙ ኢንቨስትመንቶች እንዴት ይካሣሉ? - (ህጉ ምን ይላል?)

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    • ወጣቱ አገሩንና ንብረቱን የሚያወድመው የት ሊኖር ነው?
           • ትልቁ የሥራ ዕድል ፈጣሪና ቀጣሪ የግሉ ዘርፍ ነው
          • የፀጥታና የደህንነት ችግር ትልቁ የኢንቨስተሮች ፈተና ነው

            የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚገኙ አነስተኛና ትላልቅ የንግድ ተቋማት እንዲሁም ኢንቨስትመንቶች በከፍተኛ ሁኔታ ወድመዋል፡፡ እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከወደሙ በኋላ ባለሀብቶች መንግስትን ካሳ ይጠይቃሉ? በኢንቨስትመንት አዋጁ መንግስት ካሳ እንዲከፍል የሚያስገድድ ህግ አለ? ከዚህ ቀደም መሰል ችግሮች እንዴት ተፈቱ? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከህግ ባለሙያና ተመራማሪ አቶ ኪያ ፀጋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ  አድርጋለች፡፡

            መንግስት በነውጥ ለሚወድሙ ኢንቨስትመንቶችና ንብረቶች ካሣ የመክፈል ግዴታ አለበት?
መንግስት ኢንቨስት ለሚያደርጉ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ንብረት ጥበቃና ከለላ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ እኔ ባለኝ ልምድ እንደማውቀው፤ በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደዚህ አገር የሚመጡት በስንት ማግባባትና ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ነው፡፡ እዚህ ከመጡ በኋላ ታዲያ ከሰሞኑ የተከሰተውን ውድመት  ጨምሮ በርካታ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል::
ለምሳሌ?
መጀመሪያ በአገራቱ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት መሠረት ነው የሚመጡት፡፡ ከቻይና፣ ከአሜሪካ፣ ከሆላንድ ወይም ከቱርክ ሊሆን ይችላል፡፡ በየሀገራቱ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት (ባይላተራል ኢንቨስትመንት ትሪቲ) መሰረት ይመጡና ከፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፈቃድ ያወጣሉ፡፡ በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ ለማውጣት ከ3-5 ቀናት ይፈጃል፡፡ ከዚያ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ እያለ ይቀጥላል፡፡ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስተሮች መከራ የሚጀምረው ከዞንና ከወረዳ አመራሮች ነው፡፡ #የኔን ዘመድ ካልቀጠርክ; ከሚል ጥያቄ ጀምሮ ኢንቨስተሮች በበርካታ የሙስና ድርጊቶች  ይሰቃያሉ፡፡ በዚያ ላይ የፌደራሉና የክልሉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽኖች ተናበውና ተቀናጅተው የመስራት ከፍተኛ ክፍተት አለባቸው፡፡ ወደ ዋናው ነገር ስመለስ፤እንዲህ አይነት አገራዊ ነውጥ ሲመጣ ብቻ አይደለም ኢንቨስተሮች የሚሰቃዩት ለማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢንቨስተር አራት የመንግስት መዋቅሮች ነው የሚያየው፡፡ ከፌደራል ወደ ክልል ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም የመሬትና የተፈጥሮ ጉዳዮችን የሚቆጣጠሩት ክልሎች ናቸው፡፡ ከክልል በኋላ ወደ ዞን ይሄድና ዞኑ ወደ ወረዳ ይልከዋል፡፡ ከዚያ ዋናውን ውሳኔ ክልሉ በኢንቨስትመንት ቦርዱ ወስኖ መሬቱን ለኢንቨስተሩ ይሰጣሉ፡፡ ምንም እንኳን መሬቱን የሚፈቅደው የክልል መንግስት ቢሆንም፣ ኢንቨስተሩ የተለያዩ አገልግሎቶችን  የሚያገኘው መሬት አቅራቢ በሆኑት የዞን ወይም የወረዳ አመራሮች ነው:: ስለዚህ ኢንቨስተሩ የደህንነትና የጥበቃ አገልግሎት የሚያገኘው መሬቱ ከሚገኝበት ዞን ወይም ወረዳ የፀጥታ አካላትና መዋቅሮች ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ኢንቨስተሩ በጣም የሚሰቃየው በነዚህ “Local Government” በሚባሉት አካላት ነው፡፡
ኢንቨስተሮች የተለያዩ ተግዳሮቶች ሲገጥሟቸው ለማን ነው አቤት የሚሉት?
ለየትኛውም ወገን አቤት ቢሉም ከፌደራል ጀምሮ ተቀናጅቶ የመስራቱ ክፍተት ስላለ ችግሮቻቸው በቶሎ አይፈታም፡፡ አንዴ መዋዕለ ንዋያቸውን በሚሊዮኖች ካፈሰሱ በኋላ ተግዳሮቶቹን ተቋቁመው ነው በስቃይ የሚቀጥሉት:: ይህን የምነግርሽ ከሩቅ ሆኜ አይደለም፡፡ ከአንዳንድ ኢንቨስተሮች ጋር የመገናኘትና የማማከርም ስራ ስለምሰራ ችግራቸውን በቅርበት አውቀዋለሁ፡፡ የወረዳ አመራሮች ችግር ሲደርስ ፈጥነው ለመድረስም ቸልተኞች ናቸው፡፡ ዝቅተኛ የወረዳ አመራሮች በራሳቸው ችግር ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ እግረመንገዴን በአጠቃላይ ያለውን ችግር ልንገርሽ ብዬ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢንቨስተሮች ችግር የሚነሳውና ዜና የሚሰራው እንዲህ አይነት ውድመት ሲደርስባቸው ብቻ  ነው፡፡ በኢንቨስተሮች ላይ ችግር ሲደርስ ራሱ የዞን ወይም የወረዳ አመራሩ ችግራቸውን ከመረዳት ይልቅ አክቲቪስት ሆኖ ይመጣባቸዋል:: ይሄ ሁሉ ችግር መፈተሽ አለበት ለማለት ነው:: ይሄ በብዙ ክልሎች ላይ የሚስተዋል ነው፡፡ ኢንቨስተሩ ችግር የለበትም፤ ፍፁም ነው ማለቴም አይደለም፡፡ መሬት አጥሮ ከማስቀመጥ ጀምሮ በርካታ ጥፋቶችን የሚያጠፉ አሉ፡፡ ይህም እንዳለ ሆኖ በወረዳ አመራሮች ከሙስና ጀምሮ በርካታ በደልና የፍትህ መጓደል በኢንቨስተሮች ላይ ይደርሳል፡፡ በእርግጥ የፀጥታ ችግር ሲከሰት ወረዳ ላይ በቂ የሰው ሃይል ላይኖር ይችላል፡፡ ክልሉ አፋጣኝ ምላሽ እስኪሰጥ ግን ወረዳው ባለው የፀጥታ ሃይል እንኳን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ የፀጥታና የደህንነት ችግር ትልቁ የኢንቨስተሮች ፈተና ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ በዚያ ኢንቨስትመንት ላይ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛም ውሃ ቀጠነ ብሎ አድማ ይመታል፡፡ አድማ የሚመታው ደግሞ ማሽን በማውደም፣ እቃ በመስበርና ጥሬ እቃ በማውደም ነው፡፡ ይሄን ሁሉ ተቋቁሞ ነው ኢንቨስተሩ ለመስራት የሚታገለው፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ እንመለስና---በኢንቨስትመንቶች ላይ ውድመት ሲደርስ መንግስት ካሣ የመክፈል ግዴታ አለበት የለበትም?
ከላይ እንደገለፅኩልሽ፤ መንግስት ዋናው ግዴታው ኢንቨስተሮችንና ኢንቨስትመንትን ከጥቃትና ከውድመት መከላከልና መጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ሆኖ ንብረትና ሀብት በሚወድምበት ጊዜ በሌሎች ያደጉ አገራት ኢንሹራንስ አለ፡፡ ለምሳሌ የፖለቲካ ቀውስና ሁከት ተነስቶ ንብረት በሚወድምበት ጊዜ ኢንሹራንስ የሚከፍሉ ኩባንያዎች አሉ:: ያደጉና ሀብታም ሀገራት በዚህ አይነት መንገድ ንብረታቸው የወደመባቸውን የመካስ ስራ ይሰራሉ፡፡ አሁን ግን የኛ መንግስት ከወደመው ንብረት አንፃር ለሁሉም የወደመ ሀብትና ንብረት ካሣ ለመክፈል አቅሙ አለው ብዬ አልገምትም፡፡ ፍላጐቱ ቢኖረውም አቅሙ አይፈቅድለትም::
ከህግ አንፃር ግን መንግስት ለወደሙ ኢንቨስትመንቶችና ንብረቶች ካሣ የመክፈል ግዴታ አለበት የለበትም?
ከህግ አንፃር መንግስት ካሣ የመክፈል ግዴታ አለበት የሚል የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም መንግስት ራሱን እንዲህ አይነት ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ውስጥ አይከትም:: ነገር ግን ቀጥታ ውድመት (Direct Damage) ሲኖር ማለትም በመንግስት የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ ወይም ቃጠሎ በማድረሱ አሊያም በመፈንዳቱ መንግስት ለዚያ ለወደመ ንብረት ካሳ ይከፍላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ቀውስና ብጥብጥ ለወደመ ንብረት ካሳ ይከፍላል የሚል ነገር አልተቀመጠም፡፡
ውድመት የደረሰባቸው ባለንብረቶች ታዲያ ማንን ነው የሚጠይቁት?
እርግጥ ውድመት የደረሰባቸው ኢንቨስተሮች በተለይም የውጭ ኢንቨስተሮች በሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ መንግስት ምን ያህል አቅም ኖሮት ይከፍላል የሚለው ጉዳይ እንጂ ኢንቨስተሮቹ በመንግስት ቸልተኝነት ምክንያት ንብረታችንና ሀብታችን ወድሟል፤ ስለዚህ በዚህ በዚህ መንገድ ይካሰን ብለው የመጠየቅ መብት አላቸው:: ሙግቱ ግን ምን ይሆናል መሰለሽ---አንደኛ ከአቅም በላይና ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ ነው ንብረቱ የወደመው የሚለውና መንግስት ካሣ ለመክፈል ፍላጐት ቢኖረኝ እንኳን የመክፈል አቅም የለኝም የሚለው ነገር ይመጣል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ በውይይት የሚፈታ ነው የሚሆነው:: ለምሳሌ በአገራዊ ለውጡ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ንብረቶች ወድመዋል:: ለምሳሌ ባህርዳር አካባቢ የአበባ እርሻዎች ተቃጥለዋል፡፡ ባለሀብቶቹ መንግስትን ካሣ ጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን በአገር ላይ የተከሰተ ቀውስ ያስከተለውን ውድመት መንግስት ባለው ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ መካስ አይችልም፤ አቅምም የለውም፡፡ አንድን ኩባንያ መካስ ቢጀምር የሌላውም ኢንቨስተር ጥያቄ ይቀጥልና አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል፡፡ ከሰሞኑ በተከሰተው ቀውስ እንኳን ከመስታወት ጀምሮ የወደመው ንብረት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል፡፡ የመንግስት ህንፃ ተቃጥሏል፤ የመንግስት ተቋማትም ወድመዋል፤ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
ቅድም ንብረት የወደመባቸውን ቀጥታ በክፍያ ከመካስ ውጪ ሌላ የሚክስበት አማራጭ የለውም ወይ ወዳልሽው ስመለስ፤ ምናልባት መንግስት ለተጐጂዎቹ ብድር በመፍቀድ፣ ድጐማ በመስጠት፣ ታክስ በመቀነስ፣ ኢንቨስተሮቹ ድጋሚ በሚገነቡበት ጊዜ እቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ በማድረግና በመሰል ትብብሮች ጉዳቱን ሊያካክስላቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ መኪናው ለተቃጠለበት ለአንድ ባለንብረት መኪናው ስለመቃጠሉ አሳማኝ ሰነድ ሲያቀርብ፣ መኪና በድጋሚ በሚያስገባበት ጊዜ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን በማድረግ መካስ ይችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ሙሉ በሙሉ የወደሙ ኢንቨስትመንቶችን ለማነቃቃት የማበረታቻ የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል እንጂ ሙሉ ለሙሉ ካሣ ለመክፈል የመንግስት የአቅም ደረጃ አይፈቅድም፡፡ ለምሳሌ የአትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የወደመ ንብረት ብቻ ወደ 200 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ዜና ላይ ሰምቻለሁ፡፡ ታዲያ መንግስት በምን አቅሙ ነው ለወደሙ ኢንቨስትመንቶች ሁሉ ካሣ መክፈል የሚችለው፡፡
እንዲህ አይነት ውድመቶች በተለይም በውጭ ኢንቨስተሮችና ኢንቨስትመንቶች ላይ ውድመት ሲደርስ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው ስምምነት በምን መልኩ ነው የሚዳኘው?
እኔ እንግዲህ ኢንቨስተሮቹና የኢትዮጵያ መንግስት ቁጭ ብለው ቢመካከሩና ቢወያዩ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም አገር አቀፍ ችግር ተከስቷል፤ ንብረት ወድሟል:: ችግሩን በጋራ እንዴት እንፍታው? ምንስ ብናደርግ ይሻላል? በሚለው ላይ ሰላማዊና ወዳጅነትን ያልለቀቀ ምክክር ማድረጉ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ መንግስትም ቅድም ባልኩሽ መልኩ ታክስን በመቀነስ፣ ከቀረጥ ነፃ እቃ እንዲያስገቡ በማድረግ፣ ብድር በማመቻቸት የሚችለውን ቢያደርግ፤ እነሱ እንደ አማራጭ የሚያቀርቧቸው ሃሳቦችም ካሉ አድምጦ የሚያስማማ ከሆነ ያንን ማድረጉ የተሻለ ነው፡፡ በሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ችግር ሲያጋጥም የሚቀድመው በውይይት መፍታት ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያና ቻይና የተፈራረሙት ስምምነት አለ፡፡ የቻይና ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኢንቨስተሮች በቻይና የሚስተናገዱበት መንገድ እኩልና ከአድልኦ የፀዳ ነው ይላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት ችግር ሲከሰት የሚቀድመው በውይይት እንዲፈታ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ኤምባሲዎችን አሳትፎ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ እንዲሰጡት ማድረግ ነው፡፡ የመጨረሻው የግልግል ጉባኤ እንደ መጨረሻ አማራጭ ተቀምጧል፡፡ ዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ግጭት አፈታት ማዕከል (ኢክሲድ) ይባላል፡፡ በዚያ ተቋም አማካኝነት ግለሰብ ኢንቨስተሮች የኢትዮጵያን መንግስት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሊከስሱ ይችላል፡፡ ዋሽንግተን ሄደው በዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፍርድ ቤት የመክሰስ መብት አላቸው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነት ውስጥ የገባበትን የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት ሊያከብርና ሊያስፈፅም ባለመቻሉ፡፡ በተለይ መንግስት ኢንቨስተሮችን ከጥቃት መጠበቅና መከላከል ባለመቻሉ ጉዳት እየደረሰባቸው ነወ፡፡ እንዲህ አይነት አገራዊ ችግር ሲከሰት በተለይ ዞኖችና ወረዳዎች ከጥቃት ሳይከላከሉ መቅረታቸው ትልቅ የኢንቨስትመንት መብት ጥሰት ነው:: በእርግጥ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት፤ ኢንቨስተሮቹ ቀጥታ ወደ ግልግል ጉባኤ መሄድ የመጨረሻው አማራጭ በመሆኑ ከመንግስት ጋር መወያየትና መመካከር ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ሃላፊዎች የኢንቨስተሮችንና ኢንቨስትመንቶችን ደህንነት ጥበቃ በተመለከተ ዘላቂ መፍትሄ በአስቸኳይ  መፈለግ አለባቸው፡፡ ጉዳት የደረሰባቸው ከጉዳታቸው የሚያገግሙበትና የመፍትሄ አቅጣጫ የሚፈልጉበት እንዲሁም ተመሳሳይ ውድመት ዳግም እንዳይከሰት ዋስትና በመስጠት ኢንቨስተሮችን ከጥርጣሬ በማውጣት የእርግጠኝነት ስሜት እንዲፈጠርባቸው ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል፡፡ አለበለዚያ ግን መንግስት መሰረታዊ ግዴታዎቹን አልተወጣም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ኢንቨስተሮች ይህ ሁሉ ውድመት ደርሶብን ከፍተኛ የመንግስት አካላት መጥተው እንኳን አላፅናኑንም ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ በቅርበት የማውቃቸው በዝዋይ፣ ቡልቡላና አዳሜ ቱሉ አካባቢ ያሉ ኢንቨስተሮች፡፡ ሌላው ቀርቶ የክልል ወይም የዞን አመራሮች ቦታው ድረስ ሄደው ምን ያህል ተጐዳችሁ ብለው አይዟችሁ እንኳን አላሏቸውም፡፡ ይሄ ኢንቨስተሮቹን ተስፋ ያስቆርጣቸዋል፡፡ አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ኢንቨስተሮች ንብረታችን የወደመው ፖሊሶች ቁጭ ብለው ቁርስ እየበሉ ባሉበት ነው ብለውኛል:: ላንጋኖ የሚገኝ የአንድ ሎጅ ባለንብረት ናቸው ይህን የነገሩኝ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ፖሊሶች ሎጁ ውስጥ ቁጭ ብለው ቁርስ እየበሉ ነው ነውጠኞቹ መጥተው ነው ድራሹን ያጠፉት:: ይህን ሁሉ ስትመለከቺ የቁልቁለት ጉዞ ላይ መሆናችንን ትገነዘቢያለሽ፡፡ የወረዳና የዞን አመራሮች ለሁሉም ሲሉ፣ የአካባቢው ማህበረሰብም ለራሱ ሲል ኢንቨስትመንትን የማይጠብቅ ከሆነ፣ ነገ ልጆቹ ለማኝ ነው የሚሆኑት:: የሥራ እድል ከየት ይመጣል? ቢማሩም ባይማሩም ጐዳና ላይ ነው የሚወጡት፡፡
አንድ እውነት ልንገርሽ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት በአጠቃላይ የቀጠረው ሰራተኛ 1 ሚሊዮን፣ ቢበዛ 1.5 ሚሊዮን ቢሆን ነው:: ተወደደም ተጠላም ትልቁ የስራ እድል ፈጣሪና ቀጣሪ የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ታዲያ የሥራ እድል የፈጠረለትን ኢንቨስተር ማህበረሰቡስ ቢሆን ለምን አይጠብቅም? መንከባከብም ጭምር ነው ያለበት፡፡ የግል ዘርፉን እያወደሙና እያቀጨጩ ወጣቱን ምን ሊያደርጉት እንዳሰቡ አይገባኝም:: በየዓመቱ የሚመረቀውን ተማሪ ወዴት ሊወስዱት እንዳሰቡም አላውቅም፡፡ ይሄ በጣም ያሳዝናል፡፡
በተለይ የዞንና የወረዳ አመራሮች በጣም በጣም አስቸጋሪና የኢንቨስተሮችን ህይወት ሲኦል የሚያደርጉ በመሆናቸው በክልልና በፌደራል መንግስት ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ኢንቨስተሩ እዚህ መምጣቱን ትቶ ኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ወደ ሌሎች የተሻለ ሰላምና ፀጥታ ያሉባቸው አገራት ይሄዳል:: በቅርቡም ይህንን ያደረጉ ኢንቨስተሮችን አውቃለሁ፡፡
በመጨረሻ መናገር የምፈልገው፣ ወጣቱ አገሩን የሚያወድመው የት ሊኖር ነው? ይሄ የተቃውሞ ሰልፍ ሳይሆን አይን ያወጣ ዘረፋና ቅሚያ ነው፡፡ በዚህ ላይ መንግስት ከፍተኛ ስራ መስራት ይገባዋል፡፡ ሕብረተሰቡም ዘራፊና ቀማኛዎችን በጉያው አቅፎ ከመያዝ አውጥቶ ለህግ ማቅረብ አለበት፡፡ አለበለዚያ ነገም ተመሳሳይ ጥፋት  ላለመደገሙ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡    


Read 1785 times