Saturday, 18 July 2020 15:55

የሽንኩርትን ‘ምሳሌነት’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ክረምቱ ምነው ገና ከመጀመሪያው ወራት እንዲህ ጨከነሳ! ብርዱ ከአሁኑ እንዲህ “እትቱ በረደኝ…” ያሰኘን ነሀሴን አንዴት እንደምንወጣው እሱው ነው የሚያውቀው:: ሻይ ማግኘት ፈተና የሆነበት መአት ሰው ባለበት… አለ አይደል… አንድ ሰሞን ‘ወተት ለጤና ጥሩ ስለሆነ በየቀኑ ጠጡ…” ምናምን የሚሉ የህንጻ ግንብ የሚያካክሉ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ከተማዋን ሞልተዋት ነበር…ወተት ጠቃሚ መሆኑን አናውቀው ይመስል! ይልቅ ወተቱን አይደለም በየቀኑ በሳምንት አንድ ቀን የምናገኝበትን መንገድ  ቢነግሩን አሪፍ ነበር:: እናማ…ምን ለማለት ነው አደራ “ለብርዱ መከላከያ በቀን ሦስት ብርጭቆ ጠጡ” ምናምን እንዳትሉንማ!
ስሙኝማ… ይቺ ሽንኩርት እንዲህ የካምቦሎጆ ኳስ ታድርገን! በዚህ ላይ የተፈላሳፊው ብዛት! “የሽንኩርት ዋጋን ማረጋጋት የሚቻለው እንዴት ነው ትላለህ?” ይሄ እንግዲህ ቅሽም ያለ የእኛ ቁጥራችን በብዙ እጥፍ እየበዛ ያለነው የቀሺሞች ጥያቄ ነው፡፡ እሱዬው ግን በአይ.ኪው ብዙ እጥፍ ስለሚበልጠን እንደ እኛ ማሞ ቂሎ ምናምን ነገር አይሆንም፡፡
“ስለ ዋጋ መረጋጋት ከመነጋገራችን በፊት መቅደም ያለበት ነገር አለ…”
“ለምሳሌ…?”
“ለምሳሌ የሽንኩርት ዋጋ እንዲህ ዓቢይ አጄንዳ የሚሆነው ይህን ያህል ለህይወት አስፈላጊ ሆኖ ነው ወይ የሚለውን መመለስ አለብን፡፡” ማን የሚሉት ፈላስፋ ነው ለእኩለ ሌሊት አምስት ጉዳይ ሲል የመጣብን!
“ይሄ ጥያቄ መነሳት አለበት እንጂ ሽንኩርት አስፈላጊ መሆኑን ማንም ያውቃል::" ይሄ ሰውዬ ተናግሮ ሊያናግረኝ ነው እንዴ!
“አስፈላጊ ሊሆን ይችላል ግን ወሳኝ ነው ወይ?” ወይ ጣጣ፡፡ እኛ ካለፉት ሰባት ቀናት በአምስቱ የሽንኩርት አስተዋጽኦ ሰማንያ አምስት ፐርሰንት ቀንሶብናል፣ ይፈላሰፍብኛል እንዴ!
“ልትለው የፈለግኸው ነገር  እስካሁን  አልገባኝም፡፡”
“ምን መሰለህ ሽንኩርትን እንዲህ አስፈላጊ እንዲሆን ያደረገው የእኛ ዘመናዊ ያልሆነ አመጋጋብ ከሆነስ?” ሒድ ወዲያ! ምን ሰው ያናግራል! አሀ…እኔ  ገና ለገና ሦስት ፍሬ ድፍን ምስር ገባች ብሎ ሆዴ መከራዬን እያበላኝ ነው አቧራ ያቦንብኛል እንዴ!
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ምን ስልችት አለህ አትሉኝም…ፈላስፋ በዛ! በጣም በዛ! በቦተሊካው፣ በስነጥበቡ፣ በእለታዊ ኑሮው ፈላስፋ በዛ፡፡ ኑሮ ሲከብድ ያፈላስፋል የሚባለው እውነት ነው እንዴ! እንደዛ ከሆነ ምነው እኛ አንፈላሰፍ! ምነው የተባበሩት መንግሥታት ወይ የሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት የኛ አገርንም የዘመናዊ ፈላስፎች አገር አይላትም!
“አየህ እኛ ኦልተርኔቲቩን መፈለግ ሲገባን ሽንኩርት ላይ ስለተጣበቅን ሽንኩርት የዋጋ ጭማሪ ቪክቲም ሆነ፡፡”
አንተ ሰውዬ ምን አለ ዝም፣ ጭጭ ብትል! የራሴ ሰይጣን የት እንዳለ ገና ስላልደረስኩበት ከሌሎች ተውሼ “ሰይጣኔን እንዳታመጣብኝ!” ካልኩ እኔም ፈላስፋ ሆኜ ቦታ እንዳላስለቅቅህ! (ያው “በናፍቆት ይጠበቅ የነበረው ፈላስፋ በአደባባይ ተሳትፎውን መጀመሩን ስንገልጽ ደስታ ይሰማናል…” ምናምን ነገር ይባልልኝና ቴሌቪዥን ላይ አርባ ሰባት ጊዜ፣ ሬድዮ ላይ ሠላሳ ዘጠኝ ጊዜ መቅረቤ አይቀርም፡፡ ደግሞ ከአንድ መቶ ዝግጅቶች ውስጥ በዘጠና ሰባቱ በክብር  እንግድነት መጠራቴም አይቀርም:: አሀ…እዚህ ሀገር ‘ፌም’ ብዙ ሳታለፋ ትገኛለቻ!)
እኔ የምለው፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በሆነ ነገር ተበሳጭቶ “አንቺ ሴት ሰይጣኔን አታምጪው!” ብሎ የሚፎክር አባወራ እኮ በል አንድ፣ በአንድ ተናገር ሳይሉት የሚናዘዝ አይነት እኮ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ቢያንስ እኮ አንድ ነገር አምኗል ማለት ነው፡፡ “ምን?” ብትሉኝ…  ሰይጣን እንዳለበት ነዋ! ቂ…ቂ…ቂ… ታዲያ መቼም የሌለ ነገር እንዳታመጪብኝ አይል! ልክ እኮ በቴክስት ሜሴጅ ወይ ምናምን ስማ “ሰይጣኔ፣ የእኔ ሰይጣን… ለጉዳይ ስለምፈልግህ አሁኑኑ ኮንትራት ታክሲ ይዘህ ናልኝ!” ብሎ የሚጠራው ነው የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “በህልሜ ሽንኩርት ስልጥ አየሁ፣” ቢባል… አለ አይደል… “ጠንቀቅ በይ ሊልጥሽ የሚፈልግ ሰው አለ ማለት ነው” ይባል ነበር፡፡ ወይ ደግሞ እንደ እኔ አይነቱ…ወዶ ገብ ህልም ፈቺ… “ሽንኩርት የጥሩ ነገር ምልክት ነው፡፡ ግን ደግሞ እሱን ከሚያሳይሽ የአቮካዶ ጁስ ስትፈጪ ቢያሳይሽ ኖሮ ጥሩ ነበር!” አይነት ነገር ሊባል ይችላል፡፡ ዘንድሮ ህልሙም፣ ፍቺውም ሳይለወጥ አይቀርም፡፡
“ስሚ ዛሬ ሊሊት የሚገርም ህልም አላይ መሰለሽ!”
“ምን ስታደርጊ አየሽ?”
“በትልቁ የድግስ ወጥ መስሪያ ድስት ሽንኩርት እስካፉ ሙልት ብሎልሽ አንድ በአንድ እያነሳሁ ስልጥ፡፡”
እናላችሁ…እንደ ቀድሞ ቢሆን… “እንኳን ደስ አለሽ፣ ቆጥረሽ የማትጨርሺው ሲሳይ እቤትሽ ሊገባ ነው…” ይባል ነበር፡፡ ግን ደግሞ ዛሬ ‘ቀድሞ’ አይደለም፡፡ የተቀደደውን ከመስፋት ይልቅ ደህናውን የምንቀድ የበዛንበት ዘመን ነው፡፡ ዋናው አውራ ጎዳና ፊት ለፊታችን ወለል ብሎ በውስጥ ለውስጥ ኮረኮንች ላይ መሄዱ እየተሻለን የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ 
“ጎሽ የእኛ ዘመናይ፣ ዋጋው አልቀመስ ባለ ሽንኩርት ላጥኩ ማለትሽ ሳያንስ ጭራሽ በድግስ ድስት ሙሉ!;
“ምን ችግር አለው! ደግሞ ህልሙን ፈልጌ አላመጣሁት…”
“ነው ወይስ ልትይ የፈለግሽው ሌላ ነገር ነው?”
“ምንድነው ሌላ?”
“ሌላ ነገርማ እናንተ በእውናችሁ ያጣችሁትን ሽንኩርት እኔ በህልሜ እየተጫወትኩበት ነው ማለትሽ ነው!” ኸረ ጡር አለው! ባለ ህልሟም ብልጭ ይልባታል፡፡
“ድሮም አንቺን ሰው ብዬ ማውራቴ!” በቃ ይሄ ማለት ዬት ሀገሩን ልዑል ነገር ለሽ አድርጋ፣ የአንደኛው ዓለም ጦርነት ነው ምናምን የሚሉትን ያስጀመረች በሏት፡፡
“አንቺን ሰው ብዬ ስትይ ምን ማለት ፈልገሽ ነው፡፡ እናንተ ብቻ ናችኋ ሰዎች! ስሚ እኔ ክፉ ነገር መናገር ስላልፈለግሁ እንጂ…!”  (ማለቂያ ስለሌለው በ‘ሲዝን ቱ’ እንገናኝ፡፡)
እሷስ ካልጠፋ የሚላጥ ነገር እንዴት ነው ያውም በህልሟ ሽንኩርት ስትልጥ የምታየው! ለነገር ካልሆነ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
የእውነት ግን ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ህልም ማየት ቀረ ወይስ አገር ከባድ የሆነ የህልም ፈቺዎች እጥረት ገጠማት?
“ስሚ የሚገርምሽ ነገር፣ ትናንት በህልሜ አላይሽ መሰለሽ!”
“አትለኝም!”
“ይኸው ካንቺ ይነጥለኝ…” እጇን ሳብ አደርጎ ጯ!
“መቼም ያየኸው ደህና ነገር እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡”
“መሀል ላይ ተቋረጠ እንጂ! እውነቱን ልንገርሽ፣ በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠዋት ከእንቅልፍ መንቃቴን ረገምኩት፡፡” ኸረ እባከህ ሩጫውን ቀንስ! በኋላ አዳልጦህ ዘጭ ብለህ በጀርባህ ያረፍክ እንደሆነ የምታየው በህልምህ እሷዬዋን ሳይሆን በጀርባህ እንደተንጋለልክ በእውንህ የቀለማት አይነት አየሩ ላይ  የ‘ኒው ይር’ ርችት ሲሆኑብህ ነው::
እኔ ምለው… ነጋዴዎቻችን እንዴት ነው የሚያስቡት! ምናለ ከጊዜ ጋር አብረው ትርፍ ፈራንክ ማሳደድ ብቻ ሳይሆን ትርፍ ደግነት ቢኖራቸው፡፡ ሀገር በስንት ወገን በተወጠረችበት ጊዜ ይህን ያክል “ሁሉም ለእኔ!” ባህሪይ ምንድነው! ስንቱ ባለሀብት “ከህዝብ የሚበልጥ የለም” በሚል ህንጻውን፣ ንብረቱን “ለወረርሽኙ መከላከያ ይሁን…” እያለ የሚሊዮኖች ብር እገዛ ያደርጋል፤ ሌላው ደግሞ አግኝተን ባልላጥነው ሽንኩርት እንድናለቅስ የሚያደርገን ለምንድነው! (በነገራችን ላይ ሽንኩርት የሆነ ኢቮሊዩሽናዊ ለውጥ አድርጋ ስትላጥም፣ ሳትላጥም ማስለቀስ መቻሏ የተለየ ‘ስታተስ’ አሰጣት ማለት ነው!)
እናማ... ሽንኩርት ፊትአውራሪነቱን ትያዝ እንጂ…የሽንኩርትን ‘ምሳሌነት’ የሚከተሉ ምርቶች እየበዙ ነው፡፡ ኪሎ ሽንኩርት በ‘ሦስት ብር ተሀምሳ’ የምንሸምትበትን ዘመን ያቅርብልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 1841 times