Print this page
Saturday, 18 July 2020 15:52

መልዕክቶቻችሁ

Written by  ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
Rate this item
(1 Vote)

   ኢትዮጵያን ብሎ ዐቢይን ጥሎ?
             
             በፊታችን ያለው መንታ መንገድ፥ አንዱ መንገድ ዶ/ር ዐቢይን እየደገፍን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል የምንሄድበት መንገድ ነው፥ ሌላኛው ኢትዮጵያን ለመበተን ሌሎች የሚሄዱበት መንገድ ነው። ከዚህ ውጭ ሦስተኛ መንገድ ሊኖር አይችልም።  የውስጥ ልዩነታችንን በምርጫና ምርጫ ብቻ እንዳኘዋለን። ከዚያ ባለፈ ራሱን ዶ/ር ዐቢይን እንሞግተዋለን እንጂ በስመ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ አንጮህም። ምክንያቱም ሦስተኛው መንገድ አንድነት እንዳይኖር ውዥንብር የሚፈጥር ነውና አይጠቅመንም።  ወደምንናፍቀው ከፍታ ኢትዮጵያን በቤተሰብነት አውድና ብልፅግና ውስጥ ሊያስገባት የሚያስቸለው መንገድ ራሱ ዶ/ር ዐቢይ ባይሆን እንኳን ለዚያ በሚያበቃ ቁመና እንድንደርስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ምርጫ ያደርሰናል።
ዶ/ር ዐቢይን ዛሬ ዛሬ የሚደግፈው ሰው አማራን ይበልጥ የሚወድ፥ ወይም ኦሮሞን ይበልጥ የሚወድ፥ ወይም ሌላ የራሱን ብሔር አብልጦ የሚወድ ወይም ኢትዮጵያን የሚወድ ሊሆን አይችልም። ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል? ብንል ከአጀማመሩ እንመልከት። የዶ/ር ዐቢይን ንግግር ሰምቶ ያልወደደው ፍጡር የለም ማለት ማጋነን አይደለም። ንግግሩ ከሰብዕናው የወጣና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ራዕይ ሰንቆ፥ አርቆ በማየት ምን ማድረግና ምን መሆን እንደምንችል ፍንትው አድርጎ ሲተርክልን ያልተማረከ አልነበረም። ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉንም አስታርቆ፥ ዲሞክራሲን ላዋልድ ብሎ በጎነቱ ድክመቱ ቢሆንበትም ቅንነቱ ታይቶ፥ ተረት ተረት የሚመስለው የኤርትራ ዕርቅ እውን ሆኖ የኖቤል ሰላም ሽልማት አስጨብጦት፥ ጉድ ድንቅ እየተባለ ሳለ፥ ግና ተራ በተራ በየፌርማታው ወራጅ አለ እየተባለ ዛሬ መንታ መንገድ ላይ ደረስን።
በመጀመሪያ በእርቅና መግባባት ፍቅር ማውረድ ሲቻል ሆን ተብሎ የታሪክ ዕዳ በጥላቻ ማወራረድ ተመረጠ። ሲቀጥል በሕወሃት ሃያ ሰባት ዓመታት አብሮነታችንን የሚሸረሽር መሠሪ ትርክት በትውልድ ላይ ተቆመረ። ይህ ሳያንስ በተለያየ አቅጣጫ ሁሉም በየብሔሩ ጎራ ተሰልፎ ዶ/ር ዐቢይን ወዲያና ወዲህ ይጎትታል። ያም ሆኖ ዶ/ር ዐቢይ ሁሉንም ያመረቀነውን ራዕይ ወደ ተግባር ለመቀየር በሚሄድበት አዲስ ጎዳና በትልቅ ትዕግስት፥ ከስህተቱም እየተማረ እየነጎደ ይገኛል።  
ለምሳሌ ያህል፥ አንድ ሰሞን አዲስ አበባ የማን ናት ተባለና ተባላን። ጠቅላዩ ጭቅጭቁን ለእኛ ትቶ አዲስ አበባን ማስዋብ ጀመረ።  አብሮነታችንን፥ ታሪካችንን፥ የተፈጥሮ ፀጋችንን ባማከለ ሁኔታ ምን ልንሆን እንደምንችል በአዲስ አበባ ከተማ ዘወትር በሥራ እየታተረ ይገኛል። በጊዜ ሂደት ልብ እንደምንገዛና አብሮነታችንን እንደምናገዝፍ በራዕዩ ሃይል የታመነ ይመስላል።  ዶ/ር ዐቢይ የኦሮሞን ጥያቄ አልመለሰም ብለው የኦሮሞ ልሂቃን ይዋጉታል። ሌሎችም በብሔራቸው ቆመው እንደዚሁ ያደርጋሉ። የሚገርመው የዶ/ር ዐቢይ አካሄድ የዛሬን ጥያቄ መመለስ ብቻ ሳይሆን፥ የነገን ጥያቄ በመመለስ ሂደት ላይ ጭምር ነው። ተላለፍን።
እኛ ተፈትነን ስናንገራግር፥ የኢትዮጵያ አምላክ ዶ/ር ዐቢይን እስካሁን ረድኤቱን አልሰሰተበትም። ወደቀ ስንል እየተነሳ፥ ኢትዮጵያ ጠፋች ስንል እያመለጠች፥ አባይም እየተሞላ፥ ወደፊት እየተባለ ነው።  አሁን ላይ ግን ዶ/ር ዐቢይን ለመውደድ፥ አብሮነታችንን መውደድ ብቻ እንደሚጠይቅ አያጠራጥርም። መንገዱ ተራራና ሸለቆ የሞላበት ነው። ተራራው ላይ ስንደሰት፥ ሸለቆ ውስጥ ስናዝን፥ መሄዳችን አሁንም አይቀርም። ግን ዶ/ር ዐቢይን ለመደገፍ መንገዱን ሳይሆን አድራሻችንን (ራዕዩን) ማየት አለብን።  
በደመና ላይ ያንሳፈፈን ራዕይ፥ መሬት ሲወርድ ውጣ ውረድ አለው። በዚህ ላይ ሰው ነውና የዶ/ር ዐቢይ ድክመት ተጨምሮ፥ ብዙ ፈተና አለው።  በተጨማሪ ይህ ጉዞ ብዙ ጠላቶች መንገድ ላይ ሊያስቀሩን ምሽግ ይዘው የሚዋጉን ጭምር በመሆኑ እጅግ አድካሚ መሆኑ የታወቀ ነው።  ታዲያ መዳረሻችን የሆነው ራዕይ ለሁላችንም የምትበቃ ብቻ ሳይሆን፥ ለአፍሪካና ለዓለም የምትተርፍ ኢትዮጵያን ለማየት ዶ/ር ዐቢይን መደገፍ ኢትዮጵያዊነት ነው። ምርጫችን አብሮነታችን ይሁን። የአብሮነታችን መንገድ ደግሞ ዶ/ር ዐቢይ ነው። ስለዚህ ያለ ምንም ማመንታት መደገፍ ይሁንልን። ስናመነታ እንዳንመታ። ፈጣሪ እንደሆነ ለኢትዮጵያ መድረሱን ቸል ብሎ አያውቅም። እኛ የድርሻችንን እንወጣ።

Read 1591 times