Tuesday, 21 July 2020 00:00

ብዙ መቶዎች “መታሰቢያ” ይሻሉ!!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ አገራዊ በሽታ ምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ዛሬም አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥትና ምሁራን በተደጋጋሚ ዋናው የአገራችን ጠላት በኢኮኖሚ አለማደጋችንና  የሥራ አጡ ቁጥር መብዛት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የለማው እየወደመ፣ የእነ እከሌ ንብረት ነው ተብሎ እየተቃጠለና እየፈረሰ እንዴት ተብሎ  ነው ሃብትና ንብረት ማፍራት የሚቻለው? አገሪቱ ድህነቷንና ኋላ ቀርነቷን ከማጥፋቷ በፊት ሊያጠፋት የደረሰው  የቅርብ ጊዜ ጠላቷ  - ዘረኝነት ነው ብል አልተሳሳትኩም፡፡
ዘርና ዘረኝነት መቀላቀል የለባቸውም፡፡ ዘር ስል ለእኔ የሚገባኝ፣ ዋና መስፈሪያው ቋንቋ የሆነ፣ በአንድ አካባቢ የሚኖርና የአንድ ቋንቋ ተናገሪ  ኅብረተሰብ ነው:: ያ ኅብረተሰብ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ከምባታ፣ ጋሞ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ የአንድ ብሔረ ሰብ አባልን ከሌላው ተለይቶ  እንዲታይ የሚያደርገው ከሰፈረበት መሬት በላይ አፉን የፈታበት ያካባቢ ቋንቋና ባህሉ ነው:: ከተወለደበትና ካደገበት ወጥቶ ከወደ ሌላ አካባቢ ቢሄድ፣  ሰው ሆኖ ከተወለደበት መንደርና ቀበሌ በላይ ዘሩ ተከትሎት ይሄዳል፡፡ በዚህ ዘመን አንድ ሰው መቀሌ ላይ ኖሮ ቢያረጅ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሐረሪ ወዘተ… ተብሎ ያረጃል እንጂ ከትግሬ እንደ አንዱ ሰ ው አይቆጠርም:: በኢትዮጵያ ምድር በተዘራው ዘረኝነት የተነሳ የሚጠበቀውም ይህ ነው፡፡
ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በዚህ ዘረኛ ዘመን፣ አንድ ትግርኛ ወይም አማርኛ ተናጋሪ፣ የነቀምት ኗሪ ሆኖ፣ ልጁ በአሮምኛ አፉን ቢፈታም፣ ኦሮሞነት ሲያምረው ይቀራል እንጂ ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል ኦሮሞነትን ሊያገኝ አይችልም፡፡  እንዲህም ሆኖ በዚህ የዘር ዘመን፣  የዘር መዋሐድ እንደ ቀደመው ፈጣን ባይሆንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ዘር የአገራችን የፖለቲካ ማጠንጠኛ መዘውር ሆኖ እያሾመ እያሸለመ ቢገኝም፣  በምንም አይነት መመዘኛ ዘር ምርቃትም እርግማን ሆኖ ሊታይና ሊቆጠር አይገባውም፡፡  የተለየ ፀጋ ሆኖም መታየት ፈጽሞ የለበትም፡፡ እንቶኔ የተባለ ዘር መኖሩ እንደ ሌላው ሁሉ ዝም ብሎ መኖር እንጂ የተለየ ነገር  አይደለም፡፡ በግልጽ እነጋገር - አንተ፣ እኔ፣ እሱ፣ አሷ ወይም እነሱ ኦሮሞ፣ አማራ፣ አኝዋክ ወይም ሲዳማ የሆንነውና የሆኑት፤   ልክ ሌሎች ጉራጌ፣ ኮንሶ፣ ሐመር ወይም ዳሰነች እንደሆኑት በመሆኑ፣ ልዩ ነገር ተደርጎ የሚታይ አይደለም፡፡ በሕዝብ ብዛት አንዱ ከሌላው ከፍና ዝቅ ቢልም፣ ተወደደም ተጠላ  የዘር ትልቅም ትንሽም የለውም፡፡
ዘረኝነት የመጀመሪያ ተግባሩ  የራሱን  ዘር ከሌላው መለየት፣ ከሌላው የላቀ አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡ ሌላው ዘር  ከእርሱ ዘር እንዳይቀላቀል የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ቀጣይ ሥራው ነው፡፡ የእርሱ ዘር ያልሆነ የመኖር መብት እንዳለው መቀበል ሳይቀር ይከብደዋል፡፡ በአንድ አጋጣሚ የእርሱ ዘር ከሚኖርበት የገባ ከሌላ አካባቢ የመጣ ዘር፣ የቆይታ ዘመኑን በሥጋትና በፍርሐት የተከበበ እንዲሆን ያደርግበታል፡፡ እስከ 2010 ዓ.ም መጋቢት ወር ድረስ በመንግሥት ተደግፎ በመላው ኢትዮጵያ ሲሰበከና ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው አስተሳሰብና አሠራር፣ ይህ የዘረኝነት መንገድ መሆኑ  የታወቀ ነው፡፡ የዚህ ዘመን ሰው በሰውነቱ ቦታና ዋጋ ሊያገኝ ሊኖር ሲገባ፣ ዘሩ እየተመዘዘ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ ወይም ነባርና መጤ ተበሎ የሚፈረጅበት፣ መጤ የተባለው ቢጮህ የማይሰማብት መሆኑም ድብቅ አይደለም፡፡
ማንም ሰው የአእምሮ ጤንነት ችግር እስካልገጠመው ድረስ ዘር የሚባል ነገር መኖር የለበትም ወይም እንቶኔ የተባለ ዘር መጥፋት አለበት ብሎ ሊነሳ  አይችልም፡፡ ዘረኝነትን ግን መጥላትና መቃወም ይችላል::
አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት፣ ዘርን መሠረት አድርጎ በፖለቲካ መደራጀት  የተከለከለ አይደለም፡፡ ከ1983 ዓ.ም ግንቦት ጀምሮ በክልልም ሆነ በፊዴራል የመንግሥት ሥልጣን ይዘው የቆዩት የፖለቲካ ድርጅቶች በዘር የተደራጁ ናቸው፡፡ በመካከላቸው ዋናና ተራ ወይም አጋር የሚባል አሰላለፍ እንደነበራቸውም አይዘነጋም፡፡ የምርትና የግርድ ወይም የመሪና ያጃቢ ግንኙነቱን በማፍረስ በክልልም ሆነ በፌዴራል የሚገኙ ገዥ ፓርቲዎች “ብልጽግና" የሚባል ፓርቲ መሠረቱ፡፡ እንዲህ መደረጉ የእያንዳንዱን የፓርቲ አባል የዘር መሠረት ባያጠፋውም፣ መጥፋትም ባይኖርበትም  አስተሳሰቡንና አሠራሩን ከዘሩ  ያርቀዋል የሚል ተስፋ አሳድሮ ነበር፡፡ በኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በቢኒሻንጉል ወዘተ የሚኖር የሐድያ፣ የጌዲዎ፣ የትግራይ ወዘተ ሰው  “ዘርህ ከየት ነው?” ሳይባል በሚኖርበት አካባቢ  የፓርቲው አባል ሆኖ፣ በአገሩ ፖለቲካ የሚሳተፍበት ቀን መጣ ብዬ በግሌ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ በመንግሥት እጅ ባሉት የራዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሳይቀር፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ፣ የትግራይ ብልጽገና ፓርቲ፣ የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ ወዘተ... የሚል አጠራር  ስሰማ ግን ብልጽግና ተዋሐደ ወይስ ተለጣጠፈ? ብዬ እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡
የክልል መንግሥታት መሪዎች፣ በብሔረሰባቸው ተደራጅተው ሥልጣን የያዙ በመሆኑና ሊያገለግሉት የተሰለፉት ብሔራቸውን በመሆኑ ስለ ምን ታደላላችሁ? ብሎ መጠየቅ ያስቸግራል፡፡ ባንጻሩ በፊዴራል ደረጃ በሚገኙ ባለሥልጣናት ላይ ግን እንዲህ አይነቱን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አዲስ አበባን እንደ ዋና ከተማ የሚጠቀም ቢሆንም፣  አዲስ አበባ በዋናነት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ናት፡፡ የአፍሪካም መዲናነቷ ሳይዘነጋ፡፡ ኢንጂነር  ታከለ ኡማ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ናቸው:: አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጉት ማንኛውም ተግባር የሚታየውና የሚመዘነው ባላቸው የፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተማ የከንቲባነት ሥልጣናቸው መሠረት ነው፡፡
የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ለእኔ ተራ የአንድ ሰው ሕይወት የማጥፋት ተግባር አይደለም፡፡ የእሱን ግድያ እንደ አብሪ ጥይት ተኩስ በመጠቀም ቀደም ብሎ የተደራጀው ኃይል፣ በየአካባቢው በሚገኝ ከተማ ነዋሪዎች  ላይ ጥቃት ለመሰንዘርና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የታለመ ሴራ ነበር።  በአዲስ አበባ አንዳንድ ሰፈሮች፤ በዝዋይ‹፣ በሻሸመኔ፣ በአሩሲ ነገሌና በሌሎችም አካባቢዎች በሰዎች ሕይወትና ንብረታቸው ላይ ጥፋትና ውድመት ተፈፅሟል:: ዝዋይ ላይ አቶ ገለታው አውላቸው የተባሉ ሰው ከአምስት ቤተሰቦቻቸው ጋር ተገድለዋል:: የብዙ ሰዎች ንብረት የተዘረፈው ተዘርፎ ሌላው የእሳት እራት ሆነ፡፡ አገርና ሕዝብ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ሲቪልና የፖሊስ አባላት  ወገኖቹን፣  በቢሊዮን ብር የሚገመት ሃብትና ንብረቱን አጣ፡፡ ዘር ተኮር በሆነው በዚህ ጥቃት ውስጥ ግን ከዘረኝነት መንፈስ የራቁ የዚያው አካባቢ ሰዎች፣ የብዙ ወገኖቻቸውን ሕይወት ለመታደግ ችለዋል:: ለእነሱ ልባዊ ምስጋናና አከብሮቴን አቀርባለሁ፡፡
በሴራ ሕይወቱን ለተነጠቀው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ እንዲሆኑ በአዲስ አበባ ሁለት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ድልድይና አደባባይ በስሙ ተሰይመዋል፡፡ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፊት ለፊት ሐውልት እንደሚቆምለትም ተገልጿል:: ይገባዋል! የአሁኑ ትውልድ ብዙ እንደ ሃጫሉ ያሉ በአርአያነት የሚከተላቸውና የሚነቃቃባቸው ጀግኖች ያስፈልጉታል፡፡ በዚህ መንገድ ብቻ ነው ከአጥፊነት ይልቅ አልሚነትን የሚመርጥ ትውልድ መፍጠር የምንችለው።
ለእትጌ ጣይቱ ብጡል፣ ለባሻ አዋሎም፣ ለራስ መንገሻ ዮሐንሰ፣ ለራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ፣ ለቀኛዝማች ኡመር ሱመትር፣ ለደጃዝማች በቀለ ወያ፣  ለጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተ ወልድ፣ ለጀኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ ለሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን፣ ለጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ለደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ለቀኛዝማች ከድር ኤባ፣ ለቤትወደድ ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ወዘተ. እንደ ዋና ከተማነቷ አዲስ አበባ ምን አደረገችላቸው? ብለው ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እንዲጠይቁ ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ፡፡
የሐብተ ጊዮርጊስ ድልድይ፣ በፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ የተሰየመው መኖሪያ አካባቢያቸው ስለነበረ እንጂ ታስቦበት አልነበረም፡፡ ባልቻ ሆስፒታልም ቢሆን ሆስፒታሉ የተሠራበት አካባቢ  የደጃዝማች ባልቻ ሰፈር ስለነበርና ቦታውን የሠጡት ቤተሰቦቻቸው ሰለነበሩ መሆኑን ሰምቻለሁ:: የመርካቶው አመዴ ገበያ ለፊታውራሪ አመዴ ለማ መንግሥት ያቆመላቸው ሳይሆን፤ ከልጃቸው መሐመድ አመዴ ሱቅ ተወስዶ ሕዝብ ያጸደቀው መሆኑ መታወስ ይኖርበታል:: ስለዚህ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ወደ ኋላ መለስ ብለው ለሃገሪቱ የተለያዩ ብሔራዊ ጀግኖች ሐውልት እንዲያቆሙላቸውና መንገድ እንዲሰይሙላቸው አደራ እላለሁ:: ትውልዱም ለታሪክ ዋጋ እንዲሰጥና ታላላቆቹን (አባቶቹን) የማክበርና የማድነቅ ባህል እንዲያዳብር ያግዘዋል። ይህን መንገድ አጥብቀው ይግፉበት እላለሁ፡፡
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ፣ በሃጫሉ ሁንዴሳ ሰም  በተወለደበትና ባደገበት ከተማ አምቦ ላይ አዳሪ ትምህርት ቤት እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡
የሚሰራው አዳሪ ትምህርት ቤት “በየመንደራችን ቆመን የት አባህ፣ የት አባህ መባባል የትም አያደርሰንም” የሚለውን የሃጫሉን ሃሳብ ወደ ተግባር የሚለውጥ፣  ከመላው ኢትየጵያ የሚመጡ ተማሪዎች የሚማሩበት የልህቀት ማዕከል (Excellemce Center) እንደሚሆንም  እምነቴ የፀና ነው። የሃጫሉ መታሰቢያ አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የዘመናችን ዊንጌት ሆኖ ለማየት ያብቃን!!!
አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ለክቡር ከንቲባው ላቀርብ እወዳለሁ፡፡ የአርቲስት ሃጫሉን ድንገተኛ ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያን ወገኖቻችን፣ አንድ መታሰቢያ ያቆሙላቸው ዘንድ አጥብቄ እጠይቃለሁ፡፡ አደራ!


Read 7350 times