Monday, 20 July 2020 00:00

ምህዳራዊ አስተሳሰብ - ለአገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(1 Vote)

 “--በዚህ ጸሃፊ እምነት፤ እስከ ዛሬም ድረስ በፖለቲካችን ውስጥ ስር ሰዶ የሚታየው የመጠፋፋት ፖለቲካ የዚሁ ባላባታዊ ፖለቲካ ቅሪት ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም። ባለፉት ሃምሳና ስልሳ ዓመታት ውስጥ እንዲህ አይነቱን ፖለቲካዊ ጭሰኝነት አንቀበልም ብለው የተነሱ በርካታ ወጣቶች በየራሳቸው ድርጅቶች መቀጠፋቸውም የፖለቲካችን አንዱ አሳዛኝ ገጽታ ነው።--“
         
              እንደ መነሻ
ከሁሉ በፊት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበረው ቀጥተኛ ተሳትፎ በ1966 ተጀምሮ በ1975 ክመጨረሻው የደርግ እስር በተፈታበት ጊዜ ያበቃ ነበር። ላለፉት ሰላሳ አምስት ዓመታት በዋነኝነት በኢንዱስትሪና አካባቢ ምህንድስና መስክ በሀገር ውስጥ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያገለግል ቆይቷል። በዚህ የአገልግሎት ዘመን፣ ውስብስብ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመረዳትና ለመፍታት በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ምህዳራዊ አስተሳሰብ (systems thinking) ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ለመረዳትና በስራ ላይ ለማዋል ችሏል። ባለፉት ዓመታት፣ ምንም እንኳን በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባያደርግም እንደ ማንኛውም ዜጋ የነበረውን ሂደት በስጋትና በተስፋ ሲከታተልና ሃሳቡንም በተናጠል ውይይት ሲያካፍል ቆይቷል። በአጭር አነጋገር ፖለቲካን በሚመለከት ለበርካታ ዓመታት ከዝምተኛው ብዙሃን (silent majority) ውስጥ የሚደመር ነበር ማለት ይቻላል።
በቅርቡ በሃገራችን እየተባባሰ የመጣው የፖለቲካ ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱና ችግሩን ለመፍታት ምህዳራዊ አስተሳሰብ (systems thinking) ሊኖረው የሚችለውን አበርክቶ በመረዳት ይህን በበርካታ ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያ የሆነውን ፖለቲካዊ መጣጥፍ ለፖለቲካ መሪዎቻችንና ለህዝብ ለማካፈል ተነስቷል፡፡ ይህ መጣጥፍ በሶስት ክፍል የተከፈለ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ክፍል የሀገራችንን ፖለቲካ መሰረታዊ ህመሞችና የችግር ምንጮች ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ ይተነትናል። በመቀጠልም በሁለተኛው ክፍል፣ እነኚህን ችግሮች ከምንጫቸው በማድረቅ ወደ መፍትሔ ሊወስዱን የሚችሉትን ዋና ዋና የምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎችን ያቀርባል። በመጨረሻም በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ የሚያስፈልጉንን ዐበይት የአመለካከት ሽግግሮች ከዋና ዋና መዋቅራዊ ችግሮቻችን ጋር በማያያዝ በሶስተኛው ክፍል ለማሳየት ይሞክራል።
የፖለቲካችን ዋነኛ ህመሞች
የሃገራችንን የፖለቲካ ችግሮች በመሰረታዊ ሁኔታ ለመፍታት የመጀመሪያው እርምጃ የበሽታውን ዋነኛ ምንጮች በቅጡ ለይቶ መረዳት ይሆናል። ባለፉት ዓመታት በርካታ ምሁራን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ የተለያዩ ጽሁፎችንና ትንተናዎችን አቅርበዋል። አብዛኞቹ ትንተናዎች የችግሮቹ ዋነኛ መነሻ የአመለካከት መሆኑን በትክክል ያመላከቱ ቢሆንም ህመሙን ከምንጩ ለማከም የሚያስችል የመፍትኼ ሃሳብና አቅጣጫ ማመላከቱ ላይ ውሱንነት ታይቶባቸዋል። በዚህ ጸሃፊ እምነት፤ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት አብዛኞቹ ከሰለጠኑበት የሙያ መስክ ጋር በተያያዘ ከሚከተሉት የተቀነበበ ትንተና (reductionist analysis) ነው። በተለያየ ጥናት እንደተረጋገጠው፤ ከፍተኛ ውስብስብነት ላላቸው ችግሮች እንዲህ አይነቱን ትንተና መጠቀም ከፊል እውነታን ከማሳወቅ ባሻገር መሰረታዊ መፍትሔዎችን የማመላከት ውሱንነት ይኖረዋል። እንዲህ ዐይነቱን የትንተና ውሱንነት መሻገር የሚቻለው በምህዳራዊ አስተሳሰብ በመመራት ብቻ ነው፤ የሃገራችን ዋነኛው የፖለቲካ ችግር የአመለካከት ችግር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ የችግሮቹ ዋነኛ ምንጮች የሚከተሉት ሶስት አበይት ፈተናዎች ናቸው።
ጭፍን እመርታዎች፡ - የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ከዘመናዊው የትምህርት ስርዓት መጀመር ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው። በዘመናዊው የትምህርት ስርዓታችን ውስጥ ያለው አንዱ መሰረታዊ ችግር፣ የትምህርት ይዘቱንም ሆነ አሰጣጡን ከሃገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና ሃገር በቀል እውቀት ክምችት ጋር ለማጣጣምና ለማዋሃድ የተደረገው ጥረት ውሱን መሆኑ ነው። ይህም በመሆኑ የሃገሪቱ የተማረ የሰው ሃይል የሃገሪቱን የልማት ችግሮች ለመፍታት ካለው የእውቀት አቅም ውሱንነት ባሻገር ባብዛኛው ጭፍን የሆነ የድንበር ተሻጋሪ ዘመናዊነት አምላኪነት የተጠናወተው ሊሆን ችሏል። ይህ መሰረታዊ ህመም በዘመናዊው የፖለቲካ አስተሳሰባችንም ላይ በተናጠከረ ሁኔታ ታይቷል። በመሆኑም፣ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ከሃገራዊ እውነታና ተጨባጭ የህዝብ ፍላጎት ጋር የማይጣጣሙ የፖለቲካ አስተሳሰቦችና የማህበረሰብ እድገት ሞዴሎችን በጅምላና በጭፍን ተቀብሎ ማህበራዊ መሰረቱን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ለማራመድና ለመተግበር መሞከር የፖለቲካችን ዋነኛው መለያ ሊሆን በቅቷል፡፡ ይህ ህመም በአሁኑ ወቅትም አብዛኛዎቹ የሃገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች በሚያራምዷቸው የፖለቲካ ፕሮግራሞችና ፖሊሲዎች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሲያሳድር ይስተዋላል። ከተለያዩ ሃገሮች ማህበረሰባዊ ተመክሮና የእውቀት ክምችት መማርና ጠቃሚውን መርጦ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም። ነገር ግን ይህንን እውቀት ከሃገራዊው እውነታና የእውቀት መሰረት ጋር ማጣጣምና ማዋደድ ዘላቂና አስተማማኝ የሆነ እድገት ለማምጣት እጅግ በጣም ወሳኝነት ያለው መሆኑን ባለፉት ሰባ ዓመታት ከፍተኛ እድገት ካስመዘገቡ ሃገራት ልምድ መረዳት ይቻላል።  
የተቀነበበ ትንተና፡-  የዘመናዊው የትምህርት ዘርፍ ዋነኛ መለያ የሆነው የተቀነበበ ትንተና (Reductionist simplification) ባለፉት ሁለት ምዕተ ዐመታት ለነበረው የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ይታመናል። ይህ የትንተና ዘርፍ በአንድ የተወሰነ መስክ ሊገኝ የሚችልን ጥልቅ እውቀት ለማጠናከር ከፍተኛ ድርሻ አለው። ነገር ግን፣ የተለየ ውስብስብነት ያላቸውን የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ከባቢያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመመርመርና ለመፍታት ያለው ውሱንነት ከፍተኛ ነው። በመሆኑም በተቀነበበ ትንተና ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግሮች ለመተንተን የተደረጉት ጥረቶች ምሉእነት የጎደላቸው ከመሆናቸውም ባሻገር ብዙዎቹ እጅግ ተቃራኒ የሆኑ ማጠቃለያዎችና አቋሞች እንዲወስዱ አድርጓቸዋል። ምህዳራዊ አስተሳሰብ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየበዙና እየተጠናከሩ የመጡትን ውስብስብስ ችግሮች ለመረዳትና ለመፍታት በስራ ላይ እየዋለ የመጣ የልዕለ-ዘርፍ (transdisciplinary) ሳይንስ መስክ ነው። ምንም እንኳን ምህዳራዊ ትንተና የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሳይንስ ተብሎ የሚገመት ቢሆንም፣ ዋና ዋናዎቹ የአስተሳሰብ ሰበዞች ከበርካታ ሃገር በቀል እውቀቶች ጋር የተጣጣሙ ሆነው ይገኛሉ። የአንዳንድ ሰዎች የተፈጥሮ አስተዋይነትም እንዲህ አይነቱ አመለካከት በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ሊገኝ የሚችል አቅም መሆኑን ያመላክታል። በዚህ ረገድ የሃገሪቱ ምሁራንና የሚዲያ ሰዎች ባንድ አቅጣጫ የተቀነበበ ትንተና (linear thinking) ላይ የተመረኮዘ ፖለቲካዊ ትንተናዎች ከመስጠት መታረምና ዙሪያ መለስ እይታ ሊሰጥ በሚችለው ምህዳራዊ አስተሳሰብ ለመታነጽ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።     
ባላባታዊ የፖለቲካ ቅሪቶች፡ - ዘመናዊው ፖለቲካ ምናልባትም ካንድ ምዕት ዓመት ያልዘለለ ዕድሜ ያለው ቢሆንም፣ ሃገሪቱ ካሳለፈችው የረዥም ዘመን ታሪክ ጋር በተያያዘ ስር የሰደዱ ከባቢያዊ የፖለቲካ ባህሎች እንዳሏት አይካድም። ከነዚህም ውስጥ፣ ለሃገሪቱ የወደፊት እድገት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ በርካታ አስተዳደራዊ ልማዶች የመኖራቸውን ያህል ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረ ባላባታዊ የፖለቲካ ባህልም ነበረ፡፡ የሚያሳዝነው ነገር፣ የዘመናዊው ፖለቲካ አራማጅ ሆኖ የተነሳው የ1960ዎቹ (የእኛ) ትውልድ፣ በሃገሪቱ ከነበሩት የዘመናት ሃገራዊ የአስተዳደርና የፖለቲካ ልምዶች ጠቃሚውን ከመውሰድ ይልቅ በሚያስገርም ደረጃ የባላባታዊው የፖለቲካ ባህል እስረኛ መሆኑ ነው። ይህም በመሆኑ፣ አብዛኞቹ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅቶች በተሟላ ነጻነት ላይ ከተመረኮዘ ፖለቲካዊ አካሄድ ይልቅ ፖለቲካዊ ጭሰኝነትን (political serfdom) የሚያራምድ የፖለቲካ ሂደት ሲተገብሩ ኖረዋል። በዚህ ጸሃፊ እምነት፤ እስከ ዛሬም ድረስ በፖለቲካችን ውስጥ ስር ሰዶ የሚታየው የመጠፋፋት ፖለቲካ የዚሁ ባላባታዊ ፖለቲካ ቅሪት ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም።  ባለፉት ሃምሳና ስልሳ ዓመታት ውስጥ እንዲህ አይነቱን ፖለቲካዊ ጭሰኝነት አንቀበልም ብለው የተነሱ በርካታ ወጣቶች በየራሳቸው ድርጅቶች መቀጠፋቸውም የፖለቲካችን አንዱ አሳዛኝ ገጽታ ነው። በአሁኑ ወቅት ከዚህ ባላባታዊ የፖለቲካ ቅሪት ነጻ የሆኑ ወጣት ፖለቲከኞችና የህብረተሰብ መሪዎች በአንዳንድ ድርጅቶች ብቅ ያሉ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ፈተና እንዳይጠለፉ ከፍተኛ ስጋት አለ። ስለሆነም፣ ሁሉም የፖለቲካና የማህበረሰብ መሪዎች በተለይም ወጣቶቻችን ከእንደዚህ ዓይነቱ በሽታ ራሳቸውን ለማንጻት መጣጣር ይኖርባቸዋል።  
በጥቅሉ፣ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን አበይት ህመሞችና ሌሎችንም በጥልቀት ፈትሾ መድሃኒት መሻት የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደ በሰለና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለማሸጋገር የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሂደት ለፖለቲካ መሪዎች ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በእውቀትና አስተውሎት ላይ ለተመረኮዘ ውይይትና መግባባት የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ይህንንም ዘመኑ በሚጠይቀው እውቀት ላይ ተመርኩዞ ለማካሄድ በምህዳራዊ አስተሳሰብ መመራት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ይታመናል። በሚቀጥለው ክፍል ጽሁፍ ለዚህ ሂደት ከሚያግዙ መሰረታዊ የምህዳራዊ አስተሳሰብ መርሆዎች ዋና ዋናዎቹን እንመለከታለን።
ከአዘጋጁ፡- ደስታ መብራቱ፣ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ። ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።


Read 2831 times