Saturday, 18 July 2020 15:44

“ፍትሃዊ ምርጫ ቢካሄድ ህወኃት የመመረጥ ዕድል አይኖረውም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

       • እንደ ህወኃት የህዝብን እንቅስቃሴ የሚፈራ ድርጅት አላየሁም
         • አማራጭ ሚዲያ ቢኖር ኖሮ፣ ህዝቡ ሚዛናዊ መረጃ ያገኝ ነበር
         • ህገ መንግስትን ጥሰው የሚያደርጉት ምርጫ ውጤቱ የከፋ ነው


           የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡ ይህ እንቅስቃሴው ህጋዊ ቅቡልነቱ ምን ያህል ነው? ፓርቲዎችን በባንዳነት የሚፈርጀው ለምንድን ነው?  ክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር ያለው መካረር ወዴት ሊያመራ ይችላል? በህውኃት ላይ የሚሰሙ ተቃውሞዎች መጨመር ምን አንደምታ ይኖራቸዋል? በሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት (አረና) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቃለ ምልልስ  አድርጓል፡፡  


            በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየተከናወነ ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ በትግራይ እንዴት ይገለጻል?
በትግራይ የተለወጠ ነገር አለ ብዬ አላስብም፡፡ ለምሳሌ ሌላው ሠው በ 27 ዓመት አገዛዝና ከዚያ በኋላ እያለ ነው ከፋፍሎ  የሚያየው፡፡ በትግራይ ግን እንደዚያ ተብሎ ሊከፈል አይችልም፡፡ ያው ህወሓት  ነበር፤ አሁንም ህወኃት ነው፡፡ ስርአቱም ሲስተሙም ያው ነው፡፡ ለውጡ በትግራይ የለወጠው ነገር የለም፡፡ ለውጡ ምንድን ነው ከተባለ ከዚህ የሚተላለፉ ሚዲያዎች (የአማርኛ ቢሆንም) ሃሳባችንን እንድንገልፅ እያደረጉን ነው እንጂ ለትግራይ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ በአጠቃላይ በትግራይ ያለውን ሁኔታ ከተመለከትነው በነበረበት ነው የቀጠለው፤ እንዲያውም ብሶበታል ማለት ነው የሚቻለው፡፡
በፌደራሉና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል የተፈጠረው መካረር መንስኤው እንዲህ ነው ብሎ መግለጽ ይቻላል?
ህወሃት እንደሚታወቀው ለውጡን አይደግፍም፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ሲመረጡ የሐሳብ ልዩነታቸውን ይዘው እንደነበር ግልጽ ነው::  በመጨረሻም ኢህአዴግና አጋሮቹ ወደ ብልጽግና ሲቀየሩ  ህወኃት ወደ ቡድኑ አልገባም፡፡ የመካረሩ መባባስ ህወኃት በመስመሩ ጸንቶ መቆሙ፣ ሌሎች ደግሞ ለውጥ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ከዚያም የምርጫ ጉዳይ መጣና የበለጠ መካረሩን አሰፋው፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምም ከስልጣናቸው መልቀቅ  ልዩነቱንና መካረሩን የበለጠ ግልጽ ያደረገው ይመስለኛል፡፡ መንግስት ምርጫውን ማራዘሙ እንዳለ ሆኖ፣ ገደብ አልባ የሆነ ጊዜ መቀመጡ ግን እኛም ብንሆን የማንቀበለው ነው፡፡ ኮሮና መቼ ይቆማል የሚለውን የዓለም ጤና ድርጅት እንኳን በግልጽ አላስቀመጠውም፡፡ እንደውም ዝም ብሎ ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምት ነው ያለው፡፡ ከዚህ አንጻር የምርጫ ጊዜ ገደብ  አለመቀመጡ  አስጊ ነው፡፡ ነገር ግን ዋናው ልዩነታቸው፣ ህወኃት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ትክክል ነው ብሎ መቀጠሉና ሌሎቹ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣታቸው ነው:: ስለዚህ በአስተሳሰብ ደረጃ ተለያይተዋል ማለት ነው፡፡ በአስተሳሰብ ደረጃ ከተለያዩ በኋላ ደግሞ ከዚህ በፊት የነበሩ ጥፋቶች የማን ናቸው የሚለው ላይም ንትርክ መግጠማቸው የታወቀ ነው፡፡ ህወሓት የችግሩ መንስኤ  እኔ ብቻ ተደርጌያለሁ የሚል ቅሬታ አለው፡፡ ከኔ ጋር የነበሩት ሃላፊነት አለባቸው ባይ ነው፡፡
በሁለቱ ድርጅቶች  ውዝግብና ንትርክ  ህዝቡ ምን ይላል?
የህዝቡ አቋም የሚወሰነው በአጠቃላይ በሚዲያዎች አቅጣጫ ነው፡፡ የትግራይ ሚዲያ ሙሉ በሙሉ በህወሓት ቁጥጥር ስር ናቸው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ አሁን እየሰማ ያለው ከዚሁ አንድ መስመር ብቻ ነው፡፡ ይህ ፕሮፓጋንዳ የሚፈጥረው ተፅዕኖ  ግልፅ ነው፤ ነገር ግን ህዝቡ ይቀበለዋል ማለትም አይቻልም፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ህዝብ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንደሚሆን ግልፅ ነው::  የብዙ ሀገራት  ተሞክሮ የሚያሳየን ይሄንኑ ነው፡፡ አንድን ህዝብ ሚዲያዎች ወደ በጎም ወደ መጥፎም መንገድ ሊመሩት ይችላሉ:: ይሄ  በየትኛውም ሀገር የሚታወቅ ነው:: ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ የህወኃት የፕሮፓጋንዳ ማሽኖቹ ተፅዕኖ የላቸውም ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የሃገሪቱ ሚዲያዎች የሚያቀርቧቸው ነገሮች ለህወኃት ፕሮፓጋንዳ አጋዥ ሆነው ነው የማያቸው፡፡ እነዚህ ምናልባት ህወኃትን የሚጠሉ ሚዲያዎች ህወኃት እንዲወድቅ እየሰሩ እየመሰላቸው፣ እያጠናከሩት እንደሆነ ነው እኔ የምገነዘበው፡፡ ለህወኃት ፕሮፓጋንዳ የተመቸ ስራ ነው በብዛት ሲሰሩ የምመለከታቸው፡፡ ስለዚህ ህወኃት እየተጠናከረ ያለው ከሁለቱም አቅጣጫ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ህወኃት ህዝቡ ጠልቶታል ብሎ መናገር አያስችልም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ፍትሃዊ የሆነ ወድድር ቢደረግ፣ ህወኃት ተመርጦ መንግስት የመሆን ዕድል እንደሌለው አምናለሁ፡፡ ይሄንን እነሱም ያውቁታል፤ ለዚህም ነው ሚዲያውን በደንብ የሚቆጣጠሩት፡፡
ሚዲያውን እነሱ ብቻ ከተቆጣጠሩት ምን ዓይነት ፍትሃዊ ምርጫ ነው ሊካሄድ የሚችለው?
ህዝቡ እኮ ህወኃትን አይፈልገውም፡፡ ነገር ግን የህልውና ስጋት አለብህ ስለሚባል ስጋት አለው፡፡ ይህን በትንሽ ሚዛናዊ ስራ ማስተካከል የሚቻል ነው፡፡ ህወኃት እንዲጠናከር የሚያደርጉ ስራዎች ከቆሙ ብቻውን ነው የሚቀረው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የመሃል ሀገር ሚዲያዎች የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ጥንቃቄ የጎደላቸው ሲሆኑ ዘገባውን ለራሱ እንደሚመቸው ተርጉሞ ፕሮፓጋንዳ ሲሰራበት ነው የሚከርመው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሚዛናዊ አድርጎ ህዝቡ የሁሉንም ሃሳብ በነፃ ህሊና እንዲያዳምጥ ከተደረገ በእርግጠኝነት ህወኃት ቦታ አይኖረውም፡፡
እንዴት ነው ሚዛናዊ ማድረግ የሚቻለው?
አማራጭ አለ፡፡ አሁን በህወኃት ቁጥጥር ስር ያሉ ሚዲያዎች ሚዛናዊ ሆነው እንዲሰሩ ማድረግ፤ ካልሆነ ደግሞ ሚዛናዊ ማድረግ የሚችሉ ሌሎች የትግርኛ ሚዲያዎችን መክፈት ነው፡፡ በሚዲያዎች ህዝቡን መሰረት ያደረጉ መልካም ነገሮች በመስራት ብቻ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ በዚያው ልክ እንደ ድምፂ ወያኔ እና ትግራይ ቴሌቪዥን 24 ሰዓት የሚሰሩ የቴሌቨዥን ሚዲያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ የኦሮሚያን ልምድ ብንመለከት፤ ኦቢኤን በአንድ በኩል አለ፤ ኦኤምኤን እና ሌሎች ደግሞ በሌላ በኩል አሉ፡፡ ስለዚህ ህዝቡ የእነዚህን ዘገባዎች እያጣመረ፣ሚዛናዊ የሆነውን ፈልጎ ይቀበላል ማለት ነው፡፡ በትግራይም ተመሳሳይ የሚዲያ ሁኔታ ቢኖር፣ ህዝቡ ሚዛናዊ መረጃ ያገኝ ነበር፡፡ ይሄ የህልውና ጉዳይና የሚለውንም ህዝቡ ይገነዘበው ነበር፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ፈንቅል” የሚል እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ይሄ እንቅስቃሴ  እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አያመጣም የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ጠንካራ እንቅስቃሴ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ጥንካሬውና ህዝባዊነቱ ምን ያህል ነው?
ይሄንን እኛ እንደ ፓርቲ በጥልቀት አልገመገምነውም፡፡ ነገር ግን በዚሁ እንቅስቃሴ ሰበብ እየታሰሩ ያሉት የኛ አባላት ናቸው፡፡ እስካሁን 8 ያህል አመራርና አባሎቻችን ታስረዋል፡፡ በተንቤን 3፣ በመቀሌ 5 ታስረውብናል፡፡ ፍ/ ቤትም በ 24 ሰዓት ሊያቀርቧቸው አልቻሉም ነበር፤ ባንዳ የተባሉት ሌላ ጊዜ ደግሞ የፈንቅል አባል ናቸው እየተባሉ ነው የሚታሰሩት፡፡ ደስ ሲላቸው ሽብርተኛ ይሏቸዋል፤ ሲያሰኛቸው ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ ነበር ብለው ይከሷቸዋል፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ በእስር እየተሰቃዩ ነው፡፡ እኛ እንደ አረና የምንቆመው ለሰላማዊ ትግል ነው፡፡ ትግልን ወደ ከፍ ያለ ደረጃ ሊለውጥ የሚችለው ፓርቲ ሣይሆን ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ ሲቆጣ ነው ጠንካራ እርምጃ የሚወስደው፡፡ የትግራይ ህዝብ ከኦሮሚያና ከአማራ ህዝብ ይለያል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ከተንቀሳቀሰ ለውጥ ማምጣቱ አይቀርም፡፡ በሌላ መልኩ ህወኃት በሚሄድበት ልክ በሚዲያ በኩል እንቅስቃሴ ካልተደረገ ጠንካራ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ትግሉ ችግር እያጋጠመው ያለው የተናበበ የሚዲያ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ነው፡፡ ህወኋት እኮ ትንንሽ እንቅስቃሴ የሚያስደነግጠው ነው፡፡ ለዚህ ነው ትንንሽ እንቅስቃሴዎችን ወዲያው ለማፈን የሚሯሯጠው፡፡ እኔ እንደ ህወኃት የህዝብን እንቅስቃሴ የሚፈራ ድርጅት አላየሁም፡፡ ህወኃቶች ትናንሽ የህዝብን እንቅስቃሴ ሣይቀር ነው የሚፈሩት፡፡
የትግል ስትራቴጂ ችግር አለ ማለት ይቻላል?
አሁን በሌላው ብሄር የነበረን የግል ስትራቴጂ ነው በትግራይ ለመተግበር እየተሞከረ ያለው፡፡ የትግራይ ህዝብ ደሞ የራሱ ስነልቦና አለው፡፡ ቀደም ብሎ ትግል የተደረገበትን ስነ ልቦና ብናቀርብለት በቀላሉ አይቀበለውም፡፡ አብዛኛው ሚዲያም የህዝቡ ስነ ልቦና አይገባውም፡፡ ለአማራ ህዝብ የሰራው የትግል ስትራቴጂ ለትግራይ አይሰራም፡፡ ይሄ ማለት ወልቃይት የአማራ ነው፤ እያልክ ለትግራይ ህዝብ እታገላለሁ ማለት የማይገናኝ ነገር ነው፡፡ ይሄ አይነቱ አካሄድ ህወኃትን እንዲደግፍ ከማድረግ ውጭ ሌላ ውጤት አያመጣም፡፡ እኔ ወልቃይት የእገሌ ነው፣ የእገሌ ነው በሚለው አላምንም፡፡ ህዝብ ነው መወሰን ያለበት የሚል ነው እምነቴ፡፡ ደጋግሜ እንዳልኩት፤ ለአንድ አካባቢ ስነ ልቦና የሚሆን ሚዲያ ፈጥሮ ነው ትግል ማድረግ የሚያስፈልገው:: በዚህ  ረገድ ነው ከፍተኛ ክፍተት ያለው፡፡
የትግራይ ህዝብ የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል? የህልውና አደጋ ሊጋርጥበት የሚችለው ሃይል ማን ነው?
የትግራይ ህዝብ ላይ አደጋ ሊጋርጡ የሚችሉ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ሊፈጠሩም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በሁለቱ የፖለቲካ ሀይሎች ጦርነት ቢነሳ በመጀመሪያ የሚጎዳው የትግራይ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ ስጋት ይሄ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ለትግራይ ህዝብ ለብቻው የተደቀነ አደጋ አለ ብዬ አላስብም:: የትግራይ  ህዝብ እጣ ፈንታ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ አይሆንም፤ ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ላይ ለብቻው የሚጋረጥ የህልውና ስጋት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ያለው የፖለቲካ ችግርማ በትግራይ ህዝብ ህልውና ስጋት ሊሆን አይችልም፡፡ እንኳን የትግራይ ህዝብ ላይ እነሱ ላይም (ህወኃቶች) የህልውና ስጋት ነበረባቸው ብዬ አላምንም፤ ተደራድረው ተነጋግረው ከእልህ ወጥተው በጋራ የተሰጣቸውን  እድል ተጠቅመው መሄድ ይችላሉ፡፡
በክልሉ ምርጫ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ተብሏል፡፡ በርግጥ ምርጫው ይካሄዳል ብላችሁ ታምናላችሁ?
እንደኔ ምርጫው ምን አይነት ነው? የሚለው ነው ጥያቄ የሚሆንብኝ፡፡ ትክክለኛ የምርጫ መስፈርቶችን ያሟላ ምርጫ ያደርጋሉ የሚል እምነት የለኝም:: የምርጫው እንቅስቃሴ በአሁን ወቅት በተግባር እየተደረገ አይደለም፤ ግን የምርጫ ህግ ማፅደቃቸውን አስነግረዋል፤ በቀጣይ ሁለት ወር ውስጥ እንኳን መስፈርቱን ያሟላ ምርጫ ቀርቶ እንደነገሩ የሆነ ምርጫም ማካሄድ አይችሉም፡፡
እርስዎ የሚመሩት አረና እና ትዴፓ በባንዳነት መፈረጃቸው ይነገራል፡፡ በእርግጥ  እንደዚያ ተደርጎል?  እናንተስ ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ ምንድን ነው?
በእርግጥ ባንዳዎች ናቸው ተብለናል:: ቀደም ብሎም በህግ ደረጃ ባንዳ ብሎ ለመፈረጅ ነበር ያሰቡት፤በኋላ ይሄን ትተው በስም ደረጃ ባንዳ እንበላቸው ብለው በዚያ ፈርጀውናል፡፡ ይህን ካደረጉ በኋላ በየወረዳው ያሉ አባሎቻችን በስብሰባዎች ላይ ለየት ያለ ሐሳብ ያቀረቡ ግለሶችን ባንዳዎች እያሉ ስም ዝርዝራቸውን በየወረዳው ፅ/ቤት እየለጠፉ ነው፡፡ ይሄ አደገኛ ነው፡፡ ከወዲሁም መታረም ያለበት ነው፡፡ ካልሆነ ግን ብዙ ሰው ባንዳ ብለው ሊያስከፉት ይችላሉ፡፡ እኛ ባንዳ ስንባል እራሳችንን እንኳን ከፕሮፓጋንዳ ጥቃት መከላከል የምንችልበት የሚዲያ አማራጭ የለንም፡፡ እነሱ በአንጻሩ ያለ ሚዲያ መኖር እንደማይችሉ ስለተረዱ አንድ ቀን ቢዘጋባቸው እንዳየነው በአለማቀፍ በኩል ተሯሩጠው ከፍተዋል፡፡ ይሄ ምን ያህል ሚዲያ ላይ ተንጠላጥለው እንዳሉ ነው የሚያስረዳው፡፡
ባንዳ ተብላችሁ ከተፈረጃችሁ በኋላ ያገጠማችሁ ችግር  አለ?
በጭራሽ የለም፡፡ እነሱማ ህዝቡን ባንዳዎች ናቸው በሏቸው ብለው ነበር፡፡ ህዝቡ ግን ማንነታችንን ጠንቅቆ ያውቃል፤ ስለዚህ ምንም ችግር አልገጠመንም፡፡ እንደውም ሕዝቡ ጠበቃችን ነው የሆነው:: ይሄን ሲረዱ ነው ወደ እስርና ማንገላታት የገቡት፡፡ ነገር ግን ፕሮፓጋንዳቸውን ሚዛናዊ የምናደርግበት አማራጭ ስለሌለ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ለማካሄድ ያቀደው ምርጫ ህጋዊ ቅቡልነቱ ምን ያህል ነው?
ስለ ምርጫው ህውኃቶችን መጠየቅ የምፈልገው ነገር አለ፡፡ ምንድነው የምትፈልጉት? ምርጫውን ለማድረግ ሌላ ህግ መጣስ ለምን አስፈለጋችሁ? ከዚያስ በኋላ ምን እንዲሆን ነው የምትፈልጉት ? ልላቸው እፈልጋለሁ፡፡ በቀጣይ ፍትሃዊ ምርጫ ቢያደርጉም ላይታመኑ ይችላሉ:: ህገ መንግስትን ጥሰው የሚያደርጉት ምርጫ ውጤቱ የከፋ ነው፡፡
ህገ መንግስቱ ምርጫ ቦርድን የማቋቋም፣ የምርጫ ቦርድ  የመሾም ስልጣንን ለፌደራል መንግስቱና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ነው የሚሰጠው:: እነዚህን ሁሉ ጥሰው ሌላኛውን አንቀፅ ካላከበርን ማለት ምን ያህል ምክንያታዊ ነው? ስለዚህ ምርጫ ቢያደርጉ ከህግ ውጪ ናቸው:: ምርጫውን ባያደርጉ ግን ከፌደራል መንግስት ጋር የሚፈጠረውን ግጭት ሊቀንስላቸው ይችላል፡፡ አታካራ ውስጥ ባይገቡ ነው የሚመረጠው፡፡ የተሻለውን ምረጡ ልላቸው እፈልጋለሁ፡፡  

Read 2957 times