Print this page
Saturday, 18 July 2020 15:42

በሁከቱ 200 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ160 በላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   • 10ሺ ያህል ሰዎች ተፈናቅለዋል ተብሏል


          አለም ዓቀፉ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበር፤ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ 40 ወረዳዎች በተፈጠሩ የከፉ ግጭቶች የደረሱ ጉዳቶችን ከትላንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርት በዝርዝር አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባና በ40 የኦሮሚያ ወረዳዎች በተከሰተው ግጭት፣ በአዲስ አበባ 12፤ በኦሮሚያ 2 መቶ ያህል ሰዎች መገደላቸውንና ከ160 በላይ የሚሆኑትም ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ያመለከተው ሪፖርቱ፤ 10 ሺ ያህል ሰዎችም ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ጠቁሟል:: ከተፈናቃዮቹም ውስጥ 8ሺ 420 የሚሆኑት አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ሁከትና ግርግሩ አስከፊ በነበሩባቸው 8 የኦሮሚያ ዞኖች መካከል አርሲ ዞን ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በዞኑ 49 ሠዎች ሲሞቱ፣ 64 ያህሉ ላይ ጉዳት ደርሷል፤ 255 ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል፡፡ በምዕራብ አርሲ ዞን የሞቱ ሰዎች ቁጥር በውል እንደማይታወቅና የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት ግን 3ሺ 600 ያህል መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በነበረው ሁከትና ግርግር 7 ሰዎች ሲገደሉ፣ 7 ሰዎች በፅኑ የቆሰሉ ሲሆን 795 ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ደሞ 13 ሰዎች መገደላቸውንና 60 ያህል መቁሰላቸውን፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ግን በውል እንደማይታወቅ የገለፀው ሪፖርቱ፤ በባሌ ዞን 5 ሰዎች መገደላቸውን፣ የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር በውል ለማወቅ እንዳልተቻለና 2ሺ445 ሰዎች መፈናቀላቸውን አመልክቷል፡፡
ተቋሙ እርግጠኛ የሆነባቸውን አሀዞች ብቻ ሪፖርት ማድረጉንና በየአካባቢው የደረሱ ጉዳቶች ከዚህም ሊበልጡ እንደሚችሉ ጠቁሞ፤ በቀጣይ አዳዲስ መረጃዎችን በሪፖርቱ እንደሚያካትት አስታውቋል፡፡
በዚህ ሪፖርት ከየአካባቢዎቹ ባሰባሰበው መረጃ፣ 74 ሰዎች መገደላቸውን ማረጋገጡን፣ ከ200 በላይ ሰዎች ስለ መገደላቸው ደግሞ መረጃዎች እንደደረሱት፣ በቀጣይም ማጣራት አድርጎ የተሟላ ሪፖርት ይፋ ለማድረግ አስታውቋል፡፡
አለም አቀፉ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበር፣ ይህንን ሪፖርት ያዘጋጀው በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ መዋቅሮችን ተጠቅሞ ባደረገው ምርመራ መሆኑን ጠቁሞ፤እርዳታ ለሚያስፈልጋቸውም ከወዲሁ የተለያዩ እርዳታዎችን እያቀረበ እንደሆነ  አስታውቋል፡፡

Read 10939 times