Print this page
Saturday, 14 July 2012 10:41

“የሕትመቱ ዘርፍ እንደ አጀማመራችን አላደገም”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

ቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በስሩ ያቋቋመው “ፊደል አሳታሚ” ድርጅት ሥራ መጀመሩን ለማብሰርና በማተሚያ ቤቱ የታተሙ ስድስት መፃሕፍት ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የምረቃ ሥነ ስርዓት በሒልተን ሆቴል ተካሂዷል፡ የቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ መሥራችና ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት ባደረጉት ንግግር፤ የሕትመቱ ዘርፍ በአገራችን ብዙ ችግሮች እንዳሉበትና ችግሩን ለመቅረፍ ለሚደረጉ ጥረቶች “ፊደል አሳታሚ” የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ይጥራል ካሉ በኋላ ሕትመት በአገራችን፣ በአፍሪካና በዓለም ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ሲገልጹ፡- “በዓለም ላይ ከሚመረቱ መፃሕፍት ውስጥ 80 ፐርሰንት ያህሉን ለዓለም ሕዝብ የሚያቀርቡት አገራት በቁጥር ከ35 የማይበልጡ ሲሆን የአፍሪካ አገራት በዓለም የመፃሕፍት ማምረት ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከሁለት ፐርሰንት ያነሰ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ የአፍሪካ አገራት ከ70 ፐርሰንት በላይ የሚሆነውን የመፃህፍት ፍላጎታቸውን የሚሸፍኑት ከውጭ አገራት በሚያስገቡት መፃሕፍት” መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአፍሪካ ውስጥ መፃሕፍት አትሞ በማሰራጨት ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ናይጀሪያና ኬኒያ የተሻሉ ናቸው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ የሌሎቹ አገራት ድርሻ ኢምንት መሆኑን ጠቁመው ለዚህ ችግር ምክንያት የሆኑት በአፍሪካ አገራት የሚታየው ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ፣ የንባብ ባሕል አለመጎልበት፣ የካፒታልና የክህሎት ማነስ፣ ደካማ የግብይትና የማከፋፈል ሥርዓት እንዲሁም ለዘርፉ የሚሰጠው ድጋፍ ውስን መሆን ነው ብለዋል፡፡ አገራችንን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት ተደራሽነት እየተስፋፋና እያደገ መምጣቱን ያመለከቱት ረዳት ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት፤ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከ15 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እንደሚገኙ ገልፀው፤ የመማሪያና ማጣቀሻ መፃሕፍት እጥረት መኖሩን ዩኒቨርስቲ ኮሌጃቸው በመገንዘቡ፣ “ፊደል አሳታሚ” እህት ኩባንያን ለማቋቋም እንደተነሳሱ ተናግረዋል፡፡ “ይህ አሳታሚ ድርጅት በህትመት፣ በድምፅና ምስሎች እንዲሁም ኤሌክትሮኒክስ በሆኑ የአቀራረብ ስልቶች፣ የተለያዩ የህትመትና የፈጠራ ሥራዎችን ለማቅረብ የተቋቋመ ሲሆን፤ በአገራችን የሚታየውን የንባብ ባህል ለማዳበርና በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚታየውን የአጋዥ መፃሕፍት እጥረት ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል” ብለዋል - ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡ በንግግራቸው ማጠቃለያም፤ በ”ፊደል አሳታሚ” ተዘጋጅተው በዕለቱ የተመረቁት መፃሕፍት በአገር ውስጥና በውጭ ባለሙያዎች መዘጋጀታቸውን አመልክተው፤ መፃሕፍቱ በተለያዩ ደረጃዎች ለሚገኙ ተማሪዎችና አንባቢያን ታስበው ታትመዋል ብለዋል፡፡ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች የታተሙትን ስድስት መፃሕፍት የምረቃ ሥነ ስርዓት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የመጡት አቶ አህመድ አደምና ከትምህርት ሚኒስቴር የተጋበዙት አቶ ታከለ ገ/ኪዳን በጋራ አከናውነዋል፡፡

ሁለቱ የክብር እንግዶች ባደረጉት ንግግር፤ ለባህል ልማት ትምህርት፣ ዕውቀትና መፃሕፍት ወሳኝ ነገሮች መሆናቸውን፤ ባህል ከሚጠበቅባቸው ነገሮች አንዱ ቋንቋ መሆኑን፣ መንግሥት ይህን ታሳቢ አድርጎ እየሰራ እንደሆነ አመልክተው፤ ይህንን ዘርፍ ለማሳደግ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ “ፊደል አሳታሚ” ድርጅትን በማቋቋሙ ያስመሰግነዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕትመት ዘርፍ የደረሰበትንና ያለበትን ችግሮች በተመለከተ ደግሞ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው “በጥናት ላይ የተመሰረተ አይደለም” ያሉትን ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡ “ርዕሰ ጉዳዩ ሰፊ ነው፡፡ በአገራችን የሕትመት ዘርፍ ላይ የተሰራ ጥናት አላጋጠመኝም፡፡ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በዚህ ዘርፍ ላይ ጥናት እንዲሰራ ማነሳሳቱ ያስመሰግነዋል” ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በመቀጠል ሲናገሩ፤ “ሥራዬ ከመፃሕፍት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የማዝንበትና የምደሰትባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የሕትመት ዘርፍን በተመለከተ በአፍሪካ ደረጃ የተሰሩ ብዙ የጥናት ሥራዎች አሉ፡፡ ያንን ወስደን ብናየው ይጠቅመናል፡፡ የሕትመቱን ዘርፍ ዕድገት እንደ ፖለቲካው ዕድገት፣ እንደ ኢኮኖሚው ዕድገት … ልናስብበት ይገባል” ብለዋል፡፡ የመፃሕፍት ሕትመት ለአገር ኢኮኖሚና ለሕዝቦች ሁለንተናዊ ዕድገት ያግዛል ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ይህ እውነት መሆኑን በተግባር የታየባቸው የምሥራቅ፣ የደቡብና የምዕራብ አፍሪካ አገራትን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ መፃሕፍትን የመማሪያ፣ የማመሳከሪያና የሥነ ጽሑፍ ናቸው ብለው በሦስት የመደቧቸው የዳሰሳ ጥናት አቅራቢው፤ በአፍሪካ አገራት ውስጥ ከሚታተሙት መፃሕፍት የሚበዛው ቁጥር የመማሪያ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንንም በማሳተም ላይ ተሰማርተው የሚገኙት የየአገሩ መንግሥታትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በዚህ አሰራር ውስጥ ካሉት አደጋዎች መሐል የመፃሕፍቱ ሥርጭት በአገር ውስጥ የሚወሰን መሆኑንና መንግሥታቱ የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም በመፃሕፍቱ እንዲንፀባረቅ መደረጉ ነው ብለዋል፡፡

አሜሪካን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን … የመሳሰሉት የበለፀጉት አገራት፣ የመማሪያ መፃሕፍትን አሳትመው ከአገራቸው በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሰራጨት ታዋቂ ናቸው ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘርይሁን አስፋው፤ በዚህ ምክንያት አሳታሚ ተቋማቶቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋ ትልቅ ገበያ አላቸው ይላሉ፡፡ በአፍሪካ ግዙፍ ሊባል የሚችል አሳታሚዎች የሉም ያሉት ዳሰሳ አቅራቢው፤ በአህጉሪቱ የሚገኙ አሳታሚዎች ችግሮች ናቸው በማለትም የካፒታል እጥረትን፣ የወረቀትና ሌሎች ግብአቶች በበቂ ሁኔታ አለማግኘትን፣ ከፍተኛ ታክስን፣ የንባብ አለመዳበርን፣ የገበያ አለመኖርን …. እንደማሳያ አቅርበዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በጋራ መሥራት፣ በማህበር ተደራጅቶ መንቀሳቀስ፣ በዘመናዊ መሣሪያዎች መጠቀም፣ በባለሙያዎች መታገዝና የማስተዋወቅ ሥራን በስፋት መሥራት መፍትሔ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ በሕትመት ዘርፍም “ጀማሪ” የሚያሰኝ ታሪክ ነበራት ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘርይሁን አስፋው፤ በተለይ መፃሕፍትን በራሳችን ቋንቋ በማተም የተለየ ታሪክ ማስመዝገባችንን የውጭ አገር ሰዎችም የሚመሰክሩት እውነት ነው፡፡ እንደ አጀማመራችን ግን የሕትመቱ ዘርፍ አላደገም፤ የማደግ ተስፋ ግን አለው ብለዋል፡፡

እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ሁሉ በኢትዮጵያም በብዛት በመታተም ላይ የሚገኙት የመማሪያ መፃሕፍት ናቸው ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ በ1933 ዓ.ም ጣሊያን በተባረረ ማግስት ጀምሮ በተከታታይ የታተሙትን የከበደ ሚካኤልና የገብሬ ወዳጆን መፃሕፍት በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በአገራችን የሕትመቱ ዘርፍ ካለመስፋፋቱ ጋር በተያያዘ ደራሲያን የፀሐፊነት፣ የአርታኢነት፣ የአሳታሚነት፣ የሻጭነት … ሥራዎችን ሁሉ ደርበው እንዲያከናውኑ መገደዳቸው ከትላንት እስከ አሁን ድረስ የቀጠለ እውነታ እንደሆነ ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ ገጣሚ መንግሥቱ ለማን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ገጣሚው በ1950 ዓ.ም ባሳተሙት “የግጥም ጉባኤ” መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ፡-

“ባሁኑ ባለንበት ዘመን ደራሲዎችን የተጫናቸው ችግር በዝቷል፡፡ ከዚህ አንደኛው የጻፉትን ድርሰት ማሳተሚያ ገንዘብ ማጣታቸው መሆኑን ማን የማያውቅ አለ? ያለንበት ሁኔታ እያንዳንዱን ደራሲ ያለ ውዴታው ባለጸጋ እንዲሆን ያስገድደዋል፡፡ እኔም በበኩሌ ያ ብልጽግና የተባለው ጽድቅ ከዛሬ ነገ ይመጣና ከድርሰቶቼ አንዳንዶቹን እንኳ አሳታማለሁ ስል በተስፋ እስካሁን ቆየሁ፡፡ ሳይመጣ ሲቀር ጊዜ ነው ክቡራን አንባቢዎችን እንደዚህ ባለ ቀለምና ወረቀት የደፈርኳቸው፡፡” ሲሉ ችግሩን ገልፀዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ከትዳራቸው ሁሉ የተፋቱ ደራሲያን ነበሩ ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ እንዲህም ሆኖ በ1950ዎቹም ደራሲያን የሚያሳትሟቸው መፃሕፍት ኮፒ ከአንድና ሁለት ሺህ አይበልጥም ነበር ብለዋል፡፡ በየዘመናቱ የታተሙ የልቦለድና የግጥም መፃሕፍትን ብዛትም አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መፃሕፍት ድርጅትና ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በህትመት ዘርፉ ላይ በቆዩባቸው ዓመታት ያበረከቱትን አስተዋፅኦም አብራርተዋል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የግል ድርጅቶች ለዘርፉ ያደረጉትን ውለታ ከጠቃቀሱ በኋላም የሚመለከታቸው አካላት ዘርፉን ለማሳደግ ተባብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው በማመልከት ዳሰሳቸውን አጠቃለዋል፡፡

 

 

Read 2094 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 10:53