Saturday, 11 July 2020 00:00

ኧረ በህግ

Written by  ዋስይሁን በላይ
Rate this item
(5 votes)

ይሔ የቀዬው የአውጫጭኝ ሥርዓት ነው፡፡
ማህበረሰቡ በእምነቱና በሥርዓቱ መሠረት ይዳኝበታል፡፡ ይካሳልም ይቀጣልም፡፡ የልብ ፍርድ ሚዛን ሲደፋ ማህበረሰቡ የእውነት ዳኛ ይሆናል፡፡ የቀዬው፣ ሽማግሌዎች ብቻም ሣይሆኑ የተሰበሰቡበት ግዙፍ ዋርካም ሳይቀር ይወደዳል (ለዚህ ይመስለኛል እንኳን ሰው ግንድ ያስጥላል) የሚባለው፡፡ እዚህ መንደር ዛሬ ለየት ያለ ነገር ገጥሞታል፡፡
ስርቆሽ የተለመደ ቢሆንም የዚህ ሰሞኑ ድርጊት ግን ትንሽ በዛ አላባቸው፡፡ የወ/ሮ የውብዳር በረት ተገንጥሎ አጥቢዋ ላም፣ አጥንቱ እላዩ ላይ የሚቆጠረው ባለውለታቸው በሬ፣ አራት በጐቻቸው በርሃብ ሞታቸውን የሚጠባበቁ ሁለት አህዮች ተሰርቀዋል፡፡
ጉልበት የሌላቸውን ጉልበተኛ ገብቶ ቅስማቸውን ሰብሮታል፡፡ ከአይናቸው ጉድጓድ የሚወጣውን እንባ ያደፈ ሸማቸው አይመክተውም፡፡ ያንዠቀዥቁታል፡፡ “ሐገር ይዳኘኝ” ብለው ለቀዬው ሽማግሌዎች ተንበርክከው “አቤት” ብለዋል፡፡ አራት ቀን ሙሉ በር ዘግተው እንደ ራሄል እምባቸውን ወደ ላይ ቢያዘሩም መልስ አላገኙም፡፡ ከፍም ዝቅም ብለው የኔ የሚሉት የሚቆረቆርላቸው ወገን የላቸውም፡፡
ባለቤታቸው ያኔ ለእናት ሐገር ጥሪ ለዘመቻ እንደወጣ አልተመለሰም፤ ሞተ እንኳን ብሎ ያረዳ የለም፡፡ “የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ/ ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ” ሆኗል ነገሩ:: የባሌ ምትክ የሚሏት አንድ ልጃቸው ተንሰፍሥፈው ከመላዕከ ሞት ማስጣል ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የውብዳር ከመሬት በታች አልሆኑም እንጂ በብዙ ነገር እጦት ከሞቱ ቆይተዋል፡፡ እነሆ ዛሬ ደግሞ የከፋ አሟሟት…
ሽማግሌዎቹ ከዚህ በፊት ይዳኝበት የነበረውን መንገድ አልተከተሉም፡፡ ሶስቱም አዛውንት በቁጣ አንጀታቸው አሯል፡፡ የገዛ ጐጇቸው የተደፈረ ያህል ተንገብግበዋል:: “ሰው እንዴት ምንም ከሌለው ላይ ይሰርቃል?” ብለው ተማረዋል “ሰው እንዴት መርዳት ባይሆንለት ቅስም ይሰብራል?” የማህበረሰቡ ጥያቄ ነበር… የቀዬው ነዋሪ ተሰብስቧል፡፡ ዛሬ የገበያ ቀን ስላልሆነ ሌባው የሰረቀውን ነገር ወደ ገበያ ይዞ ሊወጣ አይችልም፡፡ ይሔ የነዋሪው ምሬት ደግሞ እሚያወላፍት እንደማይሆን ያሳውቃል፡፡
ምናልባት ከዚህ ቀዬ ወጥቶ ካልሸጣቸው በስተቀር እዚሁ በዚሁ እማይሞከር ነው፡፡
“ጐበዝ ዛሬ አንድ ፍንጭ ካላገኘን በስተቀር መሽቶ ይነጋል እንጂ ከዚህች ንቅንቅ አንልም” አሉ አቶ ኪሮስ፤ ሁሉም አጉረመረመ፡፡ የውብዳር ያነባሉ አቀርቅረው:: “እናቴ አታልቅሺ ይዋል ይደር እንጂ መገኘቱ እንደሁ አይቀርም” አሏት አጠገቧ የተቀመጡት አቶ ጉልማ፡፡ አቶ አካሉ የአቶ የጉልማ አባባል አስደንግጦት ይሁን የወ/ሮ የውብዳር ሁኔታ አሳዝኖት እንደሁ ያለቅሣል፡፡
“በሉ እንጂ መቼም እቺ መንደራችን እግዜር በምህረቱ ጠብቋት ከብዙ ነገር ተንከባለን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ቅድም እንዳያችሁት የአቶ ጫቦ ባለቤት መጥታ ሹክ ያለችን ነገር አለ… እኛም የደረስንበት ስላለ በዳይ ራሱን ያጋልጥ?” አሉ  በግራ በኩል ያሉት ሽማግሌ ጭራቸውን ከግራ ቀኝ እየነሰነሱ፤ አሁንም ማህበረሰቡ ያጉረመርም ያዘ፡፡
“ዝም በሉማ እንግዲህ ልማድ ከጠፍር ይጠነክራል ይባላል… አቶ መንገሻ የዛሬ ዓመት ልጅህ ቀየውን እንደ ክፉ ኮርማ አምሶት ነበር፤ የእጅ አመሉ ዳግም አገረሸበት መሰለኝ፤ ይኸው አሁንም የዚህችን ምስኪን አሮጊት ተመልካች የላትም ብሎ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ ለምን እያወቅህ እንዳላወቅህ ትሆናለህ፤ ጊዜያችንንም አትሻማ፤ እመንና ተበዳይን ዳኝተን ወደየ ሥራችን እንሂድ..”
አቶ መንገሻ ተበሳጭቶ የተዛባ ኮታውን እያጣፋ “ተው እንጂ አባቶቼ… በነሲብ መፍረድ ለሰማዩም ለምድሩም ኩነኔ ነው!”
በቀኝ በኩል ያሉት ሽማግሌ ከመንገሻ በላይ ተቆጥተው “ምነው ይሄ ሁሉ ሰው ቢከብድህ የልጅህን ሌብነት ልትክድ ነው?”
“ጌቶቼ የቀደመው እውነት ነው:: አሁን የኔ ልጅ ወደ አዲስ አበባ ከሄደ አመት ከመንፈቁ ነው፡፡ ለምን በትላንት ስህተት ዛሬን እንወቃቀሳለን? ለምን ትላንት በተሰራ የልጅነትና ያላዋቂነት በደል ዛሬን እንገማመታለን? ትላንትና እኮ መቆም ያለበት እዛው ትላንትና ላይ ነው፡፡ በግምትና በይሆናል መወቃቀስ ከማስተዛዘብ በዘለለ አጉል ጠባሳ ትቶ ያልፋል…”
አቶ መንገሻ እንባ ቀረሽ ንግግራቸውን ተናግረው ዝርፍጥ ብለው ተቀመጡ፤ ከመሀል አቶ ፍርድ ያውቃል ተነስተው “እንደው አባቶቼ፤ መቼም ሰው በህይወት ሳለ ለክሩና ለሐቁ መኖር አለበት እኔም…” ወዝ የጠገበ ክራቸውን ከአንገታቸው ላይ እየሳቡ “ይሔው ለክሬ ስል እመሰክራለሁ፤ የአቶ መንገሻ ልጅ እውነት ነው፤ ቀዬውን ለቆ ከሔደ ከራርሟል፡፡ ምነው ባለፈው ለእመቤታችን ንግሥ እለት ለበደልሁት በደል ላሳዘንኋችሁ ሁሉ ይቅር ትሉኝ ዘንድ የእመቤታችንን የአውደ ምህረቷን በረንዳ ማሠሪያ ጣራ ማልበሻ ብሎ አራት ሺ ብር ልኮልንማይደል እንዴት ዘነጋችሁ … እና አቶ መንገሻ  እውነት ነው ያበለውንም ነገር የለም” ብለው ተቀመጡ… ሶስቱም ሽማግሌዎች ልክ የሆነ የተገለጠላቸው ነገር ያለ ይመስል ሰውነታቸው በሀፍረት ሲሸማቀቅ አሳበቀባቸው ለጊዜው ሁሉም ፀጥ አለ… ሽማግሌዎቹም ተመካከሩና “እንደ እውነቱ አቶ መንገሻን በድለናቸዋል::” ሶስቱም ሽማግሌዎች ከተቀመጡበት ተነሱ… “መቼም በትላንት መነሻ ግምት እንጂ መድረሻ ሐሳብ አይገኝም እንደኛ አይነቱም ሽማግሌ ይስታልና ይቅርታ አድርጉልን…? ግራ ቢገባን ቢጨንቀን እንጂ ያደረግነውማ ስህተት ነው፡፡
እንዲያው ስለ ፈጣሪ ብላችሁና አቶ መንገሻም ይቅርታህን ስጠን?” ተሰብሳቢው አልጐመጐመ፤ አቶ መንገሻ ከተቀመጡበት ተነስተው በግማሽ ኩራትና በግማሽ እፍረት ካንገት በላይ በሆነ ይቅርታ ከወገባቸው ዝቅ ብለው እጅ ነሱ:: ሽማግሌዎቹም አመስግነው ተቀመጡ… ጀምበር እውነት ሽሽታ በሚመስል ሁኔታ እያዘቀዘቀች ነው:: ሽማግሌዎቹ ፊታቸው ላይ ያንፀባረቀችው ወርቃማ ፀሐይ በከፊልም ቢሆን ማህበረሰቡን ለመመልከት ጋርዳቸዋለች… (የሰው ልጅ ታውቆ የማያልቅ ፍጥረት አይደል፡፡)
ከብዙ ውርክብ በኋላ ያልታሰበው ያልተጠበቀው ጭምቱ አቶ አካሉ እንደጠወለገ፣ ድጋፍ እንዳጣ ሐረግ ሬሳ አንገቱን ሰብሮ የሆነውን ሁሉ ተናገረ… ሽማግሌዎቹ ለእውነቱ ሩቅ ቢሆኑ እርሱ ከገዛ እውነቱ እንደማያመልጥ ተረድቶ የገዛ ራሱ ላይ የነፃነት ፍርድ ፈረደ… ያልታሰበ ስለሆነ በስፍራው ሰውም ያለ እስከማይመስል ድረስ ሁሉም ረጭ አለ፡፡ ፀሐይዋም እውነት ከባለቤቱ ሲወጣ ያየች ይመስል ወደ ማደሪያዋ አሽቆለቆለች… ፀጥታውን የሚሰብር አንዳች ጉልበት ጠፋ:: ያለ ስም ለሌሎች ስም ተሰጥቷቸው ሌባ ተብለው ነበር… እማይገባቸው ክብራቸው ተነክቶም ነበር… አሁን ግን አቶ አካሉ የሁሉንም ነገር ጉሙን ገፈፈው:: ሽማግሌዎቹ ተመካከሩ አወጡ አወረዱ፤ የተሰጠው የራስ ላይ ፍርድ አሁን እነርሱ ከሚያወሩት በላይ እንደሆነ አምነዋል:: የሰው ልጅ ተራራ ቢጫንበት “ሰው ያነሳለታል” “ሰው የተጫነበት እንደሆንስ… እውነት ፍርድ ለመስጠት አይኗን በጨርቅ አልተጠቀለለችም፡፡ እውነት ሐገሯ ሩቅ አይደለም፡፡ በሽማግሌዎቹ ልብ የተመላለሰ አንድ ጠንከር ያለ ነገር የቀየውን ሰው ከወትሮው በተለየ አትኩረው ተመለከቱት…
“ይሔ ሰው እርግጥ ጥፋቱን አምኗል፤ ቢሆንም ዛሬ ቸል ያልነው ነገር ምነው በእንቁላሉ ጊዜ እንዳያስብለንና እንዳያስቆጨን… ይሔንን ወስነናል፤ በዳይ ባደረሰው በደል በማንኛውም ማህበራዊ ህይወት እንዳይሳተፍ! ማንም ለአጨዳም ይሁን ለጉልጓሎ እንዳይጠራው! የጠራው ላይ ቅጣቱ ይጠነክራል፡፡ ሰርግም፣ ሐዘንም ላይ እንዳይገኝ!! እንግዲህ ይሄ የሚሆነው ለአንድ አመት ያህል ነው፡፡ አቶ አካሉ አንገቱ ቢቀላና ቢወድቅ በቀለለው ተሰብሳቢው በከፊል ያዘነም የተደሰተም አለ፡፡ እንደ ሰው ችግሩ አሳዝኗቸው አቀርቅረው ያለቀሱ ሞልተዋል፣ እንባቸው እንዳይታይባቸው ኩታቸውን ተጠልለው የነፈረቁም አሉ:: እነዚህ ሰዎች አቶ አካሉ ደጃቸውን በተደጋጋሚ ለችግሩ ምላሽ እንዲሰጡት የለመናቸው ናቸው፡፡ አሁን ቢያለቅሱ ምን ረብ አለው እንዳይባሉ ኩታቸውን ተሸፈኑ፤የህሊናን እውነት ተሸፍኖ ማምለጥ ባይልቻም፡፡ በዳይ በጥልቅ ሀዘን ተውጦ በትካዜ ሩቅ ሔዷል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች የበየኑበት ብይን አሁን ካለበት ችግር አልበለጠም፤ ችግርም የሰውም ፊት ደቁሶታል… ይችልበት መቻል አጥቶ የተስፋ ማድረግ ጉልበቱ ለላመ ሰው በቃኝ ተሸንፊያለሁ ብሎ የተንበረከከን በእንዲህ መልክ መማረክ፣ ጀግንነትም ዳኝነትም (ቅጣትም) አይደለም፡፡
ድንገት ወ/ሮ የውብዳር ፀጥ ብሎ ከራሱ ጋር የሚሟገተውን ማህበሰብ ልብ በሚሰብር አንጀት በሚያላውስ ሁኔታ ተንበርክከው የሀገር ሽማግሌዎቹን መማፀን ያዙ… “አባቶቼ እንደው መገኖቼ በአምላክ እናት ይዣችኋለሁ… አቶ አካሉን ይቅርበሉልኝ…? እኔን አፈር ልብላ ቢብሰው ቢቸግረው እንጂ የኔን የምስኪኗን ሊሞቱ አንድ ሐሙስ የቀራቸው ከብቶች ለመስረቅ ሽቶም አይደል...! እስከአሁን ረሃብ ሳይጐበኘኝ፣ ችግር ሳያምበረክከኝ እፊታችሁ እንድቆም ያደረገኝ እርሱ ነው:: የቀዬውን ሰው እያስቸገረ መሬቴን አርሶ ሰብሌን አርሞ፣ ጐልጉሎ፣ አጭዶና ወቅቶ የሚያስገባልኝ እርሱ ነው፡፡
እንደ ሴት ውሃ ሳይቀር ወንዝ ወርዶ የሚቀዳልኝ ማንሆነና? እኔን እንዳይርበኝ ብሎ አለመነኝም… እኔ ላቀርቅር እኔን የሰው አይን ይብላኝ እርሱ መሆኑን ባውቅ ኖሮ ርሃብ ይፈነችረኝ ይሆናል እንጂ እናንተን ዳኙኝ ብዬ አላለቅስም ነበር::” ተሰብሳቢው በከፊል ተቆጣ “ምን ትላለች እቺ እዚህ ሥራ ፈት ያለ መሰለሽ እንዴ ቀኑን ሙሉ ስታጉላሊን የምትውዪ?!” “ታዲያ ይሔን ካሰብሽ ተሰብስበሽ አትቀመጭም ነበር?” ሌላም ሌላም አሏቸው፡፡ ዳኞቹ ይይዙት ይጨብጡት አጥተው ግራ ተጋቡ ሰው እንዴት የገዛ ፍርዱን “ተው” ይላል ሽማግሌን ገፍቶ ዳኝነትን ረግጦ መሔድ በቀየው ነውር ስለሆነ ነው እንጅ ገሚሱ ተነስቶ ቢሔድ በወደደ… አቶ አካሉ የልቡ ጉልበት እንደተሰበረ ተስፋውም አንገቱም ተሰብረው አቀርቅሮ አመዳሙን መሬት በእንባው እያላቆጠ የሚደረገውን ያብሰለስላል፡፡ ነፋስ ጊዜውን ተረክቧል:: ወንዱም ሴቱም ኩታና ነጠላውን ጆሮ ግንዱንና አፉን ጠምጥሞ የሚሆነውን እየተጠባበቀ ነው፡፡
ወ/ሮ የውብዳር ከተንበረከኩበት ቀና ብለው ጀርባቸውን ለሽማግሌዎቹ፣ ፊታቸውን ለማህበረሰቡ አዙረው “ወገኖቼ ዳኙኝ…? አቶ አካሉን የክፉ ቀን ደራሼን ለክፉ ቀኑ ባለመድረሴ ደጉን ሰው ማሩልኝ? ምን ሆነህ ነው? ሳትሉ የሆነውን ሁሉ እንዳልሆነ የተደረገውን ሁሉ እንዳልተደረገ ቁጠሩት፣ የመበደሌም የበዳዩም መከራ በልቤ ሚዛን ስመዝነው እኩል ሆኖ አገኘሁት፡፡
ዛሬ ፈርዳችሁ ወደየ ቤታችሁ ብትሔዱ ውለታው አንቆ ይገድለኛል፤ ደግነቱ እረፍት ይነሳኛል…?” አንድ በአርባዎቹ አጋማሽ ያለ ቦርጫም ሰው ያለ ፍቃድ ብድግ ብሎ “ይቅርታ ወገኖቼ፤ ለወ/ሮ የውብዳር እኔ አንድ እናት በግ ከነግልገሏ እሰጣታለሁ…” ሳያስቡት ከዋርካው ሥር ያሉት በሙሉ አጨበጨቡ… አቶ አካሉ በትዝታ ከነጐደበት ደንግጦ ተመለሰ… ይሰቀል ተብሎ ህዝቡ ያጨበጨበ መሰለው፡፡  እትዬ ሽታዬም እንደ ሰውየው ተነስተው… “መቼስ እግዚአብሔር በእነዚህ ምንም በሌላቸው ሰዎች እያስተማረን ነው… በፊት የሌለብንን መጨካከን ዛሬ ላይ እያየነው ነው፡፡
አንዳንዴ የበዛ ደግነትን መቸገር ይወልደዋል… በር ዘግተን መብላት ከጀመርን ቆየን! ሌላው ቀርቶ `በእንተ ስማለማርያም` የሚለውን ተሜን የለንም እያልን ማባረር ከጀመርን ሰነባበትን… ቀኝ እጅ ግራው ላይ ከፋ፤ አቶ አካሉ ምን አጠፋ…? የራሱን በረት ነው የከፈተው፤ ቤተሰቡ በሙሉ በችግር ከተቆራመዱ ሰንብተዋል… ሽንፈትን የማይወድ፣ ጉልበቱ የማይለግመው ደጅ ወጥቶ ከለመነ ቆየ፤ መቀጣት መዋረድ ካለብን እኛው ነን ተፈራጆች፤ ሆኖም ፊት ነሣነው፡፡ ማንም አይኑ እያየ ለሞት እጅ አይሰጥም እና ያደረገውን አደረገ፡፡ እኔ የሙት ልጆች ይዤ አይዞሽ ያለኝ ነበር? ግን ግን ልጆቼ የደረሱ ስለነበሩ ያን ያህል ችግር አላንበረከከኝም:: እኔ ደግሞ አንዲቷን ክበድ ላሜን ሰጥቼዋለሁ፡፡” እልልታው አስተጋባ፤ አቶ አካሉ ብዥ አለበት፤ ስቅስቅ ብሎ ማልቀሱን ተያያዘው፤ ሽማግሌዎቹ ግራ ገባቸው፡፡ ሌላ ሰው ተነሳና፤ ጥጃ፣ በግ፣ ገንዘብ፣ ቁና እህል፣ በሬ፣ ለርሱም ለወ/ሮ የውብዳርም ቃል ገቡላቸው፡፡ የገዛ ችግራችን ከኛው አይወጣ ይመስል ዋርካው እስኪገረም ተረባረቡ:: ዳኝነቱን በእንባ አረጠቡት (የትላንት መፋረጃ አንሆንም፤ ዛሬ ግን ዳኛም ከሳሽም ነው፡፡
ምስክሮቹ ግን እኛ፡፡) የመሃሉ ዳኛ እንባቸውን መግታት አቅቷቸው… “ማጣት ከሆነ የሚያፋቅረን መራብ ከሆነ የሚያስተዛዝነን መቼስ ተመስገን አይባል ይሁን እንጂ…” እንባቸውንም የረጠበ አፍንጫቸውንም በኩታቸው አበስ አደረጉ… አጠገባቸው ያሉት ለጠቁ፤ “መቼስ ይሔ ዋርካ አይፈርድብንም…? የዛሬው የተዛባ ሚዛንና ፍርድ አወቅ እውነት … ለሰማይ ቤቱ አሳልፎ ይሰጠን ነበር… እንደተባለው ባዶ ጎታችን ከሆነ የሚያወዳጀን ከዚህ በኋላ ከመሆኑ በፊት እንተሳሰብ! ከመሰበራችን ቀድመን እንደጋገፍ! አቶ አካሉ አንድ በሬውን ወስዶ ከወ/ሮ የውብዳር ጋር አጣምዶ ሲያርስ እሰይ ጐሽ፣ ተባረክ ብሎ የመረቀው አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን ልንፈርድበት ይሰቀል ልንለው ተሰባሰብን… የፈጠረንስ የሰቀሉትን የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አይደለም ያለው፣ እባክህ ማረን…?” ተሰብሳቢው በሙሉ አቀረቀረ… አቶ አካሉ ተሰብሯል፤ ከችግሩ በላይ ዛሬ የሰው ፊት ጠብሶታል… የገዛ ችግሩና እውነቱ ገፍተው ገፍተው ዛሬ ላይ አምጥተውታል… “ወገኖቼ አራተ ቀን ሙሉ አንጀቴ አልችል ብሎ ከብቶቹን ገበያ ወስዶ መሸጥ አቃተኝ፤ ያለመደብኝ ነገር ሆኖ እውነት ልቤን ቀይዳ እናንተ ፊት አምበረከከችኝ… ይቅር በሉኝ እመልሳለሁ…” ዋርካው የመንደሬውን በእምባ መራጨት አይቶ አዘነ… “የዛሬ ይቅርታ ነገን መውለድ ይችላል… እውነት ከህግ በላይ ነው፡፡ ያላመንበት ትላንት የያዝነውን ዛሬ ያስጥለናል፡፡
እኔ ደግሞ ዛሬዬን አምናለሁ፤ ትላንትና ዝናዬ ቢሆንም::” አለ አቶ አካሉ ከእንባው እየታገለ… አቶ ሞቱማ ስሜታዊ ሆነው ተነሱ “ሀገር በፍቅር ይዳኛል፤ ጉልበት የትኛውንም ነገር ይሰብር ይሆናል እንጂ ፍቅር ሆኖ አያሸንፍም፤ እስቲ በእነዚህ ሰዎች የችግር ቀዳዳ እራሳችንን እንመልከት፤ ያኔ ኧረ በህግ የሚባለው ጥያቄ መና ይሆናል፡፡
ፍርድ እንደ ራስ ነውና ፍርዱን ሰጥተዋል… የተቻለንን እንስጣቸው… እኔ ሁለት አህያ ሰጥቻለሁ ለሁለቱም…” ዋርካው ተደሰተ፡፡ ንፋስ ለምሽት ቦታውን ሰጠ፤ ተፈጥሮ በሰው ሳትፈርድ ሰው ልቡን ሰምቶ ይሔ ነውም ይሔ ነውም ሳይባባሉ ለረጅም ሰዓት ሁሉም ልቡን እየሰማ ቆየ፡፡ ለመሔድ የከጀለ እግር ልብ ገስጾት ታቅቧል ዳኝነቱ…

Read 1966 times