Saturday, 11 July 2020 00:00

"ሽልማት የሚያስፈልገው እኮ አርአያ እንዲኖረን ነው"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ስለ ሽልማት ስናስብ---ከነበረው አልወጣንም- በአስተሳሰብ ማለቴ ነው:: ሌላስ መኖር አልነበረበትም ወይ የሚል ጥያቄ አንጠይቅም፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ፋውንዴሽን አንዱ ትልቁ የሽልማት ድርጅት ነው፡፡ ይሄን  አሁን --- ብልጭ ድርግም ከሚሉት የሸላሚ ድርጅቶች ልዩ የሚያደርገው በአግሮ ኢኮኖሚ፣ በእርሻ፣ ኢንዱስትሪን ባስፋፉና በጀመሩ ሰዎች፣ በሰዓሊያን፣ በደራሲያን -- እያለ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽልማት ድርጅት ነው……እኛም የሚያስፈልገን የዚህ ዓይነቱ ይመስለኛል:: ብንችል ስፔሻላይዝ ብናደርግ ጥሩ ነው:: ለአርት ብቻ የሚሸልም ሊኖር ይችላል:: አግሪካልቸር ላይ ትልልቅ ስራ ለሰሩ ወይም አዳዲስ ኢኖቬሽን ለፈጠሩ ሰዎች፣ የሥራ ፈጠራ ላመጡ…..ኢንተርፕሩነርስ ለመሳሰሉት የሚሸልም ተቋም መናፈቅ ብቻ አይደለም--ብንችል ልንታገልለት የሚገባ ነገር ነው የሚመስለኝ፡፡ ምክንያቱም It will bring out the excellence…….ዋናው በቃ-- የመጠቀ አእምሮ አለው የሚባለውን ሰው ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤ ያስከብረዋል፡፡ ከዚያም እንዲወሳ ያደርገዋል:: ከዚያ እንግዲህ ትልቁ ነገር፣ ትውልድ አርአያ እያገኘ ይሄዳል፡፡ አርአያ እንዲኖረን እኮ ነው ሽልማት የሚያስፈልገው--ትልቁ ነገር እሱ ነው፡፡ አርአያ ስላጣንም ነው--አርአያ ሲታጣ ደግሞ እንዲሁ እንደ ውሃ መፍሰስ ብቻ ነው የምትሆኚውና---እገሌን እሆናለሁ የምትይው ነገር መኖር መቻል አለበት፡፡
ያ አይነቱ ሰው ደግሞ ከአፈርሽ የበቀለ ቢሆን ነው የሚመረጠው--እንጂ አንድ የሳይንስ ተማሪ አንስታይንን መሆን እፈልጋለሁ ሊል ይችላል --- ግን የአገርህ ሰው ለዚህ የሚያበቃ፤ ለዚህ መጠሪያ-- ለአርአያነት የሚበቃ አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ መጀመሪያ ቢጠይቅ ነው የሚሻለው:: ለልጅ ልጆች እንደ እገሌ እንድሆን ….በቃ የአበበ ቢቂላ …ጥላሁን ገሰሰ ይድርሻል  እንደምንልበት ዘመን---የሆነ የምናስባቸው ሰዎች አሉ፤ እና እገሌ የምትይው የምትጠሪው---ሩጫ ሮጠሽ እንደ ኃይሌ ገ/ሥላሴ መሆን እፈልጋለሁ….የምትይ ከሆነ…ያንን እሆነዋለሁ ብለሽ ከልጅነትሽ የምታስቢ የሚያደርግሽ መሆን አለበት፡፡
እንግዲህ ከድሮም ዶክተር እሆናለሁ…ፓይለት እሆናለሁ የሚሉት የሚታወቁ፣ የተለመዱ ናቸው፡፡ ግን እንደ እገሌ የሚለው ነገር የሚመጣው---ሽልማት እየሰጠሽ፣ እያበረታታሽ፣ ስሙን እያነሳሳሽ፣ አንዳንድ ነገሮችን እየሰየምሽለት ከሄድሽ ነው፤ከሰው አዕምሮ እንዳይወጣ የምታደርጊው…እንጂ የክፍል ጓደኞችሽን የመሳሰሉ ትላልቅ ቦታ የደረሱ ሰዎችን እናውቃለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን እዚህ  የሚነሱበት ሁኔታ ይጠፋል፤ ውጭ አገር ወይ ናሳ ገብተዋል ወይ አንድ የአውሮፕላን ድርጅት ውስጥ ናቸው…ትልልቅ ኢንጂነሮች ተብለው የተቀመጡ ሰዎች አሉ:: ታዋቂ ፊዚስቶችም  አሉ::
ግን እነሱን እዚህ የምናመጣበት መንገድ የለም፡፡ ለዚህም እንግዲህ እንዲህ አይነት ፋውንዴሽን ሲኖር፣ መጀመሪያ ኢንዴክስ ይሰራል፤ በዓለም ደረጃ ጭምር ያሉ ኢትዮጵያውያንን--- ታላላቅ ሰዎች የሚባሉትን በሙሉ ይመዘግባል---አሁን እኮ  ቢያንስ ኢንዴክስ የለሽም---ችግሩ እኮ አመልካች የሆነ ተሰብስቦ የሚገኝ ሰነድ አታይም፡፡ አንድ ጊዜ አስታውሳለሁ…ሰዓሊ ከበደች ተክለአብ ከአሜሪካ የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ አንድ ፕሮጀክት ሰጥቷት መጥታ ነበር…ምንድን ነበር ፕሮጀክቱ---ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሰዓሊዎች በሙሉ አንደር ሊስት ማድረግና መያዝ ነው…በምን በምን ትምህርት እንደተመረቁ፤ ግን መረጃ  ማግኘት አልተቻለም…አብሬያት ስዞር ነበር፤ አድራሻ ማግኘት ጭራሽ ከባድ ነው፤አሁን ትንሽ ሞባይል አቅልሎት ከሆነ …በሞባይል ደውለሽ አድራሻ ስጡኝ ልትይ ትችያለሽ:: ስልክና ስም ማግኘትም ቢሆን ከባድ ነገር አለው፡፡ የሽልማት ድርጅት መኖር አንዱ አድቫንቴጅ፣ ታዋቂ ሰዎችን አሰባስቦ የሚይዝ ዶክመንት ይኖረዋል ማለት ነው:: ሁለተኛው ለዚህ ሽልማት ለመብቃት ሌላው ወጣት ይተጋልና ነው፤ ይኼ ትልቁ ቁም ነገር ነው፡፡ ሦስተኛው ያንን ሰው ማክበር መጀመራችን ነው፤ምንም ይሁን ምን ያ የተሸለመበት ሙያ የእሱ ተከባሪነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ያንን አክብረሽለት…ምንም ዓይነት ህይወት ይኑረው…ምንም ዓይነት ኑሮ ይኑር አንቺም ማድነቅ ያለብሽ ኤክሰለንሱን ነው፤የሰውን ትልቁን ችሎታ ነው መያዝ ያለብሽ፡፡ አሁን ትልቁ ችሎታ ለሌሎች አርአያ ብቻ ሳይሆን ለስራ፣ ለትምህርት፣ ለዕውቀት፣ ለኤክሰለንስ ያለንን አክብሮት ሁሉ መንገድ ይመራናል፤ስለዚህ ሁለገብ የሆነ ሸላሚ ድርጅት ቢኖር የምመኘው…ምናልባትም የምጥረው ለዚህ ነው፡፡ ሌላው በዚህ በሥነቃል፣ በፊደል፣ በቋንቋ ረገድ እያዘቀዘቅን የምንሄድበት---በጣም አርቴፊሻልና ክልስ ዓይነት፣ ዲቃላ ዓይነት ቋንቋችንን ለማጥራት የሚችሉት፣ እንደ ሌክሲኮግራፈርስ ዓይነት ተቋማት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ባህል ሚኒስቴር ይሄን መስራት የሚያቅተው አይመስለኝም፡፡ አየሽ-- በባህል ቅርሳ ቅርስ፣ ከዚያ ደግሞ ሥነ ቋንቋ ዙሪያ አንድ ጥሩ ተቋም መኖር ያለበት ይመስለኛል፡፡ ብዙ ነገራችን ዝብርቅርቁ የሚወጣው፣ ሴንትራላይዝድ የሆነ አመራር የሚያካሂድ ባለመኖሩ ይመስለኛል፡፡
ቴሌቪዥን ላይ መነገር ያለበት ቋንቋ፣ ሬዲዮ ላይ መነገር ያለበት ቋንቋ--- የጽህፈት ቋንቋ የምትያቸው እንዴት እንደሚለያዩ ሃይ የሚል ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ከላይ ሆኖ እስቲ አረፍ በሉ እዚህ ጋ---ይሄን ቋንቋ እያበላሻችሁ ነው፤ እንዲህ ነው መሆን ያለበት የሚል የሚከበር---- ፈረንሳዮቹ ለምሳሌ አላቸው፤ ተቋሙ ነው ሁሉንም የሚወስነው:: በዘፈቀደ እንዳይሰራ እኮ ነው፤ ሁሉ ነገር ዝብርቅርቁ ሲወጣ አናርኪ ነው የሚሆነው መጨረሻ ላይ፡፡ ሁሉም ባለ ጉዳይ ይሆናል፤ ሁሉም ሃላፊ ነኝ ይላል፤እና የፈለገው ሰው የፈለገውን ቃል ፈጥሮ፣ የፈለገው ቦታ ይደነቁረዋል፤ይሄ ልክ አይደለም የሚባልበት መንገድ የለም፤ሁሉም በየቤቱ ብቻ ነው የሚያዝነው፡፡--
(ገጣሚና ተርጓሚ ነቢይ መኮንን፣ በሸገር ኤፍኤም ከጋዜጠኛ  መዓዛ ብሩ ጋር ካደረገው ጣፋጭ ወግ የተወሰደ)  
Read 543 times