Saturday, 11 July 2020 00:00

ለህዳሴው ግድብ የየድርሻችን ለመወጣት መፍቀድና መትጋት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 • የግብፅ ልጆች ከእናታቸው ጡት ቀጥሎ የህልውናቸው መሠረት ተደርጎ የሚነገራቸው ዐባይ ነው
   • ሁላችንም የየራሳችንን ችቦ ደምረን ካቀጣጠልን፣ የድህነት ጨለማ ከሀገራችን ይወገዳል
   • የዐባይን ጉዳይ ከፖለቲካና ከፓርቲ ጋር ለማገናኘት መሞከር ነውር ነው
   • የዐባይ ግድብ እኛ ታሪክ መሥራት እንድንችል የተፈጠርልን ዕድል ነው


          ቢኒ ምዕራፍ ወይም ወ/ሩፋኤል አለሙ ከ260 በላይ የሙዚቃ ክሊፖችን በዳይሬክርነትና በስክሪፕት ጸሃፊነት አዘጋጅቷል፡፡ በብስራት 101.1 ሬዲዮና በአሀዱ 94.3 ሬዲዮ ለ4 ዓመታት የሰራ ሲሆን የምዕራፍ ፕሮሞሽን ባለቤትም ነው፡፡ ቢኒ በምዕራፍ ፕሮሞሽን ለህዳሴው ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ የተሰሩት የ8100A ማስታወቂያ ቁጥር አንድና ሁለት ላይ በሃሳብ አፍላቂነት፣ በግጥምና ዜማ ደራሲነት አስተዋጽዖ ያደረገ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ለህዝብ የቀረበውን ;የዓባይ ዘመን ልጆች; የሙዚቃ ክሊፕ ግጥምና ዜማን በመድረስ ፕሩዱዩስ አድርጓል፡፡ የአዲስ አድማስ አምደኛ ደረጀ በላይነህ፤ ከቢኒ ምዕራፍ ጋር በሥራዎቹና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ወኔና መንፈስ የሚያነቃቃ ወግ አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-

                  ለህዳሴው ግድብ በሰራሃቸው ሥራዎች  ያገኘኸው ምንድን ነው?
የሠራሁት የሀገሬ ጉዳዩ ስለሚመለክተኝ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ከሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን የምስክር ወረቀት ተቀብያለሁ፤ ክፍያን በተመለከተ ድርጅቴም እኔም ያገኘነው ነገር የለም፤ የሰራነው በነፃ ነው፡፡ ለህዳሴው ግድብ ምዕራፍ ፕሮሞሽንና እኔ የሠራነው ይህ ብቻ አይደለም፤ አፋር ሉሲ የተገኘችበት ሥፍራ ድረስ ከደምፃዊው ሀሴን ዓሊ ጋር በመሄድ የአፋርኛ ዘፈን ክሊፕ ሠርተን፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ጽ/ቤት አስረክበናል:: ይህ ሁሉ ግን በገንዘብ ለማይተመነው ለሀገሬ ልማት የሠራሁት ሥራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ  ሀገራዊ ጉዳዮች ይኮሮኩሩኛል፤ ስሜት ይሰጡኛል፡፡ ለሦስተኛ ዙር የ8100A ልሠራ የተነሳሁት ክብርት ፕሬዝዳንቷ በቤተ መንግሰት ውስጥ ተዘጋጅቶ በነበረው የኪነ ጥበብ ሰዎችን ያሣተፈ ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ንግግር ልቤን ስለነካው ነው:: ፕሬዚዳንቷ ግብፆች ስለ ናይል እየሠሩ ስላለው ነገር አንስተው ከእኛ ጋር በማነፃፀር ሲናገሩ፣ ወዲያው ሀሳብ በውስጤ ተፀንሶ፣ ግጥምና ዜማውን እዚያው ጀመርኩት፡፡
“የዐባይ ዘመን ልጆች” የሚለው የሙዚቃ ክሊፕ ምን ያህል ወደ ህዝቡ ገብቷል?
በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እየቀረበ ነው:: ህዝቡም እንደተደሰተና እንደተቀበለው ልዩ ልዩ ግብረ መልሶችን እያገኘን ነው:: ገንቢ አስተያየቶች ደርሰውናል፡፡ ክሊፑን የሠራነው ቀድሞ “የኛ” የሚል ስያሜ ከነበራቸውንና አሁን “እንደኛ” እየተባሉ ከሚጠሩት ወጣቶች ጋር ነው፡፡ የእነርሱ ቡድን በተለመደው አካሄድ ከራሳቸው ቡድን ውጭ ሌላ ሰው አያሰሩም፡፡ ይህ ግን የሀገር ጉዳይ ስለሆነ ያለምንም ማቅማማት በሙሉ ልብ አብረውን ሠርተዋል፡፡  በክሊፑ ላይ መሀል የሚጫወተውን መላኩ መስፍን የሚባል ወጣት አሳትፈዋል፡፡ ለሀገር ያላቸው ፍቅር የሚገርምና የሚደንቅ ነው:: በዚሁ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ:: የመዝሙሩ ሀሳብ ሲመጣም እንዴት ልሥራው የሚለው ነገር ከብዶኝ ነበር፡፡ ስለ ዐባይ ለመሥራት “ወዴት መሄድ አለብኝ” ብዬ የሄድኩት ወደ አድዋ ድል ነበር፡፡ ዐድዋ ግዙፍ የጀግንነት ተጋድሎ ታሪክ፣ የአብሮነታችን መቀነት ነው፡፡ ወደዚያ ሀሳብ ደርሼ ስመለስ የሚያሥፈልገን ነገር አንድነት ነው፡፡ ወደ ቀጣዩ ዘመን ስመለከት ደግሞ ከፊት ለፊት ያለውን ትውልድ አሰብኩኝ፤ እሱ ደግሞ ዕዳ ያለብን ሰዎች እንደሆንን አሣየኝ፡፡ እናም አሁን ያለነው “የዐባይ ዘመን ሰዎች” ይህንን አደራ መወጣት እንደሚገባን ተሰማኝ፡፡ ይህን ባናደርግ  መጪው ትውልድ “ድህነትና ኋላቀርነት አወረሳችሁን!” ብሎ ይወቅሰናል፡፡ ስለዚህ የሦስቱን ትውልድ ሠንሠለት አቆራኝቼ ለመስራት ሞክሬያለሁ::
አባቶቻችን በደም መስዋትዕነት ነፃ ሀገር እንዳስረከቡን እኛ ደግሞ በላባችን በዕውቀታችንና ትጋታችን ከድህነት የተላቀቀች ሀገር ማስረከብ አለብን ማለትህ መሰለኝ?
ይህን ለማድረግ መጀመሪያ መግባባት መቻል አለብን፡፡ ዐባይ መጀመሪያ ለእኛ ምንድነው? ይህን መፈተሽ ያስፈልጋል:: እንደሚታወቀው የቱም ሰው ቢሆን የሚከተለውና ዋጋ የሚሰጠው ለሚወድደው ነገር ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዐባይን እንድንወድድ ተደርጎ የተሠራብን ነገር አይታየኝም፡፡ ለዚህ ነው ቢያንስ “ሰዎች ዐባይ የኛ ነው” የሚለው ስሜት እንዲሰማቸው አድርገን ለመስራት የሞከርነው፡፡ ዐባይ ለኛ ምን ጥቅም ይሰጣል? መገደቡ ያስፈለገው ለምንድነው? ዐባይ ውሃ ብቻ ነው? ጥቅም ካለው ጥቅሙ እስከ የት ድረስ ነው? የሚለውን ነገር፣ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ መፍጠር ያስፈልጋል:: ስለዚህ እኛ እንደሞተር ማስነሻ የሆነን ነገር፣ ክብሪት መጫር ነው የሞከርነው:: ሕዝቡን አነሳስተህ ጆሮውን ሲከፍትና ልቡን ሲያዘጋጅ፣ ስለ ዐባይ መናገር የሚችሉ ሰዎች  በዕውቀትና በታሪክ ላይ የተመሠረተ  ነገር መናገር ይችላሉ፡፡ ባለሙያዎች መናገር ቢችሉ ጥሩ ውጤት ይገኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሁሉም ሰው በየፈርጁና በየሙያው የሚቻለውን ሁሉ ቢያዋጣ፣ ወደ ግባችን ለመድረስ በሁሉም ላይ የእኔነት ስሜት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡
የግብፅ ልጆች ከእናታቸው ጡት ቀጥለው የታሪክ ጉዳይ ሲያነሱ የህልውናቸው መሠረት ተደርጎ የሚነገራቸው ዐባይ ነው:: ስለዚህም የዐባይ ጉዳይ ሲነሳ፣ ዐባይን የራሳቸው አድርገው እንዲያስቡት ተደርጓል:: አንዳንዶቹ የዐባይ ምንጭ ሀገራቸው ውስጥ እስኪመለስላቸው ድረስነው የተሰራው:: እኛ ግን ከምንጩ ተፈጥረን፣ ምንጩን ያለ ማወቃችን ሁኔታ ያሳዝናል፡፡ ሕዝቡም የማወቅ ጉጉት ሊኖረው ይገባል፡፡ መቼም ቢሆን ዛሬ የምትዘራው ዘር ነገ አዝመራ ይሆናል፤ ፍሬ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ስለ ዐባይ የምንሠራው በሙሉ እንድትወደው እንድትተጋለትና እንድታስፈፅመው የሚያደርግ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛም በዚህ መነሻ ትንሽ የራሳችንንን ለማዋጣት ብለን የሠራነው ነው፡፡
እንደ ዐድዋ በአብሮነት ሆነን፤
ዐባይን እንጨርሳለን!
ሆ! ብለን ተምመን በፍቅር ዜማ
ይገደብ ዐባይ ከሀገር ይስማማ!! --- ያልነው ለዚህ ነው፡፡
ዐድዋን ስታስብ ትልቅ አቅም ይሰጥሃል:: ኢትዮጵያውያን የውስጥ ልዩነቶች እንኳ ቢኖራቸው በጋራና በአንድነት ሆነው፤ ቦታው ድረስ ሄደው በመዋጋት ሀገር አስረክበውናል፡፡ እኛም ለልጆቻችንን የምንነግረው ምንድን ነው  ለሚለው ጥያቄ፤ የሚዳሰስ ሀውልት፤ የሚሻገር ታሪክ ሊኖረን ይገባል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ፤ የዐባይ ግድብ እኛ ታሪክ እንድንሠራ የተመቻቸ ዕድል ነው፡፡ ነገሩን ከፖለቲካና ከፓርቲ ጋር ለማገናኘት መሞከር ነውር ነው፡፡ “ዐባይ የእኔ ነው፤ ግድቡ የእኔ ነው” ካልክ አንተ መጀመሪያ እዚያ ውስጥ መግባት አለብህ፤ ከዚያ የእኛ ይሆናል፡፡ “የእኛ ነው” ብለህ የቡድን መጠሪያ ሰጥተኸው፣ ሁሉም ሰው ሳያምንበት ከምትቆሰቁሰው “የእኔ ነው” ብዬ እኔ ራሴ ማመን አለብኝ፡፡ ባለቤትነት ሊሰማኝ ይገባል፡፡ እኛም በዚህ ስሜት ለመስራት ሞክረናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለፈጠራና ለስራ የተዘጋጁ መሆናቸውን ማሰብ ያስፈልጋል:: ግን የሚያነሳሳቸው መሪ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ለልማት ብቻ ሳይሆን ለጥፋትም ነው፡፡ መስመር ካሳትካቸው በዚያው ስለሚፈሱ ችግር ይፈጠራል::  መልካም ዘር ከዘራህ ደግሞ፤ ወጣቱን ከያዝከውና “ያንተ ነው” ካልከው፣ ስለ ጦርነት ሳይሆን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሀገሩን ለማልማት እስከ መጨረሻው ግብ ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡
ስለ ዐባይ የምትነግረውም ነገር ሲገባው ስሜት ይሰጠዋል፡፡ ካልገባው ደግሞ ምኑም አይደለም፡፡ በተለይ ሚዲያዎች በዚህ ነገር ላይ ማርሻቸውን ቀይረው ቢሰሩ ብዙ ትርፍ እናገኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ግብፅ በከፍተኛ ደረጃ የውሃ ሙሌታችንን ለማዘግየት የማትረግጠው ደጅ፣ የማትቀጥፈው ቅጠል የለም፤ እኛ ጋ ደግሞ ክፍተት አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ታስባለህ?
አንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሰዎች በየራሳቸው የሚሠሩት ቢኖርም ግን ሁሌም እንደ አቅሙና በሚመለከተው ጉዳይ ላይ መሥራት አለበት፡፡ ለምሳሌ በውሃ ጉዳይ ላይ ያጠና ሰው፣ ስለ ውሃና ውሃ ይናገር፤ በዲፕሎማሲ የተሻለ ጥበብና ዕውቀት ያለው ሰው፣ የዲፕሎማሲ ሥራ ይስራ፡፡ ተወዳጅ የሆኑ የኪነጥበብ ሰዎች ደግሞ ሕዝቡን በማነሳሳትና በማነቃቃት ይስሩ! ሚዲያውም የራሴ ጉዳይ ነው በሚል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ቋንቋዎች የአለምን ሕዝብ የማሳመን ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡ ግብፆች የበለጡን በዚህ ይመስለኛል፡፡ በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛና በሌሎችም ቋንቋዎች የዓለምን አመለካከት ለመቀየር እየሠሩ ነው፡፡ ይሔን ደግሞ ሌሎችም እያስተጋቡላቸው ነው:: በዚህም የተነሳ ዕርዳታ የምናገኝባቸውን መንገዶችና ብድሮች ለመዝጋት ይሞከራሉ:: ይሁንና የኛ ግድብ የተጀመረው ምንም የሌላት ኢትዮጵያዊ እናት ከመቀነቷ ፈትታ ባዋጣችው፣ ወታደሩ ከደሞዙ ቆርጦ በሰጠው ገንዘብ ነው፡፡ ገበሬው ከብቶቹን በጎቹንና ጥጃዎቹን ሳይቀር ሰጥቶ፣ ህፃናት ከትምህርት ቤት ምሳቸው ቀንሰው፣ መገደብ የጀመርነው ግድብ ነው፡፡ ይህን ነገር ለሕዝቡ መንገርና ሕዝቡንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ማሳመን ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ የጥበብ እንጂ የጦር መሳሪያ አይደለም:: ስለዚህ የመገናኛ ብዙሀን (ሚዲያዎች) ሚናቸው ትልቅ የሚሆነውም ለዚህ ነው:: ዐባይ ደግሞ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአሀዱ ሬድዮ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊዲያ አበበ፣ ሬድዮ ጣቢያው ሥራ ከጀመረ አንስቶ ለዓመታት ያለማቋረጥ “የኢትዮጵያ ወንዞች” በሚል በተለይ በዐባይ ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሰራውን ስራ ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ግለሰቦች ሚዲያ ላይ ሲኖሩ ለውጥ ያመጣሉ፡፡ አሁንም እንዲህ አይነት ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡ ሚዲያ ራሱን የቻለ የጦር መሳሪያ ነው፡፡
በአብዛኛው ግን ሚዲያ ላይ የሚታየው ነገር በግል ጉዳያችን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ቢበዛ እግር ኳስ አካባቢ ነው የሚያተኩረው:: የጋራ የሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያነሰን ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ብዙ የጋራ የሆኑ አስተሳሳሪ ነገሮች ያሏት ሀገር ነች፡፡ በጋራ የሳቅናቸው ሳቆች፣ በጋራ ያለቀስናቸው ለቅሶዎች አሉ፡፡ አብረን ተርበናል፣ አብረን ተሰድበናል፣ ከልዩነቶቻችን አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ይበዛሉ፡፡ እነርሱ ላይ መስራት አለብን፡፡
ነገሮችን ከፖለቲካ ጋር ማያያዝ ያለብንም አይመስለኝም፡፡ ለሀገር የሚሰራውን ልማት ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች፤ ነገ ከስልጣን ሲነሱ ይዘውት አይሄዱም፡፡ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክትም የህዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ባለው ችሎታና አቅም፣ ዕውቀትና ክህሎት ተረባርቦ ይህንን ፕሮጀክት ከግብ ማድረስ አለብን፡፡ “የእኔ ነው!” የሚል የፀና አቋምም ያስፈልገናል፡፡ በተለይ የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ማስተባባሪያ ጽ/ቤት ያሉ ሰዎች፤ ከእኛ በተለየ በተሻሉ፣ በአራት ዓይኖች ማየት፣ በአራት ጆሮዎች መስማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግብፆች ከሚሰሩት ስራ በተመጣጠነ አቅም ውስጥ መገኘት ይጠበቅብናል፡፡ ከጎናችን የሚቆሙ ሀገራት የመኖራቸው ያህል በባላንጣነት የሚገዳደሩን እንዳሉም መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህ ብዙ መስራት አለብን፡፡ እኔና ድርጅቴ ምዕራፍ ፕሮሞሽን ያደረግነውም ይህንኑ ነው፡፡
የዐባይ ጉዳይ የሀገራችን ዐብይ ጉዳይ ነው፤ ይህንን ስራ በጊዜና በአግባቡ ካልሠራን በትውልድ ተወቃሽ ከመሆን አናመልጥም:: ለመጪው ትውልድ ዕዳ ጥለን መሄድም የለብንም፤ አሳፋሪና አስወቃሽ ከሆነ የስንፍና ስራ ወጥተን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ይህን ፕሮጀክት ከግብ ማድረስ አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተረፈ ከግብፅ ህዝብ ጋር የሚያገናኘን ምንም ዓይነት ክፉ መንገድ የለም፡፡ እኛ በልተን እነርሱ ጦም ይደሩ ማለት የኢትዮጵያውያን የሕይወት ዘይቤ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ በልተን እናንተ ጦም እደሩ! የሚለውን መቀበል ልማዳችን አይደለም፡፡ የሚያከብሩንን እናከብራለን! ከእጃችን ማስነጠቅ ግን በታሪካችን ውስጥ የሌለ ነው፡፡
በኩበት ጢስ ዓይናቸው እየተጨናበሰ፣ ዳቦ የሚጋግሩልን የዐባይ ልጆች ታሪክ መቀየር አለበት፡፡ “ደህነትን እንደውርስ መቀባበል የሚቆመው በእኛ ዘመን መሆን አለበት” ብለን በጽናት መቆም አለብን:: “የዐባይ ዘመን ልጆች” ቁርጠኛ ሆነን ድህነትን ካልቀረፍን፣ የእናቶቻችንን ህይወት ከእንግልት ካላወጣን ኖረን ማለፋችን ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ እንግዲህ እኛም በዚሁ የዕድገትና የልማት ደመራ ውስጥ አንድ ችቦ መወርወር አለብን ብለን ያለንን ሰጥተናል፡፡ ሁላችንም የየራሳችንን ችቦ ደምረን ካቀጣጠልን፣ የድህነት ጨለማ ከሀገራችን ይወገዳል፡፡ የብርሃን ዘመን ይመጣል፡፡ ስለዚህ ከሁሉም በላይ አንድ ሆነን፣ ለአንድ ዓላማ መቆም ያለብን ጊዜ አሁን ነው፡፡ ዐባይን የስላቅና የወቀሳ መዝሙር ተቀባይ ከመሆን ወደ ብልፅግና መሸጋገሪያ ድልድይ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡Read 540 times