Saturday, 14 July 2012 07:50

እምባ የላሱ እሳቶች በሶረኔ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

የአቧራ ምሠሦ የሚቆምበት ምድረበዳ፣ በዕድሜ የተጋጠ ቦረቦር … ጭራሮዋቸው የተንጨፈረረ አጫጭር ግራሮች ታዩኝ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም… የከረረ ፀሐይ፣ ያረረ ሰማይ ታየኝ፡፡ ደሞ መለስ ብሎ አፈር የመሠለ አረፋ የሚደፍቅ ወንዝ፤ … የሚያባባ የወፎች ዜማ መጣብኝ፡፡ ፍቅር የተከለከሉ ልቦች፣ ለጦርነት የተቃኙ ወጣት አእምሮዎች በቁጭት ሲቆሉ፣ ትዝታ ሲያንገላታቸው፣ እንደ ጠላ ጋን በባሩድ ሲታጠኑ፣ በእሣት ሲማገዱ ታሰበኝ፣ ይህንን ከየትም አላመጣሁት፡፡ “ሶረኔ” የሚለውን የኢሕዴን ታጋዮችን የግጥም ስብስብ ሣነብብ ፊቴ ድቅን አለ፡፡ ብዙ ነገር ወለል ብሎ ታየኝ፡፡

ግጥሞቹ ግን በሀዘን አንጀቴን አላውሥው፤ እምባዬን አሥገድደው አይኔ ዳር ላይ አንከራትተውታል፡፡ በዚያ ከባድ ደመና ሥር እንደጠወለገ አበባ መሬት እየነካ ቀጥ የሚለው ተስፋቸው ታሥቦኛል፡፡ ጥንካሬያቸውም እጅግ አሥደንቆኛል! .. ራስን ሞት አፍ ላይ መጣል የጀግንነት ጣሪያ ነው፡፡ ያንን የሚያህል ግዙፍ መንግስት ለመጣል መነሣትን ሣሥበው በነርሱ ፈንታ ልቤ ይደነግጣል! ጐበዝ ነበሩ፤ ግን የአሁኑ ሁኔታ ያሳስበኛል፡፡ ከድል ማግስት ያለው እውነታ ያሳስበኛል፡፡ እነሱንም ቢያሳስባቸው ደስ ይለኛል፡፡

አሁን ግን ትግሉን ትተን ግጥማቸውን እንፈትሽላቸው፡፡

“ትዕግስት ሲያልቅ” የሚለው የአንገረብ ግጥምም የዚያን ታላቅ ተጋድሎ ትዕግስት ፈታኝ ዘመን የሚያመለክት ይመሥለኛል፡፡ ግጥሙ የተፃፈው ኢሕዴን በይፋ ከተመሠረተ ስድስት ዓመታት በኋላ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-

ሁሉም ነገር እንዲህ ባንዴ

እንዲህ ቶሎ ይደርቃል ወይ?

ሁሉም ነገር ውሎ ሲያድር

ይጠቁራል ወይ?

ሁሉም ነገር ውበት ሊያጣ?

እንዲህ ቶሎ ሊገረጣ?

ሁሉም ነገር ገላው ሊከስም?

እንዲህ ፈጥሞ ሊኰረኩም?

ሁሉም ነገር ፈጥኖ ሊወድቅ?

እንዲህ ቶሎ ቶሎ ሊደቅ?

ለዛው አልቆ ሊሞት ሲል ነው

ወይም አውቀው ሲገድሉት ነው

ወይም ደግሞ …

ትእግስት አልቆ ሲሟጠጥ ነው፡፡

ገጣሚው ቁና እየተነፈሰ፣ እምባውን እየጨመቀ የሚፅፍ ይመሥላል፡፡ አንዳች ሀውልት ፈርሶበታል፤ አንዳች ተስፋው የአመድ ክምር ሆኗል፡፡ ወይ የጥይት አረር ጀግናውን ነጥቆታል፣ ሕልሙን ዶጋመድ አድርጐበታል! “እንዲህ ባንዴ” ሲል በዋዛ አይደለም፡፡ የብዙ ቀን ድካሙና ጥረቱን ተነጥቋል! የሚል ጥርጣሬ ያመጣል፡፡ ያሣዝናል! ያባባል! ቢሆንም ይጣፍጣል፡፡

አንዳንዶቹ ግጥሞች ፕሮፖጋንዳ ወይም ስብከት ስለሚመሥሉ አይመስጡም፡፡ “ድምፆቻችን ከጫካው!” የሚለው አይነት፡፡

“ትዝታሽ አብሮኝ እንዲኖር” የሚለው ግጥም ደግሞ እጅግ ገላጭና ሥዕላዊ - ሆኖ፣ የሚያባባ ነው፡፡ የሚባባ ልብ ላለው፡፡ የዚህ ግጥም ፀሐፊ ባለቤቱ ኢሕአፓ ስለነበረች ደርግ ገድሎበታል - የሚል ማስታወሻ ተቀምጦለታል፡፡ ከግጥሙ አለፍ አለፍ እያልኩ ላሳያችሁ እስቲ፡-

ድምፅሽ ድምፄ ውስጥ አልፎ ልሳንሽን ያስታውሰኛል

አንደበትሽን ያሰማኛል

በዓይኔ ውኃ ውስጥ መልክሽ ሁልጊዜ አልተለየኝም

በሳሩም በቅጠሉም ተሽሎክሉኮ ይታየኛል

ገና ማልዳ በምትወጣ ወርቅማ ፀሐይ ደረት ላይ

በድምቡልቦቃ ጨረቃ፣ ከክዋክብቶች ፈርጥ ውስጥ

ተፈልቅቃ በምትታይ፤

ገፅሽ አልተለየኝም፣ ድንገት ትታይኛለሽ፤

በምሻገረው የወንዝ ውኃ በእጄ አፍሼ በምጠጣው …

ፊትሽ ይውለበለባል …

አይንሽ ይምዘገዘጋል …

በዞርኩበት አገር ምድር እንደተከተልሽኝ ነሽ፤

‘ከኔ ጋር አብረሽ ዞረሻል…. እያለ ይቀጥላል፡፡

ገጣሚው ከፍቅረኛው ጋር ሲላፋ፣ ሲቀልድ፣ ሲታገልና ሲጥላት፤ እርሷም ተራዋን ስትጥለው፣ ያለው ትዕይንት ቁልጭ ብሎ ትዝታቸውን ያሣያል፡፡ ይህ ለኔ ከአቅም በላይ የሆነ ሀዘን ፈጥሮብኛል! በጣም ከባድ!

ከነዚያ ፍም ልቦች - ከነዚያ የስሜት ሞገዶች የሚንቀለቀለው እሣት ፍንጣሪ ዛሬም ምላሹን መዝዞ ልባችንን ይልሰዋል!! አንዳች የገደል ማሚቱ የሆኑ ምትሀት አለው! … ግጥሞቹ በውበት ያን ያህል የላቁ አይመሥሉም! … ግን የሚሥረቀረቅ ድምፅ፣ ልብ የሚያማልል ዜማ አላቸው፡፡ ለትውልድ ለመሞት ወስነው የተንጠለጠሉበት ትልቅ ጥርስ የሚራመዱበት ሠይፍም ይታያል! ለእንጀራ አልነበረም የኖሩት! ለእንጀራ አልነበረም በረሀ የዘለቁት! (ዛሬ እንጀራ የበላቸውን ግን ቤት ይቁጠራቸው!) ተልዕኮዋቸው እስከዚህ ድረስ እንደሆነም እነርሱ ይወቁት!... ግን እንደ ባልጩት የጠነከረ ዓላማቸውን አደንቃለሁ! የያኔውን! ደ’ሞ ውበትም ያውቃሉ፤ ጥበብ ይወድዳሉ፡፡

ሌላው ቀርቶ እርስ በርስ መፈቃቀር እየተመኙ፣ ፍቅርን ያህል ሞገድ ለመገደብ ወስነዋል፡፡ ፍቅርን ያህል ጣዕም ለራሳቸው ከልክለዋል! ፍቅር የብዙ ጀግኖችን ጉልበት የበላ ነቀዝ! አንገረብ ይህንን ፅፏል፡፡

እንደተፋቀርን ላንተያይ

ሳንተያየም ላንፋቀር

እንደመናን ካ’ለም ነገር

ከስሙ ተራ ስንባረር

በታጋይ ሕግ ተገድበን

በአጉል ኩራት ስንጠፈር

መቸስ ምን እንላለን

በተስፋ ከመሞት በቀር

አያሣዝንም? እየተዋደዱ፣ ያለመገናኘት! እንደ ባህታዊ ለምድር ፅድቅ መከልከል፣ ሰማይ ለማይከፍለው ዋጋ፣ ሞት ለማይሻገር ገድል! ለዓላማ ብቻ መሮጥ? ግጥም ስሜትም ነውና ስሜት ብቻ የሆኑ ግጥሞችም አሉ፡፡ ቢሆንም ፅፈውታል! ለምሳሌ “ጐል ማለት ይሄ ነው” በወጉ አልተፃፈም፡፡

መጽሐፉ ውስጥ ፈርጠም ያለ አቅምና ጣዕም ካላቸው ግጥሞች ውስጥ የሚመደቡት የአንገረብ ግጥሞች ወደ ተፈጥሯዊ ውበትና የስሜት ግጥሚያዎች፣ የሀሣብ ልፊያዎች ያጋድላሉ፡፡ ለምሳሌ፡- “ጨረቃም ጠለቀች” እንይ፡-

ውብ ጨረቃ የደመቀች …

ክዋክብቱን አቆራርጣ

ተሸልማ ተሸላልማ

ስትሄድ ከርማ

በደመና ተጋረደች …

ወደ መሬት አይኗን ተክላ

እየገባች አቆልቁላ

ትታ ልትሄድ … ልትገባ

ልመለስን አልመልስ … በነጋታው

ሆዷ እያባ፡፡

እንደ አንባቢ አንድ ነገር ጠረጠርኩ፡፡ እነዚህ በአፍላ ዕድሜ ፈረስ ይጋልቡ የነበሩ ወጣቶች ከከተማ ስለራቁ፤ ከቡና ቤት፣ ከካፌ ወይም ከመዝናኛ ስለተለዩ፣ ስሜታቸው ከተፈጥሮ ጋር የገጠመ፣ አድናቆታቸው ወደ ጥሬ ውበት ያፈጠጠ ይመሥላል፡፡ … የወንዙን መዝሙር፣ የተራራውን ኩራት፣ የሰማዩን ሠሌዳ ፅሁፍ የሚተርኩት ለዚያ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡

ስንኝ አደራደራቸውም ባብዛኛው ክፍት የሚባለው አይነት ነው፡፡ አውቶማቲክ፡፡ ለቅቀው ነው ቆም የሚሉት፡፡ … እንደ ክላንሽኮቭ ጠመንጃቸው ከለቀቁት በኋላ ይሆን ልጓም የሚይዙት? አላውቅም! ደግሞ እነዚህ ወጣቶች ጭቆና ጠልተው ገደብ አሥመርሮዋቸው ወደ በረሀ ስለገቡ ይሆን ብዙ ግጥሞቻቸው ሠፊ ሜዳ ተጉዘው የሚቆሙት? ልቤ እንደዚህ ይሆን ያለኝን ማለቴ ነው፡፡

የቤት አመታታቸውም ሙሉ ለሙሉ ለአይን ቤት የሚመቱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት የዘመናቸው ግጥም ስልትና መስፈርት ስለነበረ ይሆናል፡፡ አሁን አሁን ግን ከዚህ ለየት ያሉ ግጥሞችና ገጣሚዎችም አሉ፡፡ ይህንን ስል የእነሰለሞን ደሬሳን ወለሎት ማለቴ አይደለም፡፡ የእነዚህ አይነቱ ግጥሞች ለረጅም ዓመታት በአሜሪካና በእንግሊዝ ገጣሚያን “Free Verse” ተብለው ኖረዋል፡፡ ተቃዋሚ ቢኖራቸውም!

“ሶረኔ” ከሌሎቹ ግጥሞች የተለየ ዜማና ምት አለው ባልልም ስሜት አገላብጦ የሚገርፍ፣ አንዳች ትዕይንታዊ ምትሀት ያረበበት ስለሆነ መንጠቆነት ይንፀባረቅበታል፡፡ እንደገደል ማሚቶ የሚጮህ፣ ልብ ላይ የሚዘምር ከቃላት ያለፈ-መልክ /ሥዕል አለው! ምኑ ይሆን? እኔም አልገባኝም! መጽሐፉን አንብቡት እንዳልል እኔም በመከራ ነው ያገኘሁት! ዕድሜ ለመጽሐፍት ሻጭ ወዳጆቼ (ምሥጋና ይግባቸው!)

ከላይ እንደገለፅኩት “ሶረኔ” የኢሕዴን የትግል ጀማሬና ጉዞ፣ ድምፅ፣ የትግል ሥቃይና ቁንጥጫ እንጉርጉሮም ነው፡፡ ትግላቸው ከግዙፉ መንግስት ጋር ብቻ ሣይሆን ከተፈጥሮም ጋር እንደነበር መጽሐፉ በዜማ ያወራል፡፡ ለዚህም መሠለኝ ተከዜን የወቀሱት! ብቻ ወፍና አዝርዕቱን፣ አፈርና ውሃውን የሚዳስስ ስሜትና እውነት የያዙ ግጥሞች ናቸው፡፡ ተስፋ … ሀዘን… ሽንፈት፣ ድል፣ ለቅሶ … አለበት፡፡ ትውልዱ ከራሱ ሕይወት ይልቅ፣ ዓላማውን ያከበረበት ዘመን ስለነበር እጅግ የሚያስደምም ሥዕል ያሣያል! እንደ ወገንም ሆድ ያባባል … ተራራ መግፋት ይመሥላልና! መጽሐፉን ሣነብበው ኢሕዴን ዛሬ ማን ነው? እነማን ናቸው ብዬ አላሰብኩም፤ ማሰብም አልፈልግም! ግጥሞቹ ከትናንት ንፁህ የወጣትነት ልብ የፈለቁ ጣፋጭ ምንጮች ናቸውና! ምናልባት ወደ ዛሬ ብመጣ ስሜቴ ይጠወልጋል፤ ልቤም ያዝናል!

አሁን ላለው ኢሕዴን የአርሶ አደሮቹ ግጥሞች የሚያስታውሱት ነገር አለ ብዬ አምናለሁ፡፡

ለምሳሌ፡-

ለጭቁን አይራሩ ለድሆች አይረዱ

በየመስሪያ ቤቱ ሰውን ሲያዋርዱ

ብር ብር ሲሉ በጉቦ ሲፈርዱ

እዩት ምኞት አይቀር ብር ብለው ሄዱ - ይላል፡፡

እነዚህ ስንኞች ዛሬም በሙስና ተማርሮ፤ በካድሬዎች ተሠቃይቶ ሊዘምራቸው ጀምሯል፡፡ ስለዚህ የትናንት የሕዝብ ነፃነት ናፋቂዎች፣ ውድ ሕይወታቸውን አሣልፈው የሰጡ ታማኞች ዛሬ ራሳቸውንና የትግላቸውን ፍሬዎች ሊፈትሹ ይገባል! … ግጥሞቻቸው ግን ዛሬም አንጀት ይበላሉ፣ ስሜት ይኮረኩራሉ፣ የታሪክን ሥዕል በአይነ-ሕሊና ያስነብባሉ! ሶረኔ! …

ለኔ ዝብርቅርብ ስሜት የጫረች … ለነርሱ በእምባቸው ላይ የነደደች እሳት ናት… የትውልድ መዝሙር! የድል አጥቢያና የድል ማግስት ካድሬዎች የመሥዋዕትነትን ክብደት ቢያጤኑ ደስ ይለኛል! የነፃነት ትግል እንደ ቢሮ ወንበር አያነጥርም … እንደ ጋለ ምጣድ ያቃጥላል፡፡ ይህን ሶረኔ ትናገራለች፡፡

 

 

 

Read 2108 times Last modified on Saturday, 14 July 2012 07:55