Print this page
Saturday, 11 July 2020 00:00

“ከአዙሪት ለመገላገል፣ ዙሪያ ገባውን ማየት” - ሰላም ለናፈቃት አገር።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 • “ምርጫ”፣ “ዴሞክራሲ”፣… የሁሉም ችግር መፍትሄ የሚመስላቸው ፖለቲከኞች፣ ዛሬም አልባነኑም? የትኛውም ፓርቲ ቢመረጥ ችግር የለውም? በማን
     ላይ ነው የተማመኑት? ወይስ አለማሰብ ነው መተማመኛቸው?
   • በቅድሚያ፣ “ለህግና ስርአት” ክብር ካልሰጠን፣ “ምርጫና ዲሞክራሲ” ሰላምን የሚያሳጡ አደጋዎች እንደሚሆንብን እንወቅ።
   • “የሽግግር መንግስት”፤ “የስልጣን ቅርጫ”፤… በፌሽታና በእራት ድግስ የሚያልቅ፣ አዝናኝ ሽርሽር እና ጨዋታ የሚመስላቸው ፖለቲከኞችስ? የሽግግር
      መንግስት፣ የግርግር መንግስትና የአገር ትርምስ እንደሚሆን አልተገነዘቡም?
   • ስልጣን የያዙ ሁለት ፓርቲዎች፤ ባይዋደዱ እንኳን፣ ህግን አክብረው በሰላም መስራት ካልቻሉ፤ ከመቶ በላይ ፓርቲዎች እንዴት ሰላምን ይፈጥራሉ?              ወይስ፣ ይህን እውነት ላለማየት አይናችንን ብንጨፍን ያዋጣናል?
   • “የሰው ህይወት፣ የግል ህይወት” እንደሆነ፣ “ሰውን ማክበር” ማለትም፣ “የእያንዳንዱን ሰው ህልውና ማክበር” ማለት እንደሆነ እስከመቼ ይጋረድብናል?
    “የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ”፤… ከስር መሰረቱ ቀሽምም አደገኛም እንደሆነ ገና ዛሬም አልተረዳንም።
   • በዘር የመቧደን አባዜ በጊዜ ካልታረመ እንደሚባባስ፤ ዘረኝነት እና ሰላም በፍጹም አብረው እንደማሄዱ፤ አሁንም አልገባንም?
                              “በብሔረሰብ፤ በህዝብ፤ በብዙሃን፤ በምስኪኞች፤ በአገር… ስም”፣ የጋርዮሽ ሽፋን ካላለበስነው በቀር፤ “ግለሰብ” አይከበርም? ለእያንዳንዱ ሰው፤ ማለትም፣ ለህይወቱና ለንብረቱ ቀዳሚ ክብር ለመስጠት ስንለግም፤ በዚያው ልክ አመፅንና ግድያን፤ ዝርፊያንና ውድመትን እንደምንጋብዝ በቅጡ የምናውቀው መቼ ይሆን?
ግድያና ውድመትን ስናወግዝ፤ “የአገራችንን ንብረት አናቃጥል። የአገራችንን ልጅ ህይወት አናጥፋ!” የሚል ነው ትልቁ ተግሳፃችን። “የግለሰብ ህይወትንና ንብረትን ማጥፋት፤ ክፉ ወንጀል” እንደሆነ ላለመናገር ነው? ግለሰብን አለማክበራችን፣ ትልቅ የአስተሳሰብ ነቀርሳ እንደሆነ አልገባንም ማለት ነው። ዋናውን ነገር እንዴት እንስተዋለን?
“ለእያንዳንዱ ሰው ህልውና፣ ክብር መስጠት”፣ … የስነ ምግባርና የፖለቲካ መነሻ ካልሆነ፣ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የሰው ህልውናና ማንነት፣ የግል ህልውናና ማንንነት ነው። የጋራ አካል፣ የጋራ አዕምሮ የለም። ለእያንዳንዱ የግል ህልውና፣ ለኑሮውና ለንብረቱ ክብር ካልሰጠን፣… የጥሩና የመጥፎ፣ የጎጂና የጠቃሚ ልዩነት ይጠፋብናል። የቅንነትና የክፋት፣ የክብርና የውርደት ልዩነትን ማየት ይሳነናል። ይህንን አልተገነዘብነውም።
“የሰው ህልውናና ማንነት፣ የግል ህይወትና የግል ማንነት” እንደሆነ፣ እለት በእለት በገሀድ የሚታይ እውነታ ሆኖ እያለ፤ እንዴት ነው ሚስጥር የሚሆንብን? እንዴት ነው የሚጋረድብን? እንዴት ነው በየሰበቡና በየማመካኛው፣ የሰው ህይወት እየተቀጠፈ፣ የግል ንብረት የሚወድመው? ዋናዋናዎቹ ሰበቦች፣ ሦስት ናቸው - ሦስት አጥፊ የአስተሳሰብ ቅኝቶች።
ሦስቱም እጥፍ የአስተሳሰብ ቅኝቶች፤ የጋራ ስብከት አላቸው። የሰውን ዓላማዊና የግል ህልውናን የሚጨፈልቅ ነው ስብከታቸው። “በመንጋ ካልሆነ በቀር፣ የሰው የግል አእምሮና እውቀት፣ የግል ስራና ንብረት፣ የግል ህልውናና ማንነት ከንቱ ነው” የሚል ነው የጋራ ስብከታቸው። ከዚያ በኋላ በየፊናቸው በሦስት ቅኝት ያራግቡታል።
“የዚህ እና የዚያ ሃይማኖት ተከታይ” በሚል ሰበብ፣ ሰዎችን በጭፍን የሚያቧድን ሞልቷል። ይሄ አንድ ቅኝት ነው።
ድሃና ሀብታም እያለ በምቀኝነት ስሜት አቧድኖ የሚያዘምትም አለ - ሁለተኛው ቅኝት።
በዘር በብሔረሰብ አቧድኖ ለማንጋጋት የሚቀሰቅስ ደግሞ፣ 3ኛው ቅኝት ነው።
እነዚህ ሦስት የአስተሳሰብ ቅኝቶች ናቸው ዋናዎቹ የጥፋት ሰበቦች - ሰላምን አሳጥተው፣ አገርን በውድቀት አዙሪት የሚያፈርሱ ማመካኛዎች። ይህንን ካልተገነዘብን፣ ከአዙሪት መውጣት አንችልም። በማናቸውም አይነት “በጎ አላማ” ሰበብና በየትኛውም ማመካኛ፣ “የማንም ሰው ህይወትና ንብረት፣ የመስዋእት ማገዶ መሆን እንደማይገባው” እስካልተገነዘብን ድረስ፣ በየጊዜው ህይወት እየተቀጠፈ፣ ንብረት እየነደደ፣ በአዙሪት ቁልቁለት ከድጡ ወደማጡ እንወርዳለን።
ሰላም በናፈቃት አገር፣ አዲስ ታሪክ እንፍጠር - ሰላምን በማጣጣም።
ለትንሽ ጊዜ ሰክነን አገሪቱ ብትረጋጋ፣ የሰላም ጣዕም ምን-ምን እንደሚል ለቅምሻ ያህል ሞክረን ብናይስ? አዲስ ታሪክ ይሆን ነበር። በርካታ የትርምስ ምእተ ዓመታትን ትተን፤ ያለፉትን 150 ዓመታት ብቻ እንመልከት። እዚህ ውስጥ፣ የእርጋታ እና የሰላም ታሪክ ማግኘት ይከብዳል። የአገራችን ታሪክ፣ በተከታታይ ፈተናዎች የተሞላ፣ የመከራና የጦርነት ታሪክ ነው።
የእንግሊዝና የጣሊያን ተደጋጋሚ ወረራዎች፤ የቱርክና የግብጽ ዘመቻዎች፤ ከሱዳንና ከሶማሊያ በኩል ግጭቶችና ጦርነቶች፤… እነዚህ ሁሉ፤ “ዘመነ መሳፍንት” ከተሰኘው አሰቃቂ የትርምስ ወቅት በኋላ፤ እየተከታተሉና በላይ በላይ እየተደራረቡ ኢትዮጵያን አመሳቅለው ያጐሳቆሉ ጦርነቶች ናቸው። የአገር ውስጥ ጦርነቶችና ግጭቶች ሲጨመሩበት ይታያችሁ።
በሁለተኛው የአለም ጦርነት ዋዜማ፤ ለፋሽዚም ወረራ የተዳረገችና በእጅጉ የተጎዳች የመጀመሪያዋ ትልቅ አገር ናት - ኢትዮጵያ። ለአምስት አመታት በጦርነት ተተራመሰች። ጅምር የስልጣኔ ችግኞችና ውጥኖች ሁሉ ፈራረሱ። እንደገና በእግሯ መቆም፣ ብዙ ዓመታትን የሚፈጅ ፈተና እንደሚሆንባት አስቡት።
ግን የጣሊያን ወረራ ከተሰበረ በኋላ፤ አገሪቱ ሰላም አግኝታለች ማለት አይደለም። በስልጣን ሽኩቻና በመንግስት ግልበጣ ከሚፈጠሩ ሁከቶች አልራቀችም። የአመፅና የጦርነት አጥፊ ቀውሶች አልተለይዋትም።
ከጎረቤት ከሶማሊያ በኩልም፣ ኢትዮጵያ ሰላምና እርጋታ ያገኘችበት ጊዜ የለም። ሁሌም ስጋት ነው። እያሰለሰ የሚቀሰቀሰው ዓመፅና የሚሰነዘረው የታጣቂዎች ጥቃት፣ አባርቶ አያውቅም። በዚህ ላይ፣ የለየለት ወረራና ጦርነት ይታከልበታል።
ሰላምን ከሚያሳጡ ፋታ የለሽ የአገር ውስጥ ችግሮችና ቀውሶች መካከል፣ የኤርትራን ቀውስ መጥቀስ ይቻላል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ፣ ከአመጽ ወደ ጦርነት የተሸጋገረ የኤርትራ ቀውስ፣ አገርን ክፉኛ ያናጋና ሰላምን ያሳጣ ብቻ ሳይሆን አገርንም የሰነጠቀ ነው።
ምን አለፋቹ! እርጋታና ሰላም የሰፈነበት ዓመት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ማግኘት ከባድ ነው። እንዲህም ሆኖ፤ በአፄ ምንይልክ ዘመን፤ በአፄ ሀይለ ስላሴ ጊዜ፤ በከፊል ሻል ያለ እርጋታ ታይቷል።
የደርግን ዘመን ብንተወው ይሻላል። በአመጽና በሽብር የተሞላ፤ ከጅምሩ በሶማሊያ በኩል አስከፊ ጦርነት የገጠመው፤ በሰሜን በኩል የትጥቅ አመፅና ውጊያ ተደርቦበት፤ እርጋታና ሰላም እንዳጣ የተዘጋ ታሪክ ነው - የደርግ ዘመን። ከዚያ ወዲህስ? ከደርግ ጊዜ የተሻለ ቢሆንም፣ አገሪቱ ከአገር ውስጥ አመፅና ከጎረቤት ጦርነት አላመለጠችም።
በኢህአዴግ ዘመን፤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፤ የብዙ ሺዎች ህይወት ረግፏል። ብዙ ሃብት ወድሟል። ለ20ዓመታት፤ ለእንቅስቃሴ የተዘጋና በስጋት የታጠረ ሆኖ ዘልቋል። በሶማሊያ በኩልም፤ የተሟላ ሰላም አልተገኘም።
2007 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ፤ በአገር ውስጥ አመፅና ሁከት፤ ባለፈው ሳምንት ጭምር እንዳየነው፣ በየጊዜው ሰላም እየጠፋ እልፍ ህይወት ተቀጥፏል። ሀብትና ንብረት ወድሟል። ሚሊዮኖች ከኑሮ ተነቅለው ለስደት ተዳርገዋል።
በአጭሩ፣ ከሰላም ታሪክ የራቀች ሀገር ውስጥ ነው የምንኖረው ማለት ይቻላል።
ትንሽ ሰክነን፣ አገሪቱ ፋታ አግኝታ ብትረጋጋ፣ የሰላምን ቅምሻ ለማጣጣምና ምን ሊፈጠር እንደሚችል ሞክረን ለማየት ብንደፍር፤ አዲስ ታሪክ ይሆናል። አገሪቱ የሰላም ፋታ እንዳጣች፤ በርካታ ምዕት ዓመታት ተቆጥረዋልና።
የሰላም ዕጦት በጣት ከሚቆጠሩ ዋና ዋና የሕልውና ጉዳዮች አንዱ ነው። በአንድ በኩል የሰላም እጦት፣ ከህልውና አደጋዎች የሚመነጭ ውድቀት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሰላም እጦት፣ የህልውና አደጋዎችን ያባብሳል። እንዴት?
የሰላም እጦት፣ ያለ ምክንያት በአንዳች እርግማን የሚከሰት መዓት ወይም እጣ ፈንታ አይደለም። አመፅና ሁከት፤ ትርምስና ጦርነት... ተጨማሪ መዘዞችን ሳያስከትሉ፣ በራሳቸው ጊዜ መክነው የሚቀሩ ጣጣዎች አይደሉም።
ከሰላም የራቀች አገር፤ ህግና ስርዓት የሰፈነባት አገር ልትሆን ትችላለች? አትችልም። ትረበሻለች። ህግና ስርአት ሲጓደል፣ እንደገና ሰላም ይደፈርሳል። ሰላም ሲሸረሸርም፤ ስርአት አልበኝነትና ህገወጥነት ይባባሳል። አዙሪት ነው። ይህ ብቻ አይደለም።
የስራና የምርታማነት፤ የኢቨስትመንትና የቢዝነስ፤ የእድገትና የብልጽግና ደሴት አይኖረውም-ሰላም ያጣ አገር። የተረበሸ አገር፣ ምንድነው? የድህነት፤ የስራ አጥነትና የረሀብ አድራሻ ነው። በዚህ አያበቃም። ድሃ አገር፣ ተጨማሪ መከራዎችን ጎትቶ ያመጣል። ድሃ አገር፣ የአገር ውስጥ አመፅንና ትርምስን ይጋብዛል፤ አልያም የውጪ ወራሪንና ጦርነትን ይጠራል። ለጥቃት ይጋለጣል - ደካማ ድሃ አገር።
አንድ ችግር ሌሎች ችግሮችን ይፈለፍላል እንጂ፤ በራሱ ጊዜ አንዳች መፍትሄ አይወልድም። ህግና ስርአት ከመሻሻል ይልቅ ሲበላሽ፤ በየጎዳናው ቀማኛ ወሮበሎችና ነፍሰ ገዳዮች ይበራከታሉ። ለሌሎች ነውጠኞች ምቹ መንገድ ይከፍትላቸል። በየአካባቢው፣ እልፍ የመንደር “ጉልቤዎችና”፤ የሰፈር “አምባገነኖች” ይፈለፈላሉ። በስርአት አልበኝነትና በህገወጥነት ሳቢያ አገሬው ሲተራመስ?
ያኔ፣ “ሁሉንም ሰጥለጥ አደርጋለሁ” ብሎ ለሚመጣ ጨካኝ አምባገነን መንግስት፣ ምቹ አጋጣሚ ይፈጠራል። ህግና ስርአት የማይገዛው አምባገነን መንግስት፤ ለጊዜው “ሰጥለጥ” ማድረግ ይችል ይሆናል። ነገር ግን፣ ውሎ አድሮ ወደ አመፅ፤ ወደ ጦርነትና ወደ ትርምስ ማምራቱ መች ይቀራል? አዙሪት ነው።
ይሄ ሁሉ የሚሆነው፤ በድንጋይና በዱላ፤ በክላሽና በታንክ ብቻ አይደለም። እንዲህ አይነት የጥፋት አዙሪት፣ ሁሌም በጭፍን አስተሳሰቦች የሚቀሰቅስና የሚታጀብ ነው።
የግለሰብ ህልውናን፣ ኑሮንና ንብረትን በሚያናንቁ፣ ከዚያም አልፈው በሚያጥላሉ ጭፍን አስተሳሰቦች ሳይታጀብ የሚፈጠር የህልውና አደጋና የጥፋት አዙሪት የለም።
እነዚህን አስተሳሰቦች በግልጽ ለመገንዘብና ለማስተካከል እስካልጣርን ድረስ፣ አገሪቱ ከህልውና አደጋ የመራቅ፣ ከውድቀት አፋፍ የመውጣት፣ ከአሳዛኝ እልቂትና ከውድመት አዙሪት የመገላገል ዕድልና የሰላም ፋታ አታገኝም።

Read 525 times