Print this page
Saturday, 11 July 2020 00:00

ያዘኑትን ለማጽናናት፤ አጥፊዎችን ለማውገዝ አዲስ አበባ የመጣው የሱማሌ ክልል የልዑካን ቡድን

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 • *የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በመቆም የጠላቶቻችንን ህልም ቅዠት ማድረግ ይጠበቅበታል
  • *የአሁኑ ወጣት ከስሜታዊነት ወጥቶ ለምን ብሎ መጠየቅና እውነታውን መረዳት አለበት
  • *ክብሩ የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ መጥፋቱና ንብረት መውደሙ መወገዝ ይኖርበታል
  • *በአጥፊዎች የተፈጸመው አገር የማውደም ሥራ ሀጫሉን ዳግም የሚገድል ነው


            ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት 3፡30 ገደማ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች በተተኮሰበት ጥይት ሕይወቱ ባለፈው እውቁ የኦሮምኛ ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ምክንያት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ድንጋጤና ሀዘን ላይ መውደቁ ይታወቃል። ይህንን ተከትሎም በርካታ የመንግሥት ተቋማትና የክልል መንግሥታት የሐዘን መግለጫ ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። የሀዘን መግለጫ ከላኩት የክልል መንግሥታት መካከልም የሶማሌ ክልል ይገኝበታል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ በተለይም በሶማሌ ሕዝብ ባህል ሀዘንን በርቀት ከመግለፅ ይልቅ በቅርብ ሆኖ ማስተዛዘንና አጋርነትን መግለጽ በእጅጉ ቅቡልነት ያለው ነው በሚል በክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የተመራና 21 አባላትን ያካተተ የልዑካን ቡድን ባለፈው እሁድ ሰኔ 28 አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ጋር በመገናኘት በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ አሰቃቂ ግድያና ያንን ተከትሎም በደረሰው የንጹሃን ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የገለጹ ሲሆን በዚህም ለኦሮሞ ሕዝብ ያላቸውን ወገንተኝነት አሳይተዋል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ሀዘናቸውን ለመግለጽ ከመጡት የሶማሌ ክልል የአገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ ኡጋዞችና ወጣቶች መካከል አራቱን አነጋግራ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አስፍራለች፡፡

                          “ሀጫሉን ማንም ይግደለው ማን እናወግዘዋለን”
                                 (ገራድ ኩልሚዬ ገራድ መሃመድ ገራድ ዶል፤ የጎሳ መሪና የእርቅ ኮሚሽን አባል)


                እኔ የኩመዴ ጎሳ መሪና የጅግጅጋ ነዋሪ ስሆን የእርቅ ኮሚሽን አባልም ነኝ፡፡ እዚህ አዲስ አበባ የመጣሁት የኢትዮጵያን በተለይም የኦሮሞን ሕዝብ ለማፅናናት ነው። ሀጫሉ ሁንዴሳን እንደማውቀው ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ መብት እንዲከበር፣ ፍትህ እንዲያገኝና ከጭቆና እንዲወጣ በጽኑ የታገለ ልጅ ነው። የነፃነት ታጋይ ነው ማለት ይቻላል። እንግዲህ የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ፣ ጎረቤት የሆኑና ብዙ የሚጋሯቸው ጉዳዮች  ያሏቸው ናቸው።
በዚህ የተነሳ ሩቅ ሆነን የሀዘን መግለጫ ከመላክ ይልቅ በዚህ ፈታኝና አጣብቂኝ ወቅት ከጎናቸው ሆነን የደረሰባቸውን መሪር ሀዘን ለመካፈልና ለማፅናናት ነው የመጣነው። እዚህ ከመጣን በኋላ ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒና አዲሱ አረጋን ጨምሮ ከሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተገናኝተን፣ ሀዘናችንንና ወገንተኝነታችንን ከመግለጽ ባለፈም ውይይቶችን አድርገናል።
የሀጫሉን መገደል በተመለከተ የሚሰማኝ ከፍተኛ ሀዘን ነው። ግድያው ዘፋኙን ብቻ ሳይሆን ተከባብረውና ተባብረው የሚኖሩ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ለማባላት ያለመ ነው። ሀዘኑን ይበልጥ መራር የሚያደርገው አርቲስቱ ከተገደለ በኋላ በአስክሬኑ ላይ የተደረገው እንግልት ነው፡፡ ግድያው  አገር ለመበታተን ነውጥ ለማስነሳት፣ በተለይ በተለይ ደግሞ ትልቁን የአማራንና የኦሮሞን ሕዝብ እርስ በእርሱ ለማበጣበጥና ለማጫረስ ሆን ተብሎ ታስቦበት በጭካኔ የተደረገ ነው። ስለዚህ ሀጫሉን ማንም ይግደለው ማንም እንደ አገር ሽማግሌነቴ ድርጊቱን አወግዘዋለሁ። ዓለምም ኢትዮጵያም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አጣብቂኝ ውስጥ በገቡበት፣ ኢትዮጵያ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ለመጀመር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት በቀሩበትና ከግብፅ ጋር በፍጥጫ ላይ ባለንበት ወቅት ይህን መሰል አስነዋሪ ተግባር መፈፀሙ አሳፋሪ ነው፡፡ ስለዚህ በውስጥም በውጭም ጠላቶቻችን በጋራ የተቃጣብን ጥቃት መሆኑን በመገንዘብ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንጊዜውም በላይ ልዩነቱን አጥብቦ በፍቅርና በአንድነት በመቆም፣ የጠላቶቻችንን ህልም ቅዠት ማድረግ ይጠበቅበታል።
ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም በሀጫሉ ግድያ ቁጣውን በሚገልጽበት ወቅት  ነገ የሚረከበውን ሀገር ያለ ጥሪት ማስቀረትና ማወደም ተገቢ ስላልሆነ በረጋና በሰከነ ንፁሀንን ባልጎዳ መልኩ ተቃውሞ ማሰማት ይኖርባቸዋል እንጂ ነገ የሚረከቡትን አገር በማውደም ታሪካዊ ስህተት መፈጸም የለባቸውም፡፡
አያት አባቶቻችን አገርን ከጠላት ወረራ ጠብቀው ነው ያስረከቡን፡፡ የአሁኑ ወጣት ከስሜታዊነት ወጥቶ ለምን ብሎ መጠየቅና እውነታውን መረዳት አለበት እላለሁ። የእኛ ክልል ሕዝብ የመለያየትንና የጦርነትን ዋጋ ቢስነት በእጅጉ የሚረዳ፣ በብዙ ችግር ውስጥ ያለፈ ነው። የሰላምን የአንድነትንና የመተባበርን ዋጋ በእጅጉ ስለሚረዳም ሰላሙን አበክሮ ይጠብቃል፤ ሌላውም ሰላሙንና አገሩን መጠበቅ አለበት። በተለይ ወጣቱ አገሩን የመጠበቅ ግዴታ አለበትና እንደ አገር ሽማግሌነቴ እንደ ጎሳ መሪነቴ አደራ እላለሁ።
ለሀጫሉ ሁንዴሳ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አድናቂዎች እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ለኦሮሞ ሕዝብ መጽናናትን እመኛለሁ። በመጨረሻም መንግሥት የሀጫሉን ገዳዮች አድኖ ለፍርድ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን።

_______________________


                       “የኛ ፍላጎት አምቦ ድረስ ሄደን ቤተሰቡን ማፅናናት ነበር”
                                   (ወጣት አህመድ አብዲ ሳብር፤ የጅግጅጋ ነዋሪ)


               በሀጫሉ ሁንዴሳ አሳዛኝ ህልፈት ከልብ አዝኛለሁ። እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት እንዲህ አይነት አሳዛኝና ዘግናኝ ድርጊቶችን እቃወማለሁ። ሀጫሉ ትልቅ አርቲስት ነው። በተወሰነ መጠን ኦሮምኛ ስለምችል ዘፈኖቹን በደንብ አደምጥ ነበር። አብዛኛው ዘፈኑ ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነት የተቀነቀኑ ናቸው። ሀጫሉ ለነፃነት ለእኩልነት የታገለ፣ ለዚህም የተፈጠረ ነበር።
የአሟሟቱ ሁኔታ ግፍ የተሞላበት ሆን ተብሎ ታቅዶና ተቀነባብሮ የተፈፀመ፣ የአገርም ውስጥ የውጭም ጠላቶቻችን እጅ እንዳለበት ያስታውቃል። አገር ለመረበሽና ለመበጥበጥ፣ አንዱን ብሔር ከሌላው ለማጋጨትና የአገር ሰላምና አንድነትን ለማፈራረስ የታቀደ ነው። ስለዚህ አወግዘዋለሁ።  ከሞተ በኋላም  በአስክሬኑ ላይ የተፈፀመው እንግልት በዕድሜዬ ሰምቼው የማላውቅ በመሆኑ በእጅጉ አዝኛለሁ። እኔ ይህንን ድርጊት ለማውገዝ እንዲሁም የኢትዮጵያንና የኦሮሞን ሕዝብ ሀዘን ለመካፈልና ለማጽናናት ነው ከታላላቆቼ ጋር እዚህ አዲስ አበባ የተገኘሁት። የወቅቱ ሁኔታ አልፈቅድ ብሎ እንጂ አምቦ ድረስ ሄደን ብናጽናናቸውና ሀዘናቸውን ብንጋራቸው ደስ ይለን ነበር።
የሀጫሉን ሞት ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ በርካታ ንጹሀን ሕይወታቸውን አጥተዋል። በርካታ ንብረት ወድሟል። ይሄ በአጥፊዎች የተደረገው አገር የማውደም ሥራ ሀጫሉን ዳግም የሚገድል ነው። መንግሥትም ቢሆን የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር አለበት። እርግጥ ነው የሀጫሉ በሴራ መገደል ያስቆጣል፤ ያበሳጫል። ነገር ግን ቁጣን በሰላማዊ ሰልፍ መግለጽ ይቻላል። “ሰላማዊ” የሚለው ቃል የሚገልጸው ምንድን ነው? በሰላም ሀዘንን ቁጣን፣ ተቃውሞን መግለጽ እንደሚቻል ነው። የተደረገው ግን ሰላማዊ ሰልፍ ሳይሆን አውዳሚ ሰልፍ ነው። ይህ ተቀባይነት የለውም። የዕድሜ አቻዎቼ ነገ በሚረከቡት አገርና ሕዝብ ላይ ያደረሱት ጥፋት ተቀባይነት የለውም። በበኩሌ አልቀበለውም። ነገ ውለው አድረው የሚፀፀቱበትን እኩይ ተግባር መፈፀም ከምንም በላይ የሚጎዳው ራስን ነው። በሌላ በኩል፤የወጣቱ ነፍስ ማጥፋትና ንብረት ማውደም የሴረኞችን ዓላማ ማሳካት ነው። እነሱም ሀጫሉን መርጠው ሲያስገድሉ ዓላማቸው አገርን ማውደም፣ ብሔርን ከብሔር ማባላት፣ አገር የምታደርገውን የእድገት ጉዞ ማደናቀፍ ነው። የህዳሴው ግድብ ውሃ መሙላት ሊጀምር ቀናት ሲቀሩት ይህንን ዘግናኝ ድርጊት መፈፀማቸው የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ስለዚህ ወጣቱ መንቃት አለበት። ለምን ይህን አደርጋለሁ? ምን ለማግኘት? የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ይገባቸዋል:: ይህ ካልሆነ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም።
የሶማሌ ክልል የአገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዞች፣ የጎሳ መሪዎችና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እዚህ አዲስ አበባ መጥተው መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ሀጫሉን ያፈራውን የኦሮሞን ሕዝብ ሀዘን ለመካፈልና ለማጽናናት መገኘታቸው፣ ኢትዮጵያዊነትን አንድነትንና በጋራ መቆምን ከማሳየቱም በላይ ባህላችን ምን ያህል ጥብቅና ተቀባይነት ያለው እንደሆነ ገላጭ ነው።  ከሶማሌ ልዑካን ቡድን ሌላው መማር ያለበትም ይህንኑ ነው፤ የጋምቤላውም፣ የቤኒሻንጉሉም፣ የአማራውም፣ አመራሮች ሌላው ቀርቶ የትግራይ ሕዝብ (ወያኔዎቹን ማለቴ አይደለም) በቅርበት ወንድሙን የኦሮሞን ሕዝብ ማፅናናት ወገንተኝነቱን መግለጽና ሀዘኑን መካፈል አለበት። ከመቼውም በላይ በአንድነታችንና ኢትዮጵያዊነታችን ላይ የተቃጣብንን ሴራና ተንኮል በአንድነት ቆመን መመከት ያለብን ጊዜ ላይ ነን፡፡ በተረፈ ለሀጫሉ ሁንዴሳ ሰላማዊ ዕረፍትን ለቤተሰቡ፣ ለዘመድ ወዳጆቹና ለአድናቂዎቹ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እመኛለሁ። ከዚህ ውጭ መንግሥት ገዳዮቹንና አጥፊዎቹን ለፍርድ እስኪያቀርብ ድረስ በትዕግስት መጠበቅ አለብን  እላለሁ።
___________________

                      “አርቲስቱ ብዙ ሊሰራ በሚችልበት ዕድሜ ላይ መገደሉ ያስቆጫል”
                                 (ገራድ አብዱልማሊክ ገራድ ኡስማን፤ የአገር ሽማግሌ)


             ከሶማሌ ክልል የአገር ሽማግሌዎች ውስጥ አንዱ ነኝ። ዛሬ አዲስ አበባ የተገኘሁት በዝነኛው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ አስደንጋጭና አሳዛኝ ሞት ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኦሮሞ ሕዝብ ሀዘናችንን ለመግለጽና ለማጽናናት ነው። ልዑካን ቡድኑ በክልሉ ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተመራ ነው። እንግዲህ በልጁ ሞት የሶማሌ ሕዝብ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንና ድንጋጤ የክልላችን መንግሥት በላከው መልዕክት ገልጿል። ግን በቂ ስላልመሰለን በሶማሌ ባህልም ሀዘንና ብሶት የደረሰበትን ሕዝብ ቀርቦ ማፅናናትና ሀዘኑን መጋራት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ለኦሮሞ ሕዝብ ያለንን ክብርም ለመግለጽ መጥተን ሀዘኑን ተካፍለናል፤ አጽናንተናልም።
የሀጫሉ ግድያ በጣም አሳዛኝና ያልተገባ ነው። ይህ ዝነኛና ወጣት አርቲስት ለነፃነት ሲታገል የነበረ ሲሆን ተፅዕኖም ፈጣሪ ነበር:: ገና በወጣትነቱ ከዚህ በላይ መስራት በሚችልበት ዕድሜው ላይ በአስደንጋጭና በዘግናኝ ሁኔታ መገደሉ በእጅጉ  የሚያስቆጭ ነው።
ግድያው የሚያመላክተው የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም የማይፈልጉ ፀረ-አንድነትና ፀረ-ሰላም ሀይሎች አገርን ለማሸበር የሸረቡት ሴራ መሆኑን  ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የፀረ-አንድነትና ፀረ-ሰላም ሀይል የሴራ ድርጊት በጽኑ እናወግዛለን እንቃወማለን። እንደሚታወቀው የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝብ በጉርብትና የኖረ፣ የተዋለደ ሕዝብ ሲሆን ባለፈው ሥርዓት በመሪዎች ሴራ እንዲጋጭና እንዲጠላላ ሲደረግ የነበረ ነው:: ነገር ግን ሕዝቡ የሥርዓቱ መሪዎች ሴራ ሰለባ እንደሆነ በመገንዘብ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ጉርብትናውንና ወንድማማችነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ይህ የሁለቱ ህዝቦች ትስስርና ሰላም ነው ሀዘናችንን በቅርበት ለመግለጽ እዚህ ድረስ ያመጣን። የኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ ሕዝብ ነው። ከሌላው ብሔር ብሔረሰብ ጋር ተዋድዶና ተከባብሮ ብሎም ተዋልዶ የኖረ ሕዝብ ነው። ሴረኞችና ፀረ አንድነት ሀይሎች የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ ጋር ለማባላት እያደረጉ ያሉትን ጥረት በመረዳትና ድርጊታቸውን በማውገዝ፣ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በጋራ የሚቆምበት ወቅት ላይ ነው እላለሁ።
የኦሮሞ ወጣቶች ማንኛውንም ችግር በሰከነ መንፈስ በመረዳት የመፍትሄ አካል መሆን እንጂ የንፁሀንን ደም ማፍሰስ፣ ሰው ጥሮ ግሮ ያፈራውን ሀብት ማቃጠልና ማውደም በፈጣሪም በሕግም ፊት ያስጠይቃልና ከዚህ እኩይ ድርጊት መታቀብ አለባቸው እላለሁ። የኦሮሞ አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የገዳ ሥርዓት መሪዎች ወጣቱን በማረጋጋት እንዲሁም የሟች ቤተሰብን በማጽናናት በኩል ከፍተኛ ሥራ መስራት ያለባቸው  ይመስለኛል። መንግሥትም የልጁን ገዳዮችም ሆነ በዚህ አስነዋሪ ድርጊት የተሳተፉትን ሁሉ ለፍርድ በማቅረብ የሀጫሉን ቤተሰብም የኦሮሞን ሕዝብንም ሆነ ኢትዮጵያውያንን መካስ ይገባዋል፡፡ በተረፈ ለሀጫሉ ቤተሰቦች አድናቂዎችና ለመላው የኢትዮጵያና የኦሮሞ ሕዝብ መጽናናትን እየተመኘሁ፣ በዚህ ግርግር ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ቤተሰብም ፈጣሪ ጽናቱን ይስጣቸው እላለሁ፡፡ ሀብት ንብረት ለወደመባቸውም የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ።


__________________

                    “ከሰላምና አንድነት ውጪ ሌላ ምርጫ የለንም”
                               (ኡጋሳ አብዲረሺድ ኡጋስ ሮብሌ ኡጋስዶዲ፤ የክልሉ ባህላዊ ንጉስ)


            ከሱማሌ የመጣን ኡጋሶች የክልሉ ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች እንገኝበታለን፡፡ የመጣነው ለኦሮሞ ሕዝብ ያለንን አጋርነትና ወገንተኝነት ለማሳየት ብሎም ሀዘናችንን ለመግለጽና ለማፅናናት ነው። በአርቲስት ሀጫሉ ግድያ አዝነናል፤ ደንግጠናል፤ ተረብሸናል። ሁላችንም የፈጣሪ ልጆች ነን። በፈጣሪ አምሳያ የተፈጠርን ነን። ነገር ግን የሀሳብ ልዩነቶች ሊኖሩን ይችላሉ። የሀሳብ ልዩነቶቻችንን በውይይትና በንግግር መፍታት አቅቶን ወደ ጉልበትና ወደ ግድያ መሄዳችን በጣም ያሳዝናል፡፡ የሰለጠነው ዓለም ልዩነትን በውይይት እየፈታ ነው፤ እኛ ግን ዛሬም በተተኮሰብን ጥይት እንደወጣን እንቀራለን፤ ይሄ ተገቢ አይደለም። አሁንም እዚህ ስንመጣ ግድያውን ለማውገዝና ወንድም ሕዝባችንን የኦሮሞን ሕዝብ ለማጽናናት ነው። ባህላችንም፣ ሀይማኖታችንም የሰውን ችግር፣ ሀዘን እንድንካፈል እንድንረዳዳ እንድንተጋገዝ ያዝዘናል። ሀዘንን ደግሞ ከርቀት ይልቅ ያዘነውን ሰው ከጎኑ ቁጭ ብሎ ማጽናናት የተለየ ስሜት ይሰጠዋል። በደንብ ይጽናናል፤ ወገን እንዳለው ይሰማዋል። ስለዚህ እዚህ መምጣትን መርጠናል። በአሁኑ ወቅት ከሰላም ውጭ አማራጭ የለንም። የሕዝቡን ሰላም ለመጠበቅና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መወያየት ከጠላት በተቃራኒ በአንድነት መቆም ያስፈልጋል። ሰላም ውድ ነገር ነው። ያለንም አንድ አገር ነው፤ ባንዲራችንም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የአንድነታችን ፊርማ ነው።
እንዲህ እየተገዳደልን እየተበጣበጥን መቀጠል አንችልም፤ አንለማም፤ አገርም ህዝብም በብጥብጥ የሚያተርፈው የለም። ስለዚህ ከምንጊዜውም በላይ ሰላምና አንድነታችንን ማጠንከር አለብን። የሕግ የበላይነት መከበር አለበት፤ ክብሩ የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ መጥፋቱም መወገዝ አለበት። የአገርን ሰላም የሕዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ከመንግሥት በተጨማሪ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎችና ተቀባይነት ያላቸው ታዋቂ ግለሰቦች ሚና ከፍተኛ ነውና በዚህ ላይ መስራት አለባቸው፡፤
ወጣቶችም መረጋጋትና ረጅም ሀሳብ ማሰብና ማለም እንጂ በስሜት እየተነዱ አገር ማጥፋትና ማውደም ስለማይገባቸው  በተረጋጋ መንፈስ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ።
የደረሰው ጥፋት ቀላል አይደለም፤ ከልብ የሚጠፋም አይደለም፤ ነገር ግን ከተጨማሪ ጥፋት ራሳችሁን አቅቡ ብዬ እንደ አባትነቴ መምከር እፈልጋለሁ። በተረፈ ለአርቲስት ሀጫሉ ቤተሰቦች ወዳጅ ዘመዶች፣ አድናቂዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እመኛለሁ። የአርቲስቱን ህልፈት ተከትሎ በተከሰተ ሁከትና ብጥብጥ ሕይወታቸውን ላጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሀዘኔን እገልጻለሁ፤ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እመኛለሁ።      


Read 596 times