Saturday, 11 July 2020 00:00

“በራሱ ጠብ ገላጋይ"

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ማይኬን ይዤ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለማናገር ብቅ ማለቴን ለማሳወቅ ያህል ነው፡፡ የመጀመሪያው እንግዳዬ በእድሜ ጠና ያሉ ናቸው፡፡
ጋዜጠኛው፡— እንግዳዬ ስምዎን ቢነግሩኝ?
እንግዳ አንድ፡— ቢገርመው ታዘበ፡፡
በለው! በቃ፣  ሲገርማቸው ጊዜ፣ የሚያደናግሩ ነገሮች ቢበዙባቸው ጊዜ ሊያደርጉ የሚችሉት ትልቁ ጉልበታቸው መታዘብ ነው፡፡ አሁን ብዙ ሰው ብዙ ነገሮችን እየታዘበ እንዳለው ማለት ነው፡፡ እናማ…ምን መሰላችሁ… ‘ቢገርመው ታዘበ’ የእንግዳዬ ስም ቢሆንም፣ የብዙዎቻችን ቅጽል ስምም እንደሆነ ይታወቅልንማ!
ጋዜጠኛው፡— አቶ ቢገርመው መቼም ሰሞኑን ሚዲያ ላይ ሳይሰሙ አልቀሩም፡፡ ግብጽ የዓባይን ውሀ በሙሉ ካልወሰድኩ እያለች ነው፡፡
እንግዳ አንድ፡— ምን ይገርማል!  ድሮ ጀምሮ ስትል የኖረችው ነው፡፡ እኔ የሚገረምኝ ይሄ ለቀባሪው የምታረዱት ነገር ነው፡፡
ጋዜጠኛው፡— ቢያስረዱኝ…
እንግዳ አንድ፡— እምቢተኝነቱ አዲስ አይደለማ!
ጋዜጠኛው፡— ቢሆንም አሁን ነገሮች ጠንከር እያሉ ነው፡፡ ካልሆነ ጦርነት እከፍታለሁ ብላ ካገኘችው ቦታ ሁሉ መሳሪያ እየሸመተች ነው፡፡
እንግዳ አንድ፡— (ከት ብለው ይስቃሉ::)  ስማኝ፣ እንደ አፏ ቢሆን ኖሮማ፣ ድሮውኑ መሀል አራዳ ላይ ፒራሚዴን ካልተከልኩ ትል ነበር፡፡ ብቻ ሰዉ ፈራ እንዳትለኝ…
ጋዜጠኛው፡— መፍራት እንኳን ሳይሆን፣ በዚህ ዘመን ጦርነት ለማንም አይጠቅምም ለማለት ነው፡፡
እንግዳ አንድ፡— ጦርነት ለማንም እንደማይጠቅምማ እነሱ ናቸው ቀድመው ማወቅ ያለባቸው፡፡ አንዴ በዚህ በኩል፣ አንዴ በዚያ በኩል ሲመላለሱ በረሀ ለበረሀ እያሯሯጥን ነው የመለስናቸው፡፡ ስማ ታሪክ በዚህ ዘመን መጫወቻ ሆነና ነው እንጂ፣ የጥላቻ አረቄ አናቱ ላይ የወጣውም፣ የስልጣን ጥማት ማሰቢያውን የነጠቀውም ምኑም፣ ምናምኑም አበላሸው አንጂ… ብቻ… ብቻ…ተወው፡፡
ጋዜጠኛው፡— እንደው አይበለውና ድንገት ጦርነት የሚነሳ ከሆነ፣ ህዝቡ ምንም ማድረግ አለበት ይላሉ?
እንግዳ አንድ፡— (እንዴት እንደገላመጡኝ እኔ፣ ማይኬና ካሜራማኑ ብቻ ነን የምናውቀው፡፡ ዘመናዊ ‘እንቁላል ሻጭ’ ሆንኩባቸው መሰለኝ፡፡) ህዝቡ ምን ማደረግ አለበት መሰለህ… “ጠላት መጥቶብሀልና ያለህን ብረት እየወለወልክ ውጣ፣” ሲባል ምን ማለት እንዳለበት ልንገርህ…
ጋዜጠኛው፡— ቢነግሩኛ ደስ ይለኛል፡፡
እንግዳ አንድ፡— ብቅል እየፈጨሁ ነው፣ ብሎ ይጩህ፡፡ (በጉደኛ ግልምጫ ሰማይ አድርሰው አፈረጡኝና ሊሄዱ መንገድ ጀምረው ዘወር አሉና ዋጋዬን ሰጡኝ፡፡) ምን ይላል ይሄ! በራሱ ጠብ ገላጋይ የሆነ ጉድ ይግጠመኝ!
ለምን ይዋሻል፣ በወይራ ሽመል ቢያንቆራጥጡኝም የዛን ያህል አይሰማኝም ነበር፡፡ ምን እንዲሉኝ ነበር የፈለግሁት!  አሀ…እኔስ ምን ላድርግ…“ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?” ጥያቄ  በቃ ፋሺን ነዋ!   
ለነገሩ ለዚህ ጥያቄዬ አለቃዬ ማይኬን እንደማይነጥቀኝ እርግጠኛ ሆኜ ነው የጠየቅሁት፡፡  አሀ እሱ ራሱ ጠምዶ ያርስ ይመሰል በቀደም እለት ካሜራ ፊት…“የዝናቡ ወቅት እየገባ ስለሆነ አርሶ አደሩ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?” ተብሎ ሲጠየቅ አመላላሱ የአይንስታይንን ንድፈ ሀሳብ አፈር ድሜ የሚያስገባ አዲስ ግኝት ባለቤት ይመስል ነበራ!
ወደ ሌላ እንግዳዬ ልግባ መሰለኝ…
ጋዜጠኛው፡— እመቤቴ…ስምዎን ቢነግሩኝ…
እንግዳ ሁለት፡— ብርቱካን ደረሰ፡፡
ጋዜጠኛው፡— የእኔ እናት፣ በምን ሙያ ነው የሚተዳደሩት?
(ቴሌቪዥኑ እኮ የጉልት መደባቸውን መልሶ መላልሶ እያሳየ ነው፡፡)
እንግዳ ሁለት፡— እንደምታየው ጎመኑንም፣ ድንቹንም፣ ሽንኩርቱንም እየሸጥኩ ነዋ፡፡ በዚሁ ነው ልጆቼን የማሳድገው፡፡
ጋዜጠኛው፡— ሰሞኑን ሰምተው እንደሆነ ግብጾቹ የዓባይን ውሀ ሙሉ ለሙሉ ካልወሰድን ብለው ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡
እንግዳ ሁለት፡— አፈር በበላሁ  ግብጥ ነው ያልከኝ?
ጋዜጠኛው፡— አዎ እማማ፡፡
እንግዳ ሁለት፡— እኮ ይቺ ግብጥ እዛ ላይ ማዶ ያለችው?
ጋዜጠኛው፡— አዎ እማማ፡፡
እንግዳ ሁለት፡— ምን እንሁን አሉ ነው የምትለኝ?
ጋዜጠኛው፡— የዓባይን ውሀ በስምምነት ተካፍለን እንጠቀምበት ስንል አይ ለብቻችን ነው አንጂ እናንተ ጠብታም አትወስዱም እያሉን ነው፡፡ (ነገር ማሳመር የሚባለውን ዘዴ ለማወቅ ሙከራ ላይ እንደሆንኩ ልብ ይባልማ!)
እንግዳ ሁለት፡— ታዲያ የምን ማባባል ነው! ከዚሁ ቁልፍ ማድረግ ነዋ!
ጋዜጠኛው፡— እማማ እንደሱ ከሆነ ደግሞ ጦርነት ነው የምንከፍተው እያሉ ነው፡፡
እንግዳ ሁለት፡— (በአንድ ጊዜ ሁለመናቸው ተለዋወጠ፡፡) ታዲያ ይክፈቱዋ! ደግሞ ለግብጥ የምን ፊት ማሳየት ነው! እነሱ ይለፍልፉ እንጂ ሙያው ላይ የታሉበትና ነው!
ጋዜጠኛው፡— እማማ ግን እኮ ጦርነት ብዙ ውድመት ያስከትላል፡፡ እኛም እንጎዳለን፡፡
እንግዳ ሁለት፡— ታዲያ ጦርነት ምን ሊሆንልህ ነበር! (የበፊተኛው ሰውዬ ‘የግልምጫ ሁሉ እናት’ አይነት አጠጡኝ ስል፣ የእኝህኛዋ ይባስ!) ይልቅ ነቅታችሁ ጠብቁ፡፡ (ፊታቸውን ወደ ገበያተኛ አዞሩ::) የእኔ እመቤት ምን ልስጥሽ? ያው እንግዲህ “አትጨቅጭቀኝ፣ ከፊቴ ጥፋልኝ” ማለታቸው መሆኑ ነው፡፡ ከፊታቸው ጠፋሁላቸው፡፡
ሦስተኛው እንግዳዬ ፖለቲከኛ ይሁን አይሁን እንጃ እንጂ እንደ ፖለቲከኛ የሚያደርገው ነው፡፡ ግን ሁሉም ቦታ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያለው ከፍተኛ ባለ አክስዮን ይመስል የማይቀርብበት የቴሌቪዥን ጣቢያ የለም፡፡
ጋዜጠኛው፡— እንግዳዬ ስምዎን ቢነግሩን፡፡
አቤት መኮሳተር! ግንባር ላይ አስር እጥፋት እሺ ይሁን፣ አስራ አምስት እጥፋት እሺ ይሁን…ሰውየው እኮ መቶ ሀምሳ እጥፋት ነው ያለው!
እንግዳ ሦስት፡— ስም ማለት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ስም እኮ ተግባርን አይገልጽም፡፡
ይቺ ናት ጨዋታ! ገና ሳልጀምር ፕሌቶ፣ ምናምንቶ ሊሆንብኝ ነው እንዴ! ድሮም ስሙ ሰልችቶኛል፣ የራሱ ጉዳይ፡፡
ጋዜጠኛው፡— ስለ ሰሞኑ ሁኔታ አንዳንድ ነገር ልጠይቅዎት ብዬ ነው፡፡
እንግዳ ሦስት፡— ስሜ ኮራበል በጊዜው ነው፡፡ (አይ ምነው! እሱን እኮ ጨርሼ  ወደ ሌላ ጥያቄ ሄድኩ!)
ጋዜጠኛው፡— ሰሞኑን በዚህ በናይል ውሀ አጠቃቀም ጉዳይ የግብጾቹን አቋም እንዴት ነው የሚያዩት?
እንግዳ ሦስት፡— መጀመሪያ ይህ ችግር እንዴት ጀመረ ብለን መርመር አለብን… (ይሄን ደግሞ እነ ማን ላይ ሊያላክክ ነው!)
ጋዜጠኛው፡— ግዴለም እሱን በሌላ ፕሮግራም በሰፊው እንነጋገራለን፡፡ አሁን ግብጾቹ የያዙትን "ሁሉም ነገር ለእኛ" ለሚል አቋም፣ የእኛ ምላሽ ምን መሆን አለበት ብለው እንደሚያምኑ ቢነግሩኝ?
እንግዳ ሦስት፡— በዚህ ጉዳይ መጀመሪያ እኛ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን መነጋገር አለብን፡፡ (እንዴት ነው ነገሩ!)
ጋዜጠኛው፡— መነጋገር ሲሉ ስለ ማን ነው እየጠቀሱልኝ ያሉት?
እንግዳ ሦስት፡— እዚህ ያለነው ፖለቲከኞች ተደራድረን… (ለካሜራማኑ መልእክት ሰጠሁትና ካሜራውን አጠፋው:: ‘ቦተሊከኛው’ ግን ሀገር እየሰማኝ ነው ብሎ ዲስኩሩን ቀጥሏል፡፡ ከስህተት ሁሉ ስህተት እየሰሙኝ ነው ብሎ ሰሚ በሌለበት መደስኮር ነው፡፡
የመጀመሪያው እንግዳዬ ግን “በራሱ ጠብ ገላጋይ የሆነ ጉድ፣” ብለው የተረቱብኝ ነገር ከእኔ ጋር መክረሟ አይቀርም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1499 times