Print this page
Saturday, 11 July 2020 00:00

ሁከትና ግርግር፤ ጥፋትና ውድመት - እስከ መቼ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  • ዳር ቆሞ መመልከትም ሆነ እኔ የለሁበትም ማለት ከተጠያቂነት አያድንም
     • በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የነፃነት ትግል ያስፈልጋል ብዬ አላምንም
    • እያንዳንዳችን ለንጋት ተግተን ካልሰራን የምንፈልገውን ውጤት አንቀዳጅም

             ከሰሞኑ በኦሮሚያ የተፈጠረው ግርግርና ሁከት ባስከተለው የከፋ የህይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ዙሪያ ከቀድሞው የፓርላማ አባልና ፖለቲከኛ አቶ ግርማ ሰይፉ ጋር የአዲስ አድማሱ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡

             የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሣን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት የሰው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ምን ስሜት ፈጠረብዎ?
ስሜታቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ልጆችን አነሳስቶ እንዲህ ያለው ድርጊት እንዲፈፀም ማድረግ ለሰው ልጆች ሕይወት ምን ያህል ግድ የሌለን መሆኑን ያመላክታል። በሌላ በኩል፤እኛ ለምንፈልገው ትንሽ ጉዳይ ሌሎች ውድ ዋጋ ቢከፍሉ ደንታ የሌለንና ማመዛዘን የማንችል እንደሆነ ነው ያሳየኝ፡፡  
በየጊዜው በሚፈጠሩ ሁከትና ግርግሮች ከፍተኛ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመቶች የሚከሰቱት በምን ምክንያት ይመስልዎታል?
መነሻው ፖለቲካ ቢሆንም መጨረሻ ላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ድቀት ነው የሚያመጣው። ነገር ግን ይሄን ለማገናዘብ አለመቻል ነው ብዙ ችግር እየፈጠረ ያለው። ለምሳሌ አንዳንድ ቦታዎች ላይ እዚያው ቤት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች፣ ደሞዝ የሚያገኙበትን፣ የገቢ ምንጫቸውን ከሌሎች ጋር አብረው አውድመዋል። ይሄ አርቆ አለማሰብ ነው። የውስጣዊ ጥላቻና ምቀኝነት ውጤት ነው። ሰው የሚባላበትን ሳህን አንስቶ ከሰበረ ነገ በምን እንደሚበላ ማገናዘብ አቅቶታል ማለት ነው፡፡ ይህን በምንም አይነት አመክንዮ ማስረዳት አይቻልም፤ ያው የግንዛቤና የአርቆ አስተዋይነት ችግር ነው። ለጥፋትና ውድመት ከወጡት ወጣቶች ውስጥ ብዙዎቹ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጥቂት የማይባሉት ወደ ቤታቸው አልተመለሱም። ስለዚህ ወጣቶች ከእነዚያ ከማይመለሱት አንዱ ልንሆን እንችላለን ብለው ቢያስቡ መልካም ነው። ወጥቶ አለመመለስ የሚፈጥረውን ስሜት ወልዶ መከራውን አይቶ ባሳደገ ወላጅ ጫማ ውስጥ ሆኖ ማየትን ይጠይቃል:: ንብረት ከማውደም ምንም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አይገኝም፤ ከዚያ ይልቅ ለልጅ ልጅ የሚደርስ ግፍ ነው የሚያተርፈው፡፡  
አገሪቱ ወደ ሥርዓት አልበኝነት እያመራች ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ?
እኔ ያን ያህል ወደ ሥርዓት አልበኝነት ገብተናል ብዬ አላምንም፡፡ የማንገባበት እድል የለም ማለት ግን አይቻልም፡፡ ሁኔታው ቸል ከተባለ ወደ ለየለት ሥርዓት አልበኝነት የምንገባበት እድል መፈጠሩ አይቀርም:: ከሁለት ዓመት በፊት ኢሕአዴግ እንደ ሥርዓት እንዲቀጥል ስንስማማና የመጣውን የለውጥ ሀይል ስንደግፍ፣ የምንፈልገውን ጥያቄ ሁሉ ይመልስልናል ብለን አይደለም፤ አገር ውድ ዋጋ እንዳትከፍል እኛ መተው ያለብንን ነገር መተው አለብን ብለን ነው:: በየአመቱ የመቶና ሁለት መቶ  ሰዎች ሕይወት እየገበርን የምንሄድ ከሆነ እኮ ያስቀረን የመሰለንን ውድ ዋጋ እየከፈልን ነው ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ ሕይወቱ ውድ ነው፤ መኖር የሚችለው አንዴ ነው። ንብረት ይተካል የሚለውንም እኔ አልስማማበትም፤ ትክክለኛ እሳቤ አይደለም። ማን ነው የወደመውን የሚተካው? ሰው በ30 እና 40 አመት ልፋት ያፈራውን ሀብት እኮ ነው እያጣ ያለው። ሎተሪ ደርሶት ነው የሚተካው ወይስ በምንድን  ነው? ስለዚህ ንብረት ይተካል በሚል ሁኔታውን ማቃለል ተገቢ አይደለም፡፡    
በአሁኑ ወቅት ህዝባዊ አመጽ የመቀስቀስ የትግል ሥልትን ለመጠቀም የሚያስገድዱ ፖለቲካዊ ችግሮች ያሉ ይመስልዎታል?
ትልቁ ችግር የሚመስለኝ፤ የምንጠቀምበትን የትግል ስልት መቼና በምን አይነት ሁኔታ መጠቀም እንዳለብን  አለማወቅ ነው። ለምሳሌ ውይይትና ንግግር አልፈልግም የሚልን መንግስት በማንኛውም መንገድ እታገለዋለሁ ብለህ መሳሪያ አንስተህ ወይም ሕዝባዊ አመፅ ቀስቅሰህ ልትታገለው ትችላለህ። አሁን ያለው መንግሥት ግን እንወያይ፣ እንነጋገር፣ ምርጫ እናድርግ እያለ ነው። ይሄን ሀይል አይ መጀመሪያ እኔ አንተ ያለህበት ቦታ ላይ ቁጭ ብዬ ነው መነጋገር ያለብን; ከተባለ ግን አይሆንም። በአሁኑ ጊዜ የምትከተለውና አፈና ባለበት ጊዜ የምትከተለው የትግል ስልት የተለያየ ነው። በሰላማዊ ትግል ወቅት ሰላማዊ ያልሆነ፣ ሀይል የቀላቀለበት ትግል ማድረግ ተገቢ አይደለም፤ ወንጀልም ነው። አለበለዚያ ደግሞ አንደኛውን ;ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ ነው የምታገለው# በማለት አቋምን ይፋ አድርጎ ሚናን በግልጽ ማሳወቅ ይገባል፡፡ ነገር ግን ሰላማዊ ትግል ነው የምናደርገው እያሉ፣ በተግባር ሰላማዊ አለመሆን ሕገወጥም ወንጀልም ነው።  አሁን የሚታየው በሰላማዊ ትግል ስም ሰላማዊ ያልሆኑ ትግሎችን እየቀላቀሉ የማድረግ አካሄድ   ነው። ይሄ  መነወር ያለበት ነው። ከዚያ ባለፈም ወንጀል ሆኖ ማስጠየቅ አለበት።
አሁንም የሚደረገው ከጭቆና ነፃ የመውጣት የነፃነት ትግል ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የነጻነት ትግል ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ?
የነፃነት ትግል ነው የሚያስፈልገው ብለው ነፃ ለመውጣት የሚታገሉ ወገኖች እንዳሉ አላውቅም። ለኔ የነፃነት ትግል የሚያስፈልገው፤ በቅኝ ግዛት የተያዘ አገር ወይም ነፃነትን የነፈገ ሀይል ሲኖር ነው። ያንን ጨቋኝ ሀይል በመለመን ሳይሆን በግድ ነው ማስወገድ የሚቻለው፡፡ በእኛ አገር ያለው ግን የበለጠ ዴሞክራሲን የማስፈን ትግል ነው። ከዚህ ውጭ በቅኝ ግዛት ውስጥ ነው ያለነው ብለው የሚያስቡና ከቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት የሚደረግ ትግል እንዳለ የሚያምኑ ወገኖች ካሉ፣ይሄ ሀገርን ለማፍረስ የሚደረግ ትግል ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ እኛ የኢትዮጵያ አንድነት የምንል ሀይሎችም በመሳሪያ እንታገላለን ማለት ነው። በጉልበት እታገላለሁ ብሎ ለተነሳ ወገን ምላሹ በጉልበት ይሆናል ማለት ነው። ይሄ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳለው፤ ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው የሚባልበት አይደለም። የነፃነት ትግል ነው ያለው ካሉን ይንገሩንና እኛም የነፃነት ትግሉን እንቀላቀላለን። እኔ ግን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የነፃነት ትግል ያስፈልጋል ብዬ አላምንም።
በአንድ በኩል፤ ወጣቶችን ለሁከትና ግርግር የሚያነሳሳው የሥራ አጥነት ችግር ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ይህን አስተያየት ይቀበሉታል?
አንደኛ ሥራ አጥነት በዚህ መልኩ አይፈታም፤ የበለጠ ሥራ አጥነት ያሰፍናል እንጂ። ሁለተኛ መንግሥት የተለየ አስማታዊ ጥበብ የለውም፤ ሁሉንም በአንድ ጊዜ ስራ የሚያስይዝበት። ሰላም ሲኖር፣ ባለሃብቶች ባለው ሰላም ተማምነው ንብረታቸው እንደማይወድም እርግጠኛ ሆነው አገር ውስጥ ኢንቨስት ሲያደርጉ ነው ሥራ የሚኖረው። አሁን ያለው ግብታዊ እንቅስቃሴ ግን በሥራ ላይ ያሉትንም ከሥራ የሚያስወጣ፣ በአጠቃላይ ወደለየለት ማህበራዊ ቀውስ የሚመራ ነው። በዚህ በኮሮና ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የተሻለ እድል እያገኙ ያለበት ጊዜ ነበር። በአለም ላይ ያሉ አገሮች የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ትንተና ከኮሮና በፊትና በኋላ በሚል እየተቀየረ የነበረበት ጊዜ ነው። ኢትዮጵያ ከኮሮና በኋላ ሊጎበኙ ከሚችሉ 5 የዓለም ምርጥ ቦታዎች አንዱ ተብላ የተመረጠችበትና ይሄን እድል ለመጠቀም መዘጋጀት ያለችበት ጊዜ ላይ ነበርን፡፡ አሁን ግን ቱሪዝምን በእጅጉ በሚጎዳ ግጭትና ቀውስ ውስጥ እየዳከርን ነው። ይሄ ሥራ አጥነትን በከፍተኛ ሁኔታ ያባብሳል እንጂ አዎንታዊ ውጤት አያመጣም፡፡ ኢንቨስት ለማድረግ አስበው የነበሩ ሰዎች ሀሳባቸውን በድጋሚ እንዲያጤኑ ወይም እንዲመረምሩ የሚያደርጋቸው ሁኔታ ነው እየተፈጠረ ያለው፡፡ ይሄ ድርጊት በጥቅሉ የእይታ፣ አርቶ የማስተዋል ችግራችንን አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
ባሰብነው ልክ የሥራ ዕድል በግል ዘርፎች ካልተፈጠረ ምን እንደሚፈጠር ግልጽ ነው። አሁን ማን ነው በቂ ገንዘብ ቢኖረው ሻሸመኔ ሄዶ ኢንቨስት የሚያደርገው? አርሲ ነገሌ ሄዶ ኢንቨስት የሚያደርገው? በምንም መንገድ የሚታሰብ አይሆንም። ሻሸመኔና አርሲ ነገሌ ያሉ አካላት የሰሩት ሥራ ያተረፉት ነገር ለአካባቢያቸው የበለጠ ድህነትን፤ የበለጠ ጠላትነትን ነው። እዚያ አካባቢ አራት አምስት ትውልድ የኖሩ ሰዎች የሚሄዱበት ሌላ ቦታ እንኳ የላቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች ከዚህ በፊት እንደነበረው ማህበራዊ ግንኙነት ይኖራቸዋል ወይ? የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው። በየቀኑ የሚገናኙ፣ አብረው የሚገበያዩ፣ በደስታም በሃዘንም አብረው ያሳለፉ ሰዎች በዚህ መጠን አለመተማመን ውስጥ የሚከት ነገር መፈጠር የሚያስከትለው የማህበራዊ ግንኙነት ቀውስ ቀላል አይደለም። ከዚህ በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳ መገመት የሚያዳግትበት ሁኔታ ነው ያለው። በቀጣይ ሁኔታውን የሚያስተካክል ሥራ በቅጡ ካልሰራን ወደ ብዙ ምስቅልቅል ውስጥ ያስገባናል፡፡ በዋነኛነት በዚህ እየቆመሩ ያሉ ወገኖች ለጠቅላላው ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል ሥርዓት ማስያዝ የፖለቲካ ባለሥልጣናት ዋነኛ ተግባር መሆን አለበት። አሁን እሹሩሩ ማለት ማብቃት ይኖርበታል::  
በውጭ ያሉ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች እያደረጉ ያሉትን የተቃውሞና አመጽ ቅስቀሳ እንዴት ያዩታል?
እኔ #ዳውን ዳውን ዐቢይ; የሚለው ተቃውሞ ብዙም አያሳስበኝም። እኛም ፓርቲ አቋቁመን ለምርጫ ስንቀርብ ዐቢይን በምርጫ ለማውረድ ነው። እኛ #ዳውን ዳውን ወያኔ; ሲባል ደስ ይለን የነበረው ወያኔ በምርጫ አልወርድም ብላ በጠመንጃ ነካሽነቷ በመጽናቷ ነው። ዐቢይ ግን ምርጫ እናድርግና በምርጫ ከተሸነፍኩ እወርዳለሁ ብሎ በተደጋጋሚ እየነገረን ነው። ስለዚህ የሚያወርደው የሕዝብ ድምፅ ከሆነና ያ የሕዝብ ድምጽ ሰላማዊ ከሆነ፣ ብዙም የሚያሳስበኝ አይደለም። አሁን ግን እየሰማን ያለነው #ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ; የሚል ፉከራ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚደረግ ዘመቻ መንግሥት ርህራሄ ማሳየት የለበትም። የኢትዮጵያን መውደም ለሚፈልግ የውጭ ሀይል ትዕግስት ማድረግ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ይዞ የሚንቀሳቀስ ወገን  በእንዲህ ያለ ጉዳይ ላይ ሲሳተፍ የመጨረሻው ቀይ መስመር መሆን ይኖርበታል፡፡  
ከሰሞኑ በአገራችን የተከሰተውን ሁከትና ብጥብጥ ግብጽ እንዴት የተቀበለችው ይመስልዎታል?
ግብጽ ኢትያጵያ ውስጥ በጥርሷም በጥፍሯም እንደምትንቀሳቀስ እናውቃለን። ለምሳሌ ከሰሞኑ የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ እርስ በእርስ ጦርነት አድርገው ሲያወሩት ነው የሰነበቱት፡፡ ለእነርሱ ክስተቱ ሰርግና ምላሽ ነበር፡፡ እነሱ በዚህ ጉዳይ ቢደሰቱ ከአገራቸው ጥቅም አንጻር ምንም ሊገርመን አይችልም። እኛ እንደ አገር፣ እንደ ዜጋ ራሳችንን እዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መዶላችን ግን  ያሳፍራል። ታሪክም ይፋረደናል። የኢትዮጵያ ፖለቲከኛ ነኝ ብሎ በዚህ መንገድ የሚንቀሳቀስም ታሪካዊ ስህተት እየፈጸመ  ነው።  
ህወኃት ምርጫ አካሄዳለሁ የሚል ውዝግብ ውስጥ መግባቱ፣ ደቡብ በክልልነት ጥያቄ ውስጥ መሆኑ እንዲሁም ከሰሞኑ በኦሮሚያ የተፈጠሩ ግርግሮች ተደማምረው፣ አገሪቱን አደጋ ውስጥ ከተዋታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ስጋት የለም ማለት አይቻልም። ነገር ግን ስጋትን ማስወገጃ መንገድ አለ። ያ ስጋት ማስወገጃ መንገድ ግን ያለ ብዙ ኪሳራ ቢሆን ጥሩ ነው። አገር ማለት ሳር ቅጠሉ አይደለም፤ ሰው ነው። የስጋቱ ፈጣሪዎች ቢሳካላቸውና የለኮሱት እሳት በሰፊው ቢቀጣጠል እነሱንም አብሮ ነው የሚያነዳቸው። ጫካን ያቃጠለ ክብሪት የተሰራበት እንጨት አይተርፍም። ግን እምነት አለኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝም ብሎ ተነስ ስለተባለ ብቻ ተነስቶ እርስ በእርሱ የሚባላ አይደለም፡፡
ብሄራዊ መግባባትና የእርቀ ሰላም ሂደት ይሄን ችግር አባብሶታል የሚሉ አሉ እርሰዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
በሀሳብ ደረጃ እርቅና ሰላም የሚጠላ ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን በእርቅና በሰላም ስም አንዳንድ ወገኖች የራሳቸውን አጀንዳ የሚጭኑበት መድረክ እንዲሆን አልፈልግም። ለምሳሌ ብሔራዊ ውይይት ይደረግ እያሉ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አሉ። የዚህ ብሔራዊ ውይይት የመጨረሻ አላማ ምንድን ነው ተብለው ሲጠየቁ ግን የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ይላሉ፡፡ በመጀመሪያ ሰላም መፈጠር ያለበት ከራስ ጋር ነው። ይቅርታና እርቅም መጀመሪያ ከራስ ነው መጀመር ያለበት። የእርቅና የሰላም ጉባኤ ካላደረግን አገር ትፈርሳለች እያሉ እዚህና እዚያ እሳት የሚጭሩ ካሉ ግን በፍፁም ሀሳባቸውም አላማቸውም ሰላምና እርቅ አይደለም። በአቋራጭ ስልጣን መያዝ ነው። አሁን እየጠራ የመጣውም ይሄው ሀሳብ ነው። ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስፈልገው የተረጋጋ የምርጫ ሥርዓት ለመፍጠር መነጋገር ነው። ከዚህ በመለስ በታሪክ ጉዳይ ላይ ንትርክ ውስጥ መግባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባር አይደለም። ምናልባት በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ውስጥ ሊያካትቱት ይችላሉ። አሁን የሚያስፈልገው፤ሕግና ሥርዓትን አክብሮ መንቀሳቀስና  በምርጫ ሕዝብ የሚፈልገውን መንግሥት ማቋቋም ነው።
በቀጣይ በአገሪቱ ሊፈጠሩ የሚችሉ የቢሆን ግምቶች ማስቀመጥ ይቻላል?
የቢሆን ሳይሆን መሆን ያለበትን ነው ማስቀመጥ የምፈልገው። ከዚህ ቀደም በዴስቲኒ ኢትዮጵያ በኩል ያስቀመጥነው ቢሆን አለ። በዚህም በዚያም መጓተቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን አገር ወደ ንጋት ትሄዳለች የሚል ነው። እኔ የምናገረውም ሆነ የማደርጋቸው ነገሮች ይህቺ አገር ወደ ንጋት እንድታመራ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠናክረው እንዲሄዱ የሚያመላክት ነው። ስለዚህ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን የትኛው ጋ ነን ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። በንግግራችን፣ በድርጊታችን አገሪቱን ወደ ሰላም የሚወስድ ነገር ውስጥ ነን ወይ? ብለን ሁሌም መጠየቅ አለብን። እያንዳንዳችን ለንጋት ካልሰራን የምንፈልገውን ውጤት አናገኝም። ዳር ቆሞ መመልከት፤እኔ የለሁበትም ማለትም ከተጠያቂነት አያድንም።

Read 1069 times
Administrator

Latest from Administrator