Print this page
Saturday, 11 July 2020 00:00

ተጨማሪ ሞትና ውድመት ለማስቀረት!?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ‹‹በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የሕግ የበላይነት መስፈን ይገባዋል፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን በምናደርገው ትግል መርሳት የሌለብን ቁም ነገር ሕዝባችን የሚፈልገው የሕግ መኖርን ብቻ ሳይሆን የፍትሕን መረጋገጥንም ጭምር ነው፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ከፍትሕ የተፋታ ደረቅ ሕግ ሳይሆን በፍትሕ የተቃኘ ለፍትሕ የቆመ የሕግ ሥርዓት ነው፡፡›› -
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) (መጋቢት 24 ቀን 2010፤ ለተወካዮች ምክር  ቤት ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)
            
            ብዙ ጊዜ አዳዲስ መሪዎች ወደ ሥልጣን በመጡ ጊዜ እንደሚያደርጉት ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም  ከሀገር ውጭ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሀገር እንዲገቡ እንዲሁም በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ መሣሪያቸውን አሰቀምጠው ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲመለሱ  ጥሪ አቀረቡ:: ሁሉም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሪውን ተቀብለው አገር ቤት ገቡ፡፡ ዘግይቶ የመጣው የኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅት መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ ከውጭ የመጡትንም ሆነ ትጥቃቸውን አስቀምጠው ወደ ሰላማዊ ትግል የተመለሱትን የክልልና የፌደራሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከፍ ያለ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ይታወሳል፡፡ አቀባበሉን ያደመቀው ሕዝብም፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተሻለ መንገድ ሊይዝ ይችላል  የሚል ተስፋ አሳደረ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን በያዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቀሌ አንድ ስብሰባ ተካሄደ:: በዚያ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ሥዩም መሥፍን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሥልጣን የበቁበትን መንገድ "የቀለም አብዮት" በማለት ገለጹት፡፡ ሌላው ተናገሪ አቶ ኅላዌ ዮሴፍ፤ "ከደመወዝ ዝርዝር ሊስት ያወጡን ይሆናል እንጂ ከትግሉ ሜዳ አያወጡንም" ሲሉ ተናገሩ፡፡ ምን አይነት ትግል በምን መንገድ እንደሚያካሂዱ ግን  አላመለከቱም፡፡  ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ (ጀኔራል)  ለትግራይ ቴሌቭዥን  በሰጡት መግለጫ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመሩትን መንግሥት ለመታገል ጠላት ብሎ መፈረጅ እንደሚያስፈልግ አመልክተው መንግሥቱን "የትግራይ ሕዝብ ጠላት" አድርገው ደመደሙ፡፡ እነዚህ የተጠቃቀሱ ጉዳዮች በተለያዩ አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮች ሕወሓት ከጀርባ አለ ወደሚል ጥርጣሬ ሰዎችን መገፋፋቱ አልቀረም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ መንግሥት በይፋ ሕወሓትን እየከሰሰና እየወነጀለ ይገኛል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከኤል ቲቪ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ‹‹ማን ትጥቅ ይፈታል፤ ማንስ ደግሞ ትጥቅ ያስፈታል›› የሚል መልስ ሰጡ፡፡ ይህ መልስ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል የሚለውን ሁኔታ አስከተለ፡፡ በቂና አጥጋቢ መልስ የሰጠ አካል አልተገኘም እንጂ የአቶ ዳውድ ኢብሳና የመንግሥት ስምምነት ምንድን ነው? የሚል ጥያቄም ተነስቶ ነበር፡፡ አቶ ዳውድ ሊቆጣጠሯቸው የማይችሉ የግንባሩ ወታደሮች፤ በምዕራብ ወለጋ መሣሪያ አንስተው ከመንግሥት ጋር መፋለም ጀመሩ፡፡ በአካባቢው የሰላም መደፍረስ ከማስከተሉም በላይ  የመንግሥት መዋቅርን  መፍረሰ አመጣ፡፡ አማጺዎቹ ማንም ምንም እንዳይል በነዋሪው ላይ ጠንካራ ክንዳቸውን አሳረፉ፡፡
አሁን አሁን ;ኦነግ ሼኔ; እየተባሉ የሚጠሩት ኃይሎች ወደ መሣሪያ ትግል በገቡበት ሰሞን ሁለት የቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት በጉዞ ላይ እንዳሉ ተገደሉ፡፡ ከወራት በኋላም የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅና  የሥራ ባልደረባቸው ተገደሉ፡፡ አማጺው ቡድኑ በሚንቀሰቀስባቸው አካበቢዎች የሚገኙ አስራ ስምንት ባንኮች መዘረፍም መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ በልዩ ልዩ መንገድ የሚመጣው ችግር ያማረራቸው ያካባቢው ነዋሪዎች የፈለገው ይምጣ ብለው ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት መንግሥት እንዲደርስላቸው ተማጸኑ፡፡ ሕዝቡ ወዶና ፈቅዶ አማጺውን ያስጠጋ ይመስል  ;ወዳችሁ የገባችሁበት ነው; በሚል መንፈስ መንግሥት ለኡኡታው የሰጠው ምላሽ ፈጣን እንዳልነበር አስታወሳለሁ፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ያሉበት የአገር ሽማግሌዎችና የአባ ገዳዎች ቡድን ተልኮ ያመጣው  ውጤትም ጥቂት ሰዎችን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ከማድረግ በላይ ብዙ አልተራመደም፡፡ የኦሮሞ ምሁራን ሙከራም ከቀደመው እምብዛም የተለየ ውጤት ያሳየ አልመሰለኝም፡፡ መንግሥት ነገሩን ሲበዛ አለዝቦ መያዙ ቡድኑን የበለጠ ጉልበት እንዲሰማውና ‹‹አባ ተርቤ›› ማለትም ማነህ ባለ ሳምንት የሚባለውን የነጭ ሽብር ተመሳሳይ የግድያ  እርምጃ በግለሰቦች ላይ ወደ መውሰድ እንዲሻገር አደረገው፡፡ ወደ ኋላ በተወሰደበት ወታደራዊ እርምጃ ትንሽ ደንገጥ ያለ ቢመስልም፣ መሣሪያውን አስቀምጦ ወደ ሰላም እንዲገባ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ‹‹ታፍኖ የኖረ ቤት ሲከፈት የሚፈጥረው ሽታ አለ›› ብለው ነገሩን፤ ሁኔታውን ጊዜያዊ አድርገው ቢያዩትም፣ በእርሳቸው ዘመነ መንግሥት ከአንድ ዓመት በላይ የቆየው በየአካባቢው በሚገኙ ተጎራባች ብሔረሰቦች መካከል በሚፈጠረው ግጭት ፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከመኖሪያ ቀበሌው እንዲፈናቀል፣ ሃብት ንብረቱን እንዲያጣ ሕይወቱንም እንዲገብር አስገድዶታል፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ጥግ ቡራዩና አሻዋ ሜዳ በተፈጠረ ችግር የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በአንዳንዶች ላይ የተፈጸመው ግድያ ለማድረግ አይደለም ለመናገርም እንደሚከብድ የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል፡፡ ዛሬም ድረስ አንድ እልባት ያላገኘው የተጠለፉ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይም ከሚያብሰለስሉ የሀገሪቱ ችግሮችና የመንግሥት ፈተናዎች አንዱ ሆኖ ዘልቋል፡፡  
በጥቅምት 2012 ዓ.ም አቶ ጀዋር መሐመድ "ተከብቤያለሁ" ሲሉ ባስተላለፉት ጥሪ፣ ደጋፊዎቻቸው በሰነዘሩት ጥቃት ዘጠና ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ከርሞ ከርሞ ሰሞኑን ገልጧል፡፡ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን፣ ቤታቸው የተቃጠለባቸውንና ድርጅታቸው የወደመባቸውን ቤት ይቁጠራቸው ከማለት ሌላ ምን ይባላል?
በቤኒሻንጉል ክልል በልዩ ልዩ አካባቢዎች፣ በአማራ ክልል በከምሴ ዙሪያ፣ ጎንደር ውስጥ በቅማንትና ባካባቢው ሕዝብ መካከል በተፈጠረ ግጭት ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡ በአማራ ክልልና በሌላውም አካባቢ በርካታ የሃይማኖት ተቋማት መቃጠላቸው ይጠቀሳል፡፡  እዚሁ በአማራ  ክልል ውስጥ በምርምር ሥራ ላይ እንዳሉ በፈጠራ ወሬ የተገደሉ ወጣቶች ጉዳይም ሣር እንዲበቅልበት የማይፈለግ የፍትሕ ጥያቄ ነው፡፡  
እስካሁን በዘረዘርኳቸው አካባቢዎች በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የክልል መንግሥታት  የተጠረጠሩ ሰዎች ተያዙ ብለው ቁጥር ከመግለጥ ውጪ ለፍትሕ አቅርበው የቀጡት ስለመኖሩ እምብዛም አይታወቅም፡፡ የፍርዱ መዘግየት ወንጀሉን የተፈቀደ አድርጎ ሊያስቆጥረው ምንም አልቀረውም ለማለት ያስችላል፡፡ እናም አንድ መቶ አንድ ጊዜ ፍትሕ ለተበደሉ እላለሁ!!
የሰሞኑ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት፣ በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ የመንግሥትን የወንጀል መከላከል አቅምና ዝግጁነት ጥያቄ ላይ አጥብቆ የጣለ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ለሃጫሉ እነማን ናቸው ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ የሰጡት? ለምንስ ክትትል ሳይደረግባቸው ቀረ? ባለ ጉዳዩ ከስ ማስመዝገብ አልፈለገም?   ነገሩ ቸል መባል ነበረበት? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡  መንግሥት ለፍትሕ ተቆርቋሪነቱን ሊያሳይ ይገባል፡፡ ሃጫሉ በማን እጅ ተገደለ?  ከግድያው ጀርባ የማንና የእነ ማን እጅ አለ? መንግሥት ላቡን ጠብ አድርጎ ሊፈልገው የሚገባ እውነት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች፣ ከአዲስ አበባ ውጪ በናዝሬት (ቢሾፍቱ)፣ ዝዋይ ፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ  ወዘተ ከተሞች ላይ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፡፡ በተለይ ሻሸመኔ እንዳልነበረች ሆናለች እየተባለ ነው፡፡ የአካባቢው ሰዎች የሚናገሩት ደግሞ ጥቃት አድራሾቹ ምን ምን እንደሚያጠፉ ዝርዝር ይዘው፣ የአራትና የአምስት ሰዓት የእግር ጉዞ አድርገው የመጡ መሆናቸውን ነው:: ይህ ወንጀሉ ለረጅም ጊዜ ታስቦበት ዝግጅት ተደርጎበት የተፈጸመ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የክልልም ሆነ የፌደራሉ የደህንነት ቢሮ ራሱን መልሶ ማየት እንዳለበት አፍ አውጥቶ የሚናገር ነው:: ዶ/ር ዐቢይ ያላቸውን የደህንነት የሥራ ልምድ መተግበርና ማካፈል የሚገባቸውም አሁን ላይ ነው፡፡
የክልል ፕሬዜዳንቶችም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጥርሳቸውን ነክሰው በየአካባቢው የሚከሰቱ የሰዎች ሞትና መፈናቀል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚቆምበትን መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል፡፡ ሻሸመኔ ሰው ተዘቅዝቆ የተገደለባት ከተማ ናት፡፡ አንድ ሁኔታ ሲፈጠር ጢስ የሚታየው እዚያ ነው፡፡ እንደነዚህ ያሉ አካባቢዎችን ለይቶ በቋሚነት የጸጥታ ኃይል የመመደብን ነገር መንግሥት በግድ ሊያስብበት ይገባል፡፡
በሕወሓት ኢሕዴግ በጉልበት የተፈጠረው የደቡብ ክልል መፍረስ ጀምሯል:: ሲዳማ ክልል ሆኗል፡፡ ሌሎች ዞኖች የክልልነት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ አንዳንዶችም የራሳቸውን ቀነ ገደብ አስቀምጠው ይህ ካልሆነ እንዲህ እናደርጋለን እያሉ ናቸው፡፡ ክልሉም የፌዴራል መንግሥቱም መፍትሔ ያሉትን ሃሳብ ማቅረባቸው የታወቀ ነው፡፡ ክልል መሆን ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ነው ብለው የተነሱት ክፍሎች ግን አልተቀበሉትም፡፡ ሌላ ሞትና ውድመት በዚህ አካባቢ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡  በሕገ መንግሥቱ መሠረት፤ የየዞኑ ሕዝብ ድምጽ ሰጥቶ ክልል መሆን ወይም አለመሆኑን የሚወስንበት ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ በትዕግሥት እንዲጠብቁ ማድረግ የመንግሥት ሥራ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት፣ ሕግን ስለ ማክበር፣ ፍትሕን ስለ ማስፈን የገባውን ቃል ይፈጽም ዘንድ  ደግሜ አሳስባለሁ፡፡
 ‹‹ዶ/ር ዐቢይ፤ ከመቶ ሃያውን ቆራጥነትና ፍጥነት ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፤ ከመቶ ሃያውን ሴረኝነት ከአቶ መለስ ዜናዊ ወስደው በራሳቸው ባሕሪ ላይ ቢጨምሩ፣ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚመቹ መሪ ይሆኑ ነበር›› ብሏል፤ አንድ የቸገረው ወዳጄ፡፡  ለዛሬ ነገሬን በዚሁ ቋጨሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ የተንጸባረቀው ሃሳብና አመለካከት ጸሃፊውን ብቻ የሚወክል መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡



Read 905 times