Saturday, 04 July 2020 00:00

የዋህ

Written by  ከኦሉ ዳራ
Rate this item
(6 votes)

 ከእንቅልፉ እንደነቃ እንደነገሩ አጣጥፎ ወንበር ላይ ያስቀመጣቸውን ልብሶቹን ለበሰና ማሠሪያቸውን ሳይፈታ ያወለቃቸው ጫማዎቹን በትግል ተጫምቶ፤ ያደረ ፊቱን ውሃ እንኳን ሳያስነካ የቤቱን በር ቆልፎ ወጣ::
ለደቂቃዎች ተጉዞ ቴዎድሮስ አደባባይ ሲደርስ፤ አስፋልቱን ተሻግሮ፤ ቁልቁል ወረደና ቴሌው ፊት ለፊት ባለችው ቀጭን፣ ቁልቁለት መንገድ አቋርጦ፤ ጎላ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን ደጃፍ ደረሰ፡፡
ትናንት ማታ ከጓደኛው ጋር ያደረገውን ክርክርና ሌሊት በህልሙ ስላያቸው ሽማግሌ በማሰብ ተጠምዶ የነበረው አእምሮው፤ ቀንበሩ ወርዶለት፤ ቤተ ክርስትያኑ ጋ መድረሱን የተረዳው ወደ ቤተ ክርስትያኑ የሚገቡና ከቤተ ክርስትያኑ የሚወጡ፤ ነጠላ የለበሱ ምዕመናን ትከሻውን ከግራና ከቀኝ እየገጩ ከሀሳቡ ካናጠቡት በኋላ ነበር፡፡
ቤተ ክርስትያኑ ጋ እንደደረሰና በየት በኩል አድርጎ እንደመጣ ሲረዳ ደነገጠ፡፡ ሌላ ጊዜ ወንዙ ጋ የሚሰበሰቡ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ፍራቻና ወንዙ የሚያወጣውን መጥፎ ሽታ ጥላቻ በኢሚግሬሽን በኩል ዞሮ ነበር ቤተ ክርስትያን የሚሳለመው፡፡ አሁን ግን በሀሳብ ተወጥሮ፤ ሰክሮ እንኳን የማይሠራውን ስህተት እንደሠራ ሲረዳ ደነገጠ፡፡ መልሶ ግን የምጠላውን ካላየሁና ካላሸተትኩ፤ በዚህ ጋ መጣሁ በዛ ምንድነው ለውጡ ሲል እራሱን አረጋጋ፡፡
ከተረጋጋ በኋላ ወደ ቤተ ክርስትያኑ ቅጥር ከሚገቡና ከሚወጡ ምዕመናን ጋር ላለመጋጨት አንዴ ቆም፤ ሌላ ጊዜም ፈጠን እያለ የግቢውን በር ቀኝ ይዞ፤ ጥግ ላይ ቆሞ ጸሎት ለማድረግ፤ እረኛ እንደሌላቸው በየቦታው የተበታተኑትን ሀሳቦቹን መሰብሰብ ጀመረ፡፡ የቻለውን ያህል ከሰበሰበ በኋላ፤ አልሰበሰብ ያሉትን ሀሳቦች በረጅሙ ተንፍሶ አወጣቸውና ተመልሰው እንዳይመጡበት አማትቦ ጸሎቱን ማድረስ ጀመረ፡፡
ለደቂቃዎች በተመስጦ ሆኖ በውስጡ እየተመላለሱ እረፍት ለነሱት ጥያቄዎች መልስ ያገኝ ዘንድ እንዲረዳው አምላኩን እየጠየቀ ሳለ ድንገት አንድ እጅ ትከሻው ላይ አረፈ፡፡ ከተመስጦው ብንን ብሎ ባለ እጁን ዞሮ ተመለከተ፡፡ የቀይ ዳማ ቆዳና ብሩህ ቡናማ ዓይን ያላቸው፣ ጸጉራቸው ዳባ የመሰለ፤ ጺማም ሽማግሌ ፈገግ ብለው ሲያዩት ተመለከተ፡፡ ያየውን ባለማመን ደነገጠ፡፡ ማታ በህልሙ እየተመላለሱ፤ አንዳች ነገር ሊነግሩት ሲሞክሩ የነበሩት ሽማግሌን ይመስላሉ፡፡
ሽማግሌው ትከሻውን ጨምድደው ሙሉ ለሙሉ ወደሳቸው ዞሮ እንዲቆም አደረጉት:: በድንጋጤ እንደተዋጠ ሽማግሌውን ከላይ እስከ ታች ተመለከታቸው፡፡ በብጫ አፈር የቀድሞ መልኩ የጠፋበት ልብስ መናኝነታቸውን ይናገራል፡፡ ጫፉ ላይ አረንጓዴ፣ ብጫ ቀይ ባንዲራ የተቋጠረበት እረጅም የብረት መስቀል ይዘዋል፡፡ ጫማ ያልተጫማው እግራቸውን ሲመለከት ጥራቱና ልስላሴው፤ በጫማ ሙቀት ከሚቀቀለው ከእሱ እግር እንደሚበልጥ ጠረጠረ፡፡
‹‹ልጄ›› አሉት ሽማግሌው፡፡ ድምጻቸው በጣም ያምራል፡፡ ድንጋጤው ስላለቀቀው ዝም ብሎ አፍጥጦ ተመለከታቸዉ፡፡
‹‹እግዝያብሔር የዋህ ስለሆንክ ነው የሚጠብቅህ›› አሉት፡፡
‹‹እ?›› አላቸው የሞት ሞቱን፡፡
‹‹የየዋህ አምላክ የዋሆቹን ይጠብቃል፡፡ አንተንም እየጠበቀህ እስከ ዛሬ አድርሶሀል:: ይሄ ማለት ሌሎቹን አይጠብቅም ማለት አይደለም፡፡ እንዳንተ አይነቱ ልዩ ጥበቃ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ልጅቱ ትቅርብህ:: ገዝታ የሰጠችህንም ሹራብ ከዛሬ ጀምሮ አትልበሰው ብሎሀል፡፡››
‹‹ምን?......ምን?›› በሂደት የለቀቀው ድንጋጤ ተመልሶ መጥቶ ሰፈረበት፡፡
‹‹‹በየዋህነት የሚረግጡ እግሮችህን እስካሁን መንገድህ ላይ አጽንቼ አቆምኩልህ› ብሎሀል፡፡ እንደርሱ ባይሆን ይሄኔ መንገድህን ይዛብህ ሄዳ ነበር፡፡ አንተም ባንድ ነጭ ሹራብ መንገድህን ሸጠህላት ነበር፡፡ የዋሆች ነጭ ነገር ሁላ ያታልላችኋል፡፡››
‹‹ምንድን ነዉ የሚሉኝ አባት?›› ግራ በመጋባት ጠየቀ፡፡ ድንጋጤው በግራ መጋባት ተተክቷል፡፡
‹‹የየዋህ አምላክ ‹ተነስ መንገድህን ተሸክመህ ሂድ› ብሎሃል፡፡ ልጄ መንገዱ ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ በመንገዱ ላይ መሄድ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም መንገዱን እራሱ ተሸክሞ መሄዱ ግድ ይላል፡፡ ጠላት እንቅፋት የሚያበጀው ለእግሮች ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንዴም መንገዱን እራሱ ማደናቀፍ ይፈልጋል፡፡››
‹‹ቆይ የምን መንገድ ነዉ አባቴ? ደግሞ ስለ እኔና እሷ እንዴት አወቁ?››
‹‹እኔማ ምን አውቃለሁ ብለህ ነው ልጄ! ሁሉን የሚያውቅ እርሱ በተለያየ መንገድ ንቃ ብሎ መልዕክት ቢሰድብህም አልነቃም ስላልክ ነው እኔን ወዳንተ የላከኝ፡፡››
‹‹ማለት? ምንድን ነው የሚሉኝ አባቴ?››
‹‹ለምሳሌ ትናንት በጓደኛህ ‹ንቃ! ልጅቱ ላንተ አልተፈጠረችም፡፡ ተዋት› የሚል መልዕክት ተላከብህ፡፡ አንተ ግን በክፋት ተርጉመኸው ጓደኛህን ተቀየምህ፡፡ ሌቱን እኔም በህልምህ እየተመላለስሁ እንድትነቃ ልነግርህ ሞከርኩ፡፡ አንተ ግን ህልሙን እንደ ቅዠት ቆጥርህ ስትጨነቅ አደርህ:: ይኸዉ አሁን በአካል መጥቼ መልዕክቴን አድርሻለሁ፡፡ ንቃ! ንቃ ልጄ!››
ሽማግሌዉ ፊታቸዉን አዙረው መንገድ ሊጀምሩ ሲሉ እጃቸውን ይዞ አቆማቸውና በጥያቄ ዓይን ተመለከታቸው፡፡ ለደቂቃዎች በጥያቄ ዓይን እየተያዩ ቆሙ፡፡ መፋጠጡ ሲያስፈራውና ባለጉዳዩ እሱ እንጂ እሳቸዉ እንዳልሆኑ ሲረዳ
‹‹ቆይ ንቃት፣ ንቃት የምትሉኝ ምንድን ነው? መች ነው ሳልነቃ የቀረሁት?››
‹‹ልጄ አሁን እራሱ ከእንቅልፍ መች ነቃህ? በእንቅልፍ ልብህ ነው ቤተ ክርስትያን የመጣኸው፡፡››
‹‹እና መምጣቴ ጥፋት አለው ማለት ነው?›› በትዝብት ተመለከታቸው፡፡
‹‹ልጄ ምንም ለማድረግ ንቃት ያስፈልግሀል፡፡ ነቅተህ ነው መምጣት ያለብህ! ለምን፣ መቼ፣ እንዴት ሆነህ መምጣት እንዳለብህ፤ ከመምጣትህ በፊት ማወቅ አለብህ፡፡››
‹‹ደግሞ ቤተ ክርስትያን ለመምጣት…ከፈጣሪዬ ቤት ለመምጣት ይሄን ሁሉ ጥያቄ መመለስ አለብህ ነዉ የሚሉኝ? ጉድ እኮ ነው!››
‹‹ልጄ ለመዳን በሽታህን ማወቅና ለበሽታህ የሚሆነውን መድኃኒት መርጠህ መውሰድ አለብህ፡፡››
‹‹እግዝያብሔር ሁሉንም በሽታ በአንድ መድኃኒት መፈወስ ይችላል አባቴ!››
‹‹ከፈጣሪ ጋር ልታጣላኝ እየሞከርህ ነው እንዴ ልጄ?››
‹‹አይደለም የፈጣሪን ኃያልነት እየመሰከርኩ ነዉ፡፡ እርስዎ የባህታዊ ልብስ ስለለበሱ ብቻ የሚሉትን ሁሉ ማመን የለብኝም፡፡ መርምሩ ይላል እኮ!››
‹‹እሱን እኮ ነው የምለው ልጄ - መርምር!:: የምታደርገውን ነገር ለምን እንደምታደርግ መርምር፡፡ መቼና እንዴት ማደረግ እንዳለብህ እራሱ መርምር ነው የምልህ፡፡››
‹‹አባቴ ምንም አሉ ምንም ወደ ፈጣሪ ቤት መቼ እንደምመጣና ለምን እንደምመጣ አልመረምርም፡፡ ጥያቄ ካለኝ እመጣለሁ፡፡››
‹‹ጥያቄ ካለህ ነው ወይስ መልሱን ከዓለም ፈልግህ ካጣህ?››
‹‹ማለት?››
‹‹ለምሳሌ ትናንትና መጠጥ ቤት ከጓደኛህ ጋር ተቀምጠህ ስታማክረው እሱ የምትፈልገውን መልስ ቢሰጥህ ኖሮ ዛሬ ትመጣ ነበር?››
‹‹እየፈረዱብኝ ነዉ እንዴ አባቴ? አትፈረድ ይላል እኮ መጽሐፉ፡፡››
ባህታዊዉ በፈጣሪ ሥራ ተገርመው አናታቸዉን ነቀነቁ፡፡ በውስጣቸዉ ‹አንተ ፈጣሪ ተፈጥሮህ ግሩም ነዉ፡፡ ቆይ ምንን ነው የምትመረምረው? አሁን ይሄ ልጅ ምኑ ነው የዋህ? በላ አይደል እንዴ!…ፈጣሪዬ ሆይ ይቅር በለኝ!...እኔ ያንተ መልዕክተኛ ነኝ፡፡ አንተ ያልከውን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡› አሉና ወደ ወጣቱ ዞረው፤  
‹‹ልጄ እኔ አልፈረድኩብህም! እኔ ማነኝና ነው በሰው የምፈርድ? እኔ የእሱ መልዕክተኛ ነኝ፡፡ እሱ እንኳን አልፈረደብህም፡፡ ቤተ ክርስትያን ሳትመጣ እንኳን እዛው እምትጠጣበት ቤት መልስ ልኮልህ ነበር›› አሉት፡፡
‹‹አባቴ እኔ በዚህ ሰዓት ንቃ የሚለኝ ሰው አይደለም የምፈልገው፡፡ እኔ ምን ማድረግ እንዳለብኝ የሚነግረኝ ሰው ነው የምፈልገው::››
‹‹ልጄ ንቃቱ እኮ ቢኖርህ ምን ማድረግ እንዳለብህ እራስህ ታውቅ ነበር፡፡ ደግሞ ማድረግ ያለብህን ነግሬሀለው፡፡ ልጅቱን ተዋት፡፡ ነጭ ሹራቡን አውጥተህ ወርውረዉ:: ደግሞ ቃሉ የኔ አይደለም፡፡ ፈጣሪ ነው እንደዛ ያለህ፡፡ ልጅቱ ቀድማህ መንገድህን ነጥቃ ይዛብህ ከመሄዷ በፊት መንገድህን ይዘህ ሽሽ ብሎሀል ፈጣሪ፡፡››
‹‹አባቴ ቆይ መንገዴን ተሸክሜ በምን መንገድ አድርጌ ነዉ የምሸሸው?...ደግሞስ ወዴት ነዉ የምሸሸው? ሁሉም ቦታ እርሷ እኮ ነች ያለችው፡፡›› በረጅሙ ተነፈሰ፡፡
‹‹ቆይ ሳትሞክረው መንገድህን ተሸክመህ የምትሄድበት መንገድ እንደሌለህ እንዴት አወቅህ? ሳታየው ሁሉም ቦታ እርሷ እንዳለች እንዴት ደረስህበት?››
‹‹አባቴ፤ እሷ እኔ ውስጥ ነግሳ ነው ያለችው፡፡ እኔ ካለሁ እሷ አለች፡፡ ሰዉ ከእራሱ መሸሽ ይችላል እንዴ? ደግሞስ እግሬ እሷ ሆና ሳለች መንገድ መቀያየሩ ምን ጥቅም ይኖረዋል?››
‹‹ልጄ ጸሎትህን የሽኮኮ አታድርገው፡፡ ጥያቄ ጠይቀህ መልስ ሲሰጠህ መልሱ እኔ እንደምፈልገው አይደለም ብለህ መልሱን አልቀበልም አትበል፡፡ የምትፈልገውን ዓይነት መልስ ከፈለግህ ቅደሙንስ ለምን ጠየቅህ?››
‹‹የኔ ጥያቄ ልሽሻት ወይስ መንገዴን ተሸክሜ ልሂድ አይደለም፡፡››
‹‹ቆይ ጥያቄህ ምንድነው?›› ሽማግሌው በግርምት ጠየቁ፡፡
‹‹ጥያቄውን እንኳን ሳያውቁ ነዉ እንዴ መልስ ይዘውልኝ የመጡት?›› አፈጠጠባቸው፡፡
‹‹ልጄ፤ እኔ የእግዝያብሔር መልዕክተኛ ነኝ፡፡ አድርስ የተባልኩትን መልዕክት ማድረስ እንጂ ለማን?...ምን ሆኖ?...ለምን? እያሉ ፈጣሪን መጠየቅ የኔ ሥራ አይደለም::››
‹‹እሺ የኔ ጥያቄ ምን መሰለዎት…›› እጃቸውን ይዞ ሄዶ ድንጋይ ላይ አስቀመጣቸውና ከጎናቸው ቁጭ ብሎ በተረጋጋ ድምጽ ማስረዳት ጀመረ፡፡
‹‹ይኸውልዎት አንዲት የምወዳት ሰብለወንጌል የተባለች ጓደኛ አለችኝ፡፡››
‹‹ሥሟስ መልካም ነበረ፡፡ ልጄ ያንተስ ሥም ማነዉ?››
‹‹ሥሜንም አያውቁትም? እሺ ሠይፈ እባላለሁ - ሠይፈ ገብርኤል….እና አባቴ ከሰብለ ጋር ተዋደን ነው የተገናኘነው፡፡ አብረን ስንሆን ደግሞ በጣም ስለተጣጣምን ሁለታችንም ሲበዛ ደስተኞች ሆንን፡፡ ነጭ ሹራብ ገዝቼ ሰጠኋት፡፡ ነጭ ሹራብ ገዝታ ሰጠችኝ፡፡ እሱ በጣም አመሳሰለን፡፡››
‹‹እና ምን ተፈጠረ ልጄ?››
‹‹ምን መሰለዎት አባቴ፤ ሰብለ አንዳችን ያንዳችን ብቻ መሆናችንንና ፍቅረኛ ተብለን መጠራታችንን አትፈልገውም፡፡ ‹በቃ ዛሬን ብቻ እያሰብን በመዋደዳችን እንደሰት:: ዛሬን ብቻ እንኑር፡፡ ፍቅር፣ ፍቅር እያልን እራሳችን በሠንሠለት አንጠፍር› ነው የምትለው:: የሚገርመው አባቴ በፊት፣ በፊት ሴቶቹ አልቀመስ አሉኝ እንጂ እንደዚህ ዓይነቱን ግንኙነት ስፈልገው ነበር የኖርኩት፡፡ አሁን ሳገኘው ግን የፈራሁት ደርሶ፤ የጠላሁት ወርሶ፤ እነዛ ስገፋቸው የነበሩት ሴቶች እንደሚያደርጉት ሰብለን ‹አሁን የት ላይ ነዉ ያለነው? ግንኙነታችን ወስዶ የት ነው የሚያደርሰን? ነገ ምን ይዞልናል...› እያልኩ ነጋ ጠባ እጠይቃታለሁ፡፡ ሰሞኑን እግሯን ቀንሳለች፡፡ ስልኬንም እንደ በፊቱ አትመልስም፡፡››
‹‹ልጄ ዝሙት ሀጥያት እንደሆነ ታውቃለህ አይደል?››
‹‹እሱን የማያውቅ ማን አለ አባቴ?››
‹‹ባለማወቅና አውቀው ያወቁትን ተግባራዊ ባለማድረጉ መሀል ያለው ልዩነት ምንድነው ልጄ?››
‹‹አባቴ ዛሬ ግን መች ነው?›› ከጠየቁት ጥያቄ የራሱ ሀሳብ በልጦበት ጥያቄአቸውን በጥያቄ መለሰ፡፡
‹‹ማለት ልጄ?›› ሽማግሌው ግራ ተጋቡ፡፡
‹‹ዛሬን እንኑር፤ ዛሬን እንደሰት፤ ስለ ነገ አንጨነቅ ትላለች፡፡ ወንጌሉም እንደዛ ይላል::››
‹‹ወንጌሉ እንደዛ አይልም ልጄ!፡፡››
‹‹አሁን ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም፡፡ ከእሷ መለየቱን እፈራዋለሁ:: የኔ ብቻ እንዳልሆነች ማሰቡንም፤ እራሴን አሳልፌ ልሰጣት ብፈልግም የእሷ ብቻ እንድሆን እንደማትፈልግ ሳስብም እናደዳለሁ፡፡ እሷ የምትለው ዛሬ መቼ እንደሆነ ልረዳው አልቻልኩም፡፡ እርስዎ ምን ይመክሩኛል አባቴ?››
ቀና ብሎ ባህታዊውን በጥያቄ አይን ተመለከታቸው፡፡ ባህታዊው ሲያዩት ቆዩና የሚሉትን ለመስማት እንደጓጓ ሲረዱ ጉሮሯቸውን ጠራርገው፤
‹‹ለዚህ እኮ ነዉ ፈጣሪ እንድትለያት የነገረህ›› አሉት፡፡
‹‹አባቴ እስኪ የፈጣሪን ይተውት እና እርስዎ እንደ ራስዎት ምን ማድረግ እንዳለብኝ ንገሩኝ፡፡›› አላቸው፡፡ ባህታዊዉ በትዝብት ሲመለከቱት ቆዩና፤
‹‹ከፈጣሪ መልስ የኔ የአንድ ተራ ሰው መልስ ይሻልሀል ልጄ?››
‹‹አባቴ እንደዛ ማለቴ አይደለም፡፡ በቃ ፈጣሪ ፈጣሪ ነው፡፡ ፈጣሪ ፍጹም ነው፡፡ ሰው ጎዶሎና ደካማ ነው፡፡ ጎዶሎና ደካማ ሆኖ የፍጹምን መልስ ከመስማቱ ይልቅ የጎዶሎው ያሳምናል፡፡››
‹‹ቆይ ፍጹም የሆነው ፈጣሪ የምትፈልገውን ዓይነት መልስ ቢሰጥህ ኖሮ አልቀበልም ብለህ፤ ጎዶሎና ደካማ ወደሆነው ሰዉ ትሄድ ነበር?›› አሉት፡፡ ወጣቱ አቀርቅሮ ሲያስብ ቆየና፤
‹‹አላውቅም አባቴ፡፡ ሰውነት የሚባለው እንዲህ መሆኑ መሰለኝ፡፡ አባቴ አሁን ከቻሉ መልስዎን ይስጡኝ፡፡›› አለና መልሶ አቀረቀረ:: ባህታዊው ትንሽ ሲያስቡ ቆዩና፤
‹‹እሺ እንደ ራስህ ተናገር ካልከኝ እንደራሴ ሆኜ ልንገርህ…›› ባህታዊው ቀና ብለው ተመለከቱት፡፡ እየሰማቸው እንደሆነ አረጋገጠላቸው፡፡ ቀጠሉ፤
‹‹እንደኔ እንደኔ አንተ ምንም የዋህ አይደለህም፡፡ የፈጣሪ ሥራ ግን ግሩም ነው:: ምንህን መርምሮ፣ በምን መዝኖህ የዋህ እንዳለህ ማሰቡ ድንቅ ነዉ፡፡ ብቻ እሱ ሁሉን አዋቂ ነው፡፡ ቃሉ እውነት ነው፡፡››
‹‹እውነት ነው አባቴ!›› አላቸው፤ ወደው ሳይሆን በግዳቸው የተቀበሉትን የዋህነቱን ለማስረገጥ፡፡
‹‹ልጄ የሰው ልጅ አመጸኛ ነው፡፡ ሰው በሰው ላይ ያምጻል፣ በእናት አባቱ ላይ ያምጻል፤ በእራሱ ላይ እንኳን ያምጻል፡፡ እሱ አልበቃ ሲለው ደግሞ፤ አልፎ፣ ተርፎ በፈጣሪውም ላይ ያምጻል፡፡ የምፈልገውን እንጂ የሚያስፈልገኝን አልፈልግም ብሎ ያምጻል፡፡ ቃሉን የሚያውቅና በቃሉ የሚኖር ሰው እንኳን ከአመጻ አይመለሰም፡፡ እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ? ቆይ ልጅቱ ለምን ዛሬን ብቻ እንኑር ያለችህ ይመስልሀል?››
‹‹እሷማ ከዚህ በፊት በፍቅር ተጎድቻለሁ:: ድጋሚ በፍቅር ሥም መጎዳት አልፈልግም ነው የምትለው፡፡ እንደዚህ እንደተዋደድን እየተደሰትን እንኑር ነው የምትለኝ፡፡ ሌላ ሴት ብትሆን እኮ ችግር የለውም ነበር፡፡ እሷ ሆናብኝ እኮ ነው እንደዚህ የተጨነቅሁት፡፡››
‹‹ልጄ እሷ ስለሆነችብህ አይደለም የተጨነቅከው፡፡›› አሉት ባህታዊው፡፡
‹‹ነው እንጂ አባቴ፡፡ በጣም ነው የምወዳት፡፡››
‹‹ልጄ እንደዚህ አይነት የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መግባት የሰው ልጅ ተፈጥሮ አይደለም፡፡ እሷም ብትሆን እንደዚህ ያለችህ ፍቅረኛዋና የትዳር አጋሯ እንዲሆን ከምትመኘው ሰው የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ካንተ ላይ ስላላገኘች ነዉ፡፡ አንተ የምታፈቅራትን ግማሹን ያህል ብታፈቅርህ ኖሮ እንዲህ ማሠሪያህን አታስረዝመውም ነበር፡፡››
‹‹ማለት? ግን እኮ ከእኔ ጋር ሆና ደስተኛ እንደሆነችው በህይወቷ ደስተኛ ሆና እንደማታውቅ ነግራኛለች፡፡››
‹‹ልጄ የሁሉም ሰው ፍላጎት እኮ ደስተኛ መሆን አይደለም፡፡ ሰዉ እንደየመልኩ የተለያየ ፍላጎትና የህይወት ግብ ነው ያለው::››
‹‹በእርግጥ አንድ ቀን እንደዚህ ደስተኛ ከሆነች ለምን የኔ ብቻ መሆን እንደማትፈልግ ስጠይቃት ‹ለደስታ ብቻ ብዬ ከአንተ ጋ መሆን አልችልም› ብላኛለች፡፡›› አለና አቀረቀረ፡፡
‹‹ልጄ እሷ እንደዚሁ ሆነን እንቆይ ያለችህ ምናልባት መቼ ካንተ ጋር መለያየት እንዳለባትና አንተን ለማን ስትል መተው እንዳለባት ስለምታውቅ ይሆናል፡፡ አንተ ደግሞ ነገሩ የከበደህ ከእሷ መለየት ስለማትፈልግ ብቻ ሳይሆን ምናልባት መቼ ከእሷ መለየት እንዳለብህ ስለማታውቀው ይሆናል፡፡››
ወጣቱ አዝኖ አንገቱን እግሮቹ ውስጥ ቀብሮ አቀረቀረ፡፡  ባህታዊ ጀርባውዉን እየደባበሱ፤
‹‹ልጄ ንቃ! እግዝያብሔር አዋቂ ነው፡፡ ለበጎ ነው የሚለዉ ቃል ቀላል እንዳይመስልህ:: የፈለግከውን ማግኘት ስሜትህን ሊያረካ ይችላል፤ የሚያስፈልግህን ማግኘት ደግሞ ነብስህን ነው የሚያስደስተው፡፡ ከፈጣሪ ምላሽ ፍለጋ ደጁ የሚያስመጣ ጉልበት ካለህ በፈጣሪ ለማመን አትፍራ፡፡ ማመን ደግሞ ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ አንዳንዴም ለማመን ‹አለማመኔን እርዳው› ብለህ መጸለይ ይኖርብሀል፡፡››
ወጣቱ አንገቱን እንዳቀረቀረ ተንሰቅስቆ አለቀሰ፡፡ የሚፈልገውን ትቶ የሚያስፈልገውን መቀበል እንዳለበት ማመኑ ይሆናል ያስለቀሰው፡፡ ባህታዊዉ አታልቅስ አላሉትም፡፡ ጀርባውን በእጃቸው እያሻሹ፤
‹‹ልጄ አንተ የምታስበውን ንገረኝ ካልከኝ ዘንዳ አሁን የምነግርህን ነገር ልብ ብለህ አድምጠኝ፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን አብረሀት ለመኖር የምትፈቅዳት ሴትን ስትመርጥ፤ በመቶኛ ስታሰላው፤ ከመቶ ሃያ አምስቱን እጅ ስታያት ዓይንህ የምትገባ፤ አንተም በእሷ ዓይን ውስጥ የምትገባ እንደሆንክ አረጋግጥ:: ሁለተኛው ሃያ አምስት እጅ ደግሞ አንተን ለማስደሰት የምትጥር፤ አንተም እሷን ለማስደሰት ለመጣር ዝግጁ እንደሆንክ አረጋግጥ፡፡ ባደረገችልህም የምትደሰት፤ ባደረክላት የምትረካ መሆኗንም መርምር፡፡
ሦስተኛው ሃያ አምስት እጅ ደግሞ የማትወድላት ባህሪ ቢኖራት እንኳን ችለኸው መኖር እንደምትችል፣ እሷም እንደዛ ማድረግ እንደምትችል አረጋግጥ፡፡ የመጨረሻው ሃያ አምስቱ እጅ ደግሞ ጭራሽ የማትወድላትና የማትችለው ባህሪ ሊኖራት እንደሚችልና በእሱም እየተበሳጨህ፤ ለሰባ አምስት እጁ ስትል ብቻ አብረሀት እንደምትኖር አምነህ መግባት ነው፡፡ እሷም ብትሆን ሁሉ ነገርህንና ሁሉ ባህሪህን ልትወድልህ ስለማትችል በዚህ ተስማምታ አብራህ ለመኖር መፍቀዷን አረጋግጥ፡፡ በተረፈ ግን ልጄ ደጋግሜ እንዳልኩህ እራስህን አንቃ:: ለመንቃት ደግሞ ጠይቅ፣ መርምር:: ለጥያቄና ለምርምርህ መልስ ልትፈልግ ስትሞክር ደግሞ እራስህን ማሳወቅ ትጀምራለህ፡፡››
ባህታዊው ንግግራቸውን ሲጨርሱ በእጃቸው ጀርባውን ቸብ ቸብ አደረጉት:: ሠይፈ እንባውን እንደ ምንም ውጦ ካቀረቀረበት ቀና ሲል ባህታዊው ከተቀመጡት ድንጋይ ላይ የሉም፡፡ ከተቀመጠበት ተነስቶ ቆሞ አንዴ ወደ ቤተ ክርስትያኑ ቅጥር ግቢ፣ አንዴ ወደ መንገዱ ዓይኑን ሰዶ ፈለጋቸው፡፡ ባህታዊው ግን የሉም፡፡


Read 1854 times