Saturday, 04 July 2020 00:00

የኮቪድ ነገረ - ወግ

Written by  ምዕራፍ ዳዊት (ቡቻ)
Rate this item
(0 votes)

   ይህ….
…. በመካከለኛና አንገብጋቢ ሞገድ ተቀናብሮ፣ ላለፉት ጥቂት ወራት በሚጢጢዋ አንጎሌ ‘ነገር ማብላያ’ ክፍል ውስጥ እየተዘጋጀ፤ ሲብላላና ሲበላኝ ኖሮ፣ ወደ እናንተ የተላለፈ የእኔ የጀብደኛው ድምፅ ነው፡፡ ክብራትና ክቡራን፣ እንኳን ወደ ‘ክታበ - ድምፅ’ ጀብደኛ ‘ፕሮግራሜ በግድም በውድም በሰላም መጣችሁ እያልኩ፣ ይህንን በአንገብጋቢ ሞገድ ተቃኝቶ፤  በጀብደኝነት መረጃ የደለበ ጣቢያዬን/ችሁን/ችንን ምርጫችሁ በማድረጋችሁ፣ በአብዛኞቻችሁና በራሴ ስም - ሲግጥና ሲያመነዥገኝ፣ ሲኮፈስና ሲደቁሰኝ ከርሞ ‘Shamelesly’ ‘ሼም’ ያከናነበኝን ጀብደኝነቴን ታቅፌና አንገቴን ሰብሬ ‘ክታቦ - ድምፄን’ እየከወንኩ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ። (ከመሸጋገሪያው ‘እንጉርጉሮ’ በኋላ ተመልሰን እንገኛለን - … ‘ርቀታችሁን በመጠበቅ’… አብራችሁኝ ታደሙ…)
እስቲ ይህቺን ነጥብ ላስቀድም’… (የአክብሮት ውዳሴና ምስጋናዬን ነው… ግን እንጃልኝ… ቃላትና ሀረጐቼ ላይበቁ ተኮሳምነው ‘የልቤን ሀሳብ’ ህልው መሆንን አደብዝዘው ‘ሀቄን’ እንዳያጨነግፉብኝ.. ፈራሁ!)
“... ሞቼ ብነሳና ዳግም የመኖር ዕድል ቢሰጠኝ?... በዘመነ - ካሌብ ብፈጠር ደስ ይለኛል። አይሆንም ከተባልኩ የጃንሆይን ዘመን እመርጣለሁ። እሳቸው በዘመናዊ ትምህርት ሊኮተኩቱን ደክመው ነበር። እኛ ግን ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኞቻችን ጨነገፍን።”  (መስመር - ከእኔ)
አዘውትሬ ባወድስና ለአክብሮቴም ቃል ባጣላት ለሚገባው - ለታላቁ የጥበብ ሰው፣ ጋሼ ዘነበ ወላ ምስጋና ይሁን [አሜን!] - ረጅም እድሜ ከሺ ኩንታል ጤና ጋር [አሜን!] - ከላይ ያሰፈርኳትን ቅንጭብ (ነገር ግን ትርጉመ የትየለሌ) ጽሑፍ የተዋስኩት ጋሼ ዘኔ - ለአንጋፋው ጥበበኛ ጋዜ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር መዘከሪያ ይሆነን ዘንድ ‘ማስታወሻ’ ሲል በ2009 ካሳተመልን መጽሐፍ (ገጽ - 103) ላይ ነው። ቅንጭቢቱን ሃሳብ የተናገራት ራሱ ጋሼ ስብሃት ነው።
‘ከጥቂቱ’ - እንጂ ‘ከጥቂቶቻችን’ አላለም… (አንድ - እውነት!)
‘አብዛኞቻችን ጨነገፍን’ - እንጂ - ጥቂቶቻችን ብቻ ጨነገፍን አላለም… (ብዙ እውነት!)
በጋሼ ዘንዬ በኩል የጋሼ ስብሃትን ምናባዊ ምኞት ያዙልኝና - ወዲህ ደግሞ የእኔን ስሙልኝ’ስቲ… ጎሽ አንዴ’!…
(...ክብራትና ክቡራን!! እውነት አምናችሁኝ እንዳይሆን ብቻ… ቀጥል’ ያላችሁኝ?!...) ጎበዝ! ጋሼ ስብሃት’ኮ ምኞትን ሲጀምር ‘ሰው’ ሆኖ ነው!! ሰውነቱን አገናዛቢ አንጎሉ በ“ልክነት ሚዛን” አምኖበት’ኮ ነው!! እኔ (እና አብዛኞቻችሁ) በምናብም በላብም ‘ለመመኘት’ኮ ሰው ሆኖ መገኘትን… ይጠይቃል። እኛ ግን ጨንገፈናል። ትጠራጠራላችሁ እንዴ?
(አንድ የጣቢያው ተከታታይ መስመር ላይ ገብቷል…) (…እሺ ታዳሚዬ አመሰግናለሁ) ጠያቂዬ ለተሳትፎህ - ለራስህ አጨብጭብ።
‘ቁጠር’! ነው ያለው - ተሳታፊዬ። ለመጨንገፋችን ማስረጃና እማኝ ቁጠር!
መቼ እንደምጨርሰው እርግጠኛ ባልሆንም - የ“ነገር ማብላያ” ክፍል ባልደረባዬና የእናንተን የተሳታፊዎቼን ‘ደረቅና’ - ‘ርጥብ’ ጥያቄዎች ተቀባዩ ‘ጀብደኛ’ አንጎሌ፤ የአየር ሰዓት የለም እያለኝ ነው። የመሬት ሰዓት ግን ስላለን ‘መሬት’ ላይ ያሉትን የማስረጃ ሀቆች መቁጠሬን ጠንክሬ እቀጥላለሁ -
(ክቡራትና ክቡራን - ለአረዳድ እንዲያመቸን (የጋርዮሽ አግባቦት እንዲኖረን) እናም ደግሞ ይህ ‘ጀብደኝነታችን’ ፍክትክት ብሎ ለመታየቱ ድምቀት ሲባል ወደ ጣቢያው ልመልሳችሁ) በጋሼ ስብሃት ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ ‘ጭንጋፍ’ መሰረት፣ ራሳችሁን ከ“ጥቂቱ” አሊያም ከ“አብዛኞቻችን” ቡድን ውስጥ አሰልፉልኝ። (ጥብቅ ማሳሰቢያ!! በሁለቱም ቡድን ውስጥ ‘አለሁበት’ የሚል ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን፣ አክቲቪስት፣ አክተር፣ ፓስተር፣ ማስተር፣ ፕሮፌሰርና ሌሎችም… ከምትወስዱት ክኒን በፊት በ‘አእምሮ - ልክነት’ ማረጋገጫ የማህበረሰብና አገር አቀፍ ጠቃሚነት ፈተናዎች ኤጀንሲ፣ ዜሮና ከዜሮ በታች ያገኛችሁበትን የጀብደኝነት ሰርተፊኬት እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ማስረጃዎችን እንድታቀርቡ (እዛው ለራሳችሁ!) - እኔ ወደ ቆጠራ ልግባ… (በውስጥ መስመር ተሳትፏችሁ እንደቀጠለ ስለሆነ … በርቱልኝ!)
የኮሮና (ኮቪድ - 19) በኢትዮጵያ መከሰት “አዲስ ነው” ብሎ በመቀበል የተደሰኮረ ‘ነጭ’ ሽምጠጣ!
ልዩ አጨነጋገፍ ቁጥር 1.
አንቀጽ - 0 መሬት ላይ ያለ እውነታ - ቫይረሱ ወትሮውንም ቢሆን ኢትዮጵያችን ውስጥ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ እንደገና ሌላ እውነት - የቫይረሱ የቀድሞ አቋም (መገለጫ) ቫይረሳዊ ባይሆንም የዲ.ኤንኤ’ አወቃቀሩ ብቸኛ ባለመብቶች ነን!!
አንቀጽ - 0.0  ባለመብትነት ሲብራራ…
ክብራትና ክቡራን… አሁን ‘ኮሮና - (ኮቪድ - 19) ለኛ አዲሳችን ነው’ እያላችሁኝ ነው? - ኧረ በደንብ አስቡ። መዳፋችንን በየሰዓቱ መታጠብ…. አዲሱን ቫይረስ ከመዳፍ ላይ ለማስወገድ? እርስ በርስ መራራቅ? ርቀትን መጠበቅ?!... (ወይ ነዶ!)
ወደ ቅድመ - የኮቪድ’ ትውስታችን… ልውሰዳችሁ - ቡራዩ! አምቦ! ሻሸመኔ!... የጊዜን መዘውር የኋሊት ሸጉረን... እንሂድ’ስቲ… ይሄው ራሱ መዳፋችን አይደለም እንዴ ድንጋይ፣ ቆመጥና ገጀራ ይዞ፣ የገዛ ወገንን፣ የራስ ደምን ሲያፈስስ… የራስ አካልን ሲበልት… ዘቅዝቆ ሲሰቅል… የነበረው?
ውረዱ - እንውረድ… ወደ 97ቱ ድራማ (መቁጠር አይደል የያዝነው…) የክላሽንኮቩን ሰደፍና ቃታ ወድሮ ባንጣጣው የቀትር ጥይት… ይኸው ‘መዳፍ’ አይደለም እንዴ… ስንቶቹን እናቶች… ወጣቶች… ስንትና ስንቶቹን “እኛ” ዎቻችን ያጠፋው? ወይስ ‘ባላየ ባልሰማ’ ብለን አልፈነዋል። ውረዱ ኑ ደግሞ እንውረድ ካስፈለገም - ወደ 91’ዱ - 92’ቱ ኮቪዳዊ ድራማችን…! በመሪዎቻችን የግል ጠብ አይደለም እንዴ… መቶ ስንት ሺህ ከወዲህ፣ መቶ ስንት ሺህ ደግሞ ከወዲያ ርግፍፍ - ብሎ የቀረው… በእርስ በርስ ጦርነት! (በውስጥና መስመር ቆጠራዬን ለማስተጓጎል የገባህ - የገባሽ ዲጂታል - ተሳታፊ! በሕግ አምላክ ውጣ! ውጡ!)-
ሌላ የኮቪድ ትውስታ፡-
ፀረ - አንድነት?
ፀረ - ኢትዮጵያዊነት?
እንጭጭና ከጠባብም ጥብብ ያለ - ብሄረኝነትን… ሲሰብክንና በሥጋት ወረንጦ ላይ ሰቅዞ እርስ በእርስ ሲያናክሰን የኖረ ትንፋሽ ሲያሳጣን የነበረ የ“አክ-ቲቪስት” በሉት የ“ፖለቲካ አውቃለሁ” ባዩ … ወላ ተቃዋሚ ምናምን… አንደበት  ውስጥ “ኮቪድ - በወሬና ትንኮሳ” መልክ ሲንሸራሸርብን አልኖረም ወይ?! ንገሩኛ!... ደሞ ለመቁጠር…  ኮቪድ - My people! ማራራቁ፣ እርስ በርስ ማጠራጠሩ፣ ማጨካከኑ፣ ሰላምና ደህንነት ማሳጣቱ፣ በስጋት መወጠሩ… ዛሬ አይደለም የጀመረው… በእኛ ዘንድ ኮቪድ ከቀይ ሽብር/ ነጭ ሽብር ዘመን ጀምሮ… ከዛም በፊት ሆነ አሁንም ድረስ በየፈርጅ ፈርጁ ሲበላንና ሲያመነዥገን… የኖረ ተውሳካችን ነው!
ይልቅዬ ልንገራችሁ… አዲስ ከተባለ አዲሱን አብሬ ልቁጠርላችሁ… ያዙ!... በኮሶ ትል፣ አሜባ፣ ወስፋትና ሌሎች ከንጽህና ጉድለት (በተለይ በተለይ እጅን በወጉ ካለመታጠብ) ነግሰውብን በሽምቅ  ሲዋጉን የኖሩ የሆድ ተውሳኮቻችን አያሌ ነበሩ። … እድሜ ለ‘ቫይረሳዊው ኮቪድ’... እጅ መታጠብን ‘ሰጥ ለጥ’ አድርጎ አስተማረን!!
በእርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጅ መታጠብ ልማዱ ላይ ያሳየነው ቸልተኝት ለተውሳኮቹ ሰርግና ምላሽ እንደሆነላቸው አልጠራጠርም…ቆጠራውን ብቀጥል በወደድኩ… መጨረሻዬን አላገኘውም’ንጂ… ቢሆንም - ቢሆንም የአብዛኞቻችን ጭንጋፍ ማንነት ዛሬ ላይ የት  እንደደረሰና በእርግጥም የጀብደኝነታችን ማዳመቂያ ማህተም ሳልረግጠው ብቀር ለጣቢያውም ‘ሼም - ይሆናል?! - እኛን እና ድፍን ዓለሙን እንደ ክረምት እሸት ኮቪዳዊ መርገምት እየቀቀለ እየቆላን ሳለ፣ የፖለቲካ ካቲካላ ያሰከራቸው የኛው ዘር ማንዘሮች… የ‘ምርጫ ይደረግ!- ካልተደረገ አስረሽ - ምቺው አይቀሬ ነው’ እያሉን ነው - ‘ሼምለሶች’...! ምርጫ ለማካሄድና ለመምረጥ እኮ ለመመረጥም ቢሆን የሕዝብ ድምፅ ያስፈልጋል’ኮ! በተለይ በተለይ  ተመራጭ ሆኖ ለመወዳደር ትልም ላለው ወገን በመጀመሪያ ‘ሰው’ ያስፈልገዋል - ህዝብ! ከአገርና ህዝብ ጥቅም በፊት ለሥልጣን ጥመኝነት ቅድምያ መስጠት ሌላው የኮቪድ ቫይረሳዊ መገለጫ መሆኑ መቼም አይጠፋችሁም፡፡
ፕሮግራማችንን ከማጠቃለላችን በፊት ለምስኪኗ አገሬ… ለትጉህና ቅን አሳቢ (እናም ተባባሪ) መሪዎቻችን፣ እንደ ጋሞና አባ ገዳ አባቶች ላሉ ጥቂቶችም ‘ኢትዮጵያ’ የሚለውን የቴዲ አፍሮ ዘፈን በውስጥ መስመር፤ ለተቀረነው ደግሞ በውጭም በውስጥም መስመር እለቃለሁ። የ‘አብዛኞቻችን ጨነገፍን’ ውስጠ ወይራ ቅንጭብ  እሳቤን፣ አብዛኞቻችን ‘ሚጢጢም ብትሆን ባለችን አንጎል አብላልተን አላምጠን፣ የጋሼ ስብሃት ‘ሞቼ ብነሳ…’ ምኞትን በከንቱነት ከመሞታችን በፊት ለራሳችን አትርፈን፣ ለትውልድ እንደ ታሪክ የምንከትበው ‘ተግባረ - ክንድ ወ አንድነት’ የተሰኘ ጥዑም ትርክት እንዲኖረን ከ‘ጥቂቶች’ እንማር፡፡
የ‘ነባሩ ኮቪዳዊ’ አካሄድና አሰራር ተሽንቀጥሮ መተቃቀፋችን እንዲሰፋልን… የማራራቅና - መራራቅ አይዲዮሎጂ ከፋፋይና አናካሽ የሆነው ጠባብ የብሄርተኝነት መንጋጋና ክራንቻ ይርገፍ! በ‘ማስክ’ የተሸፈኑ ሸንጋይ፣ አስመሳይ፣ ከንቱና ጀብደኛ አንደበቶች ተጠርቅመው ይቅሩ በዛው ልሳነ - ክፋታቸውን ዘግቶልን ያሳየን… ሌላ ምን ይባላል?! ‘ጥቂቶቹ’ በዝተው የሰላሙን አንቀፅ ያስፉልን፤ አሜን! (በውስጥ መስመር አንድ ታዳሚ ገብቷል… ወጥቼ ላናግረው’ስቲ…)
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኖራለች!!
(በውድም - በግድም!!)


Read 582 times