Saturday, 04 July 2020 00:00

ታላቁ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (PhD)
Rate this item
(0 votes)

 የኢትዮጵያ የክፉ ጊዜ ወዳጅ - ሩሲያዊያን!
                            


              ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ
በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ከነበራቸው የአውሮጳ አገሮች ውስጥ አንደኛዋ ሩሲያ ናች፡፡ ለዚህም  ሁለት ዋና ምክንያቶችን ለመጥቀስ ይቻላል:: አንደኛው፤ ሩሲያ በአፍሪካ ቅኝ ግዛት የሌላት ሀገር በመሆኗ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ሩሲያ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታይና የታላቁ ኢትዮ-ሩሲያዊው ባለቅኔ የአሌክሳንደር ፑሽኪን ቅድመ አያቶች ሀገር በመሆኗ ነው፡፡ በተጨማሪም እንደነ አሌክሳንደር ቡላቶቪች፤ እንደነ ፎን ሊዎንቲቭና ቱራየቭ የመሳሰሉት ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያ በሚያወጡዋቸው ጽሑፎች ሩሲያውያን ኢትዮጵያን ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራቸው ጭምር ነው፡፡ በሩሲያውያን ዘንድ ‘የከፋ መሐንዲስ’ እስከመባል የደረሰው ቡላቶቪች ከዐድዋ ጦርነት በኋላ ወደ ሀገራችን መጥቶ  የተሳተፈ፤ ራስ ወልደ ጊዮርጊስ 16 ሺህ ሠራዊት ይዘው ወደ ጂማና ወደ ሩዶልፍ ሐይቅ ወደ ቱርካናዎች ምድር ሲዘምቱ፣  አውራ መንገድ ሠሪና ቀያሽ ፎቶግራፍ አንሺና የጦሩን ዜና መዋዕል ጸሐፊ፤ተመራማሪና አሳሽ  ሆኖ ሠርቷል:: በሪፖርቱም  በሪሲያ አንባቢዎች ላይ ተጽእኖ ፈጥሯል፡፡
የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት ተሟሙቆ (ዓለማየሁ አበበ 2006፤399) የተጀመረው  ደግሞ በ1894 በኤ፡ ቪ፡ኤሊሴየቭና በኤስ ሊዎንቲቭ የተመራ የሩሲያ ሳይንሳዊ ቡድን ወደ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት ነው:: ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የወታደራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሆኖ ሠርቷል፡፡ የተጀመረውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር ሲባልም በሰኔ ወር 1895 መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሚሲዮን ወደ ፒተርስበርግ ሄደ፡፡ በዚያ ወቅት በሁለቱ ሀገሮች መኻከል የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመመሥረት ከስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ እ.ኤ.አ በግንቦት 28 ቀን 1896 ሐረር የገባው የሩሲያ የጤና ጥበቃ ቡድን፣ በዐድዋ ጦርነት ወቅት በዐድዋ ጦር ሜዳ  ጊዜያዊ ክሊኒክ በማቋቋምና የቆሰሉ ኢትዮጵያውያንን  በማከም፤ የጦር መሣሪያ ርዳታም በማድረግ ከፍ ያለ እገዛ አድርጓል፡፡ በ1897 ደግሞ በሩሲያና በኢትዮጵያ መኻከል ኦፊሴላዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተከፈተ። በየካቲት ወር 1898 ሚስተር ፒዮተር ቭላሶቭ የሩሲያ ዲፕሎማሲ ሚሲዮን መሪ ሆኖ አዲስ አበባ ገባ፡፡
ኢትዮጵያ ከብዙ የዓለም ሀገሮችና ከጎረቤቶቿ ጋር  መልካም የሆነ ግንኙነት ያላት ሉዓላዊት ሀገር ናት። በተለይም የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል ከሆነች በኋላ ከብዙ ሀገሮች ጋር  የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመፍጠር፣ የዜጎቿን ጥቅም ስታስከብር ቆይታለች። ይህም ሲባል የዓለም መንግሥታትን ሕግ በመጻረር በደል የፈጸሙባት ሀገሮች የሉም ማለት አይደለም። በኢትዮጵያ የጥንት ዘመን ታሪክ፣ ደመኛ ጠላቶቿ ተብለው ከሚታወቁት ቱርኮች፣ ግብጾችና ደርቡሾች በበለጠ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ኢጣልያ ያደረሰችባትን በደል የሚያህል ያደረሰባት ሀገር  በታሪኳ ይኖራል ብሎ  መገመት ያስቸግራል።
ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም በኃይልና በግፍ በወረረችበት ዘመን፣ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙና በተጻራሪው ኢጣልያንን የደገፉ ሀገሮች ነበሩ። በዚያ የመከራ ዘመን የኢትዮጵያ ችግር በዓለም መንግሥታት ማኅበር /በሊግ ኦፍ ኔሽን/ ሲመረመር፣ የሶቭየት ኅብረት ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያን  ደግፎ፣ የኢጣሊያን  ወራሪነት ነቅፎ ታላቅ ወዳጅነቱን አስመስክሯል። እ.ኤ.አ የካቲት 4 ቀን 1936 በታላቁ የኢትዮጵያ ወዳጅ በሚካኤል ካሌኒን ስም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጻፉት ደብዳቤ፤ “ኢትዮጵያ የጠላቷን ወረራ ለማክሸፍ በምትከላከልበት በአሁኑ ሰዓት ሶቭየት ኅብረት እኛን ደግፋ ከጎናችን ስለተሠለፈች፣ ለእውነትና ለነጻነት ለቆሙት ለሚካኤል ካሌኒን ጤንነትን፣ ለሶቭየት ሶሻያሊስት ሪፐብሊኮች ደግሞ ብልጽግናን እንመኛለን።’’ ብለዋል። በወቅቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደብዳቤ በክሬምሊን ቤተ መንግሥት ተቀባይነትን ከማግኘቱ ባሻገር የዲፕሎማሲና የሞራል ድጋፍ ለኢትዮጵያ አስገኝቶላታል። የሶቭየት ኅብረት መንግሥትም በኢጣሊያ ፋሽስት የወረራ ዘመን  ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆም ምክንያት ሆኗል።      

የሶቪየት ሪፐብሊኮች መሪና የኢትዮጵያ ወዳጅ የነበሩት ሚካኤል ካሌኒን
እ.ኤ.አ በ1935 ዓ.ም  በዓለም መንግሥታት ማኅበር ስለ ኢትዮጵያና ኢጣሊያ  ቅራኔ ጥያቄ ተነሥቶ በነበረት ወቅት ሶቭየት ኅብረት በወሳኝነት ኢትዮጵያን በመደገፍና ሁኔታውን ለዓለም መንግሥታት ማኅበር በማስረዳት ወረራውን ተቃወመች። “በተባበሩት መንግሥታት ማኅበር ሕግ መሠረት የአባል ሀገሮች ሉዓላዊነትና ነጻነት ፈጽሞ በጉልበት መደፈር የለበትም” ስትልም ተናገረች። በዚያ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሽዝምን ወረራ በመቃወምና በየጦር ግንባሩ በመዋደቅ ላይ እንደሚገኝም አሳሰበች። እ.ኤ.አ መስከረም 1935 ዓ.ም ጀኔቭ ውስጥ  የዓለም መንግሥታት ማኅበር ምክር ቤት በዋነኛነት የኢትዮጵያንና የኢጣልያን ግጭት ለመፍታት ተሰባሰበ። ውይይቱን በንግግር የከፈቱት ፀረ ኢጣልያ አቋም የነበራቸው የታላቋ ብሪታንያ ተወካይ ኤይዴን ናቸው። ኤይዴን ሁለቱ ኃያላን መንግሥታት እንግሊዝና ፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ባደረጉት ስብሰባ፣ የኢትዮጵያን ግዛት በተመለከተ ኢጣልያ ስምምነት ላይ እንድትደርስ የተነጋገሩበትን በመረጃ መልክ በስብሰባው ላይ አቀረቡ።
“እኔ በአሁኑ ሰዓት ሁለቱም ሀገሮች በተሳካ ሁኔታ ግጭታቸውን ይፈታሉ ብዬ አምናለሁ’’ ሲሉም ተደመጡ። ሌሎች መልእክተኞች፤ ከተናገሩት ንግግር በመነሣትም አሊዩዚ የተባለው የኢጣልያ መንግሥት መልእክተኛ “ተናጋሪው ስለ ኢትዮጵያ የተናገረው በግልጽና በድፍረት ነው’’ ካለ በኋላ “መላው የኢጣሊያ ሕዝብ ኢትዮጵያ ከዓለም መንግሥታት ማኅበር እንድትወገድ ይፈልጋል። ስለዚህ ለኢትዮጵያ የኢጣልያ የበላይነትና ሞግዚትነት ያስፈልጋታል፡፡ መስፋፋትና በአካባቢው በሞግዚትነት መቆምም ይገባታል። ታሪክ እንደሚያስረዳው  የኢጣልያ ዋነኛ  ዓላማ፤ ለሁልጊዜም ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ለማድረግና ሕዝቧንም ለመደገፍ ነው። አንድ ወቅት የቀረበ አንድ ጥናት አንብቤ እንደተረዳሁት፤ ኢትዮጵያ የሰውን ልጅ ነፃነት የማታከብርና ሰውን እንደ ባሪያ የምትሸጥና የባሪያ ንግድ የምታራምድ ሀገር ናት። ከዚህም የተነሣ ይች ሀገር የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል መሆን የለባትም። ስለሆነም ይህንን ጭካኔ የተመላበትን የኢትዮጵያ ውስጣዊ ፖለቲካ ለማጥፋት ኢጣልያ ታሪካዊ ግዴታ አለባት። በአፍሪካ ምድር በቁጥጥርዋ ሥር የሚገኙ ሕዝቦችዋን መብት የማስከበርና ለዚህም ሲባል ርምጃ የመውሰድ ታሪካዊ ኃላፊነነት በኢጣሊያ ላይ ተጥሎባታል።” ሲል ተደመጠ፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 5 ቀን 1935 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጥያቄ ላይ ቀጣዩ ስብሰባ ተደረገ። በስብሰባው ላይ ንግግር ያደረጉት የሶቭየት ኅብረት መልእክተኛ ማክሲም ሊትቪኖቭ ናቸው። ሊትቪኖቭ በወሳኝነት ኢትዮጵያን ደግፈው ንግግር አሰሙ-
“‘የሶቭየት ኅብረት መንግሥት የኮሎኒያሊዝምን ሥርዓት አጥብቆ ይቃወማል። ፖለቲካውንም፣  ሞግዚትነቱንም አይቀበልም። በዚህ ዓይነት መንገድ  እኔ የኢምፔሪያሊዝምን ዓላማ አወግዛለሁ። ይህንን እንደ መፈከር አንሥቶ ከሚሯሯጠው የኢጣሊያ መንግሥት ጋርም አልስማማም። ይህ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር የሚሰጠው ጥቅም የለም። ድርጊቱ በአባል ሀገሮች መካከል ልዩነትን ይፈጥራል፣ ነጻነታቸውን፣ የውስጥ አስተዳደር ሥርዓታቸውን ይዳፈራል። ይህንን የምንወስነው በቆዳችን ቀለም ምልክትነት ነው? ወይንስ በሥልጣኔ ደረጃ? ያም ሆነ ይህ ለኢትዮጵያውያን ታላቁ ክብራቸውና መብታቸው የመንግሥታቱ ማኅበር አባል  እስከሆኑ ድረስ በቀዳሚነት ግዛታቸውን መጠበቅና ነጻነታቸውን ማስከበር ነው።” አሉ፡፡ ንግግራቸውን በማራዘምም “እኔ እንደማስበው፤ ሌሎች ሀገሮችን በአባልነት ከተቀበልናቸው  በውስጥ ጉዳያቸው ጣልቃ መግባት  የለብንም። ስለ ሥልጣኔ የምናስብ ከሆነ በጥቂቱም ቢሆን ስለ ጦርነት ማሰብ ይኖርብናል። ከአንድ ዓመት በፊት መንግሥታት ሁሉ ስለ መንግሥታት ማኅበር አንድነት፣ ስለ ሰላም  ወዳድነት፣ ዓለምን ለመጠበቅ ሌሎች ሕዝቦች ስለሚያደርጉት አስተዋጽኦ ሲያወሩና ሲናገሩ ነበር፤ ግን በተግባር ይህንን ሲያደርጉ አይታዩም’’ ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ህልውና እጅግ በጣም ጠቃሚ በሆነው በዚያ ወቅት ሶቭየት ኅብረት በርቀት ላይ ከምትገኘው  አፍሪካዊት ሀገር ጎን ተሰልፋ የዲፕሎማሲ ትግል አካሂዳለች።
                  
ማክሲም ሊትቪኖቭ
እ.ኤ.አ መስከረም 6 ቀን 1935 ዓ.ም “አምስተኛው ኮሚቴ’’ በሚል ስብሰባ ተሰየመ። በስብስቡ ውስጥ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የፊንላንድ፤ የእስፓኝና የሌሎች ሀገሮች መልእክተኞች ነበሩበት። የኮሚቴው አባላት ከኢትዮጵያና ከኢጣልያ ጋር ያለውን ቅራኔ ለማርገብ የሚያስችል  ፕሮጀክት ቀርጸው አቀረቡ። እ.ኤ.አ መስከረም 18 ቀን 1935 ዓ.ም  አምስተኛው ኮሚቴ ሥራውን አጠናቅቆ ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር ለማኅበሩ፣ ለኢጣልያና ለኢትዮጵያ መልእክተኞች አቀረበ። የመፍትሔ ሐሳቡም “የኢትዮጵያ ነጻነት መከበር አለበት” የሚል ነው። የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ “የዓለም አቀፍ ቁጥጥር በኢትዮጵያ ላይ እንዲደረግና የሀገሪቱ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቷንም እንድታሳድግ አስፈላጊውን ማድረግ አለበት። በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፉን ግንኙነት መሠረት አድርጎ፣ ጎረቤቶቹን መደገፍ ይኖርበታል” የሚል ነው። በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ግዛት የተወሰነው ለኢጣልያ ይሰጥ የሚል ሐሳብ ቀርቦ የኢጣሊያ መንግሥት በእጅጉ ተቀይሞና ተቃውሞም አቅርቦ ነበር። በውሳኔው መሠረትም፤ የኢትዮጵያ ግዛት እንዲከበር ከስምምነት ላይ ተደረሰ። ኮሚቴው ግን ኢጣልያ ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ለመያዝ ከፍተኛ የሆነ ስሜት ያላት መሆኗን ተረዳ።  በመሆኑም ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን  ቀረ። ኢጣሊያ የቀረበላትን የማግባቢያ ሰነድ ተቀብላ ችግሩን በማርገብ ፋንታ ለጦርነት ትዘጋጅ ጀመር።
እ.ኤ.አ ጥቅምት 3 ቀን 1935 ዓ.ም የኢጣልያ ጦር ከሰሜን ወደ ደቡብ  የኢትዮጵያን ግዛት ሰብሮ ገባ። ጥቅምት 5 ቀን 1935 በኢትዮጵያ ጥያቄ የመንግሥታቱ ምክር ቤት ስብሰባ ተቀመጠ። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ መልእክተኛ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ንግግር አደረጉ። ተክለ ሐዋርያት በንግግራቸው የመንግሥታቱን ማኅበር የተማጸኑት በማኅበሩ አንቀጽ 16 መሠረት፣ ሁሉም አባል ሀገሮች የወራሪውን ድርጊት እንዲያወግዙ በማሳሰብ ነው። ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ከአሥራ አንድ ዓመት በላይ በሩሲያ የኖሩና የተማሩ በመሆናቸው ፀረ ኮሎኒያሊዝም አቋም ከነበራት ከሶቭየት ኅብረት መልእክተኛ ከማክሲም ሊትቪኖቭ ጋር በወቅቱ በሩሲያኛ ቋንቋ በቀላሉ ስለተግባቡ እንዲሁም የታላቁና የደመ ሞቃቱ  ባለቅኔ የአሌክሳንድር ሰርጌይቪች ፑሽኪን ቅድመ አያት ሀገር ኢትዮጵያ ስለሆነች ዲፕሎማቱ በወዳጅነት ከሀገራችን ጎን እንዲቆሙ ተጨማሪ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር መገመት ይቻላል።
ከመንግሥታቱ ማኅበር አባል ሀገሮች ውስጥ የሶቭየት ኅብረት መልእክተኞች መሪ ማክሲም ሊትቪኖቭ ቁጣና ኃይል በተሞላበት ንግግራቸው፣ አባል ሀገራት በኢጣሊያ ላይ ወሳኝ የሆነ ተጽዕኖ እንዲያሣርፉ አሳሰቡ። ‘’ከፊት ለፊታችን  ጦርነት እያየን ነው። ጦርነት ብቻም ሳይሆን ራሱ የኢጣሊያ መንግሥት የሚያስተባብለውን ወረራ እየተመለከትን ነው። እንዲያውም የኢጣሊያ መንግሥት በጦርነቱ እየገፋበት ይገኛል። እና እኛ ይህንን ወረራ መቃወም የለብንም? አንቀጽ 10 እና 15 ላይ  የመንግሥታቱ ማኅበር ያጸደቀውን ሕግ መርሳት አለብን? እና ሁሉም  የምክር ቤት አባላት ሕጉን ጥሰው በተጻራሪነት መቆም አለባቸው እንዴ? አዝናለሁ’’ ብለዋል።
እ.ኤ.አ ጥቅምት 5 ቀን 1935 ዓ.ም  ምከር ቤቱ በአስቸኳይ ሌላ ኮሚቴ አቋቋመ። በኮሚቴ አባልነት የስድስት መንግሥታት መልእክተኞች ተሰየሙ። እነርሱም  የፈረንሳይ፣ የታላቋ ብሪታንያ፣ የዴንማርክ፣ የቺሊ፣ የሩማንያና የፖርቱጋል ናቸው። የኮሚቴው አባላት የኢጣልያን የጦርነት ድርጊት አስመልክተው ውሳኔ እንዲያሳልፉ ኃላፊነት ተሰጣቸው። በሚቀጥለው ቀን ስድስት አባላት  ያሉት ኮሚቴ፣  ኢጣልያ የማኅበሩን ሕገ ደንብ  የጣሰች መሆኗን የሚያመለክት ጥናት አቀረበ። እ.ኤ.አ ጥቅምት 7 ቀን 1935 ዓ.ም  የመንግሥታቱ ምክር ቤት  ለወራሪዋ ኢጣሊያ ጥሪ አቀረበ። በጊዜው ከብዙ አባል መንግሥታት ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብታ የነበረቺው ኢጣልያ፤ ለይስሙላ ያህል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደምትቀበል አስታወቀች። ከዚህ ውሳኔ ጋር በተያያዘ አባል ሀገሮች ከአንቀጽ 16 ጋር በተያያዘ ኢጣልያንን በመቃወም  የኢኮኖሚ  ማዕቀብና ሌሎች ተጨማሪ ዕገዳዎች እንዲደረግባት ውሳኔ አሳለፉ።
የመንግሥታቱ ማኅበር ከዚህ ዓላማ በመነሣት እ.ኤ.አ ጥቅምት 9 ቀን ተጨማሪ ጉባኤ ጠራ። በሚቀጥለው ማለት ጥቅምት 10  ቀን በተደረገው ስብሰባ፣ በሁሉም አባል  ሀገሮች ውሳኔ  መሠረት በኢጣሊያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ተቀባይነት አገኘ። ለዚህም ሲባል ውሳኔውን ተግባራዊ  የሚያደርግና ማዕቀቡን በኃይል ርምጃ ጭምር ሊያስከብርና ሊያስፈጽም  የሚችል አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቋመ። አስተባባሪ ኮሚቴውም በተራው “18ኛው’’ ወይንም “ዐቢዩ ኮሚቴ’’ የተሰኘ ሌላ ኮሚቴ መሠረተ።
እ.ኤ.አ ጥቅምት 19 ቀን 1935  ዓ.ም “ዐቢዩ ኮሚቴ’’ ወደ ኢጣልያ የጦር መሣሪያ እንዳይገባ፣ ማንኛውም ሀገር  የኢጣልያን ምርቶች በዱቤም (በክሬዲት) ሆነ በካሽ (በጥሬ ገንዘብ) እንዳይገዛና ወደ ሀገሩ እንዳያስገባ ለአባል ሀገሮች ሐሳብ  አቀረበ። ይሁን እንጂ ወደ ኢጣልያ የሚገቡ ምርቶችን በተመለከተ ማዕቀብ ቢጣልም፣ ጓደኛ ለጓደኛ በመረዳዳትና ማዕቀቡን በማፍረስ ኢጣልያንን  የሚደግፉ አገሮች ተፈጠሩ። በመጀመሪያ ሁሉም አባል ሀገሮች ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁነቱ አልነበራቸውም። የታላቁን ኮሚቴ የመፍትሔ ሐሳብ  ተግባራዊ  ለማድረግ ማክሲዝም ሊትቪኖቭ፣ የመንግሥታቱ አባል ሀገሮች በአንድነት ሆነው እንዲሠሩ አሳሰቡ፡፡
የሶቭየት ኅብረት  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማክሲም ሊትቪኖቭ፣ በጉባኤው ላይ ኢጣልያንን አስመልክተው ሲናገሩ፤ “የእኔ አገር መንግሥት ከኢጣሊያ ጋር ምንም ዓይነት ጠብ የለውም። ወደ ኢጣልያም በጠላትነት ለመቅረብ አይሞክርም። በዚህ ግጭት ምንም ዓይነት የግል ፍላጐት እንደሌለውም አውቃለሁ። ይልቁንም የሶቭየት መንግሥት የሚገነዘበው ኢጣሊያ የሶቭየት ኅብረትን ምርት ከሚገዙ ሀገሮች አንዷና ዋነኛዋ መሆንዋን ነው። እኔም የምረዳው፤ የእኔ አገር መንግሥት ከእርስዋ ጋር ፈጣን የሆነ ሚዛናዊ የምርት ልውውጥ በማድረግ ላይ ያለ መሆኑን ነው። ማዕቀቡ ተግባራዊ ሲሆን ከኢጣልያ ጋር ያለን ግንኙነት በእርግጥም ይሻክራል። በሶቭየት ኅብረት ረገድም ብዙ የማቴሪያል ጉዳት ሊደርስ ይችላል። እኛ ይህ የማቴሪያል ጥፋት እንዳይመጣ ከተስማማን፣ እኛው ራሳችን ችግሩን በኃይልም ቢሆን ማስወገድ ይኖርብናል። ይህም  በዓለም  አቀፍ የስምምነት ኃይል፣ በዓለም ፍላጐትና በሁሉም ሕዝቦች ነጻነት አማካይነት ግጭቱን የመፍታት ግዴታ አለብን ማለቴ ነው። ነገር ግን ይህ ግዴታ ለሁሉም አባል ሀገሮች አንድ ዓይነት መሆን አለበት። ይህ ካልሆነ ዓለማቀፋዊ ግዴታ አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም” ብለዋል።
እ.ኤ.አ ኅዳር 2 ቀን 1935 ዓ.ም  “ዐቢዩ ኮሚቴ” ፀረ ኢጣልያ የሆነው ማዕቀብ በኃይል ጭምር ተግባራዊ እንዲሆን ወሰነ። ከማኅበሩ አባል ሀገሮች ከሠላሳ ዘጠኝ በላይ የሆኑት /መንግሥታት/ በኢጣልያ ላይ የፋይናንስ ርምጃ /ማዕቀብ/ እንዲወሰድባት መመሪያ አወጡ። በተለይ አሥር ሀገሮች እንደዚህ ዓይነቱ ርምጃ በኢጣልያ ላይ በመውሰዱ ስምምነታቸውን ገለጹ። ነገር ግን አውስትሪያ፤ ሐንጋሪና አልባኒያ በኢጣሊያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ተቃወሙት።
ሁኔታው በጥሞና ሲታይ ግን የመንግሥታቱ ማኅበር የደገፈው ወራሪውን የኢጣሊያ መንግሥት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣል  ለኢጣሊያ የጦር ስትራቴጂ ምንም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ማዕቀቡ  የነዳጅ ሁኔታንም አልተመለከተም። በተጻራሪው የመንግሥታቱ ማኅበር ምክር ቤት ኢትዮጵያን ለማገዝ ምንም ያደረገው ነገር የለም። ዐቢዩ ኮሚቴ የሚባለው የሰጠውን ማሳሰቢያ እያንዳንዱ መንግሥት በመሰለው ይተረጉመው ጀመር። የአሜሪካ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያና ኢጣሊያ የጦር መሣሪያ እንዳይገባ ከለከለ። በአፍሪካ የሶማሊያ ቅኝ ገዢ  የሆነችው ፈረንሳይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በወደቡ በኩል የጦር መሣሪያ እንዳያስገባና ወታደሮቹንም በድንበሩ አካባቢ እንዳያሠማራ አጥብቃ ከለከለች። ይልቁንም የፈረንሳይ ሶማሊያ ገዢ የሆነችው ፈረንሳይ እስከ መጨረሻ በጅቡቲ ወደብና አካባቢ ላይ ሠራዊቷን አሠፈረች። ይህንንም ያደረገችው ከጅቡቲ እስከ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ያለው የባቡር ሐዲድ በኢጣልያ ተዋጊ አውሮፕላኖች ቦምብ እንዳይመታና እንዳይፈራርስ  በሚል ሰበብ  ነው። “ለጦርነቱ ማከናወኛ እንዲሆነው በማሰብም ለኢትዮጵያ መንግሥት አሥራ አንድ  ሚሊዮን ማርክ እረዳለሁ” ብላ ቃል ገብታ የነበረችው ጀርመንም፤ ወዲያው “ገንዘቤን አልሰጥም” ብላ ሐሳቧን ቀየረች። በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ከነባራዊው ሁኔታ በመራቅ የመንግሥታቱ ማኅበር ሀገሮች እያወላወሉ፣ በኢጣሊያ ላይ መወሰድ ያለበትን ርምጃ ባለመውሰዳቸውና ውሳኔውንም ባለማክበራቸው የኢትዮጵያ ሁኔታ እየተባባሰ ሄደና ወራሪዎች በሕዝቡ ላይ እልቂት ፈጸሙ።
የመንግሥታቱ ማኅበር በኢጣሊያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥያለሁ ቢልም በኢትዮጵያ  ጦር ሜዳዎች የሚካሄደው እልቂት ሊቆም አልቻለም። እንዲያውም ማዕቀቡ የተጠበቀ ውጤት እንዳላመጣ የታወቀው ገና በመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ ነው። ተጨማሪና የማያዳግም ርምጃ በኢጣሊያ ላይ ስላልተወሰደ ነዳጅ ዘይትን ማለት ቤንዚንን ጨምሮ ወደ ኢጣልያ እንዳይገባ የተከለከለ ተጨማሪ ሸቀጥ ሆኑ በብዛት ወደ ኢጣልያ ይጎርፍ ጀመር። የኢጣልያ መንግሥት የማኅበሩ አባል ሀገሮች ከአልሆኑ መንግሥታት ጋርም የንግድ ስምምነትና ልውውጥ ያደርግ ጀመር።
የመንግሥታቱ ማኅበር አባል ሀገሮች ማዕቀብ ሲጥሉ፣ የነዳጅ ዘይት ለኢጣሊያ  የሚሰጠውን ጥቅም በደንብ አውቀውታል። ለማዕቀቡ ግንባር ቀደም ደጋፊ የነበሩት የእንግሊዙ መልእክተኛ ኤይዴይን ናቸው። ምክንያቱም ኤይዴይን የኢጣልያን የኢኮኖሚ ፖለቲካ አካሄድ ቢቃወሙ፣  አገራቸው ታላቋ ብሪታንያ በምሥራቁ የአፍሪካ ቀንድ ያላትን ይዞታ አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ሥጋት ስለነበራቸው ነው። ከመንግሥታቱ ማኅበር አባል ሀገሮች መካከል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ደግፋ በወሳኝነት የቆመችው ሶቭየት ኅብረት ብቻ ናት። ሶቭየት ኅብረት  የመንግሥታቱ ማኅበር ፋሽስት ኢጣልያን በመቃወም ያወጣው መመሪያ እንዲከበር ትግሏን ቀጠለች። የዲፕሎማሲ ትግሏን በመቀጠልም ለወራሪ የሚውለው ነዳጅ ዘይት ወደ ኢጣልያ እንዳይገባ ለአስተባባሪ ኮሚቴው አሳሰበች።
እ.ኤ.አ ታኅሣሥ 6 ቀን 1935 ዓ.ም የቀረበውን የሶቭየት ኅብረት ማሳሰቢያ የማኅበሩ አባል ከሆኑት ውስጥ የዐሥር ሀገር መንግሥታት ተቀብለውታል። ከሀገሮች ውስጥም ሩማኒያ፤ ኢራቅና ሆላንድ ይገኙበታል። ይህም ኢጣልያ 74.5% የሆነ ነዳጅ እንዳታስገባ ያደረገ ነው። ነገር ግን የማኅበሩ አባል ሀገሮች አንድ አልነበሩም። በዚህም ምክንያት በኢጣልያ ላይ  የተጣለው የነዳጅ ማዕቀብ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። ስለ ነዳጅ የተጣለው ማዕቀብ ጥያቄ አስቸጋሪ ነበር። በመጨረሻ ይህ ማዕቀብ የተጣለው በፀረ ኢጣልያ አቋም የተጨበጠ ውጤት ያስገኛል ተብሎ ነበር።
በዚያ ወቅት በእንግሊዝ የፓርላማ ምርጫ በመካሄድ ላይ ነበር። በምርጫው  ወግ አጥባቂው (ኮንሰርቫቲቭ) ፓርቲ አሸነፈ። ምርጫው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን የሆርን ፖሊሲ አጠናከረው። ሁኔታው ለሆርን መልካም አጋጣሚ ነበር። ኢጣልያንን እንዲደግፉና ወዳጅነታቸውን እንዲያጠናክሩ ረድቷቸዋል። ከዚህም በመነሣት የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ዘዴና ተግባራዊ ዕቅድ  ሊኖር ይችላል በሚል እ.ኤ.አ ታኅሣሥ 8 ቀን 1935 ዓ.ም ፓሪስ ከተማ ከፈረንሳይ ጠቅላይ  ሚኒስትር ጋር ውይይት አደረጉ። ከወይይቱ በኋላ ሁለት ሚኒስትሮች “የሆርና የላቫሊያ እቅድ’’ ወይንም “ሰላም  የሚያሰፍነው ፕሮጀክት’’ የሚል የጋራ መርሐ ግብር አጸደቁ። በዚህ መርሐ ግብር መሠረት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢጣሊያን የግዛት ጥያቄ እንዲቀበሉና ተግባራዊም እንዲያደርጉ ታዘዙ።
ኢትዮጵያ በግዴታ እንድትቀበለው በወጣው መርሐ ግብር መሠረት፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተወረርን፤ ተደፈርን የሚል የግዛትና የወሰን ጥያቄያቸውን ትተው የኢጣሊያ አማካሪዎችን እንዲያገለግሉ፤ ኢጣልያም የኢኮኖሚውን የበላይነት ይዛ ኢትዮጵያን እንድትቆጣጠር ትእዛዝ ወጣ። የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ግዛት ደግሞ በመንግሥታቱ ማኅበር ምክር ቤት ቁጥጥር ሥር እንዲውልና ተወካዮቹም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኢጣልያ እንዲሆኑ ሁለቱ ሚኒስትሮች ከስምምነት ላይ ደረሱ። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ግን ይህንን ዕቅድ ፈጽሞ  ውድቅ አደረገው። ምክንያቱም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ወደፊት የወራሪዎችን ግፍ እንድትቀበልና የሕዝብ እልቂት እንዲፈጠር የሚያደርግ ስለነበር ነው። ከግማሽ በላይ የሆነውን ግዛቷን “ለወራሪዎች ስጡ” መባሉም ወደፊት መላዋን ኢትዮጵያን ኢጣልያ እንድትቆጣጠር የሚፈቅድ ነበር። በዚያ ወቅት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመንግሥታቱ ማኅበር ተገኝተው ሲናገሩ፤ “ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የምናደርገው ጥረት አይለወጥም። በእንግሊዝና በፈረንሳይ የተወሰነብን ውሳኔ ግን ሕዝባችንን የሚጠቅም መሆን ነበረበት። የመንግሥታቱ ማኅበርና ሌሎች መንግሥታት ለእኛ የሚሰጡን የጋራ ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ተስፋ ነው።’’ ብለዋል።
በመንግሥታቱ ማኅበር “የሆርና የላቫሊ’’ ዕቅድ በሚገመገምበት ወቅት የሶቭየት ኅብረት መልእክተኛ ዕቅዱን ፈጽሞ ውድቅ አድርገው ተናገሩ።’’ …የሆርና የላቫሊ ሐሳብ  አቢሲንያን የሚከፋፍልና የግዛት ነጻነቷንም የሚደመስስ ነው። ይህ እርስ በርሱ የሚቃረን ምክር ስለሆነ ፍሬ ቢስ ነው። ማኅበሩ ለሁሉም አባል ሀገሮች አለኝታና የሉዓላዊነታቸውና የነጻነታቸው መከታ ነው እየተባለ በስሙ ቅራኔ ሲፈጠር ለግጭቱ ማርገቢያ የተጣለውን ማዕቀብም ማክበር ይገባው ነበር። እስካሁን ሰዓት ድረስ አቢሲንያ የላቫሊን፤ የሆርንና የማኅበሩን አስተሳሰብ ተቀበልኩ አላለችም። በማንኛውም መለኪያ ማኅበሩ ርምጃ አልወሰደም። እኛ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ግፈኝነትን ከመቃወምና ጦርትነትም እንዲቆም ከመታገል ወደ ኋላ ማለት የለብንም። በማኅበሩ ስምም ይህ መካሄድ የለበትም። እንደ እውነቱ ከሆነ ፈረንሳይና እንግሊዝ ለኢጣልያ ጎረቤቶች ናቸው። እና በአቢሲንያ ላይ የተለየ ፍላጐት ያደረባቸው በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነታቸው ብቻም አይደለም። ንጉሡን /ኃይለ ሥላሴን/ ላለማየት ወስነውና ጠልተዋቸው ከሆነ እኛ በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ወደ ኋላ አንመለስም። የመንግሥታቱ ማኅበር  በሁለቱም ወገን ቅራኔ የሚያባብሰውን ስምምነት መቃወም አለበት። ነባራዊ ሁኔታውን ከመተንተን መሸሽ የለብንም። በማኅበሩ ውስጥ አቢሲኒያን የሚከፋፍል ሐሳብ ሲቀርብ እያየን ዝም ማለት አይገባንም። ይልቁንም በወሳኝነት ይህንን ግፍ መቃወም አለብን። ምክር ቤቱ የአቢሲኒያን ሁኔታ ተመልክቶ ለመወሰን ያልቻለ መሆኑን ማወቅ አለበት::...’’ ብለዋል ሊትቪኖቭ።                        
በመንግሥታቱ ማኅበር ኢትዮጵያን ደግፈው ለነጻነቷ የተከራከሩላት
የሶብየት ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማክሲም ሊትቪኖቭ
እ.ኤ.አ ግንቦት 5 ቀን 1936 ዓ.ም ኢጣልያ የኢትዮጵያን ዋና ከተማ አዲስ አበባን ተቆጣጠረች። ኢጣልያ ኢትዮጵያን እንደተቆጣጠረች ለዓለም አሳወቀች። እ.ኤ.አ በ1936 መጨረሻ ጀርመን፣ አልባኒያ፣ አውስትሪያና ሐንጋሪ፣ እ.ኤ.አ በ1937 ጃፓን፣ እ.ኤ.አ በ1938 እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ቱርክና ሌሎች ሀገሮች ኢጣልያ ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ መያዟ ትክክል ነው ብለው እውቅና ሰጡዋት። ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በግፍና በወረራ በያዘችበት ወቅት እውቅና ካልሰጧት ጥቂት ሀገሮች ውስጥ ሶቭየት ኅብረት ስትሆን እንዲያውም ከተወረረችበት ጊዜ ጀምሮ  ኢትዮጵያን ደግፋ የነጻነት ጦርነት እንዲካሄድ አሳሰበች። እ.ኤ.አ ሰኔ 1ቀን 1936 ዓ.ም በመንግሥታቱ ማኅበር ስብሰባ ላይ የሶቭየት ኅብረት መልእክተኞች ኃላፊ፣ የወረራው ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ለማዳንና ውጤት ለማምጣት የሚቻለው ፀረ ወራሪ አቋም ይዞ በመታገል ብቻ  መሆኑን አስረዱ።
በ101ኛው የመንግሥታቱ ማኅበር ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አሳዛኙ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሙሉ ንግግር ከተሰማ በኋላ ማክሲም ሊትቪኖቭ ኢትዮጵያን በመከላከል ረገድ ታላቅ ንግግር አደረጉ። የሶቭየት መልእክተኞች ኃላፊ በወሳኝነት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ይዛለች የሚለውን እውቀና እንደማይቀበሉትም አስታወቁ። በዚህ አጋጣሚ በወረራው ምክንያት መሥዋዕት የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ እንዳለ ወራሪው  በጭካኔ የተሞላ የኃይል ርምጃ  ሲወስድ እውቅና መስጠት እንደማይገባ፣ ይልቁንም በወራሪው ኃይል  እየተመታ የሚያልቀውን፣ ሞራሉ ወድቆ የሚሠቃየውን ሕዝብ በማሰብ ይህን ዓይነቱን የፖለቲካ ስልት መቃወም የማኅበሩ ዋነኛ ዓላማ እንደሆነ አስገነዘቡ። የኢትዮጵያን ሕዝብ በመደገፍ ረገድ ሶቭየት ኅብረት በመከራ ዘመኗ ያሳየችው አቋም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ግምት አስገኝቶላታል። እ.ኤ.አ ሐምሌ 1944 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጋዜጣ “ኢትዮጵያን ሔራልድ” ሲጽፍ፤ “ሩሲያውያን የተመሰገኑና የተከበሩ፣ እንደ እውነተኛ የልብ ጓደኛም የሚታዩ ሕዝቦች ናቸው። በኢትዮጵያና በሶቭየት ኅብረት መካከል የዲፕሎማሲ ግንኙነት ባይኖርም በተባበሩት መንግሥታት ማኅበር ሶቭየት ኅብረት እስከ መጨረሻ የኢትዮጵያውያንን ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ወደ ኋላ ያላለች መሆኗን ሀገራችን ታስታውሳለች። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እ.ኤ.አ ሐምሌ 30 1959 ዓ.ም በክሬምሊን ቤተ መንግሥት በተካሄደ የቁርስ ግብዣ ላይ ሲናገሩ፤ “የኢምፔሪያሊስቶች ኃይል ነጻነታችንን ለማጥፋት በተንቀሳቀሰበት ወቅት በወሳኝነት የረዱን የሶቭየት ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የልዑካኑ መሪ ማክሲም ሊትቪኖቭ ናቸው። ያሉትም ከዚሁ የተነሣ ነው።...’’ ብሏል።
ወዳጄ ንጉሤ ካሣዬ ወ/ሚካኤል (ፕሮፌሰር) “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖለቲካ’’ በሚል በሩሲያኛ ያሳተመው መጽሐፍ ላይ እንደገለጸው፤ የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረትም ሆነች የአሁኗ ሩሲያ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ  ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት መሆኗን  ያስረዳል፡፡
በዚህ ረገድ በአሁኑ ጊዜም በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ወንጠለቅ ሆነው በሕገ ወጥነት  ከግብጽ ጋር የሚያቸፈችፉ ሀገሮች መጨረሻቸው እንደ ኢጣሊያ የሐፍረት አጥላስ መከናነብ ነው፡፡Read 487 times