Print this page
Saturday, 04 July 2020 00:00

“ሆድ የባሰው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ …የሰሞኑ ዝናብ አንዴት ነው? ክረምትዬው ቀድሞ መግባቱ ነው እንዴ! አንድ የሆነ ፌዘኛ ወዳጅ ነበረን… አሁን መዓት ወንዝ ተሻግሮ የሚወደው ጨጨብሳ የሌለበት አገር ነው፡፡ ስለክረምት ሲወራ ምን ይል ነበር መሰላችሁ? “የአፍሪካ ኑሮ ዘላለም ክረምት ነው…” ሳሊም ነው ማነው የሚሏቸው ሰውዬ እንዳይሰሙኝ እንጂ እኔም አንዳንዴ የደብረ ብርሃን ውርጭ ሳይሆን የሳይቤርያ በረዶ ይመስለኛል፡፡ [ቺስታነት ፈላስፋ እንደሚያደርግ እኔ ምስክር ነኝ…]
እኔ የምለው…በበጋ ባህርያችን እንዲህ ጥምም ያለ በክረምት እንዴት ልንሆን ነው? ነገራችን ሁሉ እኮ አልጨበጥ ብሏል። በቃ ሰው አንድ ነገር ሲናገር ደግ መመለስ ቀረ! ምነውሳ ሁላችን ሆድ ባሰን? [ጥያቄ አለኝ… ሰው ሆድ ሲብስው እንዴት ነው የሚያደርገው?
አንድ ጊዜ ያልለመደበትን “ደብል ደብሉን” ላይ በላይ ሲከለብስ ያገኘሁት ወዳጄን ምን እንደሆነ ብጠይቀው... ምን አለኝ መሰላችሁ?
“ሆድ ብሶኝ ነው”
“ምን ሆነህ?”
“በቃ… እንዲሁ ሆድ ባሰኝ።”
ህዝቤ ደብል ደብል የሚልፈው… ሆድ እየባሰው ነው ለካ! ከአብሮ አደግህ አትሰደድ ነው። ይሄኔ እንትና “ይሉሽን አልሰማሽ…” ሳይለኝ አይቀርም።]
በቀደም ዕለት የፈረደበት ሚኒ ባስ ላይ ተሳፍሬላችኋለሁ። [ይሄ…. ቶምቦላ ደርሶኝ ‘ቀኑብሽ’ ነገር ካልሸለሙኝ በቀር ይኸው በየጊዜው በተለያየ ስም የሚጠራ ጫማ እየጨረስኩ ወጪውም አልተቻለም። አንዳንዴማ… በቃ የሆነ ደንና ዱር አራዊት ተንከባካቢ ነገር የሆንኩ ይመስለኛል።]
እናላችሁ… የሆነ ፈርጣማ ዘናጭ ብር ከፍሎ ኖሮ አምስቱ ሳንቲም መልሱን ይጠይቃል። ወያላ ሆዬ ደግሞ “ቆይ ሳንቲም ልዘርዝር” ይላል። ዘናጭ ይናደድላችኋል።
“አምጣ!... አጭበርባሪ!” ሲል ይጮሀል። ወያላ ሆዬ ተናደደቻ።
“አይ… ስነ ሥርዓት ያዝ” ማለት።
“የምን አባክ ስነ ሥርዓት ታውቃለህና ነው…” አለ ዘናጭ። ወያላ… የሆነች ስንዝሮ ነገር የምትመስል ስድቡን አዥጎደጎደችው። ዘናጭ ይናደድና ሊማታ መጋበዝ… ወያላ በገላጋይ መሀል ተንጠራርታ አፍንጫውን ብላ አደማችው እላችኋለሁ።
ዘናጩ… አንተ ቆይ ታይሰን ነህ!... ራምቦ ነህ! ወይስ ናፖሊዮን … ነው ወይስ ሆድ ብሶሀል!
ስሙኝማ… ሆድ የባሳችሁ ዘናጮች ከወያላ አትጣሉ። [እኔ የምለው አንዳንድ ወያላዎች በ’መደበኛነት’ የተፈጠሩ ሳይሆን… በቃ የሆነ ሱማሌ ተራ ምናምን ‘ሪሳይክልድ’ የሆኑ ነው የሚመስለው።]  
እስቲ የሆነ መሥሪያ ቤት ስልክ ደውሉ… የሚያነሳው ሁሉ ቁጣ ቁጣ ይለዋልሳ! በቀደም የሆነ ወዳጄን ፈልጌ መሥሪያ ቤቱ ደወልኩ። ያነሳው ሰውዬ ገና ሳልናገር “ማነህ አንተ!” ሲል ጮኸብኝ። እኔ የምለው… እንዴት ነው ነገሩ? ማለቴ… መከባበር እኮ ‘ሊዝ’ የለው ‘ሴልስ ታክስ’ የለው ግብር የለው [መዓት ሰው እንዲሁ ሆድ የሚብሰው ገንዘብ የሚያስወጣ ነገር ሲመጣ ነው። እኔ አሁን ሽምብር በጨው ግዛልኝ ብትሉኝ ሆድ ይብሰኛል - የምር። ለቦዘና ሹሮ አንሼ ነው በሽምብራ የምገመተው!]
የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… ምን እንዳመጣው አላውቅም። የሰለቸኝ ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? … ይቺ በየስብሰባው ላይ ያለች ጭብጫቦ። [አሁን አሁንማ በቴሌቪዥንም ተጀምሯል።] በተለይም የሆነ አለቃ ነገር ከሆነማ… አረማመዱን እየተከተለ ቦታው ደርሶ ራሱ በቃችሁ እስኪል ድረስ ይቀጥላል። [የምር ግን እኔም አንድ ቀን በቴሌቪዥን የሆነ ፕሮግራም ማቅረብ አለብኝ - የምር። እህ…. ይጨበጨብልኛላ! ደግሞ ማን ያውቃል ‘ፔን ፓል’ ይገኝ ይሆናል። ቂ… ቂ… ቂ… አሉ ጋዜጠኞች። የአንዳንድ መሥሪያ ቤት ፈታሾችን አይታችሁልኛል? በቃ እኮ ከጠቅላላ የ’ሰው ዘር’ ጋ የተጣሉ ነው የሚመስሉት። [በነገራችን ላይ አሪፍ የሆኑ ፈታሾችም በየቦታው አሉ።] እና ገና ወደ በሩ ስትጠጉ በዓይን አጠቃላይ ምርመራ ይካሄድባችኋል። … እና በቃ ማርክ ይሰጣል። በቃ… ደስ ካላለው ከመፈተሹ በፊት፤
“ወዴት ነው?” ብሎ ይጠይቃል። ልብ አድርጉልኝማ! መሥሪያ ቤቱ እኮ ማንንም ሰው በምንም ሰዓት ሊገባበት የሚችል ነው።
አንድ ጊዜ የሆንኩትን ነግሬያችኋለሁ? እዚህ አራት ኪሎ ግድም አንድ መሥሪያ ቤት እገባለሁ። ፈታሹ፤
“ወዴት ነው?” አለኝ።
በቃ በሆዴ “ይቺ ፍሬሽ ፈታሽ መሆን አለባት” አልኩና “ለሥራ ጉዳይ ነው” አልኩ። አጅሬ ሊተወኝ ነው። ግንባሩን እንደከሰከሰ፤
“የምን ሥራ?” አለኝ። እህ… ቆይ እሱ የሥራ አስኪያጅ አማካሪ ነው!... ጠቅላላ አገልግሎት ነው!... ግርም እኮ የሚል ነገር ነው።
“ለሥራ ነው” አልኩት በድጋሚ። እና ምን አለኝ መሰላችሁ?
“ሳትናዘዝ አትገባትም!”
ነገርዬው እንዴት ነው? ፈታሾቹም እንደ እኛ ሆድ ብሷቸዋል እንዴ? እኔ የምለው… እንትናም ሆድ ሲብሰው… እንትናዬም ሆድ ሲብሳት… እኛ በመሀል የሁሉ የቁጣም፣ የስድብም ካልቾ ቀማሽ ሆነን እንቅር!
ስሙኝማ … “ይሄ ሰውዬ በዝናብ ብሶት ምናምን እያለ የሚደብረን ጤናም የለው እንዴ!” ሳትሉኝ አትቀሩም። እህ… ዘንድሮ እኮ… መቼም የማይሰማ ጉድ የለም። በቃ… ወይ እኔም… ኧረ በጭራሽ… የምን ሆድ መባስ።
በቀደም አምባሳደር በር ላይ “እዩት ይሄን ጉረኛ” ያልሽኝ ልጅ… ሆድ አልባሰኝም። አሁን እስቲ የእኔ ዓይነቱ… እንዴት ነው ጉረኛ የሚሆነው! ልጄ እንኳን በሀያ ሳንቲም ማስቲካ ጉራ ተነዝቶ… ‘ጭምት’ [ቂ…ቂ…ቂ…] ተሁኖም አልተቻለ።
ብቻ… ሆድ ከሚያስብስ ነገር ይሰውራችሁ።  
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1142 times