Saturday, 04 July 2020 00:00

የጭፍንነት፣ የማገዶነትና የዘረኝነት “ሃሳቦች”፣ በራሳቸው ጠማማ መንገድ ይጓዛሉ - ወደ ጥፋት።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 • ዘረኝነትንና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን እንጂ፣ መንገዳቸውንና ውጤታቸውን መቀየር አይቻልም።
    • “ሃሳቦች”፣ የራሳቸው መንገድ አላቸው። ሃሳባችንን ሳናስተካክል፣ እንዳሻን መንገድ መምረጥና ባሰኘን ጊዜ አቅጣጫ መቀየር የምንችል ከመሰለን ወይም        ካስመሰልን፣ ሞኝነት ነው። ወይም የማሞኘት ክፋት!
                   


            ድንጋይ ላለመወርወር መምረጥ እንችላለን፡፡ ወደማዶ ከወረወርን በኋላ ግን፣ እንደ ፊኛ አየር ላይ ተንሳፍፎ እንዲቀር፣ ብን ብሎ እንዲጠፋ፣ በ “rewind” መዳፋችን ውስጥ ተመልሶ እንዲቀመጥ ማድረግ አንችልም፡፡
በጭፍን፣ ማዶ ለማዶ ድንጋይ መወራወር እንዲቆም ካልመረጥን በቀር፣ ድንጋይ አስወንጭፈን ስናበቃ፣ ከእጃችን ከወጣ በኋላ፣ መንገድ አንመርጥለትም፡፡ ሃሳቦች ሲዛመቱም እንደዚያው ናቸው።
የተሳሳተ፣ አጥፊ ወይም ክፉ ሃሳብ፣ ከዓመት ዓመት፣ ሌት ተቀን፣ በእሩምታ እየተፋን፣ ዙሪያ ገባውን እየዘራን፣ (ወደ ህሊና ካልተመለስን በቀር)፣ ከአፋችን ከወጣ በኋላ፣ እንዳሻን መንገድ ልንቀይርለት አንችልም፡፡
የውሸት መረጃዎችን ለማረም፣ የስህተት ሃሳባችን ለማስተካከል መምረጥ እንችላለን። ከዚህም ጋር ከጨለማ ወደ ብርሃናማ አቅጣጫ፣ መንገድ መለወጥ እንችላለን፡፡ የሸፍጥና የጥፋት ሃሳቦችን የመተው፣ የበደልና የክፋት ሃሳቦችንም እርም የማለት አቅም አለን። ምርጫው በእጃችን ነው - በትክክለኛ ሃሳብ ወደ ተገቢው ቀና ንፁህ መንገድ ለማምራት፡፡
ይሄ ነበር፣ አዋቂ፣ ጥበበኛ፣ ሊቅ የሚሰብል የብቃትና የክብር ጉዞ፡፡
ዛሬ ዛሬ ግን፣ ተረስቷል፡፡ በተቃራኒው፣ የውሸትና የአልቧልታ ንትርክ፣ የብሽሽቅና የስድብ ውድድር፣ የዘፈቀደ ውንጀላና የዛቻ ፉክክር፣ በአንዳች ተዓምር፣ ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርሰን፣ ወይም፣ እንደ እድገት የሚቆጠርልን የሚመስለን ሰዎች በርክተናል፤ የሚያስመስሉ ሰዎች በዝተዋል - ለመሞኘትም ሆነ ለማሞኘት::
ነገር ግን፣ ከአሉባልታ እስከ ዛቻ ድረስ፣ የማገዶነትና የዘረኝነት ጭፍን ሃሳቦች በገፍ እንዲዛመቱ፤ በር እየከፈትን፣ ከጥፋት ጉዞና ውጤት አንተርፍም። ለምን? የጥፋት ሃሳቦችን፣ ባሰኘን ጊዜ ከጨለማው ወደ ብርሃናማ መንገድ እንዲያመሩ፣ ከጥፋት አቅጣጫ ወደ ልምላሜ እንዲጓዙ ማዘዝ አይቻልም።
ሌላ ሞኝነትና የማሞኘት በሽታም አለ።
ዋና ዋና ሀሳቦች፣ “የጉዳይ፣ የጊዜና የቦታ ወሰን” የላቸውም። ይህንን እውነታ መካድ ወይም ቸል ማለት ሌላው ሞኝነት ነው። “ለዚህኛው ጉዳይ፣ ለዚያኛው ጉዳይ” እያልን፤… ለአንደኛው ጉዳይ ሲሆን፣ አሉባልታንና ዛቻን መደገፍ ወይም በይሁንታ መቀበል፤ በሌላኛው ጉዳይ ላይ ግን፣ “ለእውነት ዘብ መቆም፣ ዛቻን ማስወገድ ያስፈልጋል” ብሎ መሟገት፣ አያዋጣም። ለጊዜው እንጂ አያዛልቅም።
እዚህ አካባቢ፣ “ህግና ሥርዓት ይከበር”፤ እዚያ አካባቢ ግን፣ “ሥርዓት አልበኝነትና ሕገወጥነት ይፈቀድ” የሚል የሞኝነት ሀሳብ፣ ጥፋትን ከመጋበዝ የተለየ ትርጉም የለውም። ነገር ግን፣ እንደ ብልጣብልጥነት፣ እንደ ፖለቲካ ብልሃት ይቆጠራል። ምን ዋጋ አለው? የሥርዓት አልበኝነትና የሕገወጥነት ሀሳብ፣ ቦታ አይገድበውም።
ለዛሬ እና ለ“በጎ አላማ”፣ የዘረኝነት ስብከትን ማራገብ ወይም በይሁንታ መመልከትስ? ለጊዜውና “ክፉዎችን ለማሸነፍ” በሚል ሰበብ፣ በብሔር ብሔረሰብ የሚቧደኑ ሰዎች ጥፋት ሲፈፅሙ በዝምታ ማለፍስ? ያው፣ ወደ ጨለማ ማምራቱ፣ ወደ ጥፋት ማድረሱ አይቀሬ ነው።
በአንድ በኩል፤ ተጎጂዎችን እንደማገዶ በመቁጠር፣ የዘረኝነትን መዘዝ ለማድበስበስ፣ ሰበብና ማመካኛ በመደርደር የአጥፊዎችን የወንጀል ድርጊት ለመሸፋፈን መሞከር፣… በሌላ ጊዜና በሌላ አላማ ግን፣ ዘረኝነትን ለማውገዝ፣ በብሄር ብሔረሰብ መቧደንን ለመቃወም መጮህ፤ ስንዝር አያስኬድም። የሚያስኬድ ከመሰለን፣ ተሞኝተናል። ወይም ለመሞኘት ነው። ለምን? ዋና ዋና ሀሳቦች፤ ለእገሌና ለእከሊት፣ ለዚህና ለዚያ ጉዳይ፣ ለመቼ እና ለየት ቦታ ተብለው፣ በምኞትና በዘፈቀደ የሚገደቡና የሚለቀቁ፣ የሚታጠሩና የሚሰደዱ፣ ኑ፣ ሂዱ ተብለው የሚታዘዙ አይደሉም።
ለዚህም ሰበብ ሆነ ለዚያ ሰበብ ብቻ፣ ለአንድ ጉዳይ ወይም ለሌኛው ጉዳይ ብቻ፣ ይሄን በጎ አላማ ለማሳካት ብቻ ወይም ያን ክፉ አላማ ለማክሸፍ ብቻ በሚል ማመካኛ፣… እከሌን ለመደገፍ ወይም እከሊትን ለመቃወም ብቻ እያልን፣… ለጊዜው ብቻ፣ ለዛሬ ብቻ ብለን ራሳችንን እያሳመንን… ለጭፍንነት፣ ለማገዶነት ወይም ለዘረኝነት ሀሳቦች በራችንን እስከ ከፈትን ድረስ፣… ከዚያ በኋላ መንገዱና ውጤቱ ከእጃን ውጭ ነው።
ይሄንንም፣ በተግባር እልፍ ጊዜ፣ በእልፍ ጥፋቶች አይተነዋል። የብዙዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ብዙዎች ተሰቃይተዋል። አገሪቱም እኛም ለትንሽ ብንተርፍም፤ ሃሳባችንና መንገዳችንን ካላስተካከልን አንድንም።  
“ግን፣ ምን እናድርግ? ሌሎቹ በፕሮፓጋንዳና በአሉባልታ እየዘመቱብን?” የሚል የማመካኛ ጥያቄ ከአቅጣጫው መነሳቱ አይቀርም። “ሌሎቹ፣ ከብሽሽቅና ከስድብ አልፈው፣ የዘረኝነት ስብከት እያራገቡ፣ በዘረኝነት እያቧደኑና በጥላቻ እያነሳሱ? ሌሎቹ የሰውን ሕይወትና ንብረት እንዳሻቸው እየማገዱ?” የሚሉ ሰበቦች ከዚህም ከዚያም ይጎርፋሉ።
“በዚህ መሃል፣ የእውነተኛና ትክክለኛ ሃሳብ፣ ጠቃሚና የስኬት ሀሳብ፣ የሚያዛልቅና የተቀደሰ ሀሳብ እያልን፣… ብርሃናማ፣ የተቃናና መልካም መንገድን እንከተላለን ብንል፣… የዋህነት ይሆናል” የሚል ማመካኛ፣ ከየጎራው መሰንዘሩ አይጠረጠርም። የአላዋቂ የዋህ ማመካኛ፣ አልያም የክፋት ማሳበቢያ ነው - ይሄ።
“ጨለማን ለማስወገድ ነው፤ ጨለማን የማስፋፋው” እንደ ማለት ነው ነገሩ። “ሰዎችና ንብረታቸው ማገዶ እንዳይሆኑ ለመከላከል ነው፤ ማገዶነትን የምደግፈው” ብሎ የመነጋገር ያህል ነው - የየዋህ ወይም የክፋት ማመካኛ።
“ዘረኝነትን ለመቋቋም ነው፤ ለተቀናቃኝ ዘረኝነት በር የምከፍተው” እንደ ማለት ነው - የመሞኘትና የማሞኘት መከራከሪያ። አንዱን ዘራፊ ለመግታት፣ ሌሎች ዘራፊዎች እንዲፈጠሩ መጋበዝ ነው መድሃኒቱ? የማይመስል ነገር!
ይልቅስ፣ ሰበብና ማመካኛ መደርደር ይብቃን። የጭፍንነት፣ የማገዶነት እና የዘረኝነት ሀሳቦችን እርም ብለን እንከላከል - በማንኛውም ጉዳይ ላይ፣ መቼም ይሁን የትም!  


Read 410 times