Print this page
Saturday, 04 July 2020 00:00

“የሀጫሉ ግድያ የተቀነባበረና የታቀደ ስለመሆኑ ማሳያዎች አሉ”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 (ኢ/ር ዘለቀ ሬዲ፤ የህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ)

              የሃጫሉን ግድያ ስንመለከት የተቀነባበረና የታቀደ ስለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ሃጫሉ ለምን ተመረጠ ስንል ደግሞ፣ ልጁ የዚህ አገር ጀግናና ተጽእኖ ፈጣሪ በመሆኑ ትልቅ ቀውስ ሊያስነሳ እንደሚችል በደንብ ያውቃሉ፡፡
ይህንን ብጥብጥና አለመረጋጋት ለመፍጠር እሱን ከመግደል ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ የሆኑ ሀይሎች ወይም በዚህ አገር አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚፈልጉ አካሎች አቀነባብረው ነው የገደሉት፡፡ ምክንያቱም አንደኛ በቅርብ ጊዜ ነው ኢንተርቪው የተደረገው፡፡ ሁለተኛ በኢንተርቪው ላይ ተንኳሽ ጥያቄዎችም ነበሩ፡፡ እነሱ በደንብ ተዘጋጅተው የረሳው ህዝብ እንዲያስታውሰው አድርገው ነው ግድያውን የፈፀሙት፡፡
ይህ ግድያ ሲፈፀም የግብጽ እጅ ሊኖርበትም ይችላል፤ ብቻ አንድ አካል ሌላን አካል ለማጥቃት ሂሳብ ተሰልቶና ተቀነባብሮ የተፈፀመ ስለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡
ይህ ችግር እንዲፈጠርና ክፍተት እንዲኖር ያደረገው ደግሞ ህዝቡን በአንድ ጐራ እንዲቆም ያላደረገው ማለቴ ነው በመሃል የተፈጠረው ክፍተት ነው፡፡ ለምሳሌ የግብጽ እጅ ነው ብለን በአንድ እጅ እንዳንቆም በመሀላችን ክፍተት አለ፡፡ ይህ ክፍተት ምንድነው? ለሚለው ለምሳሌ የመንግስት አካላት አንወያይም እንደራደርም አንታረቅም የሚል አቋም በመያዛቸው ነው::  የፖለቲካ ሃይሎች አሁንም መነጋገር መወያየትና አገራዊ መግባባትና እርቅ ላይ መድረስ አለ፡፡ እኔ እንደውም በቅርብ ጊዜ ስናገር ነበር፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ቁጭ ብለው ይነጋገሩ፤ አገሪቱን ከችግር እናውጣት ብዬአለሁ፡፡ አሁን ያ ውይይት እርቅና ብሔራዊ መግባባት ቢኖር ሀጫሉም አይሞትም ነበር ቢሞትም ቁጭቱና እልሁ ቁጣው የሁላችንም ይሆን ነበር እንጂ ሌላ ተጨማሪ ብዙ ሰው አይሞትም ነበር፤ አካል አይጐድልም ነበር፡፡ ንብረት አይወድምም ነበር፡፡ ጠላታችንንም አንድ ላይ ሆነን እናውቅ ነበር፡፡
አሁን ግን ያ ክፍተት በሁለት ጐራ እንድንከፈል አደረገን፡፡ ይሄ ተገቢ አይደለም:: እኛ ብዙ የቤት ሥራዎች አሉብን፡፡ አንደኛ፤ አሜሪካ የእኛ ቁጥር አንድ ጠላት ሆና ቁጭ ብላለች፡፡ ምክንያቱም የእኛ ጂኦ ፖለቲክስ ከግብጽ ጋር ሲነፃፀር ግብጽ ናት በጣም ተፈላጊዋ፤ ስዊዝ ካናልን ብትመለከቺም የብዙ ዓለማት መዳረሻም በመሆኑ ተፈላጊ አገር ናት፡፡
ሁለተኛ፤ ምርጫውን በተመለከተ ኮሮና ቫይረስ ከመምጣቱም በፊት ይራዘም እያልን ስንወተውት ነበረ፤ ምክንያቱም ህዝብ ተረጋግቶ የፓርቲዎችን አላማ በደንብ ተረድቶ፣ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሮ እኔ ኦሮሞ ነኝ፤ እኔ አማራ ነኝ ሳይባባል አማራም አማራነቱን፣ ኦሮሞውም ኦሮሞነቱን እንደያዘ ሌላውም እንደዛው ተግባብቶ ምርጫ እንዲካሄድ በማለት ነበር ይራዘም ያልነው፡፡
ለምሳሌ በወቅቱ ባለው አመለካከት ዶ/ር ዐቢይ ፓርቲውን ይዞ ወለጋ ሄዶ መቀስቀስ አይችልም ነበር፤ ይሄ አመለካከት መጥፋት አለበት፡፡ በጫካም በከተማም ካሉት ጋር ስምምነት ይፈጠር፤ ውይይት ይደረግ ስንል ነው የቆየነው፡፡ መንግስት ሆደ ሰፊ ይሁን፣ ሁሉንም ተቃዋሚ ይቀበል፣ ሁሉም ሃሳብ በየራሱ ትክክል ነው፡፡
አሁንም ቢሆን፤ ዋናው መፍትሔ አገራዊ መግባባትና እርቅ ነው፡፡ አሁን ሻሸመኔ ላይ ቤት ሰርቶ ሱቅ መስርቶ መኖር ሃጢያት አይደለም፤ ይሄ ሁሉ ንብረት ሲወድምና ሲቃጠልኮ የግለሰቦች ሳይሆን የአገር ሀብት ነው፡፡ ብዙ ህይወት እየጠፋ ነው:: የምንሰራው አገር ነው ካልን ስልጣንና አገርን መለየትና ቅድሚያ መስጠት ለሚገባን ቅድሚያ መስጠት የግድ ነው፡፡ መጀመሪያ የጐሳና የሃይማኖት ክፍተቶችን መሙላትና መግባባት አለብን፡፡
የሰሞኑ ቀጣይ ነገር በሰሞኑ ክስተት ሰው ሁሉ በፍርሃት ውስጥ ነው፡፡ የት ሄጄ ልኑር እያለ ነው፡፡ አንድ ሰው በልማት ውስጥ መሳተፍ አይችልም፡፡ እኔ ለምሳሌ ወሊሶ ነበርኩ፤ ለስራ እንደወጣሁ ይሄ ነገር ተከሰተ::
አንድ ሆቴል ውስጥ ነው ያደርኩት፡፡ እኔ ያለሁበት ሆቴል ውስጥ ገብተው እኛ ውስጥ ባለንበት ሙሉ በሙሉ አፈረሱት፡፡ ውጡ አሉን፤ ወጣን፡፡ እኔ ቋንቋ በመቻሌ ለምኜ አለፍኩ እንጂ ሊወጉኝ ነበር፤ እኔ ወሊሶ የተገኘሁት ለስራ እንጂ ለዘረፋ አይደለም፡፡ መግባባት ሳይኖር ሲቀር ትግሉን ማን እንደሚመራው ስለማይታወቅ ሰው ሁሉ ባሻው እየሄደ ያገኘውን ማጥፋት ይፈልጋል:: ይሄ ትክክል አይደለም፤ በየመንገዱ ማጥፋትና ማውደም ለደሃ አገር አይበጅም፤ ስለዚህ ዋናውና አሁን በስልጣን ላይ ካለው አካል የሚጠበቀው ቁጭ ብሎ መነጋገርና ብሔራዊ መግባባትና እርቅ መፍጠር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አማራጭ ያለ አይመስለኝም፡፡Read 529 times